ስቅለቱን ስናስብ !

የስቅለት በዓል ፈጣሪ አምላክ አንድ ልጁን በመስጠት ስለሰው ልጆች ሐጢያት ስርእየት ዋጋ የከፈለበትን ፣ የሰውን ልጅ የወደቀ ፍጥረታዊ ማንነት በማደስ ሙሉ ሰው የሚሆኑበትን የምህረት መንገድ በልጁ የህይወት መስዋእትነት ያበጀበትን ዕለት ለመዘከር የሚከበር ትልቅ መንፈሳዊ በዓል ነው።

በዓሉ የእግዚአብሄር ፍጹም ምህረት የሚታወስበት፤ ከሁሉም በላይ ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ የሆነው ልጁ የክርስቶስ እየሱስ ለሰው ልጆች የሐጢያት ስርእየት ራሱን የመስዋእት በግ አድርጎ በማቅረብ፤ የአባቱን የማዳን ሃሳብ ተጨባጭ እውነት ያደረገበት መንፈሳዊ እና ታሪካዊ ክስተት ነው።

ከአዳም አለመታዘዝ ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን የሰው ልጅ የፍጥረታዊ ማንነት መዛነፍ፣ሐጢያተኝነት ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ሞት እና የሞት ፍርሀት አሸንፎ በተለወጠ ማንነት ፤ በአዲስ የእምነት ተስፋ እና የህይወት መርህ የሚኖርበትን የቀደመ አምላካዊ መሻት ከተስፋ ወደ ተጨባጭ እውነት የተሻገረበት ነው።

በዓሉ ፍቅር እና ስለ ፍቅር የሚከፈል ዋጋ ትህትና እና ይቅር ባይነት ጨምሮ በአደባባይ በመስቀል ላይ ሞት የታየበት ፤ስለ ብዙዎች ሐጢያት አንዱ ጌታ ፈቅዶ እና ወዶ ሐጢያት የሆነበት፤ የሐጢያትንም ዋጋ ሞት የተቀበለበት፤ በዚህም ብዙዎችን ከሐጢያት የፍርድ እዳ ነጻ የሚወጡበትን አምላካዊ በጎነት የተፈጸመበት ነው።

“የሚሠሩትን አያውቁም እና ይቅር በላቸው” በሚል ከፍ ባለ የይቅርታ ልብ እና መንፈስ የከሳሾቹን እና የገዳዮቹን የከፋ ወንጀል ይቅር በማለት፤ ፍቅር እስከምን ሐጢያትን እና በደልን ይቅር እንደሚል በተግባር በመስቀል የሞት ጣር ውስጥ የታየበት፤ በዚህም የብዙዎች ልብ በፍቅርና ይቅርታ የተማረከበት ዕለት ነው።

እኛም በክርስቶስ በመስቀል ላይ ዋጋ እንደተከፈለለት ክርስቲያን ይህንን እለት ስናከብር፤ የዚህ ልብ እና መንፈስ ተካፋይ በመሆን፤ የጌታችን የመስቀል ላይ ሞት ያጎናጸፈንን፤አዲስ ፍጥረታዊ ማንነት በማሰላሰል፤ ከተከፈለልን ዋጋ አኳያ የት ጋር እንዳለን፤ ለወንድማችን ያለን ፍቅር ምን ድረስ እንደሆነ በማጤን ሊሆን ይገባል።

በዓሉን እንደ በዓል በምግብ እና በመጠጥ፤ በደስታ እና በፌሽታ ከማሳለፍ ባለፈ፤ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ፤ከአሮጌው ማንነታችን ምን ያህል ወጥተን እየተጓዝን ነው፤ በክርስቶስ እየሱስ ባገኘነው አዲስ ፍጥረታዊ ማንነት የቱን ያህል ሕይወታችንን እየመራን ነው የሚሉትን ጥያቄዎች እየጠየቅን መሆን አለበት።

ለወንድማችን እስከሞት የሚያደርስ ፍቅር እንኳን ባይኖረን ፣ የወንድማማችነት ፍቅራችን የት ድረስ ነው፤ የበደሉንን ይቅር ለማለት ያለን የልብ ዝግጁነት የቱን ያህል ነው። በዕለት ተዕለት ህይወታችን ከራሳችን አልፎ ለሌሎች የሚተርፈው የፍቅር፣ የይቅርታ እና የትህትና ሕይወታችን ምን ያህል ነው ብለን ወደራሳችን ልንመለከት ይገባል።

በክርስቶስ እየሱስ የመስቀል ዋጋ ለተከፈለለት የእኛም ሆነ የወንድማችን ሕይወት የቱን ያህል ኃላፊነት ይሰማናል ። “ወንድሙን የሚጠላ ነፍሰ ገዳይ ነው” የሚለውን ሃይማኖታዊ አስተምህሮ በየጊዜው እየሰማን አሁን ላይ ውስጣችን ስለተፈጠረው የወንድም ጥላቻ ያህል ነፍሰ ገዳይነት ይሰማናልን? ለፍርዱስ የቱን ያህል ራሳችንን አዘጋጅተናል።

ከልጅነት እስከ አዋቂነት፤ ከአዋቂነት እስከ እርጅና ዘመን፤ ስለ ሐጢያታችን /አለመታዘዛ ችን፤ በክርስቶስ ስለተከፈለው ዋጋ እየተነገረን፤ ለምን የተነገረንን ያህል ውስጣችን መለወጥ አቃተው፤ በተለወጠ ማንነት ወንድማችንን መውደድ ፣ስለወንድማችን ሕይወት ኃላፊነት መውሰድ አቃተን የሚለውን መርምረን ወደ ትክክለኛው መንገድ መመለስ ይጠበቅብናል ።

በተሰጠን አዲስ /የተለወጠ ፍጥረታዊ ማንነት ከትናንት የተለወጠ ሀገር እና ሕዝብ መሆን ለምን ተሳነን። እንደ አንድ የአባት ልጆች ቁጭ ብለን በመነጋገር ፣በመደማመጥ መስማማት አቅቶን ፣ ለምን ዘመናችንን በግጭት አዙሪት ውስጥ ለማሳለፍ ተገደድን? እነዚህን እና መሰል ጥያቄዎችን አንስተን ለመጠየቅና ወደ ትክክለኛው መንገድ ለመሄድ ከዚህ የተሻለ ጊዜ ሊኖረን አይችልም!

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You