ከበጋ መስኖ ስንዴ ከ82 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተሰበሰበ

አዲስ አበባ፡ከ2016 የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እስካሁን ከ82 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የግብርና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አቶ ከበደ ላቀው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በ2016 የስንዴ ምርትን ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ ባለው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እስከ ሚያዚያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ከ82 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተሰብስቧል፡፡

የግብርናውን ዘርፍ የስንዴን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በበጋ መስኖ፣ በበልግና በመኸር ወቅቶች በስፋት የማምረት ሥራ እየተሠራ ነው ያሉት አቶ ከበደ፤ በ2016 የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 120 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እስካሁን ድረስ 82 ሚሊዮን 670 ሺህ 200 ኩንታል ምርት ተሰብስቧል ብለዋል፡፡ በሀገሪቱ በሁሉም ክልሎች በ2016 በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሶስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን አውስተው፤ ከዚህም 120 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

በበጋ መስኖ ስንዴ በዘር ከተሸፈነው ሶስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ ከሁለት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን በላይ የሚሆነውን መሰብሰብ ተችሏል ያሉት ስራ አስፈፃሚው፤ ከተሰበሰበው ሁለት ሚሊዮን 352 ሺህ 867 ሄክታር መሬት የበጋ መስኖ ስንዴ ውስጥ አንድ ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በባህላዊ መንገድ እና 652 ሺህ 867 ሄክታሩ መሬቱ ደግሞ በኮባይነር መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የስንዴ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸው፤ የበጋ መስኖ ለምቶ የደረሰውን ቀሪ ሰብል በወቅቱ በመሰብሰብ እቅዱን ለማሳካት ሰፊ ርብርብ እየተደረገ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ፣ የለም አፈር፣ የሰው ሃይል ሀብቷን በመጠቀም የስንዴን ምርትና ምርታማነት የማሳደግ ሥራ እየተሠራ ነው ያሉት አቶ ከበደ፤ እየተሠራ ባለውም ሥራ የስንዴ አቅርቦቱ ችግር የመቅረፍ፤ ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በሀገር ውስጥ ምርት የመተካትና የመሸፈን ሥራ ማከናወን ተችሏል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የግብርና ምርቶችን በጥራትና በብዛት በማምረት የሀገር ውስጥ ፍጆታን ከማሟላት ባለፈ ለዓለም ገበያ ለማቅረብ በትኩረት እየተሠራ ነው ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

ታደሠ ብናልፈው

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You