የአፍሪካ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ከሚያካሂዳቸው ዓመታዊ ውድድሮች መካከል አንዱ የክለቦች ሻምፒዮና ነው። እአአ ከ1979 አንስቶ በመካሄድ ላይ የሚገኘው ይህ ሻምፒዮና ዘንድሮ ለ45ኛ ጊዜ በሞሮኮ ላዩን ከተማ አስተናጋጅነት መካሄድ ከጀመረ ቀናትን አስቆጥሯል። በአሕጉሪቱ በሚገኙ የእጅ ኳስ ሊጎች የተሻሉ ክለቦች በሚሳተፉበት በዚህ ሻምፒዮና አሸናፊው ክለብ ከሁሉም ኮንፌዴሬሽኖች የተወጣጡ ክለቦች በሚፋለሙበት ሱፐር ግሎብ ውድድር ላይ ተካፋይ ይሆናል።
ጠንካራ ፉክክርና አዝናኝ ውድድር በሚስተናገድበት በዚህ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ክለቦቿን ማሳተፍ ችላለች። ከትላንት በስቲያ በተጀመረው ውድድር 16 የወንድ እና 11 የሴት ክለቦች በመካፈል ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ከአዘጋጇ ሃገር ሞሮኮ እኩል ሦስት ክለቦችን በማሳተፍ በቀዳሚነት ልትቀመጥ ችላለች። ጥሩ ልምድ ሊገኝበት እንደሚችል በሚጠበቀው በዚህ መድረክ ላይ ሃገራቸውን የወከሉት ክለቦችም መቻል የእጅ ኳስ ክለብ፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የእጅ ኳስ ክለብ እና መቐለ 70 እንደርታ የእጅ ኳስ ክለብ መሆናቸውን ከኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል። ግብፅ፣ ኮንጎ፣ ካሜሩን እና ቤኒን ሁለት ሁለት ክለቦቻቸው በውድድሩ ሲካፈሉ ከኮትዲቯር እና ሴኔጋል አንድ አንድ ክለቦች የዋንጫ ፍልሚያውን ያደርጋሉ።
በወንድ ክለቦች መካከል የሚደረገው ውድድር በአራት ምድብ ሲከፈል፤ ጠንካራ ፉክክር ይጠበቃል። በተለይም ከመድረኩ ከፍተኛ ልምድ ማግኘት የቻሉትና በስፖርቱም ብቃታቸውን ያስመሰከሩት የግብፅና የአሕጉሪቷ ኃያላን ክለብ የሆኑት አል አህሊ እና ዛማሊክ እርስ በእርስ የሚያደርጉት የሻምፒዮናነት ፉክክር ተጠባቂ ነው። አል አህሊ በዚህ ውድድር ለስድስት ጊዜያት ሻምፒዮን ሲሆን፤ እጅግ ስኬታማው ዛማሊክ ደግሞ 12 ዋንጫዎችን በማንሳት የውድድሩ ድምቀቶች ናቸው። በወጣው ድልድል መሠረትም በምድብ አንድ የኢትዮጵያው መቐለ70 እንደርታ ከግብፁ አል አህሊ፣ ከኮንጎው ኢትኦይሌ እንዲሁም ከኮንጎው ሲኤፍጄኤሶ ጋር ይገናኛል።
በዚህ መድረክ ለአራተኛ ጊዜ በመካፈል ከሌሎች ክለቦች የተሻለ ልምድ ያለው ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የእጅ ኳስ ክለብ ከግብፁ ዛማሊክ፣ ከሞሮኮው ማውንታዳ እንዲሁም ከካሜሮኑ ፍሬንድሺፕ ክለቦች ጋር በምድብ ሦስት ተደልድሏል። ምድብ አራት ላይ የሚገኘው መቻል እጅ ኳስ ክለብ ደግሞ ከቤኒኑ አድጂድጃ፣ ከሞሮኮው ዊዳድ እንዲሁም ከሴኔጋሉ አስፋ ጋር ይገናኛል።
ኢትዮጵያ በ1970ዎቹ ጠንካራና ተፎካካሪ የእጅ ኳስ ቡድኖች የነበራት ቢሆንም ባለፉት በርካታ ዓመታት ስፖርቱ እየተዳከመ መጥተል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ስፖርቱ ዳግም እንዲያንሠራራና በአሕጉር ደረጃም ተወዳዳሪ ወደመሆን እየተመለሰ ይገኛል። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በቅርቡ በኢፌዴሪ ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር መስፈርት መሠረት ከ69 ከመቶ በላይ በማሟላት በአንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጡ ነው። ምሥራቅ አፍሪካ እጅ ኳስ ማኅበርን በአመራርነት ማገልገል እንዲሁም የዞን እና አሕጉር አቀፍ ውድድሮች በኢትዮጵያ እንዲካሄድ ማድረጉም ለዚህ ከፍተኛ ሚና ነበረው። የኢትዮጵያ እና የምሥራቅ የእጅ ኳስ ፕሬዚዳንት ፍትሕ ወልደሰንበት(ዶ/ር) ኢትዮጵያ በዚህ ውድድር ሦስት ክለቦችን ስታሳትፍ በእጅ ኳስ ስፖርት ታሪክ ይህ የመጀመሪያው መሆኑን ይጠቁማሉ።
ከወራት በፊት በኢትዮጵያ አዘጋጅነት በተካሄደው እና 10 ሀገራት በተሳተፉበት የምሥራቅ አፍሪካ የዞን 5 ውድድር ላይ ከ18 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኗ ሻምፒዮን በመሆን ለአሕጉር አቀፉ ውድድር ማለፉ የሚታወስ ነው። ይህ የአፍሪካ ሻምፒዮና ከጥቅምት 23 እስከ 27/2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ የሚካሄድ ይሆናል። ለዚህ ውድድርም ብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኞች የተመደቡለት ሲሆን፤ ክለባቸውን በመወከል በሞሮኮው ሻምፒዮና በመሳተፍ ላይ የሚገኙት ተጫዋቾች መመለስን ተከትሎ በቅርቡ ወደ 20 የሚጠጉ ወጣቶችን በመያዝ ዝግጅቱን እንደሚጀምርም ታውቋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም