ከ56 ዓመታት በፊት በደረሰ የአውሮፕላን አደጋ ከሞቱት ሰዎች መካከል የአራቱ አስከሬን ተገኘ

በሕንድ የተከሰከሰው አውሮፕላን ውስጥ ከነበሩ ሰዎች የአራቱ አስከሬን ከ56 ዓመታት ከስምንት ወር በኋላ ተገኝቷል።

በአደጋው ወንድሙን ያጣው ቶማስ ቶማስ የታላቅ ወንድሙ ቶማስ ቼሪያን አስከሬን ከ56 ዓመታት በኋላ መገኘቱን ያሳወቀው የፓታናምቲታ ፖሊስ ጣቢያ ስልክ ነው።

የሕንድ አየር ኃይል አውሮፕላን በአውሮፓውያኑ 1968 ነው 102 ሰዎች አሳፍሮ በአስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ምክንያት ሂማሊያን ተራራ ላይ የተከሰከሰው። የበረራ ቁጥሩ አይኤኤፍ ኤኤን-12 አውሮፕላን ለዓመታት አድራሻው አይታወቅም ነበር። አውሮፕላኑ ከራዳር ጋር ያለውን ግንኙነት የተቋረጠው በተራራማው ሮታንግ የተባለ ሥፍራ ነው።

በ2003 ተራራ የሚወጡ ሰዎች ከሟቾች መካከል የአንዱን አስከሬን ማግኘታቸው ትልቅ ዜና ሆኖ ነበር። ከዚህ በኋላ ለዓመታት የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች እና ወታደሮች ፍለጋቸውን አጠናክረው እስከ 2019 ድረስም 8 ተጨማሪ አስከሬኖች ማግኘት ችለዋል። አልፎም የአውሮፕላኑ ስብርባሪ ተራራ ላይ ሊገኝ ችሏል።

ከቀናት በፊት ደግሞ በ1968 በተከሰከሰው አውሮፕላን ምክንያት የሞቱ አራት ሰዎች መገኘታቸው ተዘገበ። ከአራቱ አንዱ ቶማስ ቼሪያን ነው። “ለ56 ዓመታት ሲያስጨንቀን የነበረው ጉዳይ ድንገት መልስ አገኘ” ሲል ታናሽ ወንድሙ ቶማስ ለቢቢሲ ተናግሯል።

የጦር ኃይል ቴክኒሺያን የነበረው ቼሪያን ቤተሰቡ ካሉት አምስት ልጆች ሁለተኛው ሲሆን፣ አውሮፕላኑ ሲከሰከስ የ22 ዓመት ወጣት ነበር። በተሰጠው ግዳጅ መሠረት ሌህ ወደተባለችው የሂማሊያን ግዛት ሲያቀና ነው አደጋው የተከሰተው።

በአውሮፓውያኑ 2003 ከሟቾቹ መካከል የመጀመሪያው አስከሬን ሲገኝ ነው መሞቱ በይፋ የታወጀው። “አባታችን በ1990 ነው የሞተው፤ እናታችን ደግሞ በ1998። ሁለቱም የልጃቸውን የመጨረሻ ዕጣ ፈንታ ዜና መስማት በጣም ይፈልጉ ነበር” ይላል ቶማስ። በጠቅላላው እስካሁን 13 አስከሬኖች ብቻ ናቸው የተገኙት።

ተራራማው ሥፍራ የአየር ሁኔታው ከባድ መሆኑ እና ብዙውን ጊዜ በበረዶ መሸፈኑ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችን ፍለጋ አዳጋች አድርጎታል። የቼሪያንን ጨምሮ የአራት ሰዎች አስከሬን የተገኘው ከባሕር ጠለል 16 ሺህ ጫማ ከፍታ ላይ በምትገኘው ዳኻ ተራራ ላይ ነው። አስከሬኖቹን ያገኙት የሕንድ ጦር ሠራዊት አባላት እና የቲራንጋ የተራራ ላይ አደጋ ጊዜ ሠራተኞች ናቸው።

የፍለጋ ሠራተኞቹ የሳተላይት ምሥል፣ ራዳር እና ድሮኖችን ተጠቅመው አስከሬኖቹን ሊያገኙ እንደቻሉ የሕንድ ጦር ሠራዊት አባል የሆኑት ኮሎኔል ላሊት ፓላሪያ ተናግረዋል።

ቼሪያን የለበሰው የጦር ሠራዊት ዩኒፎርም ‘ቶማስ ሲ’ የሚል ፅሑፍ ነበረበት። ሲ የምትለው ስትገኝ ሌሎች ኪሱ ውስጥ የነበሩ መታወቂያ ካርዶች ማንነቱን ለመለየት አስችለዋል።

የቶማስ ቼሪያን ቤተሰቦች ምንም እንኳ በሞቱ ምክንያት ኀዘናቸው ጥልቅ ቢሆንም፤ በስተመጨረሻ አስከሬኑ መገኘቱ ግን ትልቅ እፎይታ እንደሆነ ይናገራሉ።

ባለሥልጣናት የቼሪያን አስከሬን በሕንድ ባንዲራ በተሸፈነ ሳጥን ለቤተሰቡ ያስረከቡ ሲሆን፣ የቀርብ ሥነ- ሥርዓቱ ኤላንቱር በምትባል ሥፍራ ካለ አንድ ቤተ- እምነት ተካሂዷል።

የቼሪያን ብቻ ሳይሆን የሌሎች ሟቾች ቤተሰቦችም ሐዘናቸውን እየተወጡ ይገኛሉ። በርካታ ሰዎች በአደጋው ምክንያት የሞቱ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ዜና እየጠበቁ አርጅተዋል፤ ሞተዋል።

በቅርቡ አስከሬናቸው ከተገኙ መካከል ናራያን ሲንግ ነው። ሚስቱ ባሳንቲ ዴቪ የባሏን ዜና በጉጉት እየጠበቀች ሳለ ነው በ2011 ሞት የወሰዳት።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You