የገጠሩን ሕዝብ ማዕከል ያደረጉት የፀሐይ ኃይል ማመንጫ መሠረተ ልማት ሥራዎች

ኢትዮጵያ ለኤሌክትሪክ ኃይል ልማት ሊውሉ የሚችሉ በርካታ እምቅ አቅሞች እንዳላት ይታወቃል። የኤሌክትሪክ ኃይል ሊመነጭባቸው የሚችሉ አያሌ ትላልቅ ወንዞች ባለጸጋ ናት፤ በእነዚህ ወንዞች ብዙ ሺ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እያመረተች ትገኛለች። ከንፋስ ኃይልና ከፀሐይ ኃይል አቅሞቿ ኃይል ማመንጨት ጀምራለች። ከጂኦተርማል፣ ከደረቅ ቆሻሻም እንዲሁ የኤሌክትሪክ ኃይል በስፋት ለማምረት እየተሠራ ነው።

በሀገሪቱ ከተለያዩ ምንጮች ከሚመረተው የኤሌክትሪክ ኃይል በአብዛኛው ተጠቃሚ እየሆነ ያለው የከተማው ሕዝብ ነው። 80 በመቶ በገጠራማ አካባቢዎች የሚኖረው ማህበረሰብ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደማያገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ።

መንግሥት የገጠሩን ሕዝብ መቶ በመቶ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ ሀገራዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት እቅድ አዘጋጅቶ እየሠራ መሆኑን ይፋ አድርጓል። ይህን ለማሳካት ደግሞ ዋናውን የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ብቻ መጠበቅ እንደማያዋጣ ታምኖበት፣ አነስተኛ ግሪድ የሆኑ የኃይል መሠረተ ልማት ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በዚህ ምክንያት በመንግሥት ከፀሐይ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨቱ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶታል። የኢትዮጵያ መልከዓ ምድር አቀማመጥ በምድር ወገብ አቅራቢያ መገኘቱ፣ ከፀሐይ ኃይል ለሚመነጭ ኢነርጂ ምቹ እንደሚያደርጋት መረጃዎች ያመለክታሉ። በዚህ እምቅ ሀብት ላይ ሰፊ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን መሥራት እና በዘርፉ የተሰማሩ ማህበራትን ማበረታታት ዘርፉን ለማሳደግ የራሱ ጉልህ ሚና እንዳለው ይታመናል።

ኢትዮጵያ ለፀሐይ ኃይል ካላት አቅም እና ለዚህ ዘርፍ ካላት ምቹነት አኳያ ሲታይ ግን በሀገሪቱ በፀሐይ ኃይል መሠረተ ልማት በኩል ብዙም እንዳልተሰራበት ይታወቃል። በቤት ለቤት የኢነርጂ ፍላጎት ጭምር የፀሐይ ኃይል የኤሌክትሪክ አቅርቦት ላይ መሥራት ሰፊ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ሁሉ፣ አብዛኛውን የገጠር አካባቢ ከፀሐይ ኃይል ከሚመነጭ የኤሌከትሪክ ኃይል በአማራጭነት ተጠቃሚ ለማድረግ ሰፊ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ያስፈልጋሉ።

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ዋና አማካሪ አቶ ጎሳዬ መንግሥቴ፣ የፀሐይ ኃይል /solar en­ergy/ ቴክኖሎጂ በሀገሪቱ እንዲስፋፋ እየተደረገ መሆኑን አስታውሰው፣ ቴክኖሎጂው አዋጭ እየሆነ መምጣቱንም ገልጸዋል።

በፀሐይ ኃይል ልማት የተሰማሩ ማህበራት በዘርፉ ለሀገሪቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የኃይል ዘርፉን በተለይ ዋናውን የኃይል ቋት ከማስፋፋት በተጨማሪ ከዋናው የኃይል ቋት ወይም ግሪድ ውጭ የሆነውንና በአሰፋፈሩ የተበታተነውን አብዛኛውን በገጠር የሚኖር ሕዝብ ለመድረስ እየተሠራ ይገኛል። ይህን አማራጭ ኃይል ለመብራት፣ ለሞይባል ቻርጅ አገልግሎትና ለሌሎች የተለያዩ አገልግሎቶች ለማዋል ጭምር የፀሐይ ኃይል /ሶላር ኢነርጂ/ ቴክኖሎጂዎችን ለማስፋፋት እንደ ኢሴዳ (Ethiopian Solar Energy Development Associa­tion) የመሳሰሉት ማህበራት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንም አቶ ጎሳዬ ጠቅሰዋል። መሰል ማህበራት እንዲቋቋሙ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እገዛ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሀገር አቀፉን የኃይል ፕሮግራም ለማሳካት ከሚሰራባቸው መንገዶች አንዱ የግሉ ዘርፍ ማሳተፍ መሆኑን ጠቅሰው፣ የግሉ ዘርፍ ሚና ወሳኝ መሆኑንም አመልክተዋል። ከፋይናንስ አኳያ የዓለም ባንክ፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ ጂአይዜድ፣ የአውሮፓ ህብረት እና ሌሎችም የፋይናንስ ምንጮች ለእዚህ አማራጭ የኃይል ልማት ድጋፍ እንደሚያደርጉ አቶ ጎሳዬ ጠቅሰው፣ እነዚህን የፋይናንስ አቅሞች ወስዶ ተግባራዊ ማድረግ ላይ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ወይም አልሚዎች አቅማቸውን ማጎልበት እንደሚኖርባቸው አቶ ጎሳዬ አመላክተዋል። ለዚህም መንግሥት የአቅም ግንባታ ድጋፎችን እና ርዳታ ያደርጋል ብለዋል።

እንደ ሀገር ሲታይ በኢትዮጵያ የሚታየው የፀሐይ ኃይል /energy/ ተጠቃሚነት እዚህ ግባ የማይባል እንዳልሆነ የጠቀሱት አቶ ጎሳዬ፣ ካለው አቅም አኳያ ከሀብቱ ተጠቃሚ ለመሆን ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል ሲሉ አስታውቀዋል። የፀሐይ ኃይል በትልቅ የኃይል ቋት (solar farm) የሚባለውን ለመሥራት በርካታ አልሚዎች ሊመጡ የሚችሉባቸው ፕሮጀክቶች መኖራቸውንም አስታውቀዋል።

ይህ ከዋናው የኃይል ቋት ጋር ሊገናኝ እንደሚችልም ጠቅሰው፣ ከውሃ እንደሚመነጭ የኤሌክትሪክ ኃይል ሁሉ ከፀሐይ ኃይል የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ለዋናው ግሪድ የሚሸጥበት ሁኔታ እንዳለም አስታውቀዋል። 100 እና 200 ሜጋ ዋት የሚሆኑትን የግሉ ዘርፍ ሊያለማቸው የሚችሉ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ እነዚህን ያህል አቅሞች በመንግሥት እና በግል አጋርነት ማዕቀፍ እንዲገነቡ እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።

አቶ ጎሳዬ እንዳብራሩት፤ የኤሌክትሪክ ኃይል ከፀሐይ ኃይል እንዲመነጭ የሚደረግበት መንገድ ኦፍ ግሪድ ቴክኖሎጂ ይባላል፤ ኦፍ ግሪድ ከዋናው የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ጋር ካልተያያዙ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ውጭ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ለተጠቃሚዎች እንዲዳረስ የሚደረግበት መንገድ ወይም ሚኒ ግሪድ ማለት ነው።

በሚኒ ግሪድ ብዙ ጊዜ በአንዳንድ ሀገራት ከ10 ወይም 20 ኪሎ ዋት ጀምሮ እስከ አንድ ሜጋ ዋት፣ በአንዳንድ ሀገሮች ደግሞ እስከ 10 ሜጋ ዋት ድረስ እንዲመነጭ ይደረጋል። ይህም የኤሌክትሪክ ኃይል ዋናውን የማስተላለፊያ ወይም የማከፋፈያ መሥመር ሳይጠቀም ለተጠቃሚ የሚቀርብበት መንገድ ነው። የተመረተው የኤሌክትሪክ ኃይል ከአንድ አካባቢ ፍጆታ አያልፍም። ለአንድ የገጠር ከተማ በዚህ ግሪድ የመብራት አገልግሎት መስጠት ይቻላል።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ ኃይል የማመንጨትና ማሰራጨቱ ሥራ የራሱ ግሪድ ይኖረዋል። በሀገሪቱ የዚህ ዓይነት ሚኒ ግሪድ በስፋት እንዲለማ እየተደረገ ይገኛል። በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አማካይነትም 11 ሚኒ ግሪዶች በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ ሆነዋል። 25 ሚኒ ግሪዶች በአፍሪካ ልማት ባንክ ድጋፍ በተለያዩ ክልሎች እየተሠሩ ሲሆን፤ 100 ያህል ሚኒ ግሪዶች ደግም ሊሠሩ ዝግጅቶች እየተደረጉ ይገኛሉ።

በቀጣይም ከ200 በላይ ሚኒ ግሪዶች ይሠራሉ። ግማሹ በግሉ ዘርፍ፣ የተቀሩት ደግሞ በህብረት ሥራ ማህበራት ባለቤትነት ወጣቶችን በማደራጀትና በመቅጠር የሚሠሩ ይሆናሉ። ሁለት መቶ ሚኒ ግሪዶች ይሠራሉ ሲባልም በየአካባቢዎቹ በሚገኙ ኪስ ከተሞች ወይም አካባቢዎች እና ዋናው ግሪድ የማይደርስባቸውን አካባቢዎች ታሳቢ ተደርጎ ነው። ግሪዶቹ የኤሌክትሪክ ኃይል ከዋናው ግሪድ ለመሳብ አዋጭ በማይሆንባቸው አካባቢዎች የሚገነቡ ይሆናሉ።

የሚኒ ግሪዶች ተፈላጊነትም በዋነኛነት የአካባቢውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ገጽታ እንዲለወጥ ማድረግ ነው። ሌላው ትኩረት ተደርጎ የሚሠራበት መስኖ ይሆናል። ለመስኖ አገልግሎት የሚውሉት የውሃ መሳቢያ ሞተሮች ናፋጣ የሚጠቀሙ ናቸው። የናፍጣው ዋጋ ውድ እየሆነ መጥቷል። ስለዚህ በናፍጣ የሚጠቀሙ የውሃ መሳቢያ ሞተሮችን ከመጠቀም ይልቅ በፀሐይ ኃይል የሚሠሩትን መጠቀም ይሻላል።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ በፀሐይ ብርሃን የሚሰሩ ውሃ ፓምፕ አምራቹ ኃይል እንዲያመርት፣ አካባቢውንም ከመበከል ለመታደግ ያስችላል። ወጪውም ከነዳጅ ወጪ በጣም ይቀንሳል። ከተቻለም የፀሐይ ኃይል ኤሌክትሪክ ሁልጊዜ የሚገኝ እንደመሆኑ በዓመት ሁለት ሶስት ጊዜ ማምረት ያስችላል። ለመጠጥ ውኃ እና ለኤሌክትሪክ አገልግሎት ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል።

በናፍጣ የሚሠራ የውሃ መሳቢያ ፓምፕ ከአካባቢ ጋር ተስማሚ አይደለም። ሀገራት የካርቦን ልቀት ለመቀነስ ታዳሽ ኃይል ጥቅም ላይ እንዲውል ያስገነዝባሉ። ከዚህ ሁሉ አኳያ ሲታይ በፀሐይ ኃይል በሚመረት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ ፓምፓች ፋይዳ ከፍተኛ ነው። አካባቢን የማይበክል ቴክኖሎጂ መጠቀም በራሱ ከውጭ የተወሰነ የፋይናንስ ድጋፍ ለማግኘትም ያስችላል፤ ሕብረተሰቡም የዚህ ተጠቃሚ መሆን ያስችለዋል ሲሉም አብራርተዋል።

ሚኒ ግሪድ ምርታማነት ማምጣትን እንዲሁም ማህበራዊ ሕይወት መለወጥን ታሳቢ ያደርጋል። ማህበረሰቡ ምርታማ ካልሆነ፣ የሚኒ ግሪድ ታሪፍ ከዋናው ግሪድ ይወደዳል። ለምሳሌም የህብረት ሥራ ማህበራት፣ ቡና አልሚዎች፣ ሌሎች እንደ አቮካዶ ያሉ የገበያ ምርቶችን ወደ ውጭ የሚላኩ አልሚዎችና ላኪዎች ከዋናው ግሪድ አኳያ ሲታይ ታሪፉ የተለየ ቢሆንም፣ ያዋጣቸዋል ሲሉ የኢነርጂ ዘርፍ ዋና አማካሪው አቶ ጎሳዬ መንግሥቴ አስገንዝበዋል።

አቶ ጎሳዬ ወደ ሚኒ ግሪድ ልማቱ የገቡት የሀገር ውስጥ የግል ዘርፍ ማህበራት ውስን መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የሚኒ ግሪድ ልማቱ እንዲስፋፋ የግሉ ዘርፍ እና የሀገር ውስጥ ማህበራት በስፋት እንዲገቡ የአቅም ግንባታ ሥራዎች እንደሚሰሩ አስታወቀዋል።

ከዚህ ውጭም የቤት ውስጥ የፀሐይ ኃይል ኤሌክትሪክ /ሶላር ሆም ሲስተም / የሚባል እንዳለም አመልክተዋል። በየቤቱ የተለያዩ የፀሐይ ኃይል መሠረተ ልማት ዓይነቶችን በመትከል በክሊኒኮችና በትምህርት ቤቶች ጭምር ደረጃውን የጠበቀ የፀሐይ ኃይል የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት እንዲኖር በማድረግ መብራት እንዲያገኙ ለማድረግ በስፋት እየተሠራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በተለይ ገጠሩ አካባቢ ላይ ከልማቱ ጋር አብሮ የሚሄድ ወደፊት የሴቶችንም ጫና የሚቀንስ ንፁህ ምድጃ (Cleen cooking) ጭምር ለማሰራጨት የፀሐይ ኃይል /ሶላር ኢነርጂ/ ቴክኖሎጂ ፋይዳንም አስታውቀዋል። ይህ ቴክኖሎጂ ለማብሰያ በሚውልበት ሁኔታም ላይ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የማስፋፋት ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ይህም በዝቅተኛ ኑሮ ላይ የሚገኙ ማህበረሰቦችንና በጣም በርቀት ቦታ ያሉ የሚገኙ የገጠር አካባቢዎችን ማዕከል ባደረገ መልኩ በዓለም ባንክ ፕሮግራም በተለየ ፓኬጅ እንደሚሰራም አመልክተዋል።

ቴክኖሎጂ ለሚያበለፅጉ አካላትም የተወሰነ ማበረታቻ በመስጠት ቴክኖሎጂው በርካሽ ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆን እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል። በዚህም ሕብረተሰቡ እንዲደፋፈር እና እንደ ወፍጮ ቤት፣ አግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በመሳሰሉት ላይ እንዲሠራ እና እንዲለወጥ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

እነዚህን ሚኒ ግሪዶች በስፋት እየያዘ ያለው መንግሥት መሆኑን ጠቅሰው፣ የግሉ ዘርፍ መሥራት ሲፈለግ ሥራ አዋጭ እንዲሆን እና ሕብረተሰቡም ላይ አላስፈላጊ ታሪፍ እንዳይጭኑ ለማድረግ መንግሥት ለግሉ ዘርፍ ድጎማዎችን የሚያደርግበት ሁኔታ እንደሚኖርም ጠቁመዋል። ወደፊት ዋናው ግሪድ በአካባቢዎቹ ሲደርስ የሶላሪ ሚኒ ግሪዷ ወደ ዋናው ግሪድ እንደሚካተትም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ሶላር ኢነርጂ ልማት ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ተዋበች ወርቄ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ማህበሩ ንፁህ እና ታዳሽ ኃይል ለማቅረብ ዘላቂ አማራጮችን በማስተዋወቅ እየሠራ ይገኛል። ታዳሽ የኃይል አቅርቦት የሚያቀላጥፉ መሣሪያዎችን ተደራሽ እንዲሆኑም ተጠቃሚዎችንና አከፋፋዮችን በማስተሳሰር እና ከክልል የኢነርጂ ቢሮዎች ጋር የመግባቢያ ስምምነቶችን በማድረግ አቅራቢዎች ቴክኖሎጂውን ወደ ገጠሩ አካባቢ እንዲያሰራጩ እየሠራ ነው።

ማህበሩ ከተመሠረተ 10 ዓመታት የሞሉት ሲሆን፣ በእነዚህ ዓመታትም ከመንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ዘርፎች ጋር እየሠራ ነው። በተለይም ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር እንደ ፀሐይ ኃይል ባሉት /ሶላር ኢነርጂ/ ታዳሽ ኃይል ልማቶች ላይ በሚታቀድበት ወቅት ይህንኑ በሚያቀላጥፉ ተግባራት ውስጥ ይሳተፋል። ለወደፊቱ ለሚደረገው የታዳሽ ኃይል ልማት ፈር መያዝም ቁልፍ ድርሻውን እየተወጣ ይገኛል።

ተግባራዊ እንቅስቃሴው ላይም ትልቁ ተግዳሮት የነበረው ቴክኖሎጂው አዲስና በየጊዜው የሚቀያየር በመሆኑ ከታሪፍ አመዳደብ፣ እቃውን ካለማወቅ ጋር የተያያዙ ችግሮች ይገጥሙ ነበር። ቴክኖሎጂውን የመረዳት ችግር አንዱ ዋነኛ ችግር በመሆኑ ከሁለት ዓመት በፊት የሶላር ታሪፍ መመሪያ ( Solar Customs Handbook ) በማዘጋጀት ሥራ ላይ መዋሉን አስታውሰዋል። ይህም ሲዘጋጅ ከፋይናንስ ሚኒስቴር፣ ከውሃና ኢነርጂ ጉምሩክ ኮሚሽን፣ ከንግድ ሚኒስቴር፣ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ እና ኢሴዳ የግሉን ዘርፍ ወክሎ መመሪያው የበለፀገ መሆኑን ተናግረዋል። ይህ መመሪያ ከተዘጋጀ በኋላም እንደማጣቀሻ የሚያገለግል በመሆኑ በተሻለ ችግሮችን መቅረፍ መቻሉን ጠቅሰዋል።

መመሪያው ከሁለት ዓመት በኋላ በቅርቡ መሻሻሉን ጠቅሰው፣ መመሪያው የግል ዘርፉ በሶላር ሚኒ ግርድ የኃይል አቅርቦቱ ላይ ትክክለኛው ታሪፍ ምን እንደሆነ ባለማወቁ የሚፈጠሩትን የመረጃ ክፍተቶች እንደሚፈታ አመላክተዋል።

ከ350 ዋት በታች ያሉ የፀሐይ ኃይል ኤሌክትሪክ ቴክኖሎጂዎች በአጠቃላይ እውቅናቸው ሳይረጋገጥ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ የጥራት ሰርተፊኬት ከሚሰጡ ድርጅቶች ጋር እየተሠራ መሆኑንም ዋና ሥራ አስኪያጇ ገልጸዋል። ቀደም ሲል ትልቅ ተግዳሮት የሆነውና ገበያውን በብዛት የያዘው ከደረጃ በታች የሆነ ምርት እንደነበር አስታውሰው፣ ጥራቱን ያልጠበቀ የሶላር ምርት ሀገር ውስጥ እንዳይገባ አስገዳጅ ከሆነ በኋላ ችግሩን መቀነስ መቻሉንና በሂደትም ዜሮ ለማድረግ እንደሚሠራ ጠቁመዋል።

የሶላር ቴክኖሎጂዎቹን በአብዛኛው የሚጠቀመው የገጠሩ ሕብረተሰብ ነው ያሉት ወይዘሮ ተዋበች፣ የከተማው ነዋሪ በዚህ ላይ የሚገባውን ያህል እውቀት እንደሌለውም አስታውቀዋል። አርሶ አደሩን በመጠበቅ ቴክኖሎጂውን መጠበቅ እንደሚቻል ተናግረው፣ የገጠሩም ሆነ የከተማው ሕብረተሰብ የፀሐይ ኃይል ኤሌክትሪክ ኃይል ቴክኖሎጂ ላይ ግንዛቤ እንዲያገኝ ማድረግ እንደሚገባ አስታውቀዋል። ቴክኖሎጂውን ለመጠበቅ ተጠቃሚውን ጥራቱን ካልጠበቀ የቴክኖሎጂው ምርት መጠበቅ እንደሚገባ አስገንዝበው፣ የተጠቃሚውን ፍላጎት መጠበቅ ላይ በትኩረት እንደሚሠራ አስገንዝበዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You