የአዕምሮን ጦርነት ማሸነፍ

በሕይወታችን እንዳንለወጥ ያደረጉን ጠላቶቻችን ብዙ ናቸው። በጣም የምንፈልገውና በሕይወታችን ውስጥ ልናሳካ የምንመኘው ነገር እውን እንዳናደርግ ወደኋላ የጎተቱን፣ የተግባር ሰው እንዳንሆን ያደረጉን፣ እጀምራለሁ ያልነውን እንዳንጀምር፣ የጀመርነውን እንዳንጨርስ የከለከሉን በርካታ ጠላቶች አሉ። አንዳንዶቹ ጠላቶቻችን አዕምሯችንን ተቆጣጥረውታል። እነዚህ ጠላቶች ሃሳብ ብቻ፣ ጭንቀት ብቻ እንዲኖረን፣ የናፈቀንን ለውጥ እንዳናይ፣ ጊዜያችን እንዲባክን አድርገውናል።

ታዲያ እስከመቼ እነዚህ ጠላቶች ይጫወቱብናል። ስለዚህ መጀመሪያ ጠላቶቻችን እነማን እንደሆኑ ለይተን ማወቅ አለብን። ከዛ አንድ በአንድ እያንዳንዱ ላይ ጦርነት እናውጃለን። አንዳንዶቹ ጠላቶቻችንን ፊት ለፊት እንጋፈጣቸዋለን። አንዳንዶቹን ደግሞ ቀስ ብለን እያለሳለስን፤ እያጫወትን እንጥላቸዋለን። ሌሎቹን ጠላቶቻችንን ግን ወዳጃችን እንደርጋቸዋለን።

ሰን ዙ የተሰኘ ደራሲ the art of war በተባለ መጽሐፉ ‹‹ራስህንም ጠላቶችህንም የምታውቃቸው ከሆነ መቶ ጦርነት አያስፈራህም። ራስህን ብቻ የምታውቅ ከሆነ፤ ጠላቶችህን የማታውቸው ከሆነ ግን ብታሽንፋቸው እንኳን ነገ የመሸነፍና የመውደቅ ስጋት አለብህ። ጠላትህንም ራስህንም የማታውቅ ከሆነ ግን ሁልጊዜም በጦርነት በዝረራ ትሸነፋልህ›› ሲል አስፍሯል። ስለዚህ ራሳችንንም ጠላታችንንም የምናውቅበትን መንገድ ማወቅ ይኖርብናል።

ሮበርት ግሪን ዓለም ያጨበጨበለት ድንቅ ደራሲ ነው። ‹‹33 strategies of war›› በሚለው መጽሐፉ አስገራሚ 33 የጦር ሕጎችን አስቀምጧል። ሕጎቹ ጦርና ታንክ፣ መድፍና መትረየስ ታጥቀው ጦር ሜዳ ላይ ለሚደረጉ ጦርነቶች ብቻ አይደለም። በዚህ ዓለም ላይ ከራሳችን ጋር ላለን ግንኙነት፣ ከሰዎች ጋር ላለን ግንኙነት፣ አይምሯችን ውስጥ ለሚደረጉ ማንኛውም ዓይነት ጦርነቶች፣ የሃሳብና የጭንቀት ችግሮች ሁሉ መፍትሄ ናቸው። በጣም የሚያስገርመው የመጀመሪያው ሕጉ ነው። ይህ ሕግ ‹‹wage war on your enemies›› ይላል። ጠላቶችህ ላይ ጦርነት አውጅባቸው እንደ ማለት ነው።

ጠላት ጠላት ነው። አንተን ከመጣልና ወደኋላ ከማስቀረት ውጭ ሌላ ትኩረት የለውም። አንተ ደግሞ ህልም አለህ። ትልቅ ፍላጎት አለህ። ከሁሉ በላይ ደግሞ ፈጣሪህ ወደዚህ ምድር ያመጣህ ለትልቅ አላማ ነው። አላማህንና ህልምህን ለማሳካት ስትጓዝ ሊያደናቅፍህ ይችላል። እንዴት አድርገህ ነው ታዲያ ይህን ጠላት የምታሸንፈው? እነሆ መልሱ…..

የመጀመሪያው እንዳትለወጥ ያደረገህ፣ አቁሞ ያስቀረህና ትልቁ ጠላትህ ስንፍናህ ነው። ለነገ ብለህ ያሳደርከው፤ ማድረግ እያለብህ ያላደረከው። መሥራት እያለብህ ያልሰራኸው ሥራ በሙሉ ባለህበት ቆመህ እንድትቀር፤ ገቢህ እንዳይነቃነቅ አድርጎሃል። ሰዎች ሁሌም አሸናፊ የሚሆኑት ስንፍናቸውን ታግለው ሲሉ ነው። እንደውም ሰምታችሁ ከሆነ ‹‹ጀግና ማለት ራሱን የሚያሸንፍ ነው፤ ያኔ ማንም አይጥለውም›› ይባላል። እውነት ነው። ትልቁ ጦርነት ያለው ውስጥ ነው። ፊታውራሪውና ትልቁን ውስጣዊውን ጦርነት የሚመራው ደግሞ ስንፍና ነው።

እስኪ እሠራዋለሁ ያልከውን ስፖርት መሥራት ብትጀምር፣ እጀምረዋለሁ ያልከውን ንባብ ወይም አዲስ ኮርስ፣ አዲስ የቋንቋ ልምምድ አልያ በቅርቡ እጀምረዋለሁ ያልከውን አዲስ ቢዝነስ ብትጀምረው፣ ትምህርትህን በደንብ አድርገህ ብታጣና፣ ያሰብከውን፣ ያለምከውንና የቀድከውን በሙሉ ብታደርግ፣ ለራስህ የገባኸውን ቃል ብትጠብቅ ምን ዓይነት ሰው እንደምትሆን አስበው! አንተን ማን ነው የሚያቆምህ? የትኛውንም ህልምህን ታሳካዋለህ።

ይህን ግን እንዳታደርግ ስንፍና እየጎተተህ ነው። ያንተ ሕይወት የሚቀየረው መንግሥት ሲቀየር አይደለም። ሥርዓት ሲለወጥ አይደለም። ሚስትህ፣ ጓደኞችህ፣ ቤተሰቦችህ፣ በዙሪያ ያሉ ሰዎች ሲስተካከል አይደለም ሕይወትህ የሚቀየረው። ሕይወትህ የሚቀየረው ስንፍናህ ከስልጣኑ ሲወርድ ነው። ያንተን ሕይወት የሚያዘው ማነው? አንተ ነህ ወይስ ስንፍናህ ነው? እስኪ ተመልከት አንዳንድ ጊዜ ደክሞሃል። ተኛህ። ኧረ ተኝተህ አርፍድ! ለምን ቲቪ አታይም! አሁን እኮ ደብሮሃል! ፈታ የሚያደርግህ ነገር ያስፈልግሃል …. ወዘተ አድርግ እያለህ የተቆጣጠርህ ስንፍናህ ነው። እናዳትለወጥ ያደረግህ እሱ ነው።

ስንፍናህ ላይ ጦርነት አውጅ። እንዴት አድርጌ? ካልክ መጀመሪያ ምን ያህል ከምትፈልገው ነገር እያስቀረህ እንደሆነ አስብ። ያመጣብህን ጉዳት አስበው። በስንፍናህ ምክንያት ስንት ነገር እንዳመለጠህ አስብ። በነገራችን ላይ ራስህን የምትቀይረው ለራስህ ብቻ ብለህ አይደለም። አንተን የሚፈልጉና አንተን የሚጠብቁ ቤተሰቦች አሉህ። ሀገርህ ትጠብቅሃለች። ታዲያ በስንፍናህ ምክንያት እንዴት ነው ከዚህ ሁሉ ነገር የምትቀረው? ስንፍናህን ካልቀበርከው ሊቀብርህ ነው። እንዴት አድርጌ ላስተካክለው ካልክ….

ሁልጊዜ ምቾት የሚነሳህና የሚጎረብጥህን ነገር ማድረግ ተለማመድ። ምን ማለት ነው ለምሳሌ አንተ ሁልጊዜ በሙቅ ውሃ ይሆናል ገላህን የምትታጠበው። እስኪ ነገ ተነስተህ በቀዝቃዛ ውሃ ታጠብ። የጤና ችግር የማያመጣብህ ከሆነ ነው ታዲያ! ወይ ደግሞ ስፖርት እስራለሁ ብለህ ብዙ ጊዜ ለራስህ ቃል ገብተህ ሊሆን ችሏል። እስኪ በጠዋት ተነስተህ መሮጥ ጀምር። ወይም ቀለል ያለ የአካል እንቅስቃሴ አድርግ። ማንበብ የማትወድ ከሆነ ራስህን አስጨንቀህ፤ ቁጭ አድርገህ አንድ አምስት ገፅ ለማንበብ ሞክር። ይህንን በየቀኑ ደጋግመው።

ራስህን ማስጨነቅና ከምቾት ማስወጣት ስትጀምር የሆነ ነገር አስበህና አቅደህ የመፈፀም ብቃትህ ይጨምራል። ራስህ ላይ አዛዥ ሁን። ራስህን ምቾት እየነሳህ ብዙ ርቀት ውሰደው። የሆነ ነገር ልታደርግ አስበህ ግን እኮ ደክሞሃል፣ ደብሮሃል፣ ለምን አትተኛም፣ ለምን ቲቪ ከፍተህ አታይም ሲልህ፣ ከምትፈልገው ነገር ሊያስቆምህ አይምሮህ የሆነ ሃሳብ ሲያመጣ እጅ ከፈንጂ ያዘውና እንደዚህ አድርገህማ ሰነፍ አታደርገኝም ብለህ ያሰብከውን ነገር ወደተግባር ግባ። ስንፍና የተባለ ጠላታችንን መዘረር ይቻላል። ነገር ግን ትእግስትና ፅናት ይጠይቃል።

ለምን መሰለህ ዛሬ አሸነፍኩት ብለህ፤ በጣም ቆንጆ የሥራ ቀን አሳልፈህ በማግስቱ አቅሙን አሰባስቦ መጥቶ ሊያሸንፍህ ይችላል። ሰነፍ ሊያደርግህ ይችላል። ስለዚህ ሁልጊዜ ላታሸንፈው ትችላለህ። ራስህን እንዳትጎዳ ለምንድነው ጎበዝ ያልሆንኩት፣ የሰነፍኩት ብለህ አትናደድ። በፅናት ለማሸነፍ መታገል አለብህ እንጂ እጅ መስጠት የለብህም። አንዳንድ ጊዜ ትናንሽ ግጥሚያዎችን ልትሸነፍ ትችላለህ ዋናው ነገር ትልቁን ጦርነት ማሸነፍህ ነው።

መቼም ታውቃላችሁ የዋንጫ ቡድን አንዳንዴ ነጥብ ይጥላል፤ ይሸነፋል፤አቻ ይወጣል። ሁሉንም ጨዋታ በተከታታይ አያሸንፍም። ነገር ግን አብዛኛውን ጨዋታ ስለሚያሸንፍ ዋንጫውን ይበላል። አንዳንድ ጊዜ ልትሸንፍ ትችላለህ። ስህተት ልትሰራ ትችላለህ። ነገ ጠዋት እነሳለሁ ብለህ ተኝተህ ልታረፍድ ትችላለህ። ችግር የለውም! በማግስቱ ግን ራስህን መልሰህ አነቃቅተህ ወደ ሥራ መመለስ አለብህ። ስንፍናህ ላይ ጦርነት አውጅበት!

ሁለተኛው አይምሮህን ተቆጣጥሮ እንዳትለወጥ፣ በሰዎች ለውጥ እንዳትቀና የሚያደርግህ፣ አንተን ባለህበት የሚያስቀርህ ትልቁ ጠላትህ ፍርሃት ነው። ብዙ ዓይነት ፍርሃት አለ። ያመኑትን ለማድረግ የሚፈሩ ሰዎች አሉ። ብዙ ነገር መጀመር ይፈልጋሉ። አዲስ ነገር ውስጥ መግባት፣ አዲስ ቢዝነስ፣ አዲስ ሥራ ግን ቢበላሽብኝስ ሰዎች ምን ይሉኛል ብለው የሚፈሩ በርካታ ሰዎች አሉ። አንዱ አንተ ልትሆን ትችላለህ። ከስንፍና ቀጥሎ የሰው ልጅ ላይ እንደፍርሃት ጢባ ጢቤ የሚጫወት ነገር የለም።

ሰዎች እድሜያቸው ሰባና ሰማንያ ካለፈ በኋላ በሕይወታችሁ መለስ ብላችሁ ሄዳችሁ ማስተካከል የምትፈልጉት ነገር ምንድን ነው? ‹‹በጣም የሚቆጨኝ ድሮ አደርጋለሁ ብዬ ሰዎችን ፈርቼ እንዲህ ቢሆንስ ብዬ ያላደረኳቸው፤ በፍርሃቴ በምክንያት ያጧቸው ነገሮች ተመልሼ ሄጄ ባደርጋቸው›› ይላሉ። አየህ ! አንተ ብቻ አይደለህም። ብዙ ሰዎች ይፈራሉ።

እስረኛው ሁለት ምርጫ ቀረበለት። አንደኛው እዚህ ገመድ ላይ ተንጠልጥለህ ብትሞት ይሻልሃል፤ ሁለተኛው በዚህ ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ብታልፍ ይሻልሃል። መጀመሪያ የሚንጠለጠልበትን ገመድ አየው። ከዛ ድቅድቅ ጨለማውን በደንብ አየውና ቶሎ ወሰነ። አይ እዚህ ገመድ ላይ አንጠልጥሉኝ አለ። ሰዎች ግን ስቀው ያንን ትንሽ ድቅድቅ ጨለማ ብትጓጓ ኖሮ ነፃ ያወጣህ ነበር፣ ከእስር ይፈታህ ነበር አመለጠህ አንተ ግን ገመዱን መረጥክ አሉት። አንዳንድ ግዜ በሕይወታችን የምንፈራቸው ነገሮች መድረሻቸውን ስለማናውቅ ነው። ቀጥሎ ምን እንደሚፈጠር ስለማናውቅ ነው። ነገር ግን ሕይወታችንን የሚቀይሩ ነገሮች ይኖራሉ።

ከምቾት መውጣት እንፈራለን። ለምን? እንዲህ ብሆንስ፣ ይሄ ነገር ቢገጥመኝስ እንላለን። በጣም የሚገርመውና ሕይወታችንን የሚቀይረው ከፍርሃታችን ጀርባ ያለው ነገር ነው። እሺ! ፍርሃቴን እንዴት ላጥፋው ካላችሁ ፍርሃት የሚጠፋው በዝግጅት ነው፤ በጭፍን ድፍረት አይደለም። የሚዘጋጅ ሰው፣ አቅምን ያፈረጠመ ሰው ማንም ሊዋጋው አይሞክርም። ራስህን ብቁ ስታደርግ፣ ራስህን ስታዘጋጅ በእውቀት፣ በልምድ፣ በገንዘብና በማንኛውም ነገር ራስህን እያዘጋጀህ ስትሄድ ፍርሃት ራሱ ይፈራሃል።

ቀስ እያልክ ነው ፍርሃትን የምታሸንፈው። ራስህ ላይ እየሰራህ፣ በራስ መተማመንህን እየገነባህ ቀስ እያልክ ጭራውን ትይዘዋለህ። ያኔ ራስህን ለመለወጥ ትጀምራለህ። የሚያስፈራህን ነገር ትጋፈጠዋለህ። ነገር ግን በአንድ ጊዜ ከመሬት ተነስተህ ፊት ለፊት ፍርሃትህን መጋጨት የለብህም። ያ ዋጋ ያስከፍልሃል። ስለዚህ ተዘጋጅ። በሕይወትህ ትልቅ ነው ብለህ የምታስበውን ነገር ለማሳካት ምንድን ነው የሚያስፈልግህ፣ ምን ዓይነት ዝግጅት ነው የሚያስፈልግህ፣ ምን ዓይነት የትምህርት ደረጃ፣ እውቀት፣ ልምድ፣ ገንዘብ ነው የሚያስፈልግህ? በትንሹ ብትጀምረውስ? ደረጃ በደረጃ የፈራኸውን ችግር ብትዳፈረውስ ? ሕይወትህ እስከመጨረሻው ይቀየራል።

ሶስተኛው ትልቁ ጠላቶችህ አላማህ እንዳይሳካ መሰናክል የሆኑ ሰዎች ናቸው። ሁሉም ሰው ላንተ መልካም ሊሆን አይችልም። እንኳ አንተ የሃይማኖት መሪዎች ሳይቀር በሰዎች ተገፍተዋል። መልካም ሆነው ሳለ የሰዎች ምላሽ ግን አሉታዊ ይሆናል። ስለዚህ ሁሉም ሰው ይወደኛል ብለህ አታስብ። ሁሉንም ሰው ለማስደሰትም አትሞክር። እንደውም ሁለት ዓይነት ሰዎች አሉ ከአንተ አላማ ጎን የሚሰለፉ። ሌሎቹ ደግሞ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ከአላማህ በተቃራኒ የሚሰለፉ። እነዚህ ሰዎች ሁሌም ባለህበት ቆመህ እንድትቀር፣ እነርሱን እንድትመስል በተለያየ መልኩ ተፅእኖ ሊያሳድሩብህ ይችላሉ።

እነዚህ ሰዎች ፊት ለፊት መጥተው አይጫኑህም። በእጅ አዙር ግን ይቆጣጠሩሃል። ታዲያ መቼ ነው ከእነርሱ እስረኝነት ነፃ የምትወጣው? ጠላት ማለት ጎራ ለይቶ በግላጭ ፊት ለፊት የሚያጠቃ ብቻ አይደለም። አብሮ ሆኖ ስሜትና አይምሮህ ላይ የበላይነት ይዞ የሚነዳህም ጠላት ነው። እነሱ ላይ ነው ጦርነት የምታውጀው። የሆነ ነገር ስታስብ አሉታዊ ነገር የሚነግሩህ ሰዎች አሉ። ህልምህን፣ አላማህን ያሰብከውን ነገር ስትነግራቸው ሁልጊዜ በፍፁም እንደማይሆን፣ አንተ ልታሳካው እንደማትችል የሚነግሩህ ሰዎች አሉ። አትችልም፣ አርፈህ ቁጭ በል፣ የት ልትደርስ ነው፣ በዚሁ መቀጠል አይሻልህም የሚሉ ሰዎች አሉ።

ከእንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ጋር መዋል አቁም። ውሎህን ቀይር። መድሃኒት እሱ ብቻ ነው። የእነርሱን አስተሳሰብና አይምሯውን መቀየር አትችልም። መጀመሪያ ራስህን ነው መቀየር የምትችለው። ስለዚህ ሕይወት ምርጫ ነው። ወይ እነርሱን ትመርጣለህ ወይ ደግሞ አላማህን። ቀጣዩን የሕይወትህን አዲሱን አቅጣጫ ትመርጣለህ። እውነተኛ ለውጥ ስታመጣ የምትርቃቸው ጓደኞችህ ይኖራሉ። የምታስቀይማቸው ቤተሰቦች ይኖራሉ። የጠፋኸው ግን ለመልካም ነው። ራስህን በመልካም ሰዎች በሚለውጡ፣ ከአላማህ ጋር አብረው በሚሄዱ ሰዎች መክበብ አለብህ። ከዛ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጡን ታየዋለህ።

አራተኛው የራስህ ጠላት ራስህ ነህ። አንተ ራስህን የወቀስከውንና የጠላኸውን ያህል ማንም አልወቀሰህም። ብዙ ሰዎች ራሳቸውን የሚያጠፉት በውጫዊ ምክንያት አይደለም። ከራሳቸው ገራ የለየለት ግጭት ውስጥ ገብተው ነው። አንተን የሚቀየር ትልቅ ኃይል የተቀመጠው ደግሞ ውስጥህ ነው። ውስጥህ፣ ስሜትህና መንፈስህ ሲጠነክር ምንም ነገር በዚህ ዓለም አያቆምህም። ውስጥህ ሲልፈሰፈስ ግን የሰዎች መጠቀሚያ ትሆናለህ። የሆነ ነገር ሲጠፋ እየደጋገምክ ራስህን የምትወቅሰውና የምትሰድበው ከሆነ በራስ መተማመንህ ይጠፋና ስሜትህና አቅምህ ኩምሽሽ ይላል።

ከዓመታት በፊት ባጠፋኸው አንድ ጥፋት ምክንያት ሺ ጊዜ በየቀኑ ራስህን ትቀጠቅጠዋለህ። ራስህን ትወቅሰዋለህ። እንዲህ ባላደርግ ኖሮ እያልክ ትቆጫለህ። አንድ ጊዜ ራስህን ከወቀስከው አይበቃም? ለዛ ነው የራስህ ጠላት ራስህ ነህ የምንለው። እስካሁን ያወጅከው ጦርነት ነው። አሁን ግን ራስ ላይ የምታወጀው ፍቅር ነው። ያደረካቸውን መልካም ነገሮች አስብ። ፈጣሪህ ፅናቱንና ትእግስቱን ባይሰጥህ ኖሮ የማታልፋቸው ብዙ መሰናክሎች ነበሩ።

ስለዚህ ራስህን ከመውቀስ ይልቅ ፈጣሪህ ያደረገልህን ነገር እያሰብክ ማመስገን በጣም ወሳኝ ነው። ጉልበት ይሰጥሃል። ትላንት ያሳካኸውን ስታስብ ነገ አያስፈራህም። ብዙ ነገር ማሳካት እንደምትችል ልበ ሙሉ ትሆናለህ። ራስህን አበርታው፤ ራስህን አጠንክረው!!

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You