ኮሚሽኑ በዘጠኝ ወራት ከ4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ መዛግብት ላይ ውሳኔ ሰጥቷል

አዲስ አበባ፡- ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ4 ቢሊዮን 816 መቶ ሚሊዮን 90 ሺህ 70 ብር ከ 11 ሳንቲም መጠን የያዙ መዛግብትን በማከራከር ውሳኔ መስጠቱን የፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የኮሚሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አያሌው እንደገለጹት፤ በ2016 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት የቀረቡ የቅሬታ መዛግብት በብዛትና በያዙት የገንዘብ መጠን ተለይቷል፡፡

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፣ ከገቢዎች 185 መዛግብት ሲሆኑ፣ የያዙትም የገንዘብ መጠን ብር 3 ቢሊዮን 970 ሚሊዮን 250 ሺህ 197 ብር ነው፡፡ እንዲሁም ከጉምሩክ 267 መዛግብት ሲሆኑ የያዙት የገንዘብ መጠን ብር 845 ሚሊዮን 848 ሺህ 873 ብር ከ11 ሳንቲም ናቸው፡፡

እንደ ሀገር በዘጠኝ ወራት በድምሩ በ452 መዛግብት ከ4 ቢሊዮን 816 መቶ ሚሊዮን 90 ሺህ 70ብር ከ 11 ሳንቲም የገንዘብ መጠን ያላቸው የይግባኝ አቤቱታዎች በኮሚሽኑ ተመርምረው ውሳኔ ማግኘት ችለዋል፡፡

በኮሚሽኑ የይግባኝ ቅሬታዎችን በሕግና አሠራር በመመርመር ጥራት ያለው ውሳኔ የመስጠት አቅም 100% ለማድረስ በአዲሱ በጀት ዓመት መጀመሩን ፕሬዚዳንቱ አውስተው፣ ከባለፈው በጀት ዓመት የዞሩ 317 መዝገቦችን በመያዝ በያዝነው በጀት አዲስ የተከፈቱ 489 በመጨመር በድምሩ 806 የይግባኝ መዛግብት ናቸው ብለዋል፡፡

ከባለፈው በጀት ዓመት ከዞሩትና አዲስ ከተከፈቱት መዛግብት በ458ቱ ላይ የቃል ክርክር ተደርጎባቸው ለውሳኔ ተቀጥረዋል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ከተቀጠሩት ውስጥ በ452 መዛግብት ላይ ኮሚሽኑ ውሳኔውን አሳርፏል ብለዋል፡፡

ውሳኔ ካገኙት መዛግብት መካከል 267 የጉምሩክ፣ 185 ዛግብት የገቢዎች መሆናቸውን ገልፀው፣ አሁናዊ የኮሚሽኑ ውሳኔ የመስጠት አቅም 98.68 ከመቶ ደርሷል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ውሳኔ ከተሰጣቸው ውጭ ያሉት ቀሪ መዛግብት 354ቱ ይዘታቸው 30ዎቹ ለመልስ፣ 318 ለቃል ክርክር፣ 6ቱ ደግሞ ለውሳኔ ተለይተው ወደ ቀጣይ ሩብ ዓመት መዘዋወራቸውን ጠቁመዋል ፡፡

ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከቀረቡት አቤቱታዎች በብር (1 ቢሊዮን 957ሚሊዮን 58 ሺህ 147ብር ከ80 ሳንቲም ብልጫ እንዳለው ፕሬዚዳንቱ አብራርተዋል፡፡

ሙሳ ሙሀመድ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28 / 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You