ዛሬ አርብ ቢሆንም እሁድ ይመጣል …! ? “

መጋቢ ኤልደር ዊርዝሊንስ ሰሞነኛውን ስቅለትና ትንሳኤን ታሳቢ በማድረግ ” ዛሬ አርብ ቢሆንም እሁድ ይመጣል ። ” የሚል ዘመን ተሻጋሪና ወርቅ ይትበሀል ትተውልን አልፈዋል ። እኔም በምንም ሁኔታ ላይ ብሆን ቀና ቀናውን ፣ መልካም መልካሙን የማስብና የማልም ሰው ነኝ። ሀገሬም ሆነች ሕዝቤ በከባድ ፈተና ቢሆኑም ጥሩ ቀን የተሻለ ቀን ይመጣል ብዬ የማምን ኦፕቲሚስቲክ ነኝ።ለብዙዎች ይህ ሞኝነትና ተላላነት ሊሆን ይችላል።በዚህ ሞኝ ተላላ ብባል ለእኔ ስድብ አይደለም።ስሜ እንጂ።

ጦርነት፣ግጭት፣መፈናቀል፣ስደት፣ጨለማ ፣ የምድር መናዎጥ ፣ ክረምት ፣ ሰደድ እሳት ፣ በረዶ ፣ ጎርፍ ፣ መገፋት ፣ መዋረድ ፣ መገረፍ ፣ መቸንከር ፣ መሰቀል ፣ መከዳት ፣ መሸጥ ፣ መለወጥ ፣ መሰቀል ፣ ወዘተረፈ አርብ ቢሆንም ፤ መንጋቱ ፣ ብርሀን በጨለማ ላይ መንገሱ ፣ የምድር መናወጡ መቆሙ ፣ ብራ ፀደይ መምጣቱ ፣ መከበሩ ፣ መፈወሱ ፣ ትንሳኤ ፣ ቀን መውጣቱ ፣ የተሻለ ጊዜ መምጣቱ ክርስቶስ ሞትን ድልነስቶ እንደተነሳበት እሁድ ሁሉ ለእኛም ሆነ ለሀገራችን ከጦርነት ፣ ከግጭት ፣ ከኑሮ ውድነት ፣ ከዋጋ ግሽበት ፣ ከችግር ፣ ከድህነት ፣ ከተመፅዋችነት ፣ ከኋላ ቀርነት ፣ ከፈተና ፣ ከወረርሽኝ ፣ ከጭቆና ፣ ከአፈና ፣ ከጥላቻ ፣ ወዘተረፈ ነጻ የምንወጣበት ፣ አንገታችን በክብር ቀና የምናደርግበት ፤ ትንሳኤ’ችንን ፣ ህዳሴ’ችንን የምናይበት ቀን ይመጣል ።

እሁድ ይመጣል ። ” ዛሬ አርብ ቢሆንም እሁድ ይመጣል ። ” እያልን በእምነት በተስፋ እንጠባበቃለን ። ደግሞም ይሆናል ፡ ከሰባት አመት በፊት ባጋጠመኝ አደጋና የጤና እክል ሙሉ በሙሉ ሽባ ወይም ፓራላይዝ ሆኜ ቤት ለመዋል ፣ ተሽከርካሪ ወንበር / ዊልቼር / ፣ አጓጓዥ / ወከር /ና ከዘራ ለመጠቀም ተገድጄ ነበር ። ለመልበስ ፣ ለማውለቅ ፣ ውሃ ለመጠጣት ፣ ለመመገብ ፣ ለመታጠብ ፣ ለመተኛት ፣ ለመነሳት የሰው እርዳታ ያስፈልገኝ ነበር ። ስልክ ለማነጋገር ፣ የቴሌቪዥን ቻናል ለመቀየር እርዳታ ያስፈልገኝ ነበር ። ሁሉ ነገሬ በሰው እርዳት ላይ የተንጠለጠለ ነበር ። መላ ህይወቴ ተመሰቃቅሎ ነበር ። ስራዬን አጣሁ ። በጋዜጠኝነትና ኮሙንኬሽን ከአአዩ ሁለተኛ ዲግሪዬን ለመያዝ ጥቂት ሲቀረኝ ተቋረጠ ። ህልሜ ተስፋዬ ተጨናገፈ ። በመጨረሻም ለጭንቀትና ለድብርት ተዳርጌ ነበር ።ሳማይ ተደፍቶብኝ ፣ ቀን ጨልሞብኝ ነበር። አርብ ነበርና !።

እንዲህ አይነት ብዙ የሕማማት ” አርቦችን ” በህይወቴ እንዳሳለፍሁት ሁሉ እናንተም አይነቱና ደረጃው ይለያይ ይሆናል እንጂ በህይወታችሁ መውደቅ መነሳቶችን ፣ ህማማትን ፣ አርቦችን ማሳለፋችሁ አይቀርም ። በግል ህይወታችሁ ፣ በትምህርታችሁ ፣ በፍቅራችሁ ፣ በትዳራችሁ ፣ በንግዳችሁ ፣ በሕልማችሁ፣ በራእያችሁ ፣ በድርጅታችሁ ፣ በሀይማኖታችሁ ፣ በጤናችሁ ፣ በቤተሰባችሁ ፣ በማህበረሰባችሁ ፣ በሕዝባችሁ ፣ በሀገራችሁ ፣ ወዘተረፈ ላይ አርብ ሆኖባችሁ / ቀን ጨልሞባችሁ / እንደ እየሱስ ክርስቶስ ፍርድ ተዛብቶባችሁ ፣ ተገምድሎባችሁ ፣ ታስራችሁ ፣ ተገርፋችሁ ፣ ተሰቅላችሁ ፣ ተቸንክራችሁ ፣ ተዋርዳችሁ ፣ ተፈትናችሁ ፣ ባመናችሁት ተክዳችሁ ፣ በባልንጀራችሁ በ ‘ 33 ‘ ብር ተላልፋችሁ ተሰጥታችሁ ፣ ሰማይ ተደፍቶባችሁ ወዘተረፈ ይሆናል ። ዛሬም በእነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እያለፋችሁም ሊሆን ይችላል ፤ አርብ ነውና ! ።

ካለፉት 200 አመታት ወዲህ ያሉትን ጊዜያት እንኳ ብንወስድ እንደ ህዝብ እንደ ሀገር ሺህ አርቦችን ፣ በድርቅ፣ በርሀብ ፣ በቸነፈር ፣ እናት ልጇን እስከ መብላት የተገደደችበት እንደ ክፉ ቀን ያለ እንደ 67ቱ በርሀብ የሞተች እናቱን ጡት የሚጠባበት ፣ እንደ …77 … 87 … ወዘተረፈ ያሉ ጠኔዎችን ፣ ችጋሮችን አሳልፈናል ። ዛሬም ከዚህ አዙሪት በቅጡ ሰብረን መውጣት አልቻልንም ። እንደ ህዳር በሽታ ፣ ፈንጣጣ ፣ ከ76 ወዲህ ደግሞ በኤች አይ ቪ/ኤድስ ፣ ኮቪድ – 19 የእልቂት ጥላውን አጥልቶብን ነበር ። በግብፅ ፣ በደርቡሽ ፣ በቱርክ ፣ በእንግሊዝ ፣ በጣሊያን ፣ በሱማሊያ ፣ በኤርትራ ተወረናል ።ዛሬም የክተት ነጋሪት የሚያስጎሹምብን አልጠፉም ።

በመቶዎች ሊቆጠሩ በሚችሉ የእርስ በእርስ ግጭቶች አልፈናል ። ከዘመነ መሳፍንት እንኳ ብንጀምር በመሳፍንቱ ፣ በመኳንንቱ ፣ በነገስታቱ መካከል ለስልጣን፣ ለዘውድ ሲባል በተካሄደ የእርስ በእርስ ግጭት ጦርነት ወገናችን ተጨራርሷል ። አጼ ቴዎድሮስ ፣ አጼ ዩሐንስ፣ አጼ ምኒልክ ፣ ልጅ እያሱ ፣ ንግስት ዘውዲቱ ፣ ልዑል አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንንና መንግስቱ ጉዳቱ፣ ጥፋቱ ይለያይ እንጂ ሁሉም በእርስ በእርስ ግጭት ፣ ጦርነት ተፈትነዋል፤የሀገር የሕዝብ አርብ ነበርና !።

በለፉት 50 አመታት መዋቅራዊና ተቋማዊ ሆኖ በጀት ተመድቦለት ሌት ተቀን በተቀነቀነ የማንነት ፓለቲካ የተነሳ በሀገራችን ጥላቻ ፣ ቂም ፣ በቀል ፣ ልዩነት ተጎንቁሏል። ጎሳን ፣ ሀይማኖትን ፣ አይዶሎጂን መሰረት አድርገን ተጋጭተናል ። ተጋለናል ። አብያተ ክርስቲያናትን ፣ መስጊዶችን አቃጥለናል ። ቀይ ፣ ነጭ ሽብር ተባብለን ተጨራርሰናል ። አህዳዊ ፣ አሸባሪ ፣ ጁንታና ጽንፈኛ ተባብለን ተጋለናል ። እናት አባት በቀይ ሽብር የተገደሉ ልጆቻቸውን እሬሳ ሲለምኑ የጥይት ዋጋ ተጠይቀዋል ።

የዚችን ሀገር ታሪክ እስከወዲያኛው ሊቀይር የሚችል ፍም እሳት የሆነ አንድ ትውልድ በቀይና በነጭ ሽብር አልቋል ። በእርስ በርስ ጦርነት በብዙ መቶ ሺህዎች ወይም በሚሊየን የሚቆጠር ዜጋ አጥተናል ። የሀገር ሀብት ወድሟል ። ኤርትራን የመሰለ ሀገርና ሕዝብ አጥተናል ። ወደብ አልባ ሆነናል።ዛሬ ድረስ ከዚህ ሀንጎቨር አልወጣንም ። ዛሬም ከትግራይ ጦርነት ወጥተን በአማራና በኦሮሚያ ደግሞ ሌላ ዙር ጦርነት ላይ ነን፤ የሀገር የሕዝብ አርብ ነበርና !።

በህወሀት/ ኢህአዴ 27 አመታት በፓለቲካ አመለካከታችን ፣ በጎሳችን በጅምላ ተገርፈናል ። ተገልብጠናል ። ተሰቃይተናል ። ተግዘናል ። ተሰደናል ። ሰው በመሆን ብቻ ከፈጣሪ የተቸርናቸውን የማሰብ ፣ የመናገር ፣ ሀሳብን በነጻነት የመግለፅ ፣ የመሰብሰብ መብቶች ተረግጠዋል ። በደምሳሳው ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶቻችን ተጥሰዋል ። በገዛ ወንድሞቻችን እንደ ባሪያ ተገዝተናል ። ተረግጠናል ። ተገፍተናል ። ሀብታችንንና ሀገራችን በቀን በአደባባይ ተዘርፈናል ። ሀገር በቁሟ በአውሬዎች ተግጣለች ። የድሀ ጉሮሮ ታንቆና በእኛ ድህነት ጥቂቶች በተድላ ፣ በቅንጦት ፣ በደስታ ፣ በፍሰሐ ተንደላቀዋል ። እየተንደላቀቁም ነው ። ዛሬም ከዚህ ክፉ አባዜ አልወጣንም፤ አርብ ነበርና !።

ካለፉት አምስት አመታት ወዲህ ዴሞክራሲን ነጻነትን መሸከም ተስኖን ፤ የፓለቲካ ምህዳሩ መስፋትን እንደ እኩይ አጋጣሚ ተጠቅመን ዜጎችን በማንነታቸው አፈናቅለናል ፣ ገለናል ፣ ሮማውያን እንኳ ያላደረጉትን ዘቅዝቀን ሰቅለናል ። ለውጡም በተወሰነ ደረጃ ወደ ኋላ እንዲያፈገፍግ አድርገናል። ከእነ ህይወታቸው በእሳት አቃጥለናል ። ወደ ገደል ጥለናል ። ሩጦ ተጫውቶ ያልጠገበን ህጻን ብላቴና ብልት ሰልበናል ። እህቶቻችንን ደፍረናል ። ዛሬ ድረስ አግተናል ። በሕዝብ ፣ በክልልና በዩኒቨርስቲዎች ግጭት እንዲቀሰቀስ የማንነት ግጭት እንዲቀጣጠልና ሀገር ወደ ለየለት ቀውስ እንድትገባ በአደባባይ ቀስቅሰናል ፤ ለፍፈናል ፤ አርብ ነበርና !።

ለእሁድ መዳረሻ ፣ ለትንሳኤ ፣ ለንስህ ፣ ለጥሞና፣ ለአንድነት ፣ ለፍቅር ፣ ለሰላም ለይቅርታና ለሕዳሴ መጀመሪያ በግብፅ አንድ አደረገን ። እጅ ለእጅ ተያይዘን እንድንቆም አስቻለን ። ወደ ሰውነታችን ፣ ወደ ቀደመው ማንነታችን እንድንሸበለል ያለ ልዩነት የሰው ልጅንና ኢትዮጵያውያንን የሚያጠቃ ቫይረስ ሰደደብን ። ኮሮናቫይረስን ። ስናገግም ደግሞ መልሰን የቱ ጋ ነበር ያቆምነው ብለን ካቆምንበት ጀመርን። ወደ ጥላቻ ፣ ልዩነት ፣ ቂም በቀል ፣ መጠቃቃት ፣ ወዘተረፈ ገባን።እንደ ኮሮና ያለ ወረርሽኝ ወይም እንደ አድዋ ያለ ጦርነት መጥቶ አንድ እስከንሆን እየተባላን እንገኛለን።ሀገር ስትወረር አንድ የምንሆነውን ነገር ባሰብሁ ቁጥር ግራ ቢገባኝ ፤ በሰላሙ ጊዜ ለምን ችግሮቻችን ተነጋግረን ፈትተን አንድ መሆን እንዳንችል ማን ዋለብን፣ማን አሴረብን፣ማን መተት አደረገብን ስል እንደ አእምሮ ህመምተኛ ብቻየን አወራለሁ፤ እሁድ አጥቢያ ነውና !።

በኮሮናቫይረስ የተነሳ የሰው ልጅና የአለም ህልውና ላይ አደጋ ተደቅኖ ነበር ። ሁሉም ነገር ተመሰቃቅሎ ፣ ተገለባብጦ ነበር ። ፍርሀት ፣ ጭንቀት ፣ ሞት በሰማዩ ረቦ፤ ሞት እንደ ጥላችን ይከተለን ጀምሮ ፤ ከምንወዳቸው ተለይተን ፤ በየቤታችን ከተን ፤ በአጠቃላይ የአኗኗር ዘይቤ’ችን ተቀያይሮ ነበር ። ከአብያተ ክርስቲያናት ፣ ከመስጊድ ደጆች ተባረን፤ ከስራ ታቅበን ፣ ተገድበን ፣ የእለት ጉርሳቸውን በእየለቱ እየሰሩ የሚያገኙ ወገኖች ለችግር ተዳርገው፤ ትምህርት ቤቶች ዩኒቨርስቲዎች በወረርሽኙ የተነሳ በራቸውን በመዝገታቸው ተማሪዎች ቤት ለመዋል ተገደው፤የሀገርና የሕዝብ ኢኮኖሚ ክፉኛ እየተጎዳ፤ ከሕዳር በሽታ ፣ ከኤች አይ ቪ /ኤድስ፣ ከኩፍኝና ከፈንጣጣ ፣ ከፓሊዎ ፣ 1ኛውና 2ኛው የአለም ጦርነቶች በአንድ ላይ ተደምረው ፣ ከ9/11 የሽብር ጥቃት በላይ የሰው ልጅ ህልውናን የሚፈትን ወረርሽኝ ዙሪያችንን ከቦን፣ አስደንብሮን ነበር።ዛሬ ያ አልፎ ታሪክ ሆኗል።አርብ አልፎ እሁድ መጥቷል።አሁን ያለንበት ሀገራዊ ሁኔታም እንደ ኮሮናው ያልፋል።አርብ ሄዶ እሁድ ይመጣል፤ አርብ ነውና !።

ወደ ግል አርቤ ስመለስ፤” ዛሬ አርብ ቢሆንም እሁድ ይመጣል ። ” እያልሁ ዛሬም እጽናናለሁ ተስፋ አደርጋለሁ ። ዛሬ ድቅድቅ ጨለማ ቢሆን ፣ የማይነጋ ፣ ዙሪያዊ ገደል ፣ ተራራ ፣ ተስፋ ቢስ ቢመስልም ፤ ነገ ቀን ይወጣል ፣ ይነጋል ፣ ደልዳላ ይሆናል እሁድ ይመጣል እያልሁ እጽናናለሁ ። እምነቴም አምላኬም አላሳፈረኝም ። ከሞት ተርፌ ዛሬ ጤናዬ በእጅጉ መሻሻል አሳይቷል ። በቅርብ ሙሉ በሙሉ ይሻለኛል ብዬ አምናለሁ ።የምወደውን የጋዜጠኝነት ሙያዬን በደጋግ ሰዎች እገዛና ማበረታት ጀምሬ’ለሁ ። ተስፋዬ ለምልሟል ።

የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ተቆርቋሪ ድርጅትን ከመመስረት ባሻገር፤”የሸማች ድምጽ” የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም በአራዳ ኤፍ ኤም ጀምሬያለሁ።በዋሻው መውጫ ብርሀን እየታየኝ ነው ። ከፈጣሪ ጋር ያቋረጥሁትን ትምህርቴን አጠናቅቄ ሶስተኛ ዲግሪዬን እሰራለሁ ። በዚች ሀገራ የሚዲያ ኢንዱስትሪ የዜግነት ድርሻዬን እወጣለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ። ዛሬ ላይ እንዲህ ህልመኛ የሆንሁት አርብ አልፎ እሁድ እንደሚመጣ በማመኔና ተስፋን በመሰነቄ ነው ። ከስቅላቱ በኋላ ትንሳኤው እንደሚከተል በማመኔ ነው።

እየሱስ ክርስቶስ ከተዋረደባት ፣ ከተተፋባት ፣ ከተገረፈባት ፣ ከተቸነከረባት ፣ እንደ ወንበዴ ፣ ወንጀለኛ አንዳች መተላለፍ ፣ ነቀፋ ሳይገኝበት ፣ ሞት የተፈረደበት ፣ በመስቀል ተቸንክሮ ከተሰቀለባት ፣ ጎኑ ከተወጋባት በኋላ እሁድ ይመጣል !።” አርብ ” እንደ ተቀሩት የሳምንቱ ቀናት የጊዜ መለያ ብቻ አልሆነም ። የጨለማ ፣ የስቃይ ፣ የመከራ ፣ የፈተና ፣ የውርደት ፣ የግፍ ፣ የበደል ፣ የመገፈፍ ፣ የራቁትነት የመሰቀል ወዘተረፈ ተምሳሌት ጭምር እንጂ ። ኤልደር” ዛሬ አርብ ነው ” ያሉት ይሄን መሰሉን ቀን ፣ አመት ፣ ዘመን ነው ፤ ዛሬ አርብ ነውና ፤

ሆኖም መግነዙን ፈቶ ፣ የመቃብሩን ቋጥኝ አንከባሎ፣ ሞትን ድል አድርጎ ፣ በብኩርና በሶስተኛው ቀን በድል ተነስቷል ። አርጓል ። በደሙ ዘላለማዊ ድህነትን ፣ በግርፋቱ ህያው የፈውሱን አክሊል አቀዳጅቶናል ። ሀጢያትን ደምስሶ ከልዑል እግዚአብሔር አስታርቆናል ። ከኦሪታዊ ሕግ ፣ ከባርነት ፣ ከሀጢያት ነጻ አውጥቶናል ፤ እሁድ መጥቷልና !።

ቤተሰብ ፣ ማህበረሰብ ፣ ሕዝብና ሀገርም እንዲህ ባለ ተመሳሳይ ጨለማ ፣ ፈተና ፣ መከራ ፣ ቸነፈር ፣ ውርደት ፣ ግርፋት ፣ መቸንከር ፣ ደም መፍሰስ ፣ ስጋ መቆረስ ፣ ጀርባ መተልተል ፣ ግማደ መስቀሉን ተሸክሞ ተራራ መውጣት ፣ ጎን መወጋት ፣ የሾህ አክሊል መድፋት ፣ ወዘተረፈ አልፈዋል ። እልፍ አእላፍ አርቦችን አሳልፈዋል ። ዳሩ ግን የትንሳኤው እሁድ ይመጣል ።

ከእዚህ ክፉ ወረርሽኝ ፣ ከጦርነት ፣ ከግጭት ፣ ከሀሰተኛ ትርክት ፣ ከፓለቲካ ስብራት ፣ ከጥላቻ ፣ ከልዩነት ፣ ከበቀል ፣ ከስግብግብነት ፣ ከደባ ፓለቲካ ፣ ከድህነት ፣ ከእርዛት ፣ ከርሀብ ፣ ከኋላ ቀርነት ፣ ወዘተረፈ ወይም ከአርብ ወጥተን ፤ እሁድን እናያለን ። የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት አክብረን ፣ የዴሞክራሲ ተቋማትን ገንብተን አርብን አልፈን ለእሁድ እንበቃለን። ሌት ተቀን በመትጋት ፣ ሙስናን ፣ ብልሹ አሰራርን ፣ ስንፍናን ፣ ዳተኝነትነት በማስወገድ አርብን እጅ ለእጅ ተያይዘን እንሻገራለን ። እሁድን በተስፋ በእምነት እንጠባበቃለን ። ልዩነትን ፣ ጥላቻን ፣ ጎሰኝነትን ፣ የታሪክ እስረኝነትን ፣ የሴራ ፓለቲካን ወይም ብዙ አርቦችን በጽናት በብርታት አልፈን ለትንሳኤና ለህዳሴ / ለእሁድ እንበቃለን ። ደግሞም እናምናለን ይሆናል ።

” ዛሬ አርብ ቢሆንም እሁድ ይመጣል ! ”

እንኳን ለብርሀነ ትንሳኤው አደረሰን ! አደረሳችሁ !

ሻሎም ! አሜን ።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)

fenote1971@gmail.com

 

አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You