“መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር”100ኛ ዓመትን የማክበር ምጸት፤

(ክፍል አንድ)

ባለፈው ሐሙስ ሚያዚያ 17፣2016 ዓ.ም አንድ ጉምቱ የኢኮኖሚክስ ሊቃ ከአንድ የኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ ጋር ሰሞነኛ የመንግሥት ኢኮኖሚያዊ ውሳኔዎችን ማለትም የችርቻሮ፣ የጅምላ፣ የገቢና ወጪ ንግድ ለውጭ ዜጎችና ኩባንያዎች ክፍት መደረጉ ስለሚኖረው አንድምታ ሲያብራሩ ነጋድራስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝ(1879-1912 ዓ.ም) ስለገቢና ወጪ ንግድ በምሳሌ ያቀረቡትን ትንታኔ ሲያወሱ በእግረ መንገዳቸው፤”መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር” የተሰኘው የነጋድራስ መጽሐፍ የታተመበት 100ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በሳይንስ አካዳሚ ውይይት መካሄዱን ሲናገሩ ጆሮዬ ጥልቅ አለ። የሰማሁት ነገር የተደበላለቀ ስሜት ፈጠረብኝ።

በሀገራችን ኢኮኖሚ፣ በሕዝባችን ኑሮ ተርጉመን ያልገለጥነውን፤ ከመጽሐፍ መደርደሪያ ያላወረድነውን፤ አቧራውን አራግፈን ብናወርደውም ከምርምር ርካታ በላይ ሥራ ላይ ያላዋልነውን፤ በምትኩ የአዳም ስሚዝን ነፃ ገበያ፤ የእነ ኤንግልስን ሶሻሊዝም እንደወረደ ስንኮርጅ ኖረን፤ ፋና ወጊውን የነጋድራስ የፖለቲካል ኢኮኖሚ መጽሐፍ 100ኛ ዓመት ልደት ማክበር ምን ይሉታል። ምጸት እንጂ። አበው እማው የወለፈንዲ ስልቻ ጤፍ ያፈሳል ባቄላ ይቋጥራል እንዳሉት። ነጋድራስ ከመቃብር ቀና ብሎ ቢያንስ ምን ይለን። ምን ይታዘበን። መቼም ሌላው ቢቀር በስጨት ብሎ መጽሐፉን የጻፍሁት እኮ ዓመት እየቆጠራችሁ ልደት እንድታከብሩለት፣ ሻማ እንድታበሩለት ሳይሆን ሥራ ላይ አውላችሁ የሀገርንም የሕዝብን ኑሮ እንድትቀይሩበት ነው ማለቱ አይቀርም። ሲጀመር ይሄን ልደት የማክበርስ የቅስም ወይም የሞራል ልዕልና አለን ወይ የሚለውን ጥያቄ እግረ መንገድ ማንሳት ተገቢ ነው።

ከ100 ዓመት በፊት ያነሳቸው ችግሮች ዛሬም በዛ እንዳሉ ቢገነዘብ፤ በመፍትሔነት ያቀረባቸው ጥልቅ ዕይታዎችና አቅጣጫዎች አንዳቸውም ሥራ ላይ አለመዋላቸውን ሲያረጋግጥ ደግመን ደጋግመን እንደገደልነው ተሰምቶት ክፉኛ የሚያዝንብን ይመስለኛል። ታላቁ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ሰው ነጋድራስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝ ከ100 በፊት የለያቸው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ዛሬም በሀገራችን እንዳሉ ናቸው። በመፍትሔነት ያስቀመጣቸው ነጥቦችም አንዳቸውም ሥራ ላይ ባለመዋላቸው ከድህነትና ኋላቀርነት አዘቅት መውጣት እንዳንችል አድርጎናል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ሀብታሙ ግርማ በአንድ መጣጥፋቸው እንደገለጹት፣ “መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር” የሚለው መጽሐፍ በመጀመሪያዎቹ ምዕራፎቹ የሰው ልጅ ተፈጥሮን በቁጥጥሩ ሥር ማዋል እንደሚችል፣ የዓለም ሕዝቦች በሀብት ደረጃቸው እንዲራራቁ መንስዔው ጦርነት እንደሆነ፣ ጦርነት ያልነቃና ያልሠለጠነ ሕዝብ መገለጫ እንደሆነ ያብራራሉ። በኢትዮጵያም ሕዝቡ ከፍ ወዳለ ደረጃ እንዳይደርስ ያደረገው ጦርነት ነው ሲሉ ይሞግታሉ። ከ100 ዓመት በፊት ነጋድራስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝ፤ የሰው ልጅ ተፈጥሮን በቁጥጥር ስር ማድረግ ካልቻለ የተፈጥሮ ሎሌ ባሪያ ይሆናል እንዳለው እኛም ሎሌ ነን። የሰማይ ግት ሲነጥፍ ለድርቅ ለረሀብና ለቸነፈር የምንጋለጥ የተፈጥሮ ሎሌ።

የዓለም ሕዝቦች በሀብት ደረጃቸው እንዲራራቁ መንስዔው ጦርነት እንደሆነ ቢያስጠነቅቀንም ዛሬም የጦርነትንና የግጭትን ቀለበት ሰብረን መውጣት አልቻልንም። ከ100 ዓመት በፊት ነጋድረስ፣ “በኢትዮጵያም ሕዝቡ ከፍ ወዳለ ደረጃ እንዳይደርስ ያደረገው ጦርነት ነው ብሎን ሳያበቃ ዛሬም ጦርነት ላይ መሆናችንን ከመቃብሩ ቀና ብሎ ቢያየን እንዴት ያፍርብን። እንዴት ያጥርብን። በሀዘን አደባባይ ወጥቶ ልብሱን ቀዶ፤ በጸጉሩ ላይ ትቢያ እየነሰነሰ፤ በብግነት ጥርሱን እያፏጨ እንዴት ዓይኑን እንደሚያጉረጠርጥብን ሳስብ የመጽሐፉ 100ኛ ዓመት ልደት ልግጫ ቧልትና ምጸት ይሆንብኛል።

እውነት ለመናገር በሀገራችንና በሕዝባችን ያልገለጥነውን ያልተረጎምነውን መጽሐፍ ልደት ከምናከብር ለዚች ሀገርና ለዚህ ሕዝብ የነበረውን ራዕይና መሻት ዳር ባለማድረስ ከአንድም ሁለት ሶስት ጊዜ የገደልነውን የነጋድራስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝን ሙት ዓመት ብናከብር አይሻልም ትላላችሁ። የግል ትዝብቴን በዚህ እልባት ልስጥና እናንተም የራሳችሁ ዕይታ እንዲኖራችሁ የአማርኛው ሪፖርተር ጋዜጣ በዚያው ሰሞን ይዞት የወጣውን የ100ኛ ዓመት ዘካሪ ጹሑፍ ላጋራችሁ።

ይህ ሒሳዊ የምጣኔ ሀብት (ኢኮኖሚክስ) ትንታኔ ይዘት ያለው መጽሐፍ የታተመበትን 100ኛ ዓመት በማስመልከት የካቲት 2 ቀን 2016 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነ ጥበብ ማዕከል የውይይት መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር። በመድረኩ ዳሰሳ ያቀረቡት፣ የገብረ ሕይወት የኢኮኖሚ ዕሳቤዎችን ከዘመናዊ የምጣኔ ሀብት ሳይንስ፣ የንግድ ንድፈ ሃሳቦች (ቲዮሪ) እና አስተምህሮዎችን ጋር አነፃፅረው መጽሐፍ ያዘጋጁት ዓለማየሁ ገዳ (ፕሮፌሰር) ናቸው። “መንግሥትና የሕዝብ አስተዳር” በዘመናዊ የምጣኔ ሀብት ጥናትና ምርምር ውስጥ በንድፈ ሃሳብ ደረጃ በማስተዋወቅና በጀማሪነት ከሚጠቀሱት በርካታ የንድፈ ሃሳብ አመንጪዎች (theoreticians) አኳያ በርካታ ሃሳቦችን አስቀድሞ የበየነ መጽሐፍ እንደነበረ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ አስረጅና እማኝ በመጥቀስ አብራርተዋል።

“መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር” በዘመናዊ የምጣኔ ሀብት ጥናትና ምርምር ውስጥ በንድፈ ሃሳብ ደረጃ በማስተዋወቅና በጀማሪነት ከሚጠቀሱት የንድፈ ሃሳብ አመንጪዎች አኳያ በርካታ ሃሳቦችን አስቀድሞ የበየነ መጽሐፍ እንደነበር ዓለማየሁ (ፕሮፌሰር) አስረጅና እማኝ በመጥቀስ አብራርተዋል። በመጽሐፋቸው ውስጥ ለዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጠቃሚና ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ፣ ሊሠራባቸው የሚችሉና በምጣኔ ሀብት ዙሪያ ያጠነጠኑ ነጥቦች መካተታቸው ከእነዚህም መካከል በበለፀጉና ባላደጉ ሀገሮች መካከል የሚከናወነው የንግድ ልውውጥ እንደሚገኙበት አስረድተዋል።

በዚሁ የንግድ ልውውጥ የበለፀጉ ሀገሮች በፋብሪካ የተመረቱ ዕቃዎችን ላላደጉ ሀገሮች ሲያቀርቡ፣ ያላደጉ ሀገሮች ደግሞ ለበለፀጉ ሀገሮች ጥሬ ዕቃዎችን በማቅረብ እንደሚንቀሳቀሱ፣ ይህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ ደግሞ የበለፀጉ ሀገሮችን ትርፋማ እንዳደረጋቸው ነው ያመለከቱት።

ባላደጉ ሀገሮች የሚታው ግጭት/ጦርነትና ስግብግብነት ለኋላቀርነታቸው ምክንያት መሆኑንም በጽሑፋቸው ውስጥ ማካተታቸውን፣ ይህም ምክንያት ከበለፀጉ ሀገሮች ጋር እየተካሄደ ካለው የተዛባ የንግድ እንቅስቃሴ፣ ጋር ተዳምሮ ያላደጉ ሀገሮች ገቢ እያሽቆለቆለና በድህነት አረንቋ ውስጥ እንዲዘፈቁ ማድረጉንም አውስተዋል። በዚህም የተነሳ ያላደጉ ሀገሮች ገቢ ዓመት ከዓመት አንድ እየቀነሰ፣ ተስፋቸው እየተመናመነ መምጣቱን መጽሐፉ ማመልከቱን፣ ከዚህም ሌላ የኢኮኖሚ ዕድገት ከዋነኞቹ መለኪያዎች/መሥፈርቶች መካከልም የዕድገቱ ሥርጭት በኅብረተሰቡ አኗኗርና ወርሃዊ ገቢ ላይ ለውጥ ማምጣት አለበት የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ መሞከሩን ከአቅራቢው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል።

ገብረ ሕይወት በሀብት ምጣኔ ዙሪያ የሚያራምዱት ንድፈ ሃሳብ “ሌበር ቲዎሪ” እንደሚባል ከጽሑፋቸው ለመረዳት እንደተቻለ፣ በዚህም ቲዎሪ መሠረት ከፋብሪካ እየተመረተ ለሽያጭ የሚቀርበው አንድ ዕቃ ዋጋ የሚወጣለት ዕቃውን ለማምረት የፈሰሰው የሰው ጉልበትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መሆኑን አንጸባርቋል። አሜሪካ ውስጥ በቅርቡ የወጣው “ሞደርን ሞኒተሪ ቲዎሪ” መንግሥት ለሕዝብ አገልግሎት የሚውል መንገድ፣ ጤና ተቋም ወዘተ ለማሠራት ከፈለገ “በጀት” የሚባል ገደብ ሳያስፈልገው ገንዘቡን እያተመ በማውጣት ብቻ ሊጠቀምበት እንደሚገባ ያስቀምጣል። ሌሎች ወገኖች ደግሞ የመንግሥት ወጪ ከገቢው ጋር እኩል ወይም የተመጣጠነ መሆን እንዳለበት ያምናሉ። በጣም የሚገርመው ነገር ቢኖር የሞደርን ሞኒተሪ ቲዎሪና ፈረንጆች በልማት ኢኮኖሚ ውስጥ አገኘን ያሉትን ሌላ ቲዎሪ፣ ገብረ ሕይወት ከ100 ዓመት በፊት በተዘጋጀውና ሂሳዊ የምጣኔ ሀብት ይዘት ባለው መጽሐፋቸው ውስጥ እንዳንፀባረቋቸው ከዓለማየሁ ገዳ (ፕሮፌሰር) ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል።

ነጋድራስ ገብረ ሕይወት የተወለዱት በትግራይ ዓድዋ ሲሆን፣ በስምንት ዓመት ዕድሜያቸው ድንገት በመርከብ ወደ ባህር ማዶ ተሻገሩ። በዚያም ኑሯቸውን አድርገው ጀርመን በሚገኘው በርሊን ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት ተከታትለዋል። ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የጀርመን ሐኪሞች አፄ ምኒልክን ለመርዳት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ነጋድራስም በረዳትነት ተከትለዋቸው እንደመጡ፣ ነገር ግን አማርኛና ትግርኛ ስለረሱ የመግባቢያ ችግር እንደገጠማቸው፣ በዚህም የተነሳ ሰሜን ሸዋ አቶ ይገዙ በተባሉ ሰው ቤት አማርኛ ለሰባት ወራት መማራቸው ተገልጿል።

ከአማርኛ ትምህርታቸው በኋላ በሐረርና በድሬዳዋ የጉምሩክ ኃላፊ ሆነው እንዳገለገሉ፣ ‹‹አፄ ምኒልክና ኢትዮጵያ››፣ እንዲሁም ‹‹መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር›› የሚባሉ መጻሕፍትን እንዳዘጋጁ ገልጸው፣ የመንግሥቱን ሥራ ያከናወኑትና መጻሕፍቱንም ያዘጋጁት ለሰባት ወራት ያህል በተማሩት አማርኛ መሆኑንና ይህም ሆኖ ግን ጽሑፋቸውና ሥራቸው ዘመን ተሻጋሪና የተዋጣለት መሆኑንም አስረድተዋል። ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ በሕይወት ዘመናቸው በሥራቸው ጥንቁቅ፣ በአነጋገራቸው ደፋር እንደነበሩና በዚህም የተነሳ ከጊዜው ሰዎች ጋር እንደማይስማሙ ነው የተገለጸው።

በነካ እጄ ሰሞኑን ያነበብሁትን በዶ/ር ሩቅያ ሀሰን የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልሳንና ሥነ ተግባቦት ተባባሪ ፕሮፌሰር የመጽሐፍ ቅኝት ወይም የነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝን ቡክ ሪቪው ወይም የመጽሐፍ ግምገማ ላጋራችሁ። የነጋድራስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝን ሁለት መጽሐፎች በአንድ ጥራዝ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ በ2003 ዓ.ም. አሳትሞታል። የነባር ምርጥ መጻሕፍት ሕትመት በሚል ርእስ እያሳተማቸው ካለው መጽሐፎች ውስጥ ይህ ድንቅ ሥራ በመካተቱ ፕሬሱ ሊመሰገን ይገባል። በዚህ መጽሐፍ በአንድ ጥራዝ የወጡት የነጋድራስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝ ሥራዎች “አፄ ምኒልክና ኢትዮጵያ”ና “መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር” የተሰኙ ናቸው። ሥራዎቹ እንዲታተሙ ሃሳብ ያቀረቡት የወቅቱ የፕሬሱ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ እንደሆኑ የየነጋድራስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝ የልጅ ልጅ የሆኑት ወ/ሮ ዓይናለም አሸብር ገብረ ሕይወት ገልጸዋል።

ለመጽሐፉ መግቢያ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ እንዲሁም ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ ጽፈዋል። ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ በመጽሐፉ ጀርባ ላይም እንደታተመው ስለደራሲው ሁለት አስገራሚ ነገሮችን ሲጠቅሱ አንደኛው ገብረ ሕይወት ይህን የመሰለ እስካሁን ድረስ የሚያስተጋባ ጥልቅ የኢኮኖሚና ፖለቲካ ጉዳዮችን በሰላሳዎቹ እድሜ መጻፍ መቻላቸውና ሁለተኛው የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ባልሆነው በአማርኛ ውብና አጥንት የሚሰረስር ሥራ ጽፈው ማለፋቸው ነው። የሞቱት በ33 ወይም በ37 ዓመት እድሜያቸው በ1911 ከአውሮፓ በመጣው የንፋስ (ግሪፕ) የወረርሽኝ በሽታ እንደሆነ በመጽሐፉ ተገልጿል።

ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ በሁለተኛው መጽሐፍ ላይ ሰፋ ያለ አድናቆት ያስቀመጡ ሲሆን የብዙ ኢኮኖሚክስ ሃሳቦች ባለቤት እንደነበሩና ከሳቸው ከ50ና 60 ዓመት በኋላ የመጡ ምእራባውያን ኢኮኖሚስቶች የሳቸውን ሃሳብ በባለቤትነት ወስደው እንደሚታወቁበት ነገር ግን አሁንም የነጋድራስ ሞዴል እያሉ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ የሚጠሯቸው አዳዲስ የኢኮኖሚክስ ሃሳቦች እንዳሏቸው በከፍተኛ አድናቆት ጽፈዋል።

ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You