በዓለማችን በአሁን ወቅት የብዙ ዜጎችን ሕይወት እየቀጠፉ ከሚገኙ ሰው ሠራሽ አደጋዎች መካከል አንዱና ዋነኛው የትራፊክ አደጋ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እኤአ በ2023 ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው በዓለማችን በ24 ሰከንድ ውስጥ አንድ ሰው በትራፊክ አደጋ ሕይወቱን ያጣል። በየዓመቱ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በዚሁ አደጋ ሕይወታቸውን ያጣሉ።
በሁሉም የዓለም ክፍሎች የትራፊክ አደጋዎችን መስማት እየተለመደ መጥቷል። እነዚህ አደጋዎች የሕይወትና የንብረት እንዲሁም የአካል ጉዳትን በከፍተኛ ደረጃ እያደረሱ ይገኛሉ። ይህ አደጋ የማይመለሰውን የሰውን ሕይወት እየወሰደ ነው።
የትራፊክ አደጋ ቀላል የማይባል ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ ቀውስ እያስከተለ ይገኛል። ትራንስፖርት አገልግሎት ከዜጎች እንቅስቃሴና ከተሸከርካሪዎች ዝውውር ጋር ተቆራኝቶ ባለመመራቱ እየደረሰ ያለው አደጋ በየቀኑ እየጨመረ ነው።
በኢትዮጵያም በአሁን ወቅት የትራፊክ አደጋ የብዙዎችን ሕይወት እየቀጠፈ፣ ብዙዎችን ለአካል ጉዳት እየዳረገ፣ የብዙዎች ሕይወት እያመሰቃቀለ፣ ሕፃናት ያላሳዳጊ አዛውንቶችን አለጧሪ ቀባሪ እያስቀረም ይገኛል። በተለያዩ ጊዜያት የትራፊክ አደጋ አሳሳቢነት ይነሳል፤ ግንዛቤ ለማስጨበጥም ሆነ አደጋውን ለመቀነስ ንቅናቄዎች ይከናወናሉ። ይሁን እንጂ ችግሩ የሚያስከትለው የሰውም ሆነ የንብረት ኪሳራ ማስቆም አልተቻለም።
የዓለም ጤና ድርጅት በየጊዜው በሚያወጣው ሪፖርት እንዳመለከተው በዓለም ላይ የትራፊክ አደጋ እየጨመረ ነው። ለመጨመሩ ዋነኛ ምክንያት እየሆኑ ያሉት ደግሞ እያደጉ ያሉ የሶስተኛው ዓለም ሀገራት ናቸው ብሏል። ሪፖርቱ እንደተቃርኖ ያነሳው እነዚህ የዓለምን ሁለት ሶስተኛ የሚያህል ሕዝብ የያዙ ሀገራት ያሏቸው የተሽከርካሪ ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም በአደጋው ግን አንደኛ መሆናቸውን ነው።
የተሽከርካሪ ቁጥራቸው ከሕዝባቸው የሚልቅ አንዳንድ ሀገራት የትራፊክ አደጋ ምጣኔአቸው እጅግ ትንሽና የለም በሚባልበት ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው። ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ከ120 ሚሊዮን ሕዝብ ትያዝ እንጂ የተሽከርካሪዎቿ ቁጥር አንድ ሚሊዮን እንኳ የሞላው በቅርቡ ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያ ከፍተኛ አደጋ ከሚያስተናግዱ ሀገራት ተርታ የምትመደብ ነች።
ይሄ ለምን ሆነ ተብሎ በየጊዜው ጥናቶች ይጠናሉ፣ አዋጅ፣ ሕግ፣ ፖሊሲ፣ መመሪያ፣ ደንብና የመሳሰሉትም ይረቃሉ፣ ይጸድቃሉ። ነገር ግን እራሳቸው መመሪያዎቹ ይሁኑ አተገባበራቸው ለውጥ ሲያመጡ አይታይም። ከሪፖርት ፍጆታ ከመዋል አላለፉም።
በ2015 በጀት ዓመት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በደረሱ የትራፊክ አደጋዎች 3 ሺህ 577 ሰዎች ሲሞቱ 5 ሺህ 818 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሷል። ይህ ማለት ቢያንስ በየቀኑ 13 ሰዎች ይሞታሉ እንደማለት ነው። በንብረት ላይ በደረሰ አደጋ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ሀብት ከጥቅም ውጭ ሆኗል።
በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቀነስ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ቢከናወኑም የትራፊክ አደጋን መስማት የእለት ተእለት ተግባራችን ሆኗል። ለእነዚህ አደጋዎች መበራከት ድርሻ አላቸው የሚባሉ አካላት አሉ።
በመጀመሪያ የአሽከርካሪዎች የባህሪ ችግር እንደሆነ በተለያዩ ጥናቶች ተረጋግጧል። ጥናቶች እንደሚሉት 68 በመቶው በአሽከርካሪዎች ችግር፣ ሁለተኛው ለአደጋዎች መከሰት 14 በመቶ ድርሻ የያዘው የተሽከርካሪ የቴክኒክ ችግር፣ ሶስተኛው የመንገደኞች የመንገድ አጠቃቀም ችግር፣ አራተኛው የመንገድ ችግር፣ ሌላኛው የአየር ፀባይ ሁኔታ የራሱ የሆነ ድርሻ አለው።
የጥናት ውጤቶች እንደሚያሳዩት ለትራፊክ አደጋ መበራከት ምክንያት ከሆኑት ነገሮች መካከል የአሽከርካሪ ብቃት አለመኖር፣ ጠጥቶ ማሽከርከር፣ እንደ ጫት ያሉ አነቃቂ ነገሮች ወስዶ ማሽከርከር፣ የመንገድ ብልሽት ፣የተሽከርካሪ ብቃት ጉድለትና መሰል መንስኤዎች ናቸው።
ለአብነት ያህል በሀገራችን በ2014 በጀት ዓመት ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ የደረሰበት ሲሆን ከ40 ሺህ በላይ የትራፊክ አደጋዎች ተከስተዋል። ለእግረኞች ቅድሚያ አለመስጠት፣ ከፍጥነት በላይ ማሽከርከርና እርቀትን ጠብቆ አለማሽከርከር የሚሉት የትራፊክ ደንብ ጥሰቶች ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ።
በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ስድስት ወራት በተከሰቱ የትራፊክ አደጋዎች 1 ሺህ 368 ዜጎች ሕይወትን ሲቀጥፍ 2 ሺህ 600 ሰዎች ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። በዚህም የትራፊክ አደጋ ከ1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ የንብረት ኪሳራ ማድረሱም ታውቋል።
በኢትዮጵያ በአማካኝ በየቀኑ ቢያንስ 13 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ምክንያት ሲሞቱ 31 ያህሉ ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት እንደሚያስተናግዱ መረጃዎች ይነግሩናል። 68 ነጥብ 1 በመቶ ያህሉ አደጋዎች የሚከሰቱት ምቹ በሆኑ መንገዶች መሆኑ ሲሰማ በራሱ ለምን የሚል ጥያቄ እንዲነሳ ያስገድዳል። ዝቅተኛ የተሽከርካሪ ቁጥር ያላት ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ የሚከሰትባት ሀገር የሚል ቅፅል የሰጧትም አልጠፉም፤ ለኢትዮጵያ።
ይህ ለምን ሆነ ሲባል ብዙ ምክንያቶችን ማንሳት እንችላለን። በቁጥሮች ማስረጃነት ስንመለከት 68 በመቶ በአሽከርካሪዎች ብቃት ማነስና ቸልተኝነት የሚመጣ አደጋ እንዲሁም 14 በመቶ ደግሞ በተሽከርካሪ ቴክኒክ ምክንያት የሚደርስ ነው። አሽከርካሪዎች፣ የተሽከርካሪ ባለንብረቶች፣ የአሽከርካሪ ማሰልጠኛዎች፣ የተሽከርካሪ መርማሪዎች፣ ሕግ አስከባሪ አካላት ለሀገርና ለሕዝብ ቅድሚያ በመስጠት ውድ የሰው ሕይወትና የንብረት ውድመትን በማትረፍ 82 በመቶ አደጋን መቀነስ ይቻላል ማለት ነው።
ከትራፊክ አደጋዎች መበራከት ጋር ተያይዞ የደንብ አስከባሪዎችና የትራፊክ ባለሙያዎች የክትትልና የቁጥጥር ሥራ መላላት አስተዋፅኦ አለው። ባለሙያዎች ከአሽከርካሪዎች ጋር በመመሳጠር ደንብንና ሥርዓትን ከማስከበር ይልቅ በሕገ ወጥ መንገድ የግል ጥቅማቸውን ሲያሳድዱም ይስተዋላል። ታዲያ የሕግ የበላይነትን ከማስጠበቅ በኩል የአሠራር ጥሰቶችን በሚፈፅሙት ላይ ርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል።
በእጆቻችን የምንይዛቸው መኪኖች ያለብንን ኃላፊነት መወጣት እንድንችል ቀድሞ ጥያቄ የሚነሳባቸው ናቸው። በሰላም ወጥቶ መግባት ለነገ የተቀመጠ ትልቅ ህልም ማሳካት፣ ለሌሎች ሀዘን ተጠያቂ ለመሆን ይህንን እና ከፀፀት የፀዳ ቀንን እንድናሳልፍ ሁላችንም ኃላፊነታችንን መወጣት አለብን።
ከዓመታት በፊት የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የፍጥነት ወሰንን መነሻ አድርጎ ለውጥ ለማምጣትም በመንግሥት ደረጃ መጀመሩ እናስታውሳለን። ለተከታታይ ዓመታትም ንቅናቄው ስለመካሄዱ አይረሳም። ይህ የ‹‹እንደርሳለን›› ዘመቻ ያመጣው ውጤት ምንድነው? የት ደረሰ? ቀጣይስ ምን መሠራት አለበት? የሚሉና መሰል ጉዳዮችን አንስቶ ምክክር ማድረግ ያስፈልጋል።
የትራፊክ አደጋ ሀገርና ሕዝብ እያደረሰ ካለው ተያያዥ ቀውሶች አንፃር ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ህብረተሰቡም ከመዘናጋት ሊወጣ በጥንቃቄ ሊጓዝ ይገባል። ሁላችንም ዛሬ በወሬ የምንሰማው ነገ ላይ በእኛና በቤተሰባችን ላይ ሊደርስ ከሚችለው አደጋ ራሳችንን ለመጠበቅ ሌላውንም ለመጠበቅ ካሁኑ ሥራ መጀመር አለብን።
በአሽከርካሪዎች ምክንያት የሚደርስ አደጋ አንድም ሕጉን በሚገባ ባለማወቅ የሚከሰት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በአሽከርካሪ ቸልተኝነት ወይም ትኩረት ባለመስጠት ምክንያት የሚፈጠር ነው። በዚህም ብቁና ሕግ አክባሪ አሽከርካሪዎች በማፍራት ብቻ ሊደርስ ከሚችለው የትራፊክ አደጋ 68 በመቶውን መቀነስ እንችላለን ማለት ነው። ስለዚህ ብቁና ሕግ የሚያከብር አሽከርካሪ ማፍራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይጠበቃል።
ለጥቂት ጊዜ ለውጦችና ቁጥጥሮች ይታዩና ተመልሶ ወደነበረበት አዘቅት ይወርዳል። ዋና ከተማዋን ጨምሮ በሁሉም አካባቢዎች ተሽከርካሪዎች ከአቅማቸው በላይ ሲጭኑ የሚቆጣጠራቸው አካል የለም። ከስንት አንድ ቢገኝ እንኳ ብጣሽ ሳንቲም ተቀብሎ፣ የራሱንም ክብር አዋርዶ፣የሰውንም ሕይወት ክብር አውርዶ ተሽከርካሪውን ለውድመት ተሳፋሪውን ለሞት ወደሚዳርገው አደጋ ይነዳዋል።
ለእነዚህ አደጋዎች መንስኤ ከአሽከርካሪው ጀምሮ፣ ተሳፋሪዎች፣ ተቆጣጣሪዎች ሁላችንም ነንና መፍትሔውም የጋራችን መሆን አለበት። ቁጥጥሩ እውነተኛ ለውጥ ለማምጣት እንጂ ኪስን ለማደለብ እንዳይሆን የአሽከርካሪ ብቃት በየጊዜው ቢመዘን፣ ጉዳት ካደረሰም የማያዳግም ወስዶ መንጃ ፍቃዱን እስከመጨረሻው እስከመንጠቅ ድረስ መድረስ ቢቻል፣ ጥፋተኛ ተሳፋሪና እግረኞችም የሚቀጡበት መንገድ ቢመቻች፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ በዘመቻ ሳይሆን በተከታታይ ለውጥ የሚያመጣ ትምህርት ቢሰጥ አደጋው የማይቀንስበት ምክንያት አይኖርም።
በቁጥጥር ስራውም የደህንነት ቀበቶ መመሪያ በአግባቡ ስራ ላይ ማዋል፣ራዳርን በመጠቀም ከፍጥነት በላይ የሚያሽከረክሩ አሽከርካሪዎችን መከታተል፣ ፎርጅድ የመንጃ ፍቃድን መቆጣጠር፣ ከመናኽሪያ ውጪ የሚጭኑ ተሸከርካሪዎችና በተመረጡ አካባቢዎችም ድንገተኛ የቴክኒክ ምርመራ በማድረግ የቴክኒክ ጉድለት ያለባቸውን የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል።
ሰውን ያህል ትልቅ ፍጥረት ይዞ ለመጓዝ የተዘጋጀ አሽከርካሪ የተሰጠውን አደራ በአግባቡ መወጣት ከቻለ፣ ታሞ ችግር አጋጥሞት አሊያም በተለያየ ምክንያት ሕክምና ፈልጎ በቴክኒክ ብቃት ቁጥጥር ተቋም የተገኘ ተሽከርካሪ ደህንነት በማረጋገጥ በኩል ደግሞ ኃላፊነት ያለባቸው ሰዎች ሌላው ቀርቶ በዚህ መኪና የእኔ ሰው ሊጓዝ ይችላል የሚል የህሊናን ጥያቄ መመለስ ከቻሉ፣ በእግሩ የሚንቀሳቀሰው ነዋሪም ለደቂቃ መቆም ተስኖት፣ ትእግስት ርቆት ራሱን ለአደጋ ማጋለጥ ቢቆጠብ፣ እኔ ልቅደም እኔ ልቅደም ዓይነት ያልተገባ እሽቅድምድም በመንገዶች ላይ የሚያደርጉ አሽከርካሪዎች ከዚህ ተግባራቸው መታቀብ፣ ልንገለገልባቸው በራሳችን በተፈጠሩ ተሽከርካሪዎች ምክንያት መሞታችን፣ ጉዳት ማስተናገዳችን መቀነስ ከፍ ሲልም እስከ ወዲያኛው ማስቆም እንችላለን።
ታሪኩ ዘለቀ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 26 ቀን 2016 ዓ.ም