ግብፅ በዓባይ ወንዝ ላይ የምታራምደው የ “እኔ ብቻ ልጠቀም” እሳቤ ጊዜው አልፎበታል

አዲስ አበባ፡- ግብፅ የምታራምደውን የእኔ ብቻ የሚል ያለፈበት እሳቤ ትታ ከዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ጋር በትብብር መሥራት እንደሚገባት በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሰርቬይንግና ካርታ ኢንጅነሪንግ መምህር ዶክተር ኢንጅነር ጥላሁን ኤርዱኖ ገለጹ፡፡

ዶክተር ኢንጅነር ጥላሁን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ባለፉት ዓመታት የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት የትብብር ማእቀፍ ባለመኖሩ አንዱ አንዱን ለማጥፋት በሚደረግ የፖለቲካ ድራማ ላይ የተመሠረተ አካሄድ ይስተዋል ነበር፡፡ የትብብር ማእቀፉ መኖሩ አንዱ ሀገር ሌላኛውን ሀገር ሳይበድል የውሃ ዋስትናው የሚከበርበትን ሁኔታ ይፈጥራል፡፡

ግብፅም የምታራምደውን የእኔ ብቻ የሚል ያለፈበት እሳቤ ትታ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር በትብብር መሥራት ይኖርባታል ብለዋል፡፡

ሁሉም የተፋሰሱ አባል ሀገራት በባለሙያ የተደገፈ ትንተና ተካሂዶ የየሀገራቱ ፍላጎት ምን ያህል እንደሆነ ታውቆና በጋራ የሚጠቀሙበትን መንገድ መፈለግ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ይህም በርካታ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ አንዱ ሀገር በሌላው ላይ ችግር እየፈጠረ አለመረጋጋትና ሰላም ማጣት እንዲፈጠር የሚያደርግበት ሁኔታ እንደሚቀርም ገልጸዋል፡፡

ግብፅ በዓለም ከሚታወቀው ከፍተኛ የከርሰ ምድር ውሃ ካላቸው ሀገራት አንዷ ናት ያሉት ዶክተር ኢንጅነር ጥላሁን፤ ከዚህም በተጨማሪ ሁለት ባህርና ሲዊዝ ካናልም አላት፡፡ ሀገሪቱ ከግማሽ በላይ በውሃ የተከበበች ናት ብለዋል፡፡

ይህ ሁሉ የውሃ ሀብት እያላት ዓባይ ጥገኛ ነኝ ብላ መቶ በመቶ ለእኔ ነው የሚገባው የሚለው ስግብግብነት የትም እንደማያደርስ ጠቅሰው፤ የሌሎች ሀገሮች ሕዝብ እያደገ በሄደ ቁጥር በዓባይ ወንዝ የመጠቀም ፍላጎት እጨመረ እንደሚሄድ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ይህን አጀንዳ ማቆምና በምን መልኩ በትብብር መጠቀም እንደሚቻል ማሰብ መቻል አለባት ብለዋል፡፡

እንደ ምሁሩ ገለጻ፤ የግብጽ ያረጀ እሳቤ የሚያበቃበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡ ሀገራት ሕዝባቸው በጨመረ ቁጥር ያላቸውን ሀብት ወደመጠቀም ይመጣሉ፡፡ ግብጽ በዚህ ግትር አቋሟ የምትቀጥል ከሆነ ከተፋሱ ሀገራት የሚገጥማት ተቃውሞ እየጨመረ ይመጣል፡፡

ኢትዮጵያ ከዓባይ ውሃ 86 በመቶ የሚሆነውን እንደምታበረክት አስታውሰው፤ የውሃው ዋንኛ ተጠቃሚ ሆና የቆየችው ግብፅ ኢትዮጵያን እንደጠላት መቁጠሯ ግርምት የሚፈጥር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት የመጠቀም መብት አላት ብለዋል፡፡

የተፈጥሮ ሀብቷን ለምን ተጠቀመች ተብሎ የሚመጣባትን ጠላት ለመመከት መላው ኢትዮጵያውያን በአንድነትና በትብብር መመከት ይኖርባቸዋልም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ግብፅ ዛሬ ኢትዮጵያ ላይ የምታደርሰው ጫና የሚሳካላት ከሆነ ነገ ወደ ሌሎችም የተፋሰሱ ሀገራት መዞሯ እንደማይቀር ገልጸው፤ ሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት ለፍትሐዊ ተጠቃሚነት መሥራና ከኢትዮጵያ ጎን መቆም እንዳለባቸውም አመላክተዋል፡፡

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You