በክፍል አንድ መጣጥፍ መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር “100ኛ ዓመትን የማክበር ምጸት፤”ን በተመለከተ የግል ምልከታየን ከጋራሁ በኋላ የነጋድራስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝ ሁለቱ መጻሕፍት ማለትም “መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር” እና “አፄ ምኒልክና ኢትዮጵያ” በዶ/ር ሩቅያ ሀሰን የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልሳንና ሥነ ተግባቦት ተባባሪ ፕሮፌሰር የመጽሐፍ ቅኝት ወይም የነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝን ቡክ ሪቪው ወይም የመጽሐፍ ግምገማን ካቆሙበት ልቀጥል።
ነጋድራስ ለመንግሥትና ለሕዝባቸው በርካታ ምክሮችን በመጀመሪያው “አፄ ምኒልክና ኢትዮጵያ” በተሰኘው መጽሐፍ ላይ ያሰፈሩ ሲሆን በመጀመሪያ ምክሮቹ ለአፄ ምኒልክ የታቀዱ የነበሩ ቢሆንም በኋላ ግን ምክሮቹ ለልጅ እያሱ እንዲሆኑ በሚል ጽፈዋቸዋል፡፡ መጽሐፉ አጭር ሲሆን ትልልቅና ቁልፍ ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡ ነጋድራስ ካነሷቸው ቁልፍ ምክሮች ውስጥ ጥቂቶቹን እናነሳለን፡፡
ታላቁ ምሁር ነጋድራስ ገብረሕይወት ከመቶ ዓመት በፊት በጻፉት በዚህ አስደናቂ መጽሐፋቸው ለአንድ ሕዝብ ሥርዓት ወይም ሲስተም እንደሚያስፈልግ ሲገልጹ “የኃይል ምንጭ ሥርዓት ነው እንጂ የሠራዊት ብዛት አይደለም” ብለዋል፡፡ ላለመሰልጠናችንና ላለማደጋችንም በአስተሳሰብ ባለመብሰላችን መሆኑን ሲገልጹ ደግሞ እንዳሉት “እኛ ኢትዮጵያውያን ካለመስማማታችን የተነሳ ሌሎች ሕዝቦች በአእምሮና በጥበብ እየበረቱ ሲሄዱ እኛ ወደኋላ ቀረን” ነበር (ነጋድራስ ገ/ሕይወት 2003፣ 19)፡፡
በሚገርም ሁኔታ ነጋድራስ ገብረሕይወት ከመቶ ዓመት በፊት የጠቀሱት ጉዳይ ነገር ግን እኛን አሁን በደንብ የሚገልጸን የሚከተለው ገለጻቸው ነው፡፡ በመላው ዓለም ላይ ሰላም ሲሰፋ አእምሮም ስትበራ እኛ በጨለማ እንኖራለን፡፡ እርስ በርሳችን መጠራጠራችንንም አልተውንም፡፡ ሕዝቦቹም ሁሉ እርስ በርሳቸው በፍቅር ተቃቅፈው ስለልማታቸው ባንድነት ሆነው ሲደክሙ እኛ ግን ዘርና ወንድማማቾች መሆናችንን ገና አልተገለጸልንም፡፡ እርስ በርሳችን መፋጀትም እስከ ዛሬ ድረስ ጀግንነት ይመስለናል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ለብርታት የሚሆነውን ስጦታ ሁሉ ሰጥቶን ሳለ ባለቤቶቹ ሰነፍነ፡፡ ለሌሎቹም ነገሥታት እንደ ሰነፎች ይቆጥሩናል፣ ይንቁናልም (ነጋድራስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝ 2003፣ 19-20)፡፡
ነጋድራስ ገብረሕይወት የድህነታችንን ምክንያት ሲገልጹ የሚከተለውን አስቀምጠዋል፡፡
ሕዝቡም ሀብታም የሆነ መንግሥት ብርቱ ነው፡፡ ሕዝቡ የደኸየ እንደሆነ ግን ደካማ፡፡ እኛ ግን ሥርዓት የለንም፡፡ ስለዚህ ሰነፍን፡፡ በመሬታችን ውስጥ የተሸሸገውም ሀብት ፈላጊ አጣ፤ ስለዚህም ደኸየነ… ምነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከእንቅልፍህ መቸ ትነሳለህ? (ነጋድራስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝ 2003፣ 22)። ጽሑፍ ለማህበረሰብ እድገት መሠረታዊ መሆኑን ሲገልጹ እንዳሉት “ የተጻፈ ሥርዓት የሌለው መንግሥት ብዙ እድሜ የለውም” (ነጋድራስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝ 2003፣ 25)።
ከሁሉም በላይ ለዚህ ዘመን ነዋሪ እጅግ በጣም የሚያስገርመው የነጋድራስ ገብረሕይወት ሃሳቦች ውስጥ የሚጠቀሰው ስለሃይማኖት የጻፉት ነው፡፡ የሃይማኖት ነፃነት መኖር እንዳለበትና ሃይማኖት ከልብ የሆነ መሆኑንና ዳኛውም ፈጣሪ መሆኑን የገለጹበት መንገድ አስገራሚ ነው፡፡ ደግሞም በሀገራችን አንድ የድንቁርና ነገር አለ፡፡ ሃይማኖቱ ተዋህዶ ያልሆነ ሁሉ እንደ ርኩስ ይቆጠራል፡፡ ይህም እጅግ ያስቃል።፡ አእምሮ የሌለው ሕዝብ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ሳያውቅ የእግዚአብሔር ጠበቃ ሊሆን ይወዳል፡፡ … ሃይማኖት የልብ ነው፡፡ ስለዚህ ሰማያዊው ንጉስ እንጂ የዚህ ዓለም ንጉስ አይቆጣጠረውም (ነጋድራስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝ 2003፣ 28)፡፡ስለርእዮተ ዓለም ሲመክሩ ነጋድራስ ይህንን ብለው ነበር “ኢትዮጵያችን የኤሮጳን አእምሮ የተቀበለች እንደሆነ የሚደፍራት ጠላት የለም፡፡ ያልተቀበለች እንደሆነ ግን ትፈርሳለች፤ ወደ ባርነትም ትገባለች” (ነጋድራስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝ 2003፣ 28)፡፡
በስተመጨረሻ የመጀመሪያውን መጽሐፍ ያገባደዱት “መንግሥታችንም እንድትቀና የሚከተሉት አሥር ነገሮች በቶሎ ቢፈጸሙ ማለፊያ ነበር” (ነጋድራስ ገብረሕይወት፣ 2003፡ 23-27) ያሉትን በማቅረብ ነበር፡፡
- ለመንግሥት የሚሆን ገንዘብና ለንጉሡ የሚሆነውን ገንዘብ በሥርዓት ይለይ፡፡ ሹሞቹም በደመወዝ ይደሩ፡፡ ካገር የሚወጣውም ግብር ለመንግሥት ይግባ፡፡
- ሕዝቡ ለመንግሥት የሚከፍለው ግብር እንደየሀብቱ መጠን ቁርጥ ሆኖ ይታወቅለት፡፡ የሕዝቡም ቁጥር በመዝገብ ይግባ፡፡ እንዲሁም በየዓመቱ የሚወለደውና የሚሞተውም የሚጋባውና የሚፋታውም በመዝገብ ይታወቅ፡፡
- ሕዝቡም የሚከፍለው ግብር በብር እንጂ በእህል በማርም በፍሪዳም አይሁን፡፡ የመንግሥት ሥራ ሁሉም በባላገር አይስራ፤ በባለ ደመወዝ እንጂ፡፡
- የአማርኛ ቋንቋ ገና ሰዋሰው አልተበጀለትም። ስለዚህ መንግሥታችን ከያገሩ ሰዋሰው የሚያውቁትን ሊቃውንት ሰብስቦ የአማርኛን ቋንቋ ሰዋሰው ቢያስወጣ ደግ ነው፡፡… የሀገራችን ሰው ፊደልን ለመማር ቢተጋ ሀገራችን ቶሎ በቀናች፡፡ ፊደልንም መማር እጅግ ቀላል ነገር ነው፡፡
- ፍትሐ ነገሥታችን (ሕጋችን) ከዛሬው የአደባባይ ሥርዓት ጋር አይስማማም፡፡ ስለዚህ መንግሥት የሥርዓት አዋቂዎችን ሰብስቦ ከኤሮጳ ሥርዓት ጋር የተስማማ ፍትሐ ነገሥት ያውጣ፡፡
- የሀገራችን ሠራዊት ሥርዓት የለውም፡፡ ስለዚህ የኤሮጳን መኳንንት አምጥተው ሰልፍን ቢማር ማለፊያ ነበር፡፡ እንዲሁም የኤሮጳን መምህራን አምጥተው በአዲስ አበባ ላይ የጦር ትምህርት ቤት ይበጅ፡፡
- የዛሬው የመንግሥታችን ብር የተበላሸ ነው። ሥርዓት ውል የለውም፡፡ ስለዚህ መንግሥት ለመላው ኢትዮጵያ የሚሆን የገንዘብ ሥርዓት በቶሎ ያላወጣ እንደሆነ ንግድ ሊለማ አይችልም፡፡
- ለሀገራችን ነጋዴ ሥርዓት እስኪወጣለት ድረስ መንግሥታችን አይቀናም፡፡ በሩና (ኬላው) ቀራጩ ብዙ ነው፡፡ በአንድ መንግሥት ውስጥ አንድ ነጋዴ በየበሩ መቀረጥ የለበትም፡፡
- ሕዝቡ ባንድ መንግሥት ውስጥ መሆኑን አጥብቆ እንዲታወቀው ሀገሩን የሚዞሩ ተቆጣጣሪዎች ይሾሙበት፡፡
- የሃይማኖት አርነት ይታወጅ፡፡ የሃይማኖት አርነት ቢታወጅ ሃይማኖት ይታወቃል እንጂ አያጠፋም፡፡ ሃይማኖት የልብ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ሰማያዊው ንጉሥ እንጂ የዚህ ዓለም ንጉሥ አይቆጣጠረውም።
«መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር»
ሁለተኛው መጽሐፍ “መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር” ሰፋ ያለ ሲሆን ደራሲው በርካታ ቁልፍ ጉዳዮችን አንስተዋል። ይህ መጽሐፍ ኢኮኖሚክስ፣ ገንዘብ፣ ንግድና የመሳሰሉ ጉዳዮችን ይዳስሳል፡፡ ለሁሉም ነገር ቁልፉ ትምህርት እንደሆነ ሲገልጹ ይህንን ብለዋል “መንግሥት ኃይል ለማግኘት የፈለገ እንደሆነ ሕዝቡ እንዲበለጽግና እንዲማር መጣር ያስፈልገዋል” (ነጋድራስ ገብረሕይወት 2003፣ 36)፡፡ ስለዋጋ ሲናገሩ “ዋጋ ማለት የሥራ መለኪያ ማለት ነው” (ነጋድራስ ገብረሕይወት 2003፣ 68)፡፡
የኑሮ ውድነትና ጫናን ለመቀነስ እውቀት ቁልፍ እንደሆነ ነጋድራስ እኛን የመከሩን ከመቶ ዓመት በፊት እንደዚህ ብለው ነው “እውቀት ሲበዛ ለኑሮ የሚያስፈልገውን ማናቸውንም ነገር ለማግኘት መሰናክሉ ያንሳልና የማናቸውም ዋጋ ሁሉ ዝቅ ይላል” (ነጋድራስ ገብረሕይወት 2003፣ 71)፡፡ ትምህርት ለአንድ ሕዝብ የጀርባ አጥንት መሆኑን ሲገልጹ “ሕዝቡ እንዳይጎዳ የሚፈልግ መንግሥት ሁሉ አውራ ጥረቱ ትምህርት እንዲበዛ ነው” (ነጋድራስ ገብረሕይወት 2003፣ 75)፡፡
ነፃነት በእውቀትና በትምህርት የሚገኝ መሆኑን ሲገልጹ “ሰው በዓለም ላይ ጌታ የሆነው ግን በእውቀቱ ብቻ ነው።… እውቀት የሌለው ሕዝብ ሁሉ ለብቻው መንግሥት ቢኖረውም ባይኖረውም እውቀት ያላቸው ሕዝቦች ይገዙታል” (ነጋድራስ ገብረሕይወት 2003፣ 75)፡፡ እውቀት ለሰው ልጅ መበልጸጊያና ማደጊያ መሠረታዊ መሳሪያ መሆኑን ሲያሰምሩ “እውቀት ዓለምን እንዲገዛ የማይነቃነቅ ዘላለማዊ ደንብ ነው” ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ደራሲው የሰው ልጅ ሲፈጠር ጌታና ሎሌ እንዲሆን እንዳልነበረ አጽንኦት ሰጥተው አብራርተዋል፡፡ ፈጣሪ የሰውን ልጅ በምድር ሲያስቀምጥ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ አሟልቶለት እንደሆነም በሚመስጥ አገላለጽ ገልጸውታል “ለሰው የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ምድር በሆዷ ይዛለች፡፡… ማናቸውንም ነገር ሲፈልግ አንቀሳቅሶ ማጋጠም ብቻ ነው ያለበት፡፡ ማንቀሳቀስና ማጋጠም የሚሆነው በሥራ ነው። ስለዚህ የሰው እውቀቱና ገንዘቡ ሥራ ብቻ ነው” ይሉናል (ነጋድራስ ገብረሕይወት 2003፣ 80)፡፡
በእውቀት፣ በሥራና በጥረት ላይ የተመሠረተ ለውጥን የሚያቀነቅኑት አስገራሚው ነጋድራስ ገብረሕይወት “ሰውም ምድርን የሚገዛበት ምክንያት በእውቀት ነው እንጂ በጉልበት አይደለም” ያሉን ከ100 ዓመት መሆኑ ነገር ግን እና እስካሁን አዲስ ነገር እየሆነብን መሆኑ ይገርማል፡፡ እሳቸው ግን አበክረው “እውቀት የሌለው ሕዝብ ሀብታም ሊሆን አይችልም” ብለውናል (ነጋድራስ ገብረሕይወት 2003፣ 83)። የሰው ልጅ ምድርን ለመግዛት እንጂ በምድር ለመገዛትና የምድር ሎሌ ለመሆን እንዳልተፈጠረ ያስረዳሉ፡፡ ነገር ግን ደሃ ከሆንን ሌላ አማራጭ አይኖረንም፡፡ ይህንንም በአሳማኝ ሁኔታ ሲያቀርቡት እንደዚህ በማለት ነው “ድሃ የሆነ ሕዝብ የምድር ሎሌ ነው፡፡ በረሃብና በበሽታ በሞት ስታንገላታው ትኖራለች። ሀብታም ሕዝብ ግን የምድር ጌታ ነውና ምድር ሎሌ ሆኖ ታገለግለዋለች” (ነጋድራስ ገብረሕይወት 2003፣ 84)፡፡
ሌላው አስገራሚው የገብረሕይወት ገለጻ ስለሀብት የሰጡት ነው፡፡ “ሀብት ማለት የተከማቸ ሥራ ማለት ነው።… እውቀት የሌለው ሕዝብ ግን ሥራው አይከማችለትም፡፡ የፊት የፊቱ ወዲያው ያልቃል። ከድካሙም ፍሬ የሚያገኘው ጥቅም ጥቂት ነው። ስለዚህ እውቀት የሌለው ሕዝብ ድሃና የሰው ሎሌ ነው” (ነጋድራስ ገብረሕይወት 2003፣ 94)። ከውጭ ስለሚመጡና ስለምንገዛቸው ቁሶች ሲገልጹ “እውቀት ያነሳቸው ሕዝቦች እውቀታቸው ከፍ ካለ ሕዝቦች ላይ እቃ ሲገዙ እየተበደሩ ነው። የሚበደሩትም ብድር እኩሌታው ከጉልበታቸው እኩሌታው ከምድራቸው ነው” ይሉናል፡፡
ነፃነት ስላለው ሕዝብ የሚከተለውን ማብራሪያ በመግለጽ ስለሀገራችን ነፃ መሆን ይጠይቃሉ። እስቲ አሁን እኛ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርነት አለን ነው? አርነት ያለው ሕዝብ ማለት እውነተኛ ትርጉሙ ለብቻው መንግሥት ያለው ሕዝብ ማለት ብቻ አይደለም፤ ራሱን የቻለ ሕዝብ ማለት ነው እንጂ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እስከ ዛሬ ድረስ ገና ራሱን አልቻለም፡፡ እስቲ የለበስነውን እንይ፤ ከወዴት የተሠራና ማን ያመጣው ነው? የቤታችንስ እቃ ራሱ ከወዴት የመጣ ነው? የምንለብሰውስ ልብስ የምንጠጣውስ የምንበላበት ምግባችንን የምናበስልበት እቃና መሥሪያ ሁሉ ፈጽሞ ከውጭ ሀገር የመጣ አይደለምን?” (ነጋድራስ ገብረሕይወት 2003፣ 102)፡፡
የሀገር ሀብት የሚያንሰው ከሰሪው ይልቅ በላተኛው ሲበዛ መሆኑን ገልጸው ለሀገር ብልጽግና ሲባል እውቀት ብቻ ሳይሆን ሀብትም እንደሚያስፈልግ አበክረው እንደሚከተለው ይመክራሉ “የዚህ ዓለም ሕዝቦች የለውጥ መሳሪያዎቻቸው ብርና ወርቅ ብቻ ስለሆኑ ብርና ወርቅ ያነሰበት ሕዝብ ከፍ ወዳለው የእውቀት ደረጃ ደርሶ ሀብታም ሊሆን አይችልም” (ነጋድራስ ገብረሕይወት 2003፣ 131)። በተጨማሪም መሠረታዊ ፍላጎቱን ያላሟላ ሕዝብ የሀገር ፍቅር እንደማይኖረው በማሳሰብ የሕዝብን ፍላጎት ማሟላት ለሀገር ደህንነት ቁልፍ ሚና እንዳለው በዚህ መልኩ ይነግሩናል “የሚበላውና የሚለብሰውንም ያጣ ድሃ የተወለደበትን ሀገር የሚወድበትን ምክንያት ያጣልና ያገሩ መንግሥት ቢበረታ ወይም ቢጠፋ ግድ የለውም፤ ስለዚህ መንግሥት የሚጠቁም ያገሩ ሀብት በጥቂቶች ሰዎች እጅ ቢሰበሰብ አይደለም፡፡ ያገሩን ሀብት በመላው ሕዝቡ ሊከፋፈል ነው እንጂ” (ነጋድራስ ገብረሕይወት 2003፣ 142)፡፡
ሥርዓት ወይም ሲስተም ከሕዝብ ፍላጎት መመንጨት እንዳለበት ሲያብራሩ እንዳሉት “ሥርዓት የሚመች ይሆናል ተብሎ በብልሆች ሰዎች ልብ ውስጥ ተፈጥሮ አይጻፍም፤ ከሕዝብ ልብ ቀዳል እንጂ፡፡ ንጉሥ ወይም ሹም በኋለኞች ትውልዶች የሚመሰገንም በልቡ ፈልስፎ ደንብ ሲያወጣ አይደለም፡፡ የህሕቡን ሃሳብ ተርጉሞ በትርጉሙ ሲሄድ ነው እንጂ” (ነጋድራስ ገብረሕይወት 2003፣ 147)፡፡ የሕዝብና መንግሥት መሠረት ትምህርት ቤት መሆኑን ያሰመሩበት ነጋድራስ ገብረሕይወት” ትምህርት የሌለበት ሀገር አዲስ ደንብ ቢያወጣ ከሚጠቅመው የሚጎዳው ይበልጣል” ብለዋል (ነጋድራስ ገብረሕይወት 2003፣ 148)፡፡
ሥራን በመሥራት ሀብት ለማካበት በምንጥርበት ወቅት መተማመን ቁልፍ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ብር የለውጥ መሳሪያ እንጅ ሌላ ፋይዳ ያለው ነገር እንዳልሆነ አስገንዝበዋል። የሰው ልጅም መልካምና መጥፎ ባህሪ እንዳለው ሲገልጹልን “የሰው ባህሪው ሁለት ነው፡፡ አንዱ መለኮታዊ፤ ሁለተኛው ግን እንስሳዊ ይባላል፡፡ ቀስቃሽ ካላገኘ ግን ሰው መልአካዊ ባህሪውን አይከተልም፡፡ ወደ እንስሳዊ ባህሪው ያደላል። ለሰው አውራ ቀስቃሽ ግን ባላንጣ ነው” (ነጋድራስ ገብረህይወት 2003፣ 164)፡፡
አንድ መንግሥት አማካሪ እንደሚያስፈልገው የሚያ መለክት አንድ ተጨባጭ ምክር በባንክ ዙሪያ የሚከተለው ተገልጿል። ዛሬ በኢትዮጵያ የቆመው ባንክ ኦፍ አቢሲን ከቆመበት ቀን ጀምሮ እስከ ሀምሳ ዓመት ድረስ በኢትዮጵያ ሌላ ባንክ እንዳይቆም ውል ተቀብሏል። ከዚህ ቀደም እንደተረዳነው ግን ማናቸውም ነገር የጥቂቶች ሰዎች እጅ ገብቶ ሞኖፖል ሲሆን ለሕዝብም ለመንግሥትም ጉዳት ነው። ለአፄ ምኒልክ አንድ ሰው መጥቶ ባገርዎ ከኔ በቀር ሌላ ሰው እንዳያርስ ወይም በቅሎ ገዝቶ እያከራየ እንዳይነግድ ወይም እኔን ሳይጠይቅ በየቤቱ ማንም ወጥ እየሠራ እንዳይበላ ፈቃድ ይስጡኝ ብሎ ለምኗቸው ቢሆን የሚያናግራቸው ቃል ምንም ቢያምር የሰጣቸው ተስፋ ምን ትልቅ ቢሆን ያለ ጥርጥር ይቆጡት ነበር (ነጋድራስ ገብረሕይወት 2003፣ 163)፡፡
መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደርን በተመለከተ ሃሳባቸውን በሚከተሉት በአስር ነጥቦች አጠቃለው አስቀምጠዋል (ነጋድራስ ገብረሕይወት 2003፡ 124-126)፡፡
- ሰው የተፈጠረ የምድር ጌታ ለመሆን ነበር፡፡ ነገር ግን በመጀመሪያ ጥቂት እራሱን ስለሆነ የሚበቃ መሳሪያ የለውምና የምድር ተገዥ ሆነ፡፡
- በኋላ ግን እውቀት ስላገኘ ተባዛ ተባበረም፡፡
- በዝቶ ከተባበረም ዘንድ ሥራውን ተከፋፍሎ የሠራውን ሥራ እንደየሥራው መጠን መለዋወጥ ጀመረ፣ ዋጋ ማለት የሥራ መለኪያ ነው እንዳልነው ሁሉ፡፡
- ሀብት ማለት የዓለም ጌትነት መለኪያ ነው፡፡ ማንቀሳቀስና ማጋጠም የሚሆነው በሥራ ብቻ ነውና ሀብት ማለት የተከማቸ ሥራ ማለት ነው፡፡
- ማንኛውም የተሠራ ሥራ ከኋላ የሚከተለውን ሥራ ያቀላል፡፡ ማንኛውንም ሀብት የበለጠ ሀብት ይከተለዋል።
- የሕዝብ ሀብት የሚሰፋው ሕዝቡ የሚያስፈልገውን ሁሉ ለመሥራት ሥራውን በብዙ ተካፍሎ የተለዋወጠ እንደሆነ ነው፡፡
- የድካማቸውን ፍሬ የሚለዋወጡ ሠራተኞች እንዲቃረቡ መንግሥት መጣር ይገባዋል፡፡
- መንገድና የምድር ባቡርም ጥቅም የሚሆነው የሥራ ማሰልጠኛ የትምህርት ቤቶች በያይነቱ ሲሰራና ማናቸውም እቃ ሁሉ እንደሚቻል መጠን ባገሩ ውስጥ እንዲበጅ መንግሥትም ሲጥርበት ነው፡፡
- መሬቱ በጥቂቶች ሰዎች እጅ የገባ ሕዝብ በጣም ይደኸያል፡፡ የባላገሩ ጥቅም እያነሰ ይሄዳል፣ መሬትም ይረክሳል፡፡
- የመንግሥት መሠረት እርሻ ነው፡፡ ባለእርሻ የሚያገኘው ጥቅም ሲያንስ የመንግሥት መሠረት አይጠናም። ባለእርሻ ሲጠቀም ግን መንግሥትም ይጠነክራልና ይበረታል፡፡
ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ ከመቶ ዓመታት በፊት ያስቀመጧቸው እነዚህ ቁልፍ ቁልፍ ሃሳቦች በአሁኑ ሰዓት ብንተገብራቸው ራሱ ብዙ እናተርፋለን፡፡ በጣም መነበብ ያለበት ምርጥ መጽሐፍ ነው፡፡
ሻሎም ! አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25 ቀን 2016 ዓ.ም