የጀልባ መገልበጥ ደርሶ ባህር ውስጥ ይሄን ያህል ሰዎች ሰመጡ፣ በበረሃ ሲጓዙ ይሄን ያህል ሰዎች ተጎዱ፣ ከፎቅ ተወርውረው ሞቱ፣ የአካል ጉዳተኛ ሆኑ፣ ተደፈሩ፣ የሥነልቦና ጥቃት ደረሰባቸው፣ ሰብአዊ መብታቸው ተጣሱ የሚሉ ወሬዎችን መስማት ከጀመርን ዓመታት ተቆጥረዋል።
ይባስ ብሎ ደግሞ በኑሮ ለመለወጥ ነገን ተስፋ አድርገው፣ በደላላ ተዋክበው፣ ነፍሳቸውን አስይዘው፣ ጥሪታቸውን አሟጠው፣ ያሰቡት ቦታ ደርሰው እቅዳቸውን ለማሳካት ደፋ ቀና እያሉ በሀገሬው የፀጥታ ኃይል ታፍሰው እስር ቤት የሚታጎሩትም ብዙ ናቸው።
ለቤተሰቤ መከታ እሆናለሁ፤እኔም ያልፍልኛል ብለው ከሀገር የወጡ ወጣቶች ያሰቡት እንዳይሆን ሆኑ ለበርካታ ውጣ ውረዶች ይዳረጋሉ።በዚህ ሁኔታ ውስጥ ከመኖር ብዙዎች ወደ ሀገር ቤት መመለስን ቢፈልጉም ወላጆች ያላቸውን ጥሪት አሟጠው የሰጧቸውን ገንዘብ፣ ከፊሎቹም ዘመድ ወዳጅ አስቸግረው ተበድረው የወሰዱትን ገንዘብ ሳይመልሱ፣ እራሳቸውን ለውጠው የቤተሰባቸውንም ኑሮ ለማሻሻል አቅደው ከትምህርት ገበታቸውም ተስተጓጉለው፤ ቤተሰብም ተስፋ አድርጎባቸው፣ ጎረቤቱም መርቆ ሸኝቷቸው እቅዳቸውን ከዳር ሳያደርሱ ባዶ እጃቸውን መመለሳቸው ውስጣቸውን ያርደዋል።
እስር ቤት ገብተው አስታዋሽ አጥተው ለዓመታት በእስር ቤት ውስጥ የሚቆዩ፣ ለጤና ችግር ተዳርገው የሚሰቃዩ እና አለፍ ሲልም እስር ቤት እያሉ ለሞት የሚዳረጉ ጥቂት አለመሆናቸው በተለያየ ጊዜ የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።ይህንኑ የተረዳው የኢትዮጵያ መንግሥትም ለእነዚህ ወገኖች አለኝታ በመሆን ላይ ይገኛል።
ትናንት አስታዋሽ ያልነበራቸው ዜጎች ዛሬ መንግሥት ባደረጋቸው ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ከእስር ቤት ወጥተው የሀገራቸውን መሬት ለመሳም በቅተዋል። በህይወት ተርፈው ለሀገራቸው መሬት የበቁትም ዝቅም ብለው አፈሯን ሲሰሙ ተመልክተናል።
ከተመላሾች ውስጥም ከሳውድአረቢያ የሚመለሱት ከፍተኛውን ቁጥር የያዙ ቢሆኑም ከኦማን፣ ከየመን፣ በሱዳን በተፈጠረው የእርስ በርስ ግጭት ምክንያት ለረጅም ዓመታት በሱዳን ኑሮአቸውን አድርገው የነበሩ ኢትዮጵያን ሁሉ ሳይቀር ወደ ሀገራቸው በመመለስ ላይ ይገኛሉ።
ስደትን ምርጫው አድርገው ባልተገባ መንገድ ወይንም በሕገወጥ ለመሄድ የሚነሳሱት ዜጎች ለጉዞ በርካታ ገንዘብ ያወጣሉ። በትንሹ እስከ 100ሺ ብር እንደሚያወጡ ተጓዦቹ ይናገራሉ። ታዲያ በዚህ ገንዘብ እንደአቅማቸው ሀገራቸው ላይ መስራት አልፈለጉም የሚል ጥያቄ ያስነሳል።ተጓዦቹ እንደሚናገሩት፤ ለሕገወጥ ስደት የሚዳረጉት ከእነሱ ፍላጎት በላይ ወላጆችም ጭምር ስለሚፈልጉት ነው።
እንደውም በአንዳንድ አካባቢዎች ወላጆች የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ሳይቀሩ ልጆቻቸውን ለሕገወጥ ስደት መርቀው የሚሸኙበት ሁኔታ መኖሩንና ይህም ሁኔታ ሕገ ወጥነትን ትክክል አድርጎ የመቀበልና ተጓዦችንም የሚያበረታታ ሆኖ የመገኘቱ ሁኔታ መንግሥትም ደርሶበታል። ይህም ልጆቻቸውን አሳልፈው ለችግር ለመስጠት ግድ የማይሰጣቸው የማህበረሰብ ክፍሎችን ማፍራት ደረጃ ላይ መደረሱ ነገሩን ከባድ ያደርገዋል።
ከድህነት እና ከቤተሰብ ግፊት ባሻገር በተፈጥሮ አደጋ እንደ ጎርፍ፣ ድርቅ እንዲሁም በተለያየ መንገድ በሚፈጠር ግጭት ሰዎች ቀዬያቸውን ለቀው ወደሌላ አካባቢ ለመሄድ ይገደዳሉ። ሀገር አቋርጠው ለመሄድም ገፊ ምክንያት ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያሉ አስገዳጅ ሁኔታዎች
መኖራቸው ቢታወቅም፤ የብዙዎቹ በተለይም ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሀገር የሚሄዱት ዜጎች ኑሮን ከመቀየር ጋር የተያያዘ ነው።
የተሰደደ ሁሉ ያልፍለታል በሚል እሳቤ አብዛኛው ወጣት ትምህርቱን አቋርጦ መሰደድን ህልሙ ያደርጋል።ገና ሁለተኛ ደረጃ ሳይደርስ የሚያልመው ሀገር ለቆ መሰሰድን ነው። ምኞቱን ተስፋውን ይዞ ያለምንም በቂ ዝግጅት ድንበር አቋርጦ፤ኬላ አሰባብሮ መጓዝ እና በረሃን ሰንቆ ካሰቡበት መድረስ ብዙ ወጣቶች የእለት ተዕለት ህልም ነው።
ስለሚሄዱበት ሀገር ባህልና ቋንቋ፣ ስለሚሰሩትና ለሥራው ብቁ ስለመሆናቸው፣ በቂ የሆነ መረጃ ለመያዝ ወደ አእምሮአቸውም አያስገቡም። እንደምንም ገንዘብ አፈላልገው ለመሄድ ነው ፍላጎታቸው። በተለይም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ አንዲት ሴት ልጅ ስምንተኛ ክፍል ከደረሰች በኋላ ከዚያ በኋላ ትምህርት ለመቀጠል ፍላጎት የላትም ፤ህልሟ ሁሉ አረብ ሀገር መሄድ ነው።
ደላላውም እንዲህ ያለውን ሥነልቦና ነው የሚጠቀመው። ከሰማይ ገንዘብ የሚወርድላቸው እስኪመስላቸው ድረስ ልባቸው በፍላጎት እንዲነሳሳ እንጂ ያለውን ውጣ ውረድ አይነግራቸውም። በተለይ ከገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል የሚሰደዱት የከተማን ህይወት በአግባቡ ሳይረዱ ዘመናዊ ወደ ሆነ ከተማ ለመጓዝ ሲነሳሱ ከማያውቁት ዓለም ጋር መጋጨታቸው አይቀሬ ነው።
አሁን ላይ የጉዞ ሰነድ ሁሉም በአካባቢው ላይ የሚያገኝበት ሁኔታ ምቹ ከመሆኑ በፊት የጉዞ ሰነድ ለመውሰድ አዲስ አበባ ከተማ መጥተው በአታላዮች ገንዘባቸው የሚወሰድባቸው፤የሚደፈሩና የሚንገላቱ ብዙዎች ነበሩ። ስለዚህም ስቃዩ የሚጀምረው ገና ከሀገር ሳይወጡ ነው ማለት ነው።
በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ አልፈው ሄደው ግን ደግሞ ተይዘው ወደሀገራቸው የተመለሱ ዜጎች የማይድን ጠባሳ ይዘው ይቀራሉ። ከነዚህ የስደት ተመላሾች መካከል ለሳምባ፣ ለቆዳና ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች የተጋለጡ፣ የት እንዳሉና ስለቤተሰባቸው ማወቅ የተሳናቸው የአእምሮ ህመም የገጠማቸው፣ በምን ሁኔታ እንኳን በቀዶ ጥገና ከሰውነታቸው ክፍል አካላቸው እንደተወሰደባቸው በትክክል የማያውቁ፣ የተለያየ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ይገኙባቸዋል።
ምንም አይነት የጉዞ ሰነድ የሌላቸው መኖራቸው ደግሞ በማስመለሱ ሂደት ላይ የሚፈጥረው ጫና ችግሩ ውስብስብ መሆኑን ነው ከመንግሥት መረጃ የሚሰማው። ከስደት ተመላሾቹ ሀገራቸው ሲገቡ መሬት ተደፍተው ሲስሙ የነበሩበት አስቸጋሪ ሁኔታ ምን ያህል ከባድ እንደነበር መረዳት አያዳግትም።
ይሄን ሁሉ ልብ ያለው ልብ ሳይል ስደትን ማሳደዱ ለምን የሚል ጥያቄ በብዙዎች መፈጠሩ አይቀርም። በተለይም ሕገወጥነት ከዓላማ እንደሚያሰናክል እየታየ ካለው ጉዳት በላይ ምን ማስረጃ ማምጣት ይቻላል።
በሕገወጥ ጉዞ ምክንያት እየተፈጠረ ያለው ጉዳት የዜጎችን ሰብአዊ መብት ከመጣስ በተጨማሪ የሀገር ገጽታንም ያጠለሻል። ከስደት ለሚመለሱ ዜጎች የትራንስፖርት አገልግሎት ከመስጠት ጀምሮ በመጠለያ አቆይቶና የተለያዩ ድጋፎችን አድርጎ ወደቤተሰብ መቀላቀልና የሥራ ዕድለም ምቹ ማድረግ ተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጫና የሚያሳድር መሆኑም ልብ ሊባል ይገባል።
እንዲህ ያለውን ተደራራቢ ጫና ለማስቀረትም ሆነ ሕጋዊ ያልሆነ ፍልሰትን ለመከላከል ለመንግሥት ብቻ የሚተው እንዳልሆነም ከችግሩ ስፋት መገንዘብ ይቻላል። በሕገወጥ ስደት ውስጥ ያሉት ተዋናዮች ከሀገርም ያለፈ በመሆኑ ሀገራት በጋራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ከጦር መሳሪያና ከአደንዛዥ እጽ ዝውውር ቀጥሎ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር አደገኛ በሚባለው ውስጥ የሚፈረጅ በመሆኑ ትብብሩ ሊጠናከር ይገባል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም