የቀዬው ጉምጉምታ

ፈንጂ ወረዳ፤ መልከ ጽራር ቀበሌ፤ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ከእኩሌታ ሆኗል። የእድሩ ጡሩንባ ነፊው ድጋፌ፤ በግራ እጁ ጡሩንባውን፤ በቀኙ ደግሞ ከጭቃው ጋር ተጣልቶ፤ ከወደ ሶሉ ግንጥል ብሎ የቦካውን የአንድ እግር ጫማውን ይዞ መንደር ለመንደር ይዳክራል። እንደወትሮው ቢሆን ኖሮ ገና አንድ ሰዓት ሳይሞላ አጠናቆ ወይ ከቤቱ አሊያም ከእመት ባዩሽ ቤት ያደረ ጠጁን በማንቃረር ላይ በሆነ ነበር። ነገር ግን፤ ትናንትና ማታ እስከ እኩለ ሌሊት ጢንቢራው እስኪዞር ሲጠጣ አምሽቶ፤ ከሄደበት ዓለም ድንገት ሲባንን፤ ንጋት 12 ሰዓት አልፏል።

ከራስጌው ያገኘውን ደራርቦ ሲሮጥ ከወጣ በኋላ፤ ከአዳፋው ኮቱ ስር የለበሰውን ቲሸርት ቢጤ ቢመለከት የሚስቱ አስናቁ ሆኖ አገኘው። “አሄ! ደግሞ ካንቺም አልፎ ልብስሽም ይጫወትብኝ አስናቁ…” በማለት፤ በአፉ እያጉተመተመ እንዳይታይ የጃኬቱን አዝራራ ቆልፎ መገስገሱን ቀጠለ። ከዚህ ሁሉ በኋላ፤ ይሄው አሁን፤ እንደነጋበት ጅብ ሰፈር ለሰፈር ያለከልካል። ከሁሉም ቦታ ሳያዳርስ ከእርሱ ቀድሞ የስብሰባው ሰዓት ተቃርቧል።

የመጨረሻውን ልፈፋ በመንደር አራት በእነ አበጋዝ ደበበ መኖሪያ ቤት አካባቢ በማድረግ ላይ ነበር። ከመወየቡም፤ በጭቃ ከላይ እስከ ታች የተመረገው ግራጫ ካኪ ሱሪው በከፊል ያገለገለ ምድጃ መስሏል። የቁመቱ መርዘም ጠቀመው እንጂ እንደ አያያዙ ቢሆንማ ፊቱም ከመለወስ የሚተርፍ አይመስልም። ከኮፍያው ስር ላቦቱ ቁልቁል ከግንባሩ ይዥጎደጎዳል። ሰውነቱ ዝሎ ጉልበቱ እየተብረከረከ፤ እንደምንም ብሎ የሞት ሞቱን ጡሩንባዋን፤ ከአፉ ላይ እንደ ጡጦ ገጠማት።…ጡ!…ጥጥ…ትንፋሹ ተቆራርጦ ጡሩንባዋም ለገመችበት። “ኤዲያ! ምኑ ያላዝናል፤ ይሄኔ ትምባሆ ቢሆንማ ትንፋሹን ከእግር ጣቱም ቢሆን ይስበው ነበር። በአፍንጫው የሚነፋ ይመስል…” ሲሉ፤ የአበጋዙ ባለቤት ከወደ ማጀታቸው ሆነው ብስጭት እያሉ ይራገማሉ።

ጥሎባቸው ስብሰባ አይወዱም፤ ባለቤታቸው ደግሞ ከስብሰባ ቦታ ጠፍተው አያውቁም። ድጋፌ ትንፋሹን ሳብ አድርጎ፤ ኃይሉን አሰባስቦ በድጋሚ እድሉን ሞከረ፤ “ጡ…ጥ..ጡኡኡ..ጥ!…” ድምጽዋ ቢዘበራረቅም በቂ ነበረችና ከሆዱ የተጠራቀመውን አየር ወደ ውጭ አራግፎ በድምጹ ቀጠለ። “ለመልከ ጽራር ነዋሪዎች በሙሉ፤ በዞናችን ውስጥ በየሁለት ዓመቱ ለሚካሄደው ለሞዴል ቀበሌ የሽልማት ሥነ ሥርዓት፤ ቀበሌያችንም እጩ ሆና የተመረጠች በመሆኑ ለ..ዚ.. ለዚ…ህ እንኳን ደስ አላችሁ! በማለት፤ በዚህና በሌሎችም ወሳኝ ጉ…ዳዮች ዙሪያ ከማህበረሰቡ ጋር ውይይት ይካሄዳ…ል! በመሆኑም በዛሬው እለት ከጠዋቱ ሶ..ስት ሰዓት ላይ… በቀበሌው የስብሰባ አዳራሽ እንድትገኙ ተብላችኋ…ል!” ኡ..ፍ! አለ፤ ከትከሻው ላይ ኩንታል እንዳወረደ ሰው።

ሕዝቡ ከቀበሌው የስብሰባው አዳራሽ ውስጥ ተጠግጥጓል። ከወዲህና ወዲያ በጫጫታና ሹክሹክታ ተጥለቅልቋል። ነገር እየጎነጎነ በሊቀመንበሩ ላይ በማሴር ላይ ነው። በየወሬ ጀማው ጎን ለጎን፤ ለሁለትም ለሦስትም በመሆን አፍ ለአፍ ገጥመው ለተመለከታቸው፤ የቡድን ሥራ የተሰጠው ተማሪ መስለዋል። እነርሱ ግን በሊቀመንበሩ ላይ ሲዶልቱ ነበር። አብዛኛዎቹ ከእማሆይ ልኬ ዙሪያ ተኮልኩለው ምኑን እንደሆን እየመከሩና፤ እማሆይን በርቱልን…ምንም እንዳይፈሩ በሚመስል ሁኔታ ያበረታቷቸዋል።

እማሆይ ልኬ ካሉ ነገር አዋቂ፤ ለእውነት መለስ ቀለስን የማያውቁ ደፋርና ግልጽ ሴት ናቸው። እድሜያቸው ገፍቶ ሰባዎቹን ቢዘልቀም፤ ወኔና ጉልበታቸው ግን ወጣቱንም የሚያሽቀነጥር ነው። በዘውዳዊው ሥርዓት ውስጥ፤ አባታቸው እጅግ የታወቁ ባላምባራስ ነበሩ። እማሆይም ድሮውንም ቢሆን ጠመንጃ አንግበው እንደ ወንዱ ሁሉ ዘራፍ የሚሉና ጀብዱ የሚወዱ ሴት ነበሩ። በአንድ ወቅት እማሆይ መነኑና፤ ከገዳም ገቡ፤ በማለት ጉድ ተብሎ በዚያው ከተረሱ ከአስር ዓመት በኋላ ለእህታቸው ሞት መጥተው በዚያው ቀሩ። እያደር ሲታዩ አዋቂነትና መልካምነታቸው እየጎላ መጣ። ዛሬም ሕዝቡ ከቦ እንደ ቦክሰኛ የሚያራግብላቸው፤ የዶለቱትን ድግስ በድፍረት ለሊቀመንበሩ እንዲያቀርቡላቸው ነው።

በእዚህ መሃል ሊቀመንበሩ፤ ከእጃቸው የማይለየውን ግዙፍ ሳምሶናይት መሳይ አጀንዳቸውን አንጠልጥለው ወደ አዳራሹ ዘው አሉ። በፍጥነት ወደ መድረኩ እያመሩ በጨረፍታ የተመለከቱት ፊት ግን እጅግ አስፈሪ ነበር። ከመቀመጫ እየተነሱ የሚያንቋቸውም መሰላቸው። በቶሎ ከመንበረ ወንበራቸው ላይ ጉብ በማለት፤ መነጽራቸውን ከዓይናቸው ዝቅ በማድረግ፤ በያዟት መሃረብ ዓይንና ግንባራቸውን ጠረግ ጠረግ አደረጉ። ጉሮሯቸውንም ሳል ሳል በማድረግ ያለወትሮው ስብሰባውን ያለምንም የመድረክ አጋፋሪ ጀመሩት። “የተወደዳችሁ የቀበሌያችን ነዋሪዎች፤ በመጀመሪያ በማርፈዴ ይቅርታ እየጠየቅኩኝ፤ አንድ የምስራች ልንገራችሁ…በየሁለት ዓመቱ በዞን ደረጃ ለሚካሄደው የምርጥ ቀበሌ ምርጥ ተሞክሮ ሽልማት፤ ወረዳችንን በመወከል በእጩነት ከሚቀርቡት ሦስት ቀበሌዎች መሃከል አንዱ ለመሆን በቅተናልና እንኳን ደስ አላችሁ!” በማለት፤ ፈገግ እያሉ ዓይኖቻቸውን ከጥግ እስከ ጥግ አሽከረከሩት።

የጠበቁት ጭብጨባ..ፉጨትና..ጩኸት እጅግ ደብዘዝና ቀዝቀዝ ያለ ሆነ። የሁሉም አንድ ላይ ቢደማመር፤ የድጋፌን ያህል እንኳን አይሆንም። “ምነው መርዝ እንደበላች አይጥ ቅስስ አላችሁሳ… ደስ አላላችሁም ማለት ነው?” አሉ ንድድ ያለውን ውስጣቸውን በቃላት ለማለዘብ እየሞከሩ። “ኧረ በጭራሽ…ነገሩን ቀደም ብሎ፤ ጡሩንባ ነፊው ድጋፌ ስለለፈፈልን፤ የደስታውን ጮቤ እዚያው ከመንደር ስለረገጥን እንጂማ ከዚህ በላይ ሊያስደስተን የሚችል ምን ሊኖር ይችላል…” በማለት፤ አብራር ከመቀመጫው ብድግ ብሎ ምላሽ ሰጣቸው። “ይሄ ቀዳዳ! እንዲያው አፉም እንደ ጡሩንባው፤ ትንፋሽ ባገኘ ቁጥር ሁሉ ጡርር! ማለት ይወዳል።” አሉና ወደ አንዱ አቅጣጫ ቃኘት ሲያደርጉ፤ እማሆይ ከነበሩበት ጫፍ ወሬውና ሹክሹክታው እስካሁንም አልረገበም። ደርሷል ሰዓቱ በሉ ተዘጋጁ እያሏቸው ይመስላል።

ክቡር ሊቀመንበሩ የነገሩ አዝማሚያ ቀድሞውኑ ተረድተውታል፤ ይሄ ሁሉ ሹክ ሹክታ ስለምን እንደሆነ አላጡትም። የቀበሌው ነዋሪ፤ እጅግ ፈታኝና ተፋጦ የሚያፈጣፍጥ ጥያቄ ሲኖረው፤ ከፊት እማሆይን አሰልፎ እንደሚመጣ ያውቁታል። በወሬ ወሬም፤ የታሙበት አጸያፊ ጉዳይ ደርሷቸዋል። ድንገት ወርወር ያደረጉት የሊቀመንበሩ ዓይን፤ ሄዶ ከእማሆይ ዓይን ጋር ተገጫጨ። ተያዩና “እባብ ለእባብ፤ ካብ ለካብ” ተባብለው፤ ሁለቱም ሳይነጋገሩ ተግባቡ። “ክቡር ሊቀመንበራችን ሆይ፤ እኛ በድህነት እሳት መቀመጫችንን እየተቃጠልን፤ በልማትና መዋጮ ሰበብ ከሌለን ፍራንክ ላይ መቀነታችንን አስፈትተው፤ እርሶ ግን ያለምንም ሀፍረት እፊታችን ተቀምጠው ያሞኙናል። የቀበሌውን በጀት ተመሳጥረው በልተው፤ ከአንድ ትልቅ ከተማ ላይ ቪላ ቤት ገንብተዋል አሉ…እንዲያው በወላዲቷ አምላክ ይዤዎታለሁ! ይህን አድርገዋል ወይንስ አላደረጉም?” የሚለው የእማሆይ ድምጽ በአደባባይ ሲያፋጥጣቸው ታያቸውና ነገሩን ቀድመው ለማንሳት አመነቱ።

“ዛሬ ሁሉንም ነገር ገልጬ ከቻልኩ አሳምናቸዋለሁ፤ ካልሆነም ያበጠው ይፈንዳ” በማለት ቀልባቸውን ሰብሰብ አድርገው፤ ለክፉም ለደጉም በቅድሚያ የስብሰባውን አጀንዳ ለመፈጸም ጉዳዩን ወደ መጨረሻ ለመነጋገር ወሰኑ። “የዛሬው ስብሰባችን ያስፈለገውም፤ እስካሁን በነበሩን ነገሮች ታይቶ እጩ ሆንን እንጂ፤ ገና አሸናፊዎች አይደለንም። ስለዚህ ለአሸናፊነቱ በቀሩን ጥቂት ጊዜያት ውስጥ በትጋት የምንከውናቸው ነገሮች በመኖራቸው፤ ምን ምን እንሥራ ለሚሉት ጉዳዮች ተወያይቶ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ነው…” በማለት ውሃቸውን አንስተው ፉት አሉ። “ከሦስት ሳምንት በኋላ፤ ቀበሌያችን አሸናፊ የምትሆንባቸውን፤ የልማትና የማህበረሰብ አቀፍ ሥራዎችን ለመገምገም፤ ለዚሁ ጉዳይ የተዋቀሩ የኮሚቴ አባላት ከዞኑ ይመጣሉ። ስለመሆኑም በጉብኝታዊ ግምገማቸው ወቅት ነጥባችንን ከፍ ሊያደርጉልን የሚችሉ ተጨማሪ ሥራዎች ላይ የምንረባረብ ይሆናል። የሚይዟቸው መስፈርቶች ብዙ ቢሆኑም፤ ጥቂቱን ለማንሳት ያህል… የእያንዳንዱ ነዋሪ የጤና አጠባበቅና ጽዳት፤ የአካባቢ ጥበቃ፤ ሕዝባዊ ልማቶች፤ የአርሶ አደሩ የመሬት አስተራረስና ምርታማነት፤ የአርብቶ አደሩ ስኬታማነትና ልዩ ተሞክሮ፤ በሕፃናት ልጆቻችን” የትምህርት ገበታ…እና የመሳሰሉት ናቸው።” አሉና አጠገባቸው ወደነበረው ምክትል ሊቀመንበር ዞር አሉና በጆሮው ሹክ ሲሉት፤ ወዲያው በፍጥነት ተነስቶ ወጣ።

“ቀበሌያችን ብቻም ሳትሆን፤ በየዘርፉ ስኬት ላይ ለደረሱና የትጋት ተምሳሌት ሆነው ለተገኙም በግለሰብ ደረጃ፤ በሞዴልነት ተመርጠው የሚሸለሙና የሞዴልነትን የክብር ኒሻን የሚያጠልቁ ይሆናል። ስለዚህ ሁላችንም በቤትና ጓዳ፤ በጓሮና ማሳችን ጭምር ምን ሠርተን ምን እንዳለን ማሰብ እንጀምራለን። ለዚህ ደግሞ ከነገ ጠዋት ጀምሮ፤ አካባቢና ጎዳናዎቻችንን በጋራ፤ ቤትና ከአጥር ግቢያችን ደግሞ በግላችን ማጽዳትና ማልማት እንጀምራለን። በመጀመሪያም፤ ሁላችንም በየአጥር ግቢያችን ውስጥ ሽንት ቤቶችን እንቆፍራለን። ቀደም ሲል ያለን ሰዎች ደግሞ ከቻልን በቆርቆሮ ካጣንም በሸራ አሳምረን ውብና ጽዱ እናደርገዋለን። በዚህ የጽዳት ዘርፍ ማሸነፍ ከቻልን፤ የተነቃቃይ ሽንት ቤቶችን በምንፈልገው ልክ የሚሰጡን ይሆናል” በማለት ጥቂት ትንፋሽ ሳብ ከማድረጋቸው፤ የጅብ ችኩሉ፤ ቸኮል ለጥያቄ እጁን ወደላይ እንደቀሰተ፤ ፈቃዳቸውንም ሳይጠብቅ ብድግ ብሎ ተነሳ።

“በእውነቱ እጅግ ድንቅና የተቀደሰ ሃሳብ ነው፤ የሠራነውን መጥታችሁ ስሙ ከማለት እንዲህ ምን እንሥራና እንዲህ እንሥራ ስትሉን ደስ ይለናል። ጥያቄዬ ግን፤ ምግቡን በልቶ የጠገበውን ሰው እና ልጋብዝህ ማለት ምን የሚሉት ምጸት ነው…ይሄ ተገጣጣሚ ነው ግጥምጣሚ የምትሉት ሽንት ቤት የሚያስፈልገው እኮ፤ ሽንት ቤት ለሌለው እንጂ፤ ሽንት ቤት ስላለህ ተብሎ ሌላ ሽንት ቤት መመረቅ ምን ይፈይድልናል? በቀን አንዴ እየበላን ሁለት ሽንት ቤት መጠቀም፤ በምድሩ ቀርቶ በሰማዩስ አያስጠይቀንም…” የሚያውቀውን ሁሉ ፈጥኖ በማራገፍ አዋቂ የመሆን አባዜ የተጸናወተው ድጋፌ፤ የቸኮልን ንግግሩን አቋርጦ፤ ሰያፍ ገባለት። “አልሰሜን ባይ ግባ በለው!…ማነህ ቸኮል…ተነቃቃይ ሽንት ቤት ሲባል፤ የሚሰጡን ከነጉድጓዱ አይደለም። በደህና ላሜራ ተበጅቶ እንደ ቤት የሚያገለግል ነው። እዚያ ባለፈው ከሐረር ከተማ ውስጥ እንደተመለከትነው፤ የፈድሉ ኪዮስክ ሱቅ ማለት ነው። ምነው ደግሞ የኋላ ቀስ ብለህ ብትጠይቅና፤ በየዛፉ ስር እየተጸዳዱ ቅጠል ከመበጠስ፤ ቅድሚያ የተባልከውን ጉድጓድ ብትቆፍር…” አለ። “በህግ አምላክ! ይህን ሰው አስቀምጡልኝ…” ቸኮል፤ ንድድ ብሎት አካኪ ዘራፍ ማለት ጀመረ።

ሊቀመንበሩ፤ ቀድሞም እንደ እንቧይ ሊፈርጡ የደረሱትን ጎላ ጎላ ያሉ አይኖቻቸውን፤ ተራ በተራ ከሁለቱም ላይ እያጉረጠረጡ፤ “አወቅሽ አወቅሽ ሲሏት…በሉ! ሥርዓታችሁን ይዛችሁ በክብር ተቀመጡ፤ እዚህ የተሰበሰብነው የናንተን የሀረቄ ቤት እንቶፈንቶና ጭቅጭቅ ለመስማት አይደለም። የጀመራችሁትን ኋላ እዛው ትጨርሱታላችሁ። በመጀመሪያ ግብረ ገብነት ይኑራችሁ፤ ጠያቂም ሆነ መላሽ ለመሆን ፈቃድ አልጠየቃችሁም። አንተ ድጋፌ!፤ ወይ ስልጣኔንም ተረከብና አንደኛህን ከዚሁ ወንበር ላይ ተቀመጥ። እንዲያው ሥጋዬ ሆንክና ልቆርጥህ ተሳነኝ። ወንድሜ፤ ምን ዓይነቱን ቅዠት ተመልክቶ ድጋፌ ሲል ስም አወጣልህ እንጂ፤ ድጋፍስ የሚያስፈልገው ላንተው ነበር…” አዳራሹ ሙሉ በሳቅ አውካካ…ሊቀመንበሩ ግን ትክዝ ብለው የተናገሩት ከልባቸው የልባቸውን ነበር ። “ቸኮል፤ ሥርዓት አልባ ችኮላህ እንጂ ጥያቄህስ ልክ ነበር። የሚሰጡን ቤቱን ከነክዳኑ ነው። አንተ ብቻ ለመቆፈር ተዘጋጅ እንጂ፤ ካሳሰበህ ኋላ ላይ ችግኝም ቢሆን ትተክልበታለህ፤ መቼም ከዚያ በላይ አትቆፍር…” በማለት፤ ከተሰብሳቢው ሃሳብና አስተያየት ተቀብለውና የቀጣዩን የቤት ሥራ አቅጣጫ አስቀምጠው እማሆይን ተመለከቱ።

“እማሆይ” አሉ ሊቀመንበሩ። “አቤት!” በማለት ብድግ አሉ። “ቅድም ሊጠይቁኝ የፈለጉት ነገር ምን ነበር?” እማሆይ ልኬ፤ መች በዚህ ይደነብሩና ጉሮሯቸውን ጠረግ ጠረግ አድርገው፤ ገና “እህ…” ከማለታቸው፤ ይተውትና ቁጭ ይበሉ፤ ነገሩን አውቀዋለሁ” አሉ ሊቀመንበሩ። “ይኼ ጉደኛ ጭራሽ ውስጣችንንም ያሰልለው ኖሯል…” በማለት፤ እማሆይ በውስጣቸው ግርምትም ግራ መጋባትም እየተለኮሰ ቁጭ አሉ። “እኔን ታውቁኛላችሁ፤ ለምን እንዲህ አሰባችሁብኝ ብዬም አልወቅሳችሁም። ነገር ግን ባልዋልኩበት አውሎ ስምና ክብሬን ያጎደፈው፤ እፊታችሁ የቆመው ይህ ሆድ አደር ነውና እሱ ግን ቅጣቱን ይቀበላል!” ይበልጥ ግራ መጋባት ሆነ። ግማሹ በሀፍረት፤ ገሚሱ ጭንቅላቱን በመወዝወዝ፤ አንዳንዱም “ሞኝህን ፈልግ” በሚል፤ የአዳራሹ ድባብ፤ መውጫና መግቢያው የተከረቸመ ዋሻ መሰለ። የቀዬው ጉምጉምታ አሁን ከራስ ጋር ሆነ።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You