በዓሉን በመረዳዳት እናክብር!

ኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ በርካታ አኩሪ እሴቶች አሏቸው። ከእነዚህ ውስጥ የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴቶቻችን በዋነኛነት ተጠቃሾች ናቸው። ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሰራሽ ችግሮች ሲያጋጥሙ መሰናክሎችን በመረዳዳትና በመደጋገፍ የማለፍ ጥበብን ከማዳበራቸውም በላይ ለተበደሉት መሸሸጊያ፤ ለተሰደዱት መጠለያ ሆነው ዘልቀዋል።

ኢትዮጵያውያን ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሰራሽ ችግሮች ሲያጋጥማቸው በመረዳዳትና በመደጋገፍ የማለፍ ጥበብን የታለበሱ ሕዝቦች ናቸው። በረሃብም ሆነ በድርቅ፤ በግጭትም ሆነ በጦርነት ወቅት በመረዳዳት አስከፊ ጊዜያቶችን አሳልፈዋል።

ኢትዮጵያውያን የእምነት ልዩነት ሳይበግራቸው ደስታንም ሆነ ኀዘንን በጋራ ያሳልፋሉ።የሀገራቸውንም ዳር ድንበር ይጠብቃሉ፤ ወራሪን በጋራ ድል ይመታሉ፤ በልማት ይሳተፋሉ ፤ሀገራቸውን ጥሪ ስታደርግላቸው ያለምንም ማመንታት ከጎኗ ይቆማሉ። ይህ አንድነታቸውን አብሮነታቸውም ከበበርካታ የዓለም ሕዝብ ዘንድ ትልቅ ክብርና ግርማ ሞገስ አጎናጽፏቸዋል። በአርአያነትም እንዲወሰዱ አድርጓቸዋል።

ኢትዮጵያውያን ዘር ፤ ቀለምና ኃይማኖት ሳይለዩ የተቸገረን መርዳት፤ የተራበን ማብላት፤የተጠማን ማጠጣትና የታረዘን ማልበስ ያውቁበታል። እንኳን ርስ በርሳቸው ይቅርና ባህር አቋርጦ፤ ድንበር ተሻግሮ ለመጣ ስደተኛ ጭምር በራቸውን ክፍት አድርገው ፤ ያላቸውን አካፍለውና ፍቅር ለግሰው ማኖር የሚችሉ ሕዝቦች መሆናቸውን በርካታ የታሪክ መዛግብት የሚያወሱት ሃቅ ነው።

ኢትዮጵያውያን ከመካ የተሰደዱ የነብዩ መሐመድ ተከታዮችንና ቤተሰቦችን ተቀብላ በማስተናገድና በማኖርና የጎላ ታሪክ ያላትና ለእስልምና ኃይማኖትም ባለውለታ ተደርጋ የምትቆጠር ሀገር ከመሆኗም ባሻገር ይህ አኩሪ ታሪክ ሺህ ዘመናትን ተሻግሮ ዛሬም ድረስ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ተቀብላ በእንክብካቤ የምታስተናግድ ሀገር ነች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) የረመዳንን ጾም ምክንያት በማድረግ የተለያዩ የኢፍጣር (ጾመኞችን የማብላት) መርሃ ግብሮችን ሲያካሂዱ ቆይተዋል። ሀገራቸውን ጥለው የተሰደዱና ኢትዮጵያን መጠጊያ ያደረጉ የሶማሌ፤ የሶርያ፤ የየመንና የተለያዩ ሀገር ስደተኞችን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤተመንግሥታቸው ድረስ ጠርተው አስፈጥረዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ስደተኞችን ቤተመንግሥት ድረስ ጋብዞ ማስፈጠር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ጊዜ ጀምሮ የቀጠለ በጎ ተግባር ነው። በዚህ ተግባራቸውም ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የነበራትን እንግዶችን የመቀበል ታሪክ አስቀጥለዋል።

ከ98 በመቶ በላይ አማኝ የሆነው ኢትዮጵያ ሕዝብ ያለውን በማካፈል ያምናል።ሰ ዎች ሲቸገሩ የሚጨክን አንጀት የለውም። ከመሶቡ ቆርሶ፤ ከኪሱ ቀንሶ ያለውን ይሰጣል። የርሱ ቤት ደምቆ የጎረቤቱ እንዲቀዘቅዝ አይፈቅድም። ይህም አኩሪ ባህል ኢትዮጵያውን በችግር እንዳይንበረከኩና ችግርን ድል ነስተው እንዲኖሩ አድርጓቸዋል።

ይህ የመተሳሰብ ፤ የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴት በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተጠናክሮ ቀጥሏል። በተለይም አቅመ ደካማ ለሆኑ ዜጎች ማዕድ ማጋራትና የችግረኞች ቤት እድሳት በዚህ ረገድ ተጠቃሾች ናቸው።

በዝቅተኛ ኑሮ ሕይወታቸውን ሲገፉ የቆዩ ነዋሪዎችን ቤት በማደስ ዜጎች በተለይም በኋለኛ ዘመናቸው በተሻለ መጠለያ ውስጥ እንዲኖሩ የሚያደርጉ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ዛሬ የእኛነታችን መገለጫዎች እየሆኑ ነው። በየዓመቱም ክረምት በመጣ ቁጥር የበርካታ አቅመ ደካማ ዜጎች ቤቶች እየታደሱ ዜጎችን ከዝናብና ከብርድ የመታደጉ ተግባር በመንግሥት፤መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና በነዋሪው ተሳትፎ እውን እየሆነ ነው።

በሌላም በኩል በአቅም ማነስ ምክንያት በቀን አንድ ጊዜ እንኳን ራሳቸውን መመገብ የማይችሉ ዜጎችን በጋራ ማዕድ እንዲቆርሱ በማድረግ ረገድ የተጀመሩት በጎ ተግባራት የኢትዮጵያውያንን በጎ እሴቶች ማስቀጠያዎች እየሆኑ ነው። በተለይም በበዓላት ወቅት አቅመ ደካሞች በዓላትን በእኩል ተደስተው እንዲሳልፉ በበጎ ፈቃድ ወጣቶች ጭምር የሚከናወኑ የማዕድ ማጋራት በጎ ሥራዎችን ለተመለከተ በኢትዮጵያውያን መካከል ያለውን መተሳሰብና መረዳዳት የሚያመላክት ነው።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን ከመረዳዳትና ከመደጋገፍ ውጪ መገለጫም የላቸውም። ኢትዮጵያም ቆማ መቀጠል የቻለችው ዜጎቿ በሚከውኗቸው መልካመም ተግባራት ነው።ስለዚህም እነዚህን በጎ እሴቶች በማጠናከር ኢትዮጵያን የማጽናቱ ተግባር በተለይም በዚህ የትንሳዔ በዓል ወቅት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል!

አዲስ ዘመን ሚያዚያ 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You