የሆሣዕና ምስጋና

ሆሣዕና በየዓመቱ የትንሳዔ በዓል ሊደርስ አንድ ሣምንት ሲቀረው ባለው እሁድ የሚከበር በዓል ነው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ያሉ አብያ ክርስቲያናት የሆሣዕናን ዋዜማ ሌሊቱን በፀሎትና በማኅሌት (በምስጋና) ያሳልፉታል፡፡ ሲነጋ ደግሞ የኪዳን ፀሎትና ቅዳሴ ይደረጋል፡፡

ከቅዳሴ በኋላ ቀሳውስቱ እና ዲያቆናቱ የመጾር መስቀል (ትልቅ መስቀል) ይዘው በማዕጠንት እያጠኑ የሰንበት ትምህርት ቤት ህፃናት መዘምራን በከበሮ ታጅበው እየዘመሩ ቤተክርስቲያኑን ይዞራሉ፤ ይዘምራሉ፡፡ ምዕመናቱም ዘንባባ ይዘው እያወዛወዙ ሆሣዕናን ያከብራሉ፡፡

በዐቢይ ፆም ስምንት እሁድ ያሉ ሲሆን፤ ለእያንዳንዱ ሣምንት ስያሜ ያወጣው ቅዱስ ያሬድ ማህሌታይ መሆኑን የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡ በዚህም መሠረት ሳምንታቱ ዘወረደ፣ ቅድስት፣ ምኩራብ፣ መፃጉዕ፣ ደብረዘይት፣ ገብርኄር፣ ኒቆዲሞስ እና በሰሙነ ሕማማት ዋዜማ የሚከበረው ሆሣዕና በሚል ስያሜ ቅዱስ ያሬድ የሰየማቸው ሳምንታት ናቸው፡፡

የማቴዎስ ወንጌል አንድምታ ሆሣዕና ማለት መድኃኒት አሁን አድን ማለት ነው ይለዋል፡፡ ኢየሱስ የሚለውም ቃል ፍቺው መድኃኒት ማለት ነው፡፡ የደስታ ተክለወልድ ዐዲስ የማርኛ መዝገበ ቃላት ሆሣዕና የሚለውን ቃል ሲፈታው ከትንሳዔ በፊት ባለው እሁድ የሚከበር በዓል፤ ጌታችን ባህያ ተቀምጦ ሰሌንና የወይራ ቅጠል ይዘው ሆሣዕና እያሉ ስለተቀበሉት ቀኑ ሆሣዕና ተባለ፤ አሁን አድን ማለት ነው ይለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላትም ሆሣዕና፤ አሁን አድን ማለት ነው፡፡ የእስራኤል ሕዝብ የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው ‹‹ሆሣዕና›› መዝ. 118፥25፡26 በማለት እየጮሁ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ አጀቡት፡፡ ማቴ. 21፥9-15፣ ማር.11፥9 ፣ዮሐ.12፥13 በማለት ያስረዳል፡፡

ቃሉን አይሁድና ክርስቲያኖች ለአምልኮ ቃልነት (liturgical) እንደሚጠቀሙበት ከድረ ገፅ የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ሆሣዕና የአምልኮ ቃል መሆኑንና ስርወ ቃሉ ዕብራይስጥ ሲሆን በሮማይስጥና (ላቲን)፣ በግሪክ መጽሐፍ ቅዱስ ቃሉን እንዳለ እንደሚጠቀሙበት ያስረዳል፡፡ በግዕዝም፣ በእንግሊዝኛም በሌሎች ቋንቋዎችም ቃሉ ከዕብራይስጥ (አይሁድ) ወደ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳለ የተወሰደ ነው፡፡

ሆሣዕና የዘንባባ በዓልም ተብሎ ይጠራል። ዘንባባ የድልና የሰላም ምልክት ነው፡፡ ይህም ጌታችን ኢየሱስ ለሰላም መምጣቱን ሲያመላክት ነው፡፡ አንድም ዘንባባ ጫፉ እሾኻም ነው፡፡ ኃያል ነህ አሸናፊ ነህ ሲሉት ነው። እስራኤል ደስ ሲላቸው ዘንባባ ይዞ የመዘመር ባህል ነበራቸው፡፡

እስራኤል ከግብፅ ባርነት በወጡ ጊዜ፤ ዮዲት የእስራኤልን ጠላት ሆሎፎርኒስን በገደለች ጊዜ ዘንባባ ይዘው ማመስገናቸውን ወንጌል አንድምታ ያስረዳል። ሆሣዕናም በእየሩሳሌም ዘንባባ ይዘው አዕሩግና ሕፃናት ያመሰገኑት የቀድሞውን ትውፊት ተከትለው ነው፡፡

ነገሥታት የሚሄዱት በፈረስ በበቅሎ ነው። አንድም ፈረስና በቅሎ ለጦርነት የሚጠቀሙበት ከቻሉ ጠላቶቻቸውን የሚያጠቁበት፣ የሚጠቁም ከሆነው በፈረስና በበቅሎ በፍጥነት ሊያመልጡበት ስለሚያስችል ነው፡፡ እየሱስ በተናቀችው አህያ ውርንጫላ ላይ ተቀምጦ ወደ እየሩሳሌም የገባው ለሰላምና ለትህትና መሆኑን ለማስገንዘብ እንደሆነ ሊቃውንቱ ያስረዳሉ፡፡

ህፃናት ጌታችን እየሱስ በአህያ እና በአህያይቱ ውርንጭላ ተቀምጦ ወደ እየሩሳሌም ሲገባ የሠላም ጌታ መጣ ብለው የወይራ ቅንጣፊ፣ የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው እያጀቡት አመስግነውታል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተጠቀሰው እየሱስ ሁለት ደቀመዛሙርቱን አህያ ከውርንጫዋ ጋር ከቤተ ፋጌ የድሆች መንደር ታስራ ታገኛላችሁ ፈታችሁ አምጡልኝ አለ፡፡

ማንም አንዳች ቢላችሁ፤ ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ፤ ወዲያውም ይሰዳቸዋል፡፡ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 21 እንደተጠቀሰው ፤ ለጽዮን ልጅ ፡-

እነሆ ንጉስሽ በአህያ ላይና በአህያይቱ ውርንጫላ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል ተብሎ በነቢይ የተነገረው ይፈፀም ዘንድ ነበር ሲል ይገልጻል፡፡ ይህም ነቢዩ ዘካሪያስ የተነበየው ሲሆን በትንቢተ ዘካርያስ 9፥9 ተጠቅሶ ይገኛል፡፡

በአብያተ ክርስቲያናት በሣሳዕና ህፃናትም ዘንባባ ይዘው አህያ ላይ ስዕለ እየሱስ አድርገው ከበሮ እየመቱ ቤተክርስቲያኑን እየዞሮ ይዘምራሉ። ከመዝሙራቱ መካከል

ሆሣዕና ሆሣዕና በአርያም

ብሩክ ሆሣዕና አምላከ እስራኤል

ተቀምጦ መጣ በአህያ ግልገል፡፡

በጣም ደስ ይበልሽ እልል በይ ጽዮን

ንጉሥሽ መጣልሽ ሊሆንሽ መድኅን …

መጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደተጠቀሰው፤ ለጌታችን ኢየሱስ አህያይቱንና ውርንጫዋንም አመጡለት፡፡ ልብሳቸውን በእነርሱ ላይ ጫኑ፤ተቀመጠባቸውም። ሕዝቡም በመንገድ ላይ ልብሳቸውን ጭምር አነጠፉ፡፡ በተጨማሪም ከዘንባባ ከቴምር እና ከወይራ ዛፍ ጫፍ ጫፍ እየቆረጡም አነጠፉለት ይላል፡፡ ወደ እየሩሳሌም ሲገባ ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እያሉ ይጮኹ ነበር፡፡

በቤተክርስቲያን በሆሣዕና ዕለት ሲዘመርም የዐቢይ የፆም ወቅት የእየሱስ 40 ቀን የፆመበት ታስቦ ስለሚፆምና የመጨረሻው ሳምንት የመከራው ሳምንት የኀዘን ሣምንትም ስለሆነ ጭምር፤ የከበሮ መዝሙር አይዘመርም፡፡ ለሆሣዕና ግን በከበሮ ታጅበው ህፃናት ይዘምራሉ፡፡ ከመዝሙራቸው መካከል

…ሆሣዕና በአርያም

እያሉ ዘመሩ ህፃናት በኢየሩሳሌም

ሰላምሽ ዛሬ ነው ኢየሩሳሌም

ወዳንቺ መጥቷልና አምላክ ዘላለም

አንቺ ቤተልሄም የዳዊት ከተማ

የሕዝቦችሽ ብርሃን መጣልሽ በግርማ

ሆሣዕና እያሉ አመሰገኑት

በኢየሩሳሌም አዕሩግ (አረጋውያን) ህፃናት

ኪሩቤል መንበሩን የሚሸከሙለት

መስቀል ተሸከመ ሊሆነን መድኃኒት…

በግእዝም ሲዘምሩ

ዲበ እዋል ተፂኢኖ

መፃ አምላከ አድኅኖ

ሆሣዕና በደብረ ገሊላ›› ትርጉሙም በአህያ ውርንጫ ተቀምጦ፣ መጣ አምላክ ለአድህኖ ማለት ነው፡፡

በተለይ ህፃናቱ የዘንባባ ዝንጣፊና የቴምር ዛፍ ቅርንጫፍ ይዘው ይዘምሩ እንደነበር በአራቱም ወንጌላውያን ተጽፏል፡፡ እናም ህፃናት ሆሣዕና በአርያም (በሠማይ ያለ መድኃኒት) እያሉ የዘመሩበት ነበር፡፡ በዓሉ በአብያክርስቲያናቱ ሁሉ ቀሳውስትና ምዕመናቱ ሌሊት በማኅሌትና በፀሎት ቤተክርስቲያን ያሳልፉታል፡፡ በየዓመቱ ትንሳዔ አንድ ሳምንት ሲቀረው ባለው እሁድ ሆሣዕና ሲከበር ህፃናት ተሰብስበው የጌታ እየሱስን ስዕል በአህያ ላይ ይዘው ለሆሣዕና በዓል የተዘጋጁ ዝማሬዎች እየዘመሩ ቤተክርስቲያኑን ይዞራሉ፡፡

ከሰሌን ወይም ዘንባባ ዝንጣፊው የጣት ቀለበት ግንባር መስቀል በልዩ ቅርጽ እየሠሩ ያደርጋሉ፡ ፡ ካህናቱ ዲያቆናቱና ዘማሪ ህጻናቱ እንዲሁም ምዕመናን ሆሣዕናን እየዘመሩ ሲዞሩ ከአራቱ ወንጌሎች በአራቱም አቅጣጫ ሆሣዕናን አስመልክቶ የተጻፉ የወንጌል መልዕክቶች ይነበባል። ከዳዊት መዝሙር (ምስባክ) ማለትም እም አፈ ደቂቅ ወህፃናት አስተዳሎከ ስብሃት በእንተ ጸላዒ ከመ ትንስቶ ለጸላዒ ወለገፋኢ በግእዝ በዜማ ይባላል። ትርጓሜው ከህፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አንደበት ምስጋናን አዘጋጀህ ስለጠላት ጠላትና ቂመኛም ለማጥፋት ማለት ነው፡፡

ሆሣዕና ሲከበርም እንደ መስቀል ደመራ እንደ ጥምቀት ከተራ ያለ ስዕላዊ በዓል በመሆኑ ውበቱ ልዩ ነው፡፡ ራሱን የቻለ የቱሪስት መስህብ ሊሆን የሚችል ታላቅ በዓል ነው፡፡ በዓሉ በከተሞች አካባቢ የደመቀ ቢመስልም በሁሉም ቤተክርስቲያን በውጪ ባሉትም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያና ሁሉ የሚከበር ነው፡፡

ኃይለማርያም ወንድሙ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You