ትውልዳቸው ትግራይ ክልል ተንቤን ውስጥ ገብረ ስብሐት ኢየሱስ ገለበዳ አካባቢ ነው። አቶ አብርሃ መስፍን እና ወይዘሮ ምፅላል ገብረ ሚካኤል ከወለዷቸው ዘጠኝ ልጆች መካከል ንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ ስምንተኛ ልጅ ናቸው። ባል እና ሚስቱ በቅዱስ ቁርባን በተክሊል የተጋቡ ሲሆን፤ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ሁለቱም በ80 ዓመታቸው ነው። የንቡረ እድ ኤልያስ እናት እስከ ሰባት ቤተሰብ ድረስ ካህን ናቸው። የአባታቸው ቤተሰብ ደግሞ ወደ ቤተ መንግሥት የቀረቡ ናቸው።
የንቡረ እድ ኤልያስ ቤተሰቦች በግብርና የሚተዳደሩ ሲሆን፤ ጊዜው እና ቦታው በሚፈቅደው ልክ የሞላላቸው፤ ከራሳቸው አልፈው ለሌላም የሚተርፉ ደኅና የሚባል ኑሮን የኖሩ ነበሩ። አቶ አብርሃ ልጆቻቸው እንዲዋሹ፣ እንዲሰርቁ ካለመፍቀድ ባሻገር ለልጆቻቸው እንደጎረቤቶቻቸው ነፃነት አይሰጡም ነበር። በዚህ ምክንያት ንቡረ እድ ኤልያስ እጅግ ተገድበው በግ እና ፍየል እየጠበቁ መኖር ግዴታቸው ነበር። ዕድሜያቸው ከፍ ሲል ግን ከቤተሰቡ ተለይተው ፊደል ለመቁጠር የታደሉት እርሳቸው ብቻ ሆኑ።
ፊደል ለመቁጠር ዕድል የሰጣቸው ደግሞ ገና በሕፃንነታቸው በሚያነሡት የተለያዩ ጥያቄዎች ምክንያት ነበር። በአቅራቢያቸው ቤተ ክርስቲያን በመኖሩ ሕፃን ሆነው ማታ ማታ ሰዎች የቄስ ትምህርት ጮኸው ሲማሩ ይሰሙና፤ ከአባታቸው ጋር ሲተኙ ‹‹እነዚህ ሰዎች ለምን ይጮሃሉ?›› የሚል ጥያቄ ያቀርባሉ። ትምህርት እየተማሩ መሆኑ ሲነገራቸው ‹‹ትምህርት ምንድን ነው?›› የሚል ጥያቄ አቀረቡ። አባታቸው አቶ አብርሃ የሚያውቁት ዳዊት ሳይሆን የትውልድ ሐረግ ነው። ስለዚህ ለልጃቸው በራሳቸው እናት እና አባት በኩል እስከ ሃያ በሚስታቸው እናት እና አባት በኩል ደግሞ እስከ ሰባት የትውልድ ሐረግ አስቆጠሯቸው።
ንቡረ እድ ኤልያስ የትውልድ ሐረጋቸውን ሸምድደው ለመያዝ ብዙ ጊዜ አልፈጀባቸውም። ‹‹የማን ልጅ ነህ?›› ሲባሉ የቤተሰብ የትውልድ ሐረጋቸውን ያነበንባሉ። እናት እና አባታቸው ሰባት ትውልድ ላይ ቤተሰባቸው ይገናኛል። ስለዚህ እናቱን እና አባቱን አንድ የሚያደርግ ልጅ ተብለው ታዋቂነትን አተረፉ። ሰው ሲያደንቃቸው ተደሰቱ፤ ስለዚህ አባታቸው ‹‹ልጄ ትምህርት ይሆንለታል›› ብለው አሰቡ።
እናት የካህን ቤተሰብ በመሆናቸው ልጃቸው እንደ አባታቸው ካህን እንዲሆኑ እና የአባታቸውን መስቀል እንዲይዝ ፈለጉ። አባት በበኩላቸው የተወሰደባቸውን መሬት ተከራክረው ለማስመለስ ፀሐፊ ፍለጋ በመንከራተታቸው ልጃቸው ተከራክሮ እንዲያስመልስላቸው ተመኙ። ንቡረ እድ ኤልያስ ተማር ሲባሉ ፊደል ስለማያውቁ እና ጎረቤት ያዩትን ትልቅ ዳዊት ሲያዩ ያንን ሁሉ ማጥናት ይከብደኛል ብለው ስለፈሩ ለመማር ፈቃደኛ አልነበሩም። ስለዚህ ‹‹ከመማር ፍየል ጥበቃ ይሻለኛል›› ብለው ተማር የሚለውን የቤተሰብ ግፊት ከመፈጸም ይልቅ እምቢ ሳይሉ ሽሽት የጀመሩ ቢሆንም፤ አሁን ግን ተምረው ንቡረ እድ ሆነው አክሱምን ከማስተዳደር አልፈው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ እስከመሆን ደርሰዋል። አሁን በጠቅላይ ቤተ ክህነት የፕላን እና ስትራቴጂ ኃላፊ ናቸው። ከንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ ጋር ሕይወታቸውን፣ ጾሙን እና የትንሣኤ በዓልን በተመለከተ ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- ፊደል መቁጠር እና የቤተ ክርስቲያን ትምህርት እንዴት ጀመሩ?
ንቡረ እድ ኤልያስ፡- በልጅነቴ ፈጣን ነበርኩ። ትምህርት ግን ፈርቼ ነበር። ተማር ስባል ፍየል ጥበቃ ይሻለኛል ብዬ እረኝነትን ብመርጥም አባቴ መማር አለብህ ብለው ተንቤን ወስደው ለቤተክርስቲያኑ መምህር ለቄስ ካህሳይ ‹‹ፍየል ጠብቅ፤ እርሻ ሥራ፤ አረም ንቀል፤ አጨዳ እርዳኝ ብዬ አልወስደውም፤ ይኸው ልጄን ሰጥቻለሁ›› ብለው አስረከቡኝ። በወቅቱ ፊደል አልገዙልኝም ነበር። መምህሬ ግን ፊደል አምጥተው እግራቸው መሐል አስቀምጠው በስንደዶ ሆሄያትን አስቆጠሩኝ። ቄሱ ፊደል ሰጡኝ፤ ከጎበዝ ተማሪዎች ጋር ተቀላቅዬ በሳምንት ፊደል ለየሁ።
አባቴ ልጅ ይብላ፣ ይጠጣ፣ አይብረደው እንጂ ከዚያ ውጭ ሲያጠፋ መቀጣት አለበት ይላሉ። እጅግ ቁጡ ናቸው። በተጨማሪ ልጅ ምንም ጎበዝ ቢሆን ብዙም አያደንቁም። በሳምንቴ አባቴ ፊደል መለየቴን ለማወቅ ጥያቄ ሲያቀርቡ አነበነብኩት፤ አላደነቁኝም። ‹‹ገና ነህ የፊደሎቹን ክንፎች መለየት አለብህ›› አሉኝ፤ የአባቴ ፍየል ጠብቅ የሚል ትእዛዝ ሙሉ ለሙሉ ቆመ። ውሎ እና አዳሬ ቤተክርስቲያን ሆነ። ለምሳ ከቤቴ ገብቼ ምሳዬን በልቼ፤ ለእራት የሚሆን ምግብ በአንሶላዬ ጠቅልዬ በዚያው አድራለሁ። በእንዲህ ያለ ሁኔታ በአንድ ዓመት ውስጥ ዲያቆን ለመሆን በቃሁ።
ጎበዝ አንባቢ ብቻ ሳልሆን በዜማም በጣም ጥሩ በመሆኔ ‹‹ይበቃሃል ድቁና መቀበል ትችላለህ›› ተባልኩ። አባቴ መቀሌ ወስደው ክህነት እንድቀበል ፈተና እንድወስድ አደረጉ። በፈተናው ጥሩ ውጤት አምጥቼ ድቁና ተቀበልኩ። ድንቁና ከተቀበልኩ በኋላ ወዲያው ወደ ቅዳሴ አልገባሁም። ልታይ፣ ልታይ ማለት አይገባም ተብዬ ለስድስት ወር ቆየሁ። በኋላ ቀድስ ተብዬ አዲስ ልብስ ተገዛልኝ። በዐሥር ዓመቴ ሊቀ ካህናቱ ልጃችን ድቁና አምጥቷል ተብዬ ዐውደ ምህረቱ (መድረኩ) ላይ ደብዳቤ ተነበበ።
ማንም ቢሆን ደብዳቤው ሲነበብ አጎንብሶ እጅ ይነሣል። ድቁና ተቀባይ የመምህራኑንም፣ የካህናቱንም ሆነ የምእመኑን እግር እየሳመ ይመረቃል። እኔም እንደ ሥርዓቱ አደረግኩ። ከአንድ ወር በኋላ ቅዳሴ ገባሁ። አባቴም በመደሰታቸው ለካህናቱ ሙሉ ግብዣ ተደረገ። ከዚያም ጨርሷል ተባልኩ እና ተመልሼ ወደ ቤት ገብቼ ማረስ ጀመርኩ። ነገር ግን የእናቴ ወንድም ስመ ጥር የቅኔ መምህር በመሆናቸው ‹‹ይህ ልጅ ጎበዝ ነው ይፈቀድለት እና ምግቡን እኛ እንችላለን ቅኔ ይማር›› ብለው አባቴን ጠይቆ። አባቴ ‹‹ልጄ ድቁና ይበቃዋል። ደብተራ እንዲሆን አልፈልግም እርሻውን ይረስ›› አሉ። አጎቴ ቅኔ እንድማር በጣም በመፈለጋቸው ጥያቄያቸውን አላቋረጡም። አባቴም እየቆዩ ማሰብ ጀመሩ።
የአጎቴን ጉትጎታ ምክንያት አድርገው አባቴ ለአንድ ዓመት እንድማር ሲፈቅዱልኝ እኔ አልፈልግም አልኩኝ። ነገር ግን ከሁለት ዓመት በኋላ የትምህርት ፍላጎቴ አገረሸብኝ። ተማሪዎች ድጓና ጾመ ድጓ ሲማሩ፣ በቤተክርስቲያን ማኅሌታዊ መሆን እና ቅኔውን መቀኘት እንደ ገና በአእምሮዬ ይመላለስ ጀመር። አልፈልግም ያልኩትን ትምህርት እንደገና ልጀምር ማለት ከባድ ሆነብኝ። ስለዚህ ሰኔ ላይ ከመስቀል በኋላ ጠፍቼ እማራለሁ ብዬ በመወሰኔ ለልብሴ እና ለሌላውም ነገር ገንዘብ ያስፈልገኛል ብዬ አሰብኩ። ስለዚህ የአባቴንም ሆነ የእናቴን ገንዘብ የምታስቀምጠው እናቴ ናት። የምታስቀምጥበትን ቦታ አጥንቼ፤ በ1973 ዓ.ም መስከረም 29 ቀን 50 ብር ይዤ ከቤተሰቦቼ ቤት ወጣሁ።
በአውራጃችን መሪጌታ ፍሬ ሕይወት በየነ የሚባሉ ጣንቋ ምላሽ አርባህቱ እንስሳ (ጣሽማሊኸ አርባሃቱ እንስሳ) ይባላል። እርሳቸው ዘንድ የቃል ትምህርት ጀመርኩ። መሠረታዊ የዜማ ትምህርት ማለት ነው። ከውዳሴ ማርያም ጀምሮ እስከ ሠልስቱ በቃል መያዝ ያስፈልጋል። ያንን ካልተማሩ ዜማው አይገፋም፤ ዜማን በደንብ ማወቅም አይቻልም። ዝግ ይሆናል። ስለዚህ ለስምንት ወር እርሳቸው ዘንድ ተማርኩ። በመቀጠል አቋቋም የሚባል ትምህርት ለመማር አበር ገሌ ውስጥ ፂርባህ ተክለ ሃይማኖት በጣም ትልቅ መምህር ነበሩ፤ እዚያም ተማርኩ። አማራው፣ ትግሬው፣ ከፀለምትም፣ ከአገውም፣ ከትግራይም፣ ከበለሳም ከሁሉም ቦታ የሚመጣው ሌላ ሌላውም ሁሉም የሚማርበት ነበር። መምህር ዘፈረ ብርሃን ይባላሉ። ወደ እርሳቸው ሔድኩ። በመሪጌታ ደረጃ ያሉ የሚማሩበት ነው። ቀናኝና እዚያም በደንብ ተማርኩ። ሌሎቹ ትልልቅ ሆነው እኔ ሕፃን ስለነበርኩ እና የሕፃንነት ድምፅ ያምር ስለነበር መምህሩ በጣም ወደዱኝ። ትምህርታቸውም ግልጽ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ለማወቅ ብዙ አላዳገተኝም። አቋቋም የሚባለውን ትምህርት ለየሁ።
በ1975 ዓ.ም በደርግ እና በኢሕአዴግ መካከል በነበረው ጦርነት ምክንያት እንደልብ መንቀሳቀስ አይቻልም ነበር። በዚያ አካባቢ የፈለግኩትን ትምህርት መማር እንደማልችል ተረዳሁ። የትምህርት ፍቅር አድሮብኝ ስለነበር ትምህርት አቁም የሚለኝን እንደ ጠላቴ አየው ስለነበር በቦታው አንዴ ደርግ ሌላ ጊዜ ኢሕአዴግ እየመጣ ያፈናቅለናል። እኔ ብቻ ሳልሆን ተማሪዎች ሁሉ መላ መፈለግ ጀመርን። ጎንደር ሰላም መሆኑን ስለሰማን ወደዚያ በመሔድ እንደ ልብ ለመማር ስለወሰንን ለጊዜው ወደ ቤተሰብ ተመለስኩኝ። ጎንደር ለመግባት በእግር መሔድ ከባድ አደጋ ያስከትል ነበር። ዙሪያው እሳት ነው። ገንዘብ ባይኖረኝም እወጣዋለሁ አልኩ። አማራጩ መቀሌ መግባት እና በአውሮፕላን ጎንደር መሄድ ነው።
መቀሌ ገብቼ መምህር ሚካኤል አቡነ ሰላማ ፍሪምናጦስ ዘንድ ለስምንት ወር ቆየሁኝ። ለተማሪ እየጻፍኩ መጽሐፍ መሸጥ ጀመርኩኝ። ሰዎች ጽሑፌን ወደዱልኝ። መምህራንም ተጠንቅቆ ስለሚጽፍ ጽሑፉ ጥሩ ነው አሉ። ጻፍልን የሚለው ሰው በጣም በዛ። አልጽፍም እያልኩ በጭቅጭቅ በከፍተኛ ገንዘብ መጻፍ ጀመርኩ።
የአውሮፕላን ትኬት መቁረጫ ገንዘብ ተገኘ። በ51 ብር ትኬት ከመቀሌ ጎንደር ገባሁ። ወገራ ወደሚባል ደንክር ልደታ መምህር መርሐ ጽድቅ ዘንድ ሔድኩ። አቋቋሙን አጠናቀቅኩ። ለመምህርነት ሳይሆን ለጥሩ መሪ ጌታነት በቃሁ። በመምህርነት ለመመረቅ ጎንደር ከተማ ገባሁ። ጎንደርም በተመሳሳይ በልመና ሳይሆን ትምህርቴን ሳልጎዳ በመጻፍ ቀለቤን ቻልኩ። ትንሽ እየተለማመድኩ ስሔድ ቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ጀመርኩ። የ11 ብር ደሞዝተኛ ሆኜ ትምህርቴንም ሥራዬንም ቀጠልኩ። በተለይ ደጀ ሰላም ላይ የሚገኘው እህል ውኃ ደጎመኝ፤ በሂደት በከተማው ዕውቅና አገኘሁ። እንደተማሪ ሳይሆን ቃለ እግዚአብሔርን ለይቷል ተብዬ ተለየሁ።
የማውቀው ዜማ ጥልቀት እንዲኖረው በሚል ፊት አቦ መምህር ሠመረ አብ ዘንድ ድጓ እና ጾመ ድጓ በአጭር ጊዜ ተማርኩ። ምክንያቱም መጀመሪያ ስለተከፈተ እርስ በራሱ ትምህርቱም እየተደጋገፈ ቀጠልኩ። እዚያው ጎንደር ሰለሞን ገብረ ሚካኤል ከሚባሉ መምህር ዘንድ ቅኔ ተቀኘሁ፤ ዝማሬ መዋሥዕት ሲቀረኝ እንደ ትልቅ ዩኒቨርሲቲ ከሚቆጠረው ጋይንት መሔድ ስላለብኝ ወደዚያ አቀናሁ። ልክ እንደ ዩኒቨርሲቲ የብቃት ማረጋገጫ የሚሰጥባቸው የተለዩ ቦታዎች አሉ። በእነዚያም ዝማሬ በደንብ ተማርኩ።
ዙር አምባ፣ እስቴ መካነ ኢየሱስ እና ቤተልሔም የጀርመን ተራድኦ ድርጅት የትምህርቱን ታላቅነት አይተው ለተማሪ 10 ብር፣ ለመምህር ደግሞ 50 ብር ይከፈሉ ነበር። የዙር አምባ ካህናት እጅግ የተባረኩ ናቸው። እነርሱ ሳይበሉ ቀድመው ተማሪዎችን ያበሉ ነበር። እዚያ ከድፍን ኢትዮጵያ የመጣ ተማሪ አለ። የጎጃም፣ የጎንደር፣ የአስመራ፣ የወሎ፣ የሸዋ፣ የኢሊባቡር እና ሌሎችም የሰባቱም ክፍላተ ሀገራት ተማሪዎች ነበሩ። እዚያ ዜማ፣ አቋቋም ጎንደር፤ ቅዳሴ ደግሞ ደብረ ዓባይ ትግራይ መማር እና የብቃት ማረጋገጫ መያዝ የግድ ነው። ያ ሁሉ ተማሪ ግጭት እና ጠብ የለበትም። የምንተሳሰበው እንደ እናት ልጅ ነው። አሁንም የሚናፍቅ ሕይወት ነው። በዚያን ጊዜ አብረውኝ የተማሩ በየሀገሩ የተበተኑ ወዳጆች አሉኝ። የኢትዮጵያውያን አንድነት እና ወዳጅነት በትክክል የሚታይበት ቦታ ነው። ቤተክርስቲያን በፍቅር አንድ ያደረጋቸው ናቸው። አንድ ሰው ከታመመ ሁሉም ማድረግ ያለበትን ያደርጋል። ሲበላም በፍቅር ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከቤተሰብ ጋር መገናኘት ቀረ? ቤተሰብ ተረሳ ማለት ነው?
ንቡረ እድ ኤልያስ፡- ቤተሰቦቼ ጎንደር የሀገር መጨረሻ ስለሚመስላቸው መጥተው አልፈለጉኝም። ተማሪው በሙሉ ቤተሰቡን አያስታውስም። ትምህርቱ ሃያ አራት ሰዓት ነው። ቤተሰብ ከታሰበማ ትምህርቱም አይገባም። ከጋይንት በኋላ ወደ ጎንደር ሄጄ የመጀመሪያው ቤተ ክርስቲያን በአፄ ፋሲል ዘመን የተገነባው ፊት ሚካኤል ሄድኩ። እዚያ ያሉት ካህናት ጾም ሲሆን፤ ጾመ ድጓ እቆምላቸው ስለነበር ያውቁኛል። ሰው ሲፈለግ እኔን መርጠው እየጠበቁኝ ነበር። በድጋሚ ወደ ጎንደር የሄድኩት ትርጓሜ መጽሐፍ ለመማር ነበር። ነገር ግን ሥራው ሲገኝ፤ ትምህርቱን እና የደብሩን መሪጌትነት አያይዤ መሥራት ጀመርኩኝ። ደመወዝ 30 ብር ተፈቀደልኝ። ከዚያ አቋቋሙንም ሆነ ዝማሬውን ማስተማር ጀመርኩ።
በመንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም ትርጓሜ መጻሕፍትን ተማርኩ። የብሉይ ኪዳን እና የሐዲስ ኪዳንን ትርጓሜ ከሊቀ ሊቃውንት እየተማርኩ እያስተማርኩ ለሰባት ዓመት እዚያው አገለገልኩ። ትርጓሜ መራቀቅ ስለሆነ የተለያየ ቦታ መማር ጥሩ ነው በማለት አፄ ፋሲል ግንብ ውስጥ ከምትገኘው ግምጃ ቤት ማርያም ሐዲስ ኪዳን ተማርኩ፤ ትምህርቴን ሳጠናቅቅ ጎንደር የመቆየት ፍላጎት አልነበረኝም። ምክንያቱም ጎንደር ብዙ ሕዝብ አለበት። ሰው ወደሌለበት ሔጄ አስተምራለሁ ብዬ ሳስብ በመሐል አዲስ አበባ የነበሩ ጓደኞቼ ጠሩኝ። አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ከመቀሌ በአታ ፣ ከአስመራ ደግሞ መንደፍራ የሚባል ቤተ ክርስቲያን መማሪያውን ኮሌጅ ልናደርገው በመሆኑ ኑ አሉ። ወደ መቀሌ ባደላም፤ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የተከፈተበት ጊዜ ስለነበር አንድ ጓደኛዬ ላገባ ስለሆነ እሑድ እንድትገኝ ብሎ ወደ አዲስ አበባ ጠራኝ።
በዚያ ጊዜ አባቶች እነ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ሊያስቀሩኝ ፈልገው ስለነበር ይዘው አሳመኑኝ። ጓደኛዬን ትቼ መሔድ እችል ነበር። በአባቶች ጥያቄ ግን ልቤ ተሰበረ። እዚያው ማስተማሬን ቀጠልኩ። በአብነት ትምህርት ቤት፣ በሰንበት ትምህርት ቤት እና በስብከተ ወንጌል ሳስተምር ቆየሁ። ዘመናዊውንም ትምህርት በመጀመር እዚያው ቅድስት ሥላሴ እስከ ስምነተኛ ክፍል፤ ምኒልክ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ደግሞ እስከ 12ኛ ክፍል ተማርኩ። በልማት ሥራ፣ በሰበካ ጉባኤ አባልነትም ከትልልቅ ሰዎች ጋር አብረን ሰርተናል።
በአገልግሎቴም አባቶች ዓይናቸውን ይጥሉብኝ ነበር። ወደ ውጭም ኬንያ ጅቡቲ እየሄድን ሁለት ሁለት እየሆንን እናገለግል ነበር። ፍላጎቴ ዘመናዊ ትምህርቴን መቀጠል ነበር፤ ነገር ግን አልሆነም። በአባቶች ለትልቅ ሥራ ለቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ዋና ዲንነት ተመርጠዋል ተባልኩኝ። አባቶች ሹመው እምቢ ማለት አይቻልም። ማስተማር እና መማር ብቻ እንደምፈልግ ብገልፅም፤ ‹‹ግማሽ ቀን ትምህርት ግማሽ ቀን ሥራ እያሉ ግዴታዎን ተወጡ፤ ምክትል ጎበዝ ሰው ይሾምልዎታል›› ተባልኩ። ትምህርት ቤቱ ስለተበጠበጠ እባክዎ ያስተካክሉት የሚል ግዴታ ተጣለብኝ። በጥሩ ሁኔታ ሥራዬን ሠራሁ፤ ማስተካከል ያለብኝን አስተካከልኩ፡፡
ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ ለአክሱም ንቡረዕድ ተፈለገ። ለዚህ ቦታ እንደገና አባ ኤልያስ ይመረጡ ተባለ። አባቶች ተከፋፈሉ፤ ‹‹ቦታው ከባድ እሳት ያለበት ነው። አክሱሞች ለፓትሪያሪክ እንኳ የማይታዘዙ በመሆናቸው ይከብዳቸዋል›› የሚል ክርክር መጣ። በርግጥ አክሱሞች ጠንከር ያሉ ናቸው። መንግሥትነትም፣ ክህነትም፣ መቀባቱም የሚሰጠው ከእዛ ነበር። ሌላ ቦታ የነገሠ እንኳ አክሱም ሄዶ እውቅና ካላገኘ የጽዮን ንጉሥ ካልሆነ በወንጌል ወርቅ ስሙ ካልተጻፈ እርሱ የኢትዮጵያ ንጉሥነቱ አይታወቅም። ይህ ከድሮ የመጣ ሥርዓት ነው።
የትኛውም ንጉሠ አክሱም የሚገባው በፈረስ ሳይሆን በእግሩ ነው። የአካባቢው ሰው ተመርጦ ነገሥታቱን እግራቸውን ያጥባል። ነገሥታት ደግሞ በአክሱም አያዝዙም። ነገሥታቱ የሚሸልሙትን እዚያው ይሸልማሉ። አብልተው አጠጥተው፤ ርስት ጉልት ሰጥተው ጸልዩልን ከማለት ውጭ የሚሉት የለም። አክሱም የተሾመ የቤተክርስቲያን የሃይማኖቱን ብቻ ሳይሆን የመንግሥትም ሥልጣን የእርሱ ነው። ንቡረ እድ ማለት ደግሞ ሁለተኛ መንግሥት ማለት ነው። ስለዚህ እዚህ ቦታ ላይ እንዳገለግል በ1995 ዓ.ም ደብዳቤ ወጥቶ ለንቡረዕድነት ተመረጥኩ። ሊቀ ጳጳሱ ራሱ ከሕዝቡ ጋር ሆድ እና ጀርባ ሆነው በመስቀላቸው አንሳለምም እስከ ማለት ተደርሶ ነበር። ያንን ፈተና ለመፍታት ከመስተዳድሩም ሆነ ከክልሉ ጋር ብዙ ሴሚናሮችን በማድረግ ችግሩን ለመፍታት ሞክረን፤ ተሳካልን። እዛም ለሶስት ዓመታት ቆየሁ። ሁሉም ተስማምቶ ወደ ነበረበት ቦታ ተመለሰ። በመቀጠል ጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ተብዬ መጣሁ። ለሰባት ዓመታት ስሠራ ቆይቻለሁ። እዚህ ላይ ትምህርቴን በመቀጠል በማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቅኩ። ቀጥዬ የሁለተኛ ዲግሪዬንም በቲዎሎጂ አጠናቅቄያለሁ። በትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅትም ሥራ አስኪያጅ ሆኜ ሰርቻለሁ። ቤቶች እና ሕፃናት አስተዳደርም ሥራ አስኪያጅ ሆኜ አገልግያለሁ። አሁን የቤተክርስቲያናችን ስትራቴጂክ ፕላን ኃላፊ ሆኜ እየሠራሁ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በክርስትና የተለያዩ አጽዋማት አሉ። አሁን ያለንበትን የጾም ወቅት ከሌሎቹ አጽዋማት ለየት የሚያደርገው ምንድን ነው?
ንቡረ እድ ኤልያስ፡- ጾመ ሁዳዴ፣ ጾመ አርባ፣ ጾመ ኢየሱስ፣ ዐቢይ ጾም ይባላል። በክርስትና እምነት ታላቅ ጾም ነው። ታላቅ የሚያደርገው ደግሞ ጾሙን እርሱ ጌታችን ራሱ በመካከላችን ተገኝቶ በተግባር የሠራው ነው። በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ አራት ላይ ተጽፎ እንደሚገኝ አርባ ቀን እና አርባ ሌሊት ያለ እህል እና ውኃ ጾሟል። በጾሙ ዲያቢሎስን አሸንፏል። በመንፈስ እና በሥጋ ማሸነፍ ይለያያል። የሥጋ ማሸነፊያ ቁሳቁስ ድንጋይ፣ ጦር ወይም ሌላ መሣሪያ ያስፈልጋል። የመንፈስ አሸናፊነት ግን በሞራል የበላይነትን መቀናጀት ነው። ዲያብሎስ አዳምን እና ሔዋንን በጣለበት መንገድ ጌታችንን ለመጣል ፈልጎ ነበር። ዳያቢሎስ ጌታችን በጾሙ ጊዜ እንጀራ እንዲበላለት ለማንሳት ሞክሮ ነበር። ነገር ግን ጌታ ‹‹ሰው በእንጀራ አይኖርም በእግዚአብሔር ቃል እንጂ›› ብሎ አሸነፈው። ‹‹የዓለምን ሀብት እሰጥሃለሁ ለእኔ ስገድልኝ አለው፡፡›› ይህንንም ጌታችን፤ ‹‹ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ብቻ ስገድ ይላል›› ብሎታል። መላዕክት በእጃቸው እንዲያነሱህ ሰሎሞን ከሠራው ቤተ መቅደስ እናት ላይ ‹‹ውደቅ›› አለው፤ ጌታችን ግን መጽሐፍ አምላክህን አትፈታተነው ይላል አለው። በመጨረሻም ጌታ ሰይጣንን ሂድ አለው። አሁንም ማሸነፍ የሚቻለው በዚህ ሞራል ነው፡፡
ጌታችን የሰይጣንን ሃሳቦች በሙሉ ጣለ። የመጀመሪያው አዳም ተሸነፈ። ሁለተኛው አዳም ግን አሸነፈ። እኛ ክርስቲያኖች ደግሞ በአሸናፊው አሸንፈናል። ጌታችን የጾመው አርባ ቀን ነው። እኛ ግን የምንጾመው 55 ቀን ነው። 10ሩ ቀን የሕማማቱ ጊዜ ነው። አርባው ቀን የሚያልቀው ያለፈው ሕማማት ከመግባቱ በፊት ያለው ዓርብ ነው። ከቅዳሜ ጀምሮ እስከ ሳምንቱ ቅዳሜ ስቃዩን የምናስብበት ነው።
ጌታችን የተሰቀለበት መስቀል ተማርኮ ነበር። አንድ ክንፉ እኛ ሀገር ግሸን ማርያም ቢኖርም፤ መጀመሪያ ከአራት ሳይከፈል ተዘርፎ ፐርሺያ የአሁኗ ኢራን ሄዶ ነበር። በዚያ ጊዜ ኢራኖች እየሩሳሌም ላይ ዘምተው ክርስቲያኖችን እና አይሁዶችን ጨፍጭፈው መስቀሉን ይዘው ሄደው ነበር። የቤዛንታይን መንግሥት የአሁኗ ቱርክ ትልልቅ የክርስትና ጉባኤዎች የሚካሔዱባት ሀገር ነበረች። ብዙ ሊቃውንት እነ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ እነባስልዮስ፣ እነጎርጎርዮስ ዘጠኙ ቅዱሳን በብዛት ከኢስታንቡል ወደ ኢትዮጵያ ይመጡ ነበር። ከአክሱም መንግሥት ጋር የጠበቀ ግንኙነት ነበራቸው። ስለዚህ የቤዛንታይን መንግሥት (ቱርኮች) ከፐርሺያ ከአሁኗ ኢራን ጋር ለመዋጋት ጸልየው ተዋግተው መስቀሉን መልሰዋል። በዚያ ወቅት ለፈሰሰው ደም የአምስት ቀን ጾም ስለነበር ያ አሁንም ድረስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እየተጾመ ነው። እነርሱ ትተውታል እኛ ግን እስከ አሁን እየፆምነው ነው። በአጭሩ ይኸው ነው።
አዲስ ዘመን፡- የጾሙ ሳምንታት የተለያየ ስም አላቸው፤ ስሞቹ ምንድን ናቸው? የስያሜያቸው ምክንያት ምንድን ነው?
ንቡረ እድ ኤልያስ፡- ትክክል ነው። የፆሙ ወቅት በውስጡ ብዙ ክፍልፋዮች አሉ። የመጀመሪያው ሳምንት ዘወረደ ይባላል። ይህ ጌታ ለእኛ ሲል መውረዱን የምናስብበት ነው። ሁለተኛው ቅድስት ነው። ስለቅድስና ያተኩራል። ሰንበትን የሚያሳስብ ሲሆን፤ በዛ ምሳሌ በመንግሥተ ሰማይ እረፍት እንዳለ ማሳያ ነው። ሦስተኛው ደግሞ ሙኩራብ ነው። ሙኩራብ አይሁዶች የሚያመልኩበት ቤተ አምልኮ ማለት ነው። የጸሎት መታሰቢያ ነው። በየሳምንቱ ቅዳሜ እየተሰበሰቡ ጸሎታቸውን የሚያካሂዱበት፣ ሃይማኖታቸውን የሚማሩበት፣ ሐዋርያት እና ጌታ ራሱ ሃይማኖቱን ያስፋፉበት ነው።
አይሁድ ማለት አማንያን ማለት ነው። ጌታም ከአብርሃም የመጣ ዘር ነው። የድንግል ማሪያም ልጅ ነው። ክርስትና የመጣው በአይሁዳውያን በኩል ነው። ለዓለምም ያዳረሱት አይሁዳውያን ናቸው። አይሁዳውያን ክርስቶስን የሰቀሉ ብቻ ሳይሆኑ የተቀበሉም ናቸው። አይሁዶቹ ጥበበኞች ናቸው። አይሁዶች በእስያ፣ በሮም፣ በግሪክ፣ በሰሜን አሜሪካ እና በአፍሪካ በሊቢያ በግብፅ በሱዳን በኢትዮጵያ በየመን በእነዚህ ሁሉ ሙኩራብ አቋቁመዋል። ይህ ለሐዋሪያት ምቹ መደላድል ፈጥሮላቸዋል። ይመጣል የተባለው መጥቶ ተሰቅሎ ሞቶ አድኖናል ማመን አለባችሁ ብለው አንዱ ሌላውን እያሳመነ ክርስትና ተስፋፍቷል። ስለዚህ ይህ ሳምንት በሙኩራብ መሲሁ እርሱ ነው ብለው ክርስትናን ያስፋፉ እነርሱ በመሆናቸው ይህንን ለማስታወስ በሙኩራብ ክርስትና እንደተስፋፋ ለማሰብ የተሰየመ ነው። አራተኛው ሳምንት መጻጉ ነው። ይህ ሳምንት ጌታችን በፈወሰው ለ38 ዓመት በሽተኛ በሆነው ሰው ስም የተሰየመ ነው።
በአጠቃላይ ግን በፈወሳቸው ባዳናቸው እና አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግራቸው እንዲፈታላቸው ጌታችንን ጠይቀው የተፈታላቸውን ለማስታወስ ነው። እዚህ ላይ ሙታንን እንዴት እንዳስነሳ፣ የተራቡትን እንዴት እንደመገበ፣ ቤተክርስቲያን እንዴት መሥራት እንዳለባት የሚያሳይ ነው። ጌታችን ለሐዋሪያት የሞቱትን አንሱ፣ የታመሙትን ፈውሱ፣ ለምጣሞቹን አንፁ፣ በነፃ ያገኛችሁትን በነፃ ስጡ፤ የተራቡትን አብሉ፤ የተጠሙትን አጠጡ፤ የታረዙትን አልብሱ፤ የሞተውን ቅበሩ፤ የታሠረውን እና የታመሙትን ጠይቁ እንግዳ ሲመጣ ተቀብላችሁ አስተናግዱ ብሏል። ይህ ሁሉ ማኅበራዊ ግዴታ ነው። ለዚህ ነው ቤተክርስቲያን እርሱን መሠረት ያደረገችው።
አምስተኛው ደብረ ዘይት ነው። ነገረ ምጻትን የሚያስታውስ ነው። ጌታ እንደሚመጣ የሚያስታውስ ሲሆን፤ መጥቶ ሰዎች ላይ እንደሚፈርድ የምናስታውስበት ነው። ሰዎች ይነሳሉ፤ ተነስተውም እንደየሥራቸው እንደሚፈረድባቸው እና እንደሚፈረድላቸውም የምናስታውስበት ነው። ስድስተኛው ገብርኤር ይባላል። ደግ እንደቃሉ የሚኖር ተሸላሚ አገልጋይ ማለት ነው። ሰባተኛው ኒቆዲሞስ ይባላል። በጣም የተማረ የአይሁድ አለቃ በነበረ ሰው ስም የተሰየመ ነው። ይህ ሰው የነበረበት ቡድን የእየሱስ ክርስቶስ ተቃዋሚ ሲሆኑ፤ እርሱ ግን ተለይቶ የክርስቶስ ደጋፊ ሆኖ በአስተውሎት ይከታተል ነበር። ይመጣል ብለን ስንጠብቀው የነበረው መስዑ እርሱ ነው። የሚል እምነት ስለነበረው በማታ ሄዶ ጌታ ጋር ትምህርት ይማር ነበር።
ክርስቶስ ስለጥምቀት አስተምሯል። ሰው ዳግመኛ መጠመቅ አለበት። መንፈሳዊነት ያስፈልጋችኋል። መንፈሳዊነት እና የእግዚአብሔር ልጅነት የሚገኘው በጥምቀት መሆኑን ያስተማረ መሆኑን በዮሐንስ ምዕራፍ ሶስት ላይ ተቀምጧል። እርሱን እናስባለን። ቀጥሎ ያለው ሆሳዕና ነው። ሆሳዕና ማለት ትርጉሙ መድኃኒት ማለት ነው። ቃሉ ግስም ስምም ይሆናል። ግስ ሆኖ ሲፈታ አሁን አድነን ማለት ነው። ስም ሲሆን ለዳዊት ልጅ መድኃኒት መሆን ይገባሃል የሚል ነው። ዓለም በትክክል መሲዑ እንደሚመጣ የሚረዳበት ነው።
መሲዑ በአህያ ላይ ይመጣል ተብሎ ተነግሯል። ያዕቆብ የሚመጣውን መሲዑን አንበሳ ብሎ ገልጾታል። ጌታችን ክንድህ በጠላት ደንደስ ላይ ነው። መንግሥትህ እና ገዢነትህ ከአንተ አይጠፋም ተብሏል። አህያውን በወይራ ያስራል። ልብሱን በወይን ኩታውን ደግሞ በወይን ደም ያጥባል ተብሏል። እየሱስ ክርስቶስ በአንበሳ የተመሰለው አሸናፊነቱን እና ኃያልነቱን ለማሳወቅ ነው። በጠላት ደንደስ ላይ ማለት ትከሻው በዲያብሎስ ላይ መሆኑን የሚያሳይ ነው። መንግሥትነትህ የዘላለም ነው ፍፃሚ የለውም የተባለው ዘላለማዊ መሆኑን ለማሳወቅ ነው።
አህያውን በወይራ ያስራል የተባለውም አህያ ደግ እና ታዛዥ ናት። አህያ ምዕመናን ናቸው። ወይራው ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ነው። በመንፈስ ቅዱስ ምዕመናንን ያከብራቸዋል፤ ያነፃቸዋል ማለት ነው። ልብሱን በወይን ያጥባል፤ ኩታውን በወይን ደም ያጠራል ማለት በልብስ የሚመሰሉት እስራኤላውያን ሲሆኑ፤ በኩታ የሚመሰሉት ደግሞ ከእስራኤል ውጭ ያሉ እግዚአብሔርን የማያውቁ ሰዎች ናቸው። እነዚህን ሁሉ ያጠምቃቸዋል፤ ያድናቸዋል ለማለት ነው። ይህ በራሱ ቅኔ ነው። እግዚአብሔር ራሱ የቅኔ መምህር ነው። ሆሳዕና ይህንን ሁሉ ለማሳወቅ የቀረበ ነው። ትንቢት የተነገረለት ይመጣል የተባለው መድኃኒት እርሱ መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡
በዚህ ሳምንት በፊትም በኋላም በቀኝም በግራም ሽማግሌም ሕፃናትም ሴትም ወንድም ሁሉም ሰው ተከትሎት እያመሰገነ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቷል። ይህ ትንቢት የሚያሳየው ቤተመቅደሱ የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ናት። የእርሱ ተከታዮች በሙሉ መንግሥተ ሰማያት እንደሚገቡ የሚያሳይ ነው። ከዛ በኋላ ሰሞነ ህማማት ነው። ይህ ሰሞን የተቀበላቸውን መከራዎች የምናስብበት ነው። ሰኞ እና ማክሰኞ የአይሁድ ምክር ነበር። ‹‹እንግደለው፤ የለም ሕዝቡ ተቀብሎታል እና ሕዝቡ ይነሳብናል፤›› ብለው ሲከራከሩ ሰኞ እና ማክሰኞ ሳይስማሙ ቀሩ። ረቡዕ ግን እንዲገደል ተስማሙ። ለመግደል ቢስማሙም በዕለቱ ማድረግ አልቻሉም። ሐሙስ በሙሴ ጊዜ የተጀመረው የፋሲካ በዓላቸው ነበር። ስለዚህ ሐሙስ የፋሲካ በዓል ይለፍ ብለው ሐሙስ ማታ ግን ያዙት። ሌሊት ወደ ሊቀ ካህናቱ ጊቢ ወስደው ከሰሱት፤ ሲነጋ ደግሞ ሊቀካህናቱ የመፍረድ እንጂ የመግደል ሥልጣን ስላልተሰጣቸው የሮማ ወኪል ጲላጦስ ጋር ወሰዱት። ጲላጦስ በደል አላገኘሁበትም፣ ቢልም ሰሚ አጣ። ፖለቲካው እንዳይበላሽ ብሎ ፍርድ አዛባ።
ከአዳም ጀምሮ ሁሉም በአንድነት የእግዚአብሔርን መንገድ ስተዋል። አንድም እንኳን ከኃጢያት ያመለጠ የለም። ኃጢያተኛ ደግሞ ፍርድ አለበት። ስለዚህ ሁሉም ሊቀጣ ነው። እግዚአብሔር ደግሞ ቸር ነው። ሰዎችን ከቅጣት ለማዳን በእርሱ አሠራር ኃጢያታቸውን ይቅር ለማለት ቤዛነት ያስፈልጋል። ቤዛነት ኃጢያቱን የሚሸከም ተለዋጭ ነው። ምትክ ማለት ነው። ቤዛ የሚሆነው አካል ኃጢያት ያልሠራ መሆን አለበት። ሰው ሆኖ ደግሞ ኃጢያት ያልሠራ የለም። ስለዚህ ይህንን የሚችለው እግዚአብሔር ሰው ሆኖ በሰውነት አምላክ ሆኖ በእግዚአብሔርነት እርሱ ራሱ በጥበቡ የማይሞተው ለመሞት ሥጋ ለበሰ፤ ቤዛ ሆኖ በሰው ምትክ ሞቶ አዳነን።
ሞት ማለት ሥጋ እና ነፍስ ተለያየ ማለት ነው። በክርስትና እምነት የሰው ሞት ሥጋ ከነፍስ መለየት ነው። በሃይማኖት መንፈሳዊ እና ቁሳው ዓለም እንዳለ የታመነ ነው። እየሱስ ክርስቶስም ሥጋው እና መንፈሱ ተለየ። በነፍሱ ከአዳም ጀምረው ታስረው ወዳሉ ወደ ረቂቃን ነፍሳት ሄደ። ቤዛ ስለሆነላቸው ወደ ገነት አስገባቸው። በአምላካዊ ጥበብ የሞተውም ይቅር ያለውም እርሱ ነው። ፍርዱ እና አዳኝነቱን እንዴት እንዳደረገ የሚያሳይ ነው። እንደ አምላክነቱ ፈረደ፤ እንደ አባትነቱ ይቅር አለ። መሰዋዕት የሆነ፤ መሰዋዕት የተቀበለ፤ መሰዋዕት ያቀረበ እርሱ ነው። ይህ የአምላክ ረቂቅ ሥራ ነው። ከዛ በኋላም አሁንም ኃጢያት አለ። ነገር ግን በጥምቀት፤ በዕምነት፤ በደሙ ከሞት ጋር እንተባበራለን።
በትንሳኤው የመንፈስ ሞት የለም። ከሞት አዳነን የምንለው ከሥጋዊ ሞት ሳይሆን ከመንፈሳዊ ሞት ነው። እርሱም ‹‹አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ። › ብላል። እያንዳንዱ ክርስቲያን ሲሞት ነፍሱ በእግዚአብሔር እጅ ነው። ትንሣኤው ትንሳኤያችንን ማሳያ ነው። ሰው ትንሣኤ የክርስቶስ ሳይሆን የእርሱ ትንሣኤ መሆኑን ማሰብ አለበት። እግዚአብሔር እኮ አልሞተም፤ እንኳን እግዚአብሔር ሰይጣን እና መላእክት አይሞቱም። አያረጁም አይራቡም፤ አይጠሙም። የሞተው በለበሰው ሥጋ ብቻ ለእኛ ቤዛ ለመሆን ነው። ሞቱም ትንሣኤውም ለሰው ተብሎ ነው። ትሞታላችሁ ትንሣኤ አላችሁ ማለት ነው። በምጽአት ጊዜ ሙታን ተነሥተው ማለቂያ የሌለው ሕይወትን ይኖራሉ። በዚያ ማርጀትም ሆነ መታመም የለም።
አዲስ ዘመን፡-በዓሉን በተመለከተ የሚስተላልፉት መልእክት ካለ?
ንቡረ እድ ኤሊያስ፡- ይህች ዓለም ፈጣሪ እስከሚጠራን መቆያችን መሆኗ ይታወቃል። ዓለም እርስ በርሷ የምትተዛዘን የምትረዳዳ እንድትሆን አድርጎ አሳይቶናል። አሁን በሀገራችን የሰላም መደፍረስ ይታያል። ይህ ክርስቲያናዊነትን አይገልጽም። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሀገሩን አይወድም ለማለት አልደፍርም። አንዳንድ ሰው ብሶት ሊኖረው ይችላል። ነገር ግን ኢትዮጵያን እወዳለሁ ማለት በቃል ሊሆን አይገባም። በተግባር መውደድ ያስፈልጋል። በዋነኛነት ኢትዮጵያ የሃይማኖት ሀገር ናት። ሁላችንም ፈጣሪን እንወዳለን። ሃይማኖተኞች መገዳደልን የሚያወግዙ እና መገዳደል እንዳይኖር የሚያስተምሩ ናቸው። በተለይ የኦርቶዶክስ እምነት እዚህ ላይ ጠንካራ ነው። የሚረግሙህን መርቅ ይላል፡፤ የሚያሳድዱህን ፀልይላቸው የሚል ነው። ማህተብ ያሰረ የገዛ ወንድሙን መግደል የለበትም። ይህ ሲታይ ንጹህ ክርስቲያን ነን ለማለት አያስደፍርም።
መጽሐፉ ክርስቲያንን ብቻ ሳይሆን ጭራሽ የሰው ልጅን እንዳትገድል ይላል። ኢትዮጵያ ለእኛ አታንስብንም፤ ኢትዮጵያውያን ከሆንን እና በኢትዮጵያ ካመንን በድንበር የምንጣላበት ምክንያት የለም። ኢትዮጵያዊ ሆነን ለአንድ ወረዳ ድንበር መሬት መጋት የለብንም። ለማንም ኢትዮጵያዊ የኢትዮጵያ ምድር የእርሱ መሆኑን ማወቅ አለበት። ቦታው ለአስተዳደር ምቹነት ይከፋፈል ይሆናል። ከዚህ በተረፈ ሀገራችንን እያመሰ ያለውን ነገር ልብ ማለት ይገባል። ይህ ሁሉንም ይጎዳል። ስለዚህ የሁላችን ሀገር እንደሆነች አስበን መገንባት አለብን።
የሃይማኖት ተቋማትም ከማንኛውም ነገር ነፃ ሆነው የእግዚአብሔርን ቃል ብቻ ተከትለው ለሁሉም እኩል አባት ሆነው ማስተማር አለባቸው። ትልቋ ሀገር ረስተው በትንንሽ ነገሮች መጨቃጨቅ የለባቸውም። ነገሮችን በውይይት መፍታት አለባቸው። ይህቺን በተፈጥሮ ሀብቷ መተኪያ የሌላትን ሀገር በሰላም እንጠቀምባት። ሰፊ መሬት እና ምቹ አየር አለ። ስለዚህ ከመነጣጠል ይልቅ በሰላም እንኑር። የፖለቲካ ኃይሎችም ሆኑ ልሒቃን ማስተዋል አለባቸው። ይህ ሁሉ ችግር በ1960ዎቹ በተለይ የኢትዮጵያ እሴት እና ጸጋ ችላ በመባሉ የመጣ ጣጣ ነው።
ከአባቶች የወረስነውን ፀጋ በሙሉ አብዮቱ አሳጥቶናል። እምቢተኝነት እና አመፅ ፀረ ሃይማኖት ከእግዚአብሔር አርቆ እስከ አሁን እያናከሰን ነው። ይህንን ነገር ኢትዮጵያውያን ቆም ብለን ማየት አለብን። በለው ግደለው የሚባለው ቀርቶ ተወው አትርፈው፤ አፈሙዝ ቀርቶ ወንድሜ እህቴ መባባል አለብን። በውይይት ችግሮች መፈታት አለባቸው። የተበደለም ተካክሶ ለሃይማኖታችን፣ ለእሴቶቻችን፣ ለትውፊቶታችን ትኩረት ቢሰጥ እና ከአባቶች የመጣውን አጥብቆ መያዝ ቢቻል የተሻለ ውጤት ይገኛል። ስልጣኔ አይጠላም፤ ፍትሕ እና እኩልነት መኖር አለበት። እርቅ እና ይቅርታ መምጣት አለበት። የተበደለ የሚሸነፈው ሲካስ ነው። ይህ ፅድቅ ነው። ክርስቶስ በሞቱ ፍቅሩን ገልጾ ይቅር እንዳለን የይቅርታ ሰዎች እና የዕርቅ ሰዎች ብንሆን መልካም ነው። በዚህ መልኩ ትንሣኤን ማሳለፍ አለብን።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ እጅግ አመሰግናለሁ።
ንቡረ እድ ኤሊያስ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 26 ቀን 2016 ዓ.ም