የኢንዱስትሪዎችን ተረፈ ምርት መቀነስና ተወዳዳሪ ማድረግ የሚያስችለው ፕሮጀክት

ኢንዱስትሪዎች ለሰው ልጅ እጅግ አስፈላጊ ምርቶችን በማምረት ይታወቃሉ። አልባሳትን፣ የሕክምና መሳሪያዎችንና መድኃኒቶችን፤ የግንባታና የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን፤ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን፣ ወዘተ በማምረት ዓለማችን አሁን ለደረሰችበት ከፍተኛ ደረጃ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፤ እያበረከቱም ይገኛሉ።

እነዚህ ኢንዱስትሪዎች በአንጻሩ የሰው ልጅን በእጅጉ ሊጎዱ የሚችሉ ተረፈ ምርቶችን ወደ አካባቢ በመልቀቅም ይወቀሳሉ። በአየር ንብረት ላይ ለተከሰተው ብክለት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ። ለዚህ ደግሞ በማምረት ሂደት የሚከተሉት መንገድ እንደሆነ ይገለጻል።

አካባቢን በማይጎዳ መልኩ ማምረት ቢችሉ እንደ ተወደዱ ይዘልቃሉ። ይሁንና በአብዛኛው ይህን እያደረጉ አለመሆናቸው ነው የሚገለጸው። ለእዚህም ነው አመራረታቸው አካባቢን እንዳይጎዳ ማድረግ የሚያስችሉ አሠራሮች እየተተገበሩ የሚገኙት። በኢትዮጵያም ይህን አሠራር ለመትግበር ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። ኢንዱስትሪዎች የሚጠቀሙበትን ፍሳሽ የሚያጣሩባቸውን ማጣሪያዎች ገንብተዋል።

በተለያዩ የዓለም ሀገራት ኢንዱስትሪዎች ተረፈ ምርቶችን የሚያጣሩባቸው መንገዶች እየተቀየሩ ይገኛሉ። ኢንዱስትሪዎቹ እስከ አሁን ‹‹የሊኒዬር ኢኮኖሚ ሞዴል›› በመጠቀም ነበር ተረፈ ምርቶችን ሲያስወግዱ የኖሩት። ይህ ሥርዓት ወደ ‹‹ሰርኩላር ኢኮኖሚ ሞዴል›› እየተሸጋገረ ይገኛል። በርካታ ሀገሮችም ይህን አሠራር ተግባራዊ ለማድረግ በማስተዋወቅ ላይ ይገኛሉ።

‹‹ሰርኩላር ኢኮኖሚ ሞዴል›› የሚመራባቸው አልያም የሚያተኩርባቸው ሃሳቦች ተረፈ ምርቶችን እንደገና መጠቀም ወይም የምርት ሕይወት ዑደትን ማራዘም የሚሉት ናቸው። ይህ ሃሳብ ተረፈ ምርቶችን መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችሉ መንገዶችን መፍጠር፣ የተረፈ ምርት ውጋጅን መቀነስ የሚያስችሉ ዲዛይኖችን መፍጠር እና ሥራ ላይ ማዋል እና በአመራረት ሂደት ውስጥ የሚኖረውን ተረፈ ምርት ጨርሶ ማስወገድን ይመለከታል።

በሀገራችን ኢትዮጵያ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪው ለውጭ ገበያ ከሚቀርቡ ምርቶች እና ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሬን ከሚያስገኙ ዘርፎች ውስጥ አንዱ ነው። ዘርፉ በሚያመርትበት ወቅት በአካባቢ በአጠቃላይ በአየር ንብረት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ሲሰራ ቆይቷል። አሁን ደግሞ ዓለም የደረሰበትን የፋብሪካዎች አመራረት እንዲከተል ለማድረግ እየተሠራ ነው።

ከሰሞኑም በአፍሪካ ውስጥ ኢትዮጵያን ጨምሮ አራት ሀገራት ላይ በሙከራ ደረጃ የሚሠራውን የሰርኩላር ኢኮኖሚ በጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ዘርፍ ላይ የማስተዋወቅና የመተግበር ሥራን መሠረት ያደረገ ፕሮጀክት ይፋ ተደርጓል።

ፕሮጀክቱን ይፋ ያደረገው የኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ነው። የሚመራው በዚሁ ተቋም ሲሆን በአፍሪካ የሰርኩላር ሞዴል ኢኮኖሚ ኢኒሼቲቭ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና አስተባባሪ፣ የተባበሩት መንግሥታት ኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (UNIDO)፣ የጨርቃጨርቅ እና አልባሳት ኢንዱስትሪ የጥናትና ምርምር ልማት ማዕከል በጋራ ሆነው ይሰሩታል። ፕሮጀክቱ ‹‹የሰርኩላር ኢኮኖሚን በጨርቃጨርቅ እና አልባሳት ዘርፍ በማስተዋወቅ ቀጣይነት ያለው የኬሚካል እና ተረፈ ምርት ቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት›› ልንለው እንችላለን።

ፕሮጀክቱ ይፋ በተደረገበት እለት የተገኙት የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሚልኬሳ ጃጋማ የጨርቃጨርቅ ዘርፍ የሚመረትበት መንገድ በተያያዘ የአየር ንብረት እና አካባቢን በይበልጥ ይበክላል የሚባልለት ዘርፍ ነው። ኢንስቲትዩቱ በስሩ የጨርቃጨርቅ እና አልባሳት ኢንዱስትሪ የጥናትና ምርምር ልማት ማዕከል ያለው ሲሆን ብክለትን ሊቀንሱ የሚችሉ የአሠራር ሥርዓቶች በተለያየ ጊዜ ተግባራዊ ይደረጋሉ። በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ አምራቾችም ሆኑ ፋብሪካዎች ላይ ያላቸው የብክነት እና ብክለት ላይ ያለው የቁጥጥር ሥርዓት እንደሚደረግ ገልጸዋል። አንዱ ኬሜካሎችን ተጠቅመው ምርቶች በሚያመርቱ እና ኬሚካሎችና ፍሳሾችን በሚያስወግዱ የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓቶችን በተቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ይደረጋል። በመሆኑም የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች ፍሳሽ ቆሻሻ ውጋጅን ጨርሶ ማስቀረት (zero liquid discharge waste management ) መንገድን ይከተላሉ። በጨርቃጨርቅ እና አልባሳት ዘርፍ ላይ የሚደረጉ ምርቶች ከአካባቢ ጋር የተስማሙ አካባቢን የማይበክሉ፣ እንዲሁም አምራቾች ተወዳዳሪ ሆነው ምርቶቻቸውን ለገበያ ማቅረብ የሚችሉባቸውን ሁኔታዎች ለመፍጠር፣ በሀገር ውስጥና ውጭ ቀጣይነት ባለው ሁኔታ ለማቅረብ እንዲችሉ አቅም ለመፍጠር የባለሀብቶችን ጥረት ለማገዝ እንዲችል በመንግሥት እና በልማት አጋሮች የተቀረጸ ፕሮጀክት ነው። በዋናነት የሚያተኩረውም የአካባቢ ደህነት ጋር የተያያዘና ወጪ ቆጣቢ የሆነ የአመራረት ሂደትን መከተል ነው።

የሰርኩራል ኢኮኖሚ ጽንሰ ሃሳብ በሁሉም የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ኢንዱስትሪዎች ተግባራዊ ለማድረግ የታለመ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ በሙከራ ደረጃ በ10 ፋብሪካዎች ለአምስት ዓመት ተግባራዊ የሚደረግ ፕሮጀክት ነው። የተለያዩ ሀገሮች ምርቶችን ለመግዛት ሕዝብን በማይበድል፣ አካባቢን በማይበክል መልኩ የተመረቱ መሆናቸውን እንደቅድሚያ መስፈርት አድርገው አስቀምጠውታል። ዘርፉ ኤክስፖርት መር በሆነ የልማት አቅጣጫ ላይ እየተመራ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ በዚህ መንገድ ምርቶች መመረታቸው ሀገራችን የዓለም አንድ አካል እንደመሆኗ በየትኛውም የዓለም ዳርቻ የመሸጥ በስፋት ኤክስፖርት ለማድረግ የምንችልበትን አንድ አቅም ይፈጥርልናል ሲሉ አብራርተዋል።

የተመረጡት ፋብሪካዎች ካላቸው የሥራ ሂደት አንጻር ከአካባቢ ደህንነት ጋር በጣም የተቆራኘ ኬሚካልን በመጠቀም ውጋጆችን በአግባቡ መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል በጥሩ የሥራ ሁኔታ ያላቸው ናቸው ተብለው በምሁራን ጥናት ቴክኒካል መስፈርት የተመረጠ ነው።

የአፍሪካ ሰርኩላር ኢኮኖሚ ኔትወርክ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና አስተባባሪ ቤዛዊት እሸቱ በመድረኩ ላይ የሰርኩላር ኢኮኖሚን ጠቃሚነት ሃሳብ ባነሱበት ንግግራቸው ጊዜው የውድድር ነው ያሉ ገልጸው፣ ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ በጨርቃጨርቅ ዘርፍ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንድትሆን የተሻሻለ ምርት እንዲኖር እና የአየር ንብረት ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ እንዲቀንስ የሚያደርግ ፕሮጀክት መሆኑን አስታውቀዋል።

አስተባባሪዋ እንዳሉት፤ የጨርቃጨርቅ ምርት ዘርፍ በሀገራችን ከፍተኛ የሥራ እድልን ከሚፈጥር እና የውጭ ምንዛሬ በማምጣት ረገድ ለኢትዮጵያ ትልቁን ድርሻ የሚይዝ ዘርፍ ነው። በመሆኑም የዘርፉ ምርቶች የተለያዩ ሂደቶችን ተከትለው ወጪ ወጥቶባቸው፣ ጊዜን እና ጉልበትን ወስደው መመረታቸው ካልቀረ በካይነትን በመቀነሰ መልኩ ቢመረቱ እንደ ሀገር ሲታሰብ ብክለት በመቀነስ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

በጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች ከፍተኛ የውሃ እና የአየር ብክለት የቀነሱ መሆን ከሀገር አልፎ የሀገራችን ምርቶች በዓለም አቀፍ የገበያ ስፍራ ላይ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላል ሲሉ አስተባባሪዋ ጠቁመዋል። ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲያብራሩም ‹‹የዓለም ገበያው በአሁን ወቅት እንኳንስ የአየር ብክለትን በሚያስከትል መልኩ የተመረቱ ምርቶችን ማህበራዊ መብቶችን ‘SOCIAL RIGHTS’ ያላማከሉ ከሆኑ የመገዛት እድላቸው አነስተኛ ነው›› ብለዋል። ይህ የሰርኩላር ኢኮኖሚ በዘርፉ ላይ ተግባራዊ መደረግም እነዚህን ችግሮች ቀርፎ በሚመረተው ምርት አማካኝነት ወደ ዓለም ገበያ ቀርቦ የኢትዮጵያ ምርቶች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እና የሚያመጡትም የውጭ ምንዛሬ ከፍ እንዲል ያደርገዋል›› ሲሉ አብራርተዋል።

አስተባባሪዋ እንዳብራሩት፤ ዓለም አሁን በደረሰችበት ደረጃ በጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪው እጅግ ከፍተኛ ዝና እና ስም ያላቸው ትልልቅ አምራች ኩባንያዎች በሚፈልጉት ስታንዳርድ የሚያመርቷቸውን ምርቶች ፣ ባነሰ የሰው ኃይል አልያም ዋጋ ይህንን የሰርኩላር ኢኮኖሚ ወይንም የአየር ብክለትን በሚቀንስ እና በማያስጠይቅ ሥርዓት ውስጥ ለማምረት የሚችሉባቸውን ሀገራትን በእጀጉ ይፈልጋሉ።

ኢትዮጵያም እነዚህን መስፈርቶች ከሌሎች ሀገራት በተለየ፣ ጊዜውንና ዘመኑን የጠበቁ ጥያቄዎች መልሳ እና አሟልታ ከተገኘች ኢንቨስትመንትን የመሳብ እድሏን ታሰፋለች፤ ተመራጭነቷም እየጨመረ ይሄዳል ሲሉ በፕሮጀክቱ ተግባራዊ የሚደረገውን የሰርኩላር ኢኮኖሚ ጠቀሜታ አስረድተዋል። እነዚህን ሥርዓቶች /systems/ መገንባት የሚያስችል መንገድ ቢፈጠር፣ አልያም ከሌሎች ኢንቨስተሮች ጋር በመሆን መሥራት እና እነዚህን የብክለት መጠንን የሚቀንሱ አማራጮችን በራሱ ገንብቶ መሥራት የሚችል ባለሀብት መበረታታት እና መደገፍ ይገባዋል ሲሉ ገልጸዋል።

ይህ የሰርኩላር ኢኮኖሚ ከአካባቢ የአየር ንብረት ጋር ተስማሚ የሆነ እና የአካባቢ ብክለትን በማያስከትል መልኩ ከማምረት ባሻገር ፋብሪካዎች በሚያመርቷቸው ምርቶች ተጠቅመው የሚያስወግዷቸውን ውጋጆች የመቀነስ መልሶ ጥቅም ላይ የማዋል ሥርዓትና ሁኔታን የሚያበረታታ ነው። ዘርፉ በሀገራችን በአሁኑ ወቅት የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሀገር አምራች ኩባንያዎች በስፋት የሚገቡበት እና የሚሳተፉበት በመሆኑ እንደ ሀገር በኢንዱስትሪ ፓርክ ደረጃ ኢንዱስትሪው የሚስፋፋበትን የልማት አቅጣጫ ይከተላል። ይህም በተናጠል የፍሳሽ ማጣሪያዎችን ከመገንባት ይልቅ የጋራ የሆነ የፍሳሽ ማጣሪያ መገንባትና ማስተዳደር እንዲችሉ ያደርጋል።

የጨርቃጨርቅ እና አልባሳት ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አበበ ተካ የዚህ የሰርኩላር ኢኮኖሚ በጨርቃጨርቅ እና አልባሳት ዘርፍ በሀገር አቀፍ ደረጃ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ናቸው። ከዚህ ቀደም ስንከተል በነበረው መንገድ የሊኒዬር ኢኮኖሚ (take-make-waste economy) ማለትም አንድን የተፈጥሮ ሀብት ተጠቅመን ምርትን ማምረት እና የመጠቀሚያ ጊዜው ሲያበቃ ወደ አካባቢ መልቀቅ ወይም መጣል ነበር ይላሉ።

እሳቸው እንዳሉት፤ የሰርኩላር ኢኮኖሚ ጽንሰ ሃሳብ እና አካሄድ ይህ አሠራር መቀየር አለበት የሚል ነው። ጥቅም ላይ የማይውሉ ተረፈ ምርቶችን መልሶ መጠቀም የሚያስችሉ ሁኔታዎችን የፈጠራ ሃሳቦችን ማፍለቅ፣ ለሌላ አገልግሎት ማዋል እና ወደ አካባቢ መጣል የመጨረሻው አማራጭ ማድረግ እና የሚጣለውን ውጋጅ መጠን በእጅጉ መቀነስ ዋናው የሰርኩላር ኢኮኖሚ ሃሳብ ነው።

ሌላኛው ይህን ሃሳብ ተግባራዊ ለማድረግም ሆነ ለማሳካት በአመራረት ሂደት ላይ የሚፈጠረውን የሚወገድ ነገር መቀነስ ነው ሲሉም ይጠቁማሉ። በአንድ የአመራረት ሂደት ውስጥ የሚያልፍን ውጋጅ አካባቢው እና ተፈጥሮ ላይ ጉዳት እንዳይኖረው አድርጎ አክሞ መልቀቅ በራሱ ወጪ የሚጠይቅ ነው ያሉት አስተባባሪው፣ በምርት ሂደት ላይ የውሃ እና የኬሚካል አጠቃቀምን መቀነስ፣ የግብዓት አጠቃቀምን ማስተካከል ይገባል ብለዋል።

ሰርኩላር ኢኮኖሚ በነዚህ ጽንሰ ሃሳቦች ላይ ያተኩራል፤ ውጋጅ እና ተረፈ ምርትን ከሥርዓት ላይ ማውጣት ወይም መቀነስን ይጠይቃል። ተቋሙ አድርጎታል በተባለው ጥናት ከጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች 94ሺህ ቶን ተረፈ ምርት ይወጣል። ሌሎች ሀገራት በተለየ መልኩ የፈጠራ አቅምን ተጠቅመው ከዚህ ተረፈ ምርት ሌሎች ምርቶችን ያመርታሉ፤ በሀገራችን ተረፈ ምርቶችን መልሶ የመጠቀም ሁኔታ እምብዛም የተለመደ አይደለም። በሀገራችን በዚህ ዘርፍ የሚገኙ ፋብሪካዎችም ተረፈ ምርትን መቀነስ ላይ ሊያተኩሩ ይገባል። ተረፈ ምርትን በቀነሱ ቁጥር ጥራትን ማሻሻል፣ ተወዳዳሪነታቸውንም እየጨመሩ ይሄዳሉ።

ይህ ፕሮጀክት በሚተገበርባቸው ፋብሪካዎች ችግሩን የሚያሻሽሉ ሥርዓቶችን መዘርጋት እና ማስተካከል ያስፈልጋል። ይህም በአመራረት ሂደት ላይ የሚመጣውን ተረፈ ምርት መቀነስ እና የሚወጣውን ተረፈ ምርት ደግሞ ለተሻሻለ አገልግሎት መጠቀም የሚያስችል ሥርዓት፣ ልምድ፣ እውቀት መገንባት እና ማስለመድ ያስፈልጋል። በምርት ሂደት ውስጥ በካይና አደገኛ ኬሚካልን ማውጣት ከተቻለ በቀላሉ መልሶ ለመጠቀም ይቻላል።

ፕሮጀክቱ ተግባራዊ የሚደረገው በአምስት ዋና ዋና ኮምፖነንቶች ተከፋፍሎ ነው። የመጀመሪያው የሕግ ሥርዓት ማውጣት፣ ድጋሚ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ፣ የእውቀት ሥራ አመራር ሥርዓት መገንባት ነው።

በጨርቃጨርቅ ዘርፍ ውስጥ የሚወገደውን ተረፈ ምርት መልሶ መላልሶ በማጣራት ለብዙ አገልግሎት መዋል እንደሚቻል የገለጹት አቶ አበበ፣ አሁን ከሚሰጡት አገልግሎት የተሻለ አገልግሎት መስጠት የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር ይቻላል ብለዋል። ፋብሪካዎች ይህንን በማድረግ ይበልጥ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉበትን መንገድ መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል፤ ለእዚህም ተረፈ ምርቶችን መለየት የሚችል ቡድን መቋቋም እንደሚገባም ጠቁመዋል። የተለዩ ምርቶችን መልሶ በመጠቀም ሂደት የተለያዩ ሥራዎችን መሥራት ለሚችል አካልም ሆነ የሥራ ፈጣሪ ማሰራጨት እንደሚቻልም ጠቁመዋል ።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You