ለኢንዱስትሪው ዕድገት የዘርፉ ተዋንያን ከፍ ባለ የኃላፊነት መንፈስ ሊንቀሳቀሱ ይገባል!

ሀገራችን ወደ ኢንዱስትሪ ለምታደርገው ሽግግር ስኬታማነት መንግሥትን ጨምሮ የባለሀብቶች እና የሌሎች የዘርፉ ተዋንያን ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ ነው። በተለይም ዘርፉን በሚፈለገው መልኩ ውጤታማ በማድረግ ሂደት ውስጥ መንግሥት ዘመኑን የሚዋጁ ፖሊሲዎችን በመቅረጽ ለውጤታማነታቸው በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል።

የኢንዱስትሪ ዘርፍ በ1930 ዓ.ም መጀመሪያ አንስቶ እንደ ሀገር ማቆጥቆጥ እንደ ጀመረ ፣ በዚህም ከስምንት አስር ዓመታታት በላይ እድሜ እንዳስቆጠረ የታሪክ መዛግብት ይናገራሉ። በአብዛኛው በውጭ ባለሀብቶች የተጀመረው የዘርፉ እንቅስቃሴ በሂደት ፣ በመንግሥት እና በግል ባለሀብቶች ተሳትፎ እመርታ ያሳየበትም ሁኔታ ተፈጥሯል።

የእንዱስትሪው ዘርፍ በአግባቡ መሬት ባልረገጠበት ሁኔታ ፣ በ1960ዎች በሀገሪቱ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ፣ እነዚህን ኢንዱስትሪዎች በመውረስ አጠቃላይ በሆነው በዘርፉ ዕድገት ላይ ከፍ ያለ ተጽዕኖ ፈጥሯል። “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው አብዮቱን ተከትሎ የተፈጠሩ የርስ በርስ ጦርነቶች ዘርፉን የበለጠ አዳክመውታል ።

የ1983 ዓ/ም ሀገራዊ ለውጥም ቢሆን፣ ለዘርፉ ተገቢውን ትኩረት የሰጠ አልነበረም። እንዲያውም በፕራይቬታይዜሽን ስም የተደረገው የመንግሥት ፋብሪካዎችን ወደ ግል የማዘዋወር እንቅስቃሴ በብዙ ችግሮች መሞላቱ ፣ ለዘርፉ ዕድገት ተጨማሪ ፈተና በመሆን በዓለም አቀፍ ጫና ሳይቀር በፖሊሲ ደረጃ የተወሰዱ ርምጃዎች ውጤታማ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

ይህ ሀገራዊ እውነታ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ላይ ጥቁር ጠባሳ በመጣል ፣ የውጭ ባለሀብቶችን ጨምሮ ዜጎች በዘርፉ ሀብታቸውን አፍስሰው ተጠቃሚ የሚሆኑበትን የቀደመ መነሳሳት አቀዝቅዟል። ከዚያም ባለፈ በዘርፉ ተሰማርተው የሚኖሩ ባለሙያዎች /ወዝአደሮች/ ባላቸው እውቀት እና ክህሎት ተወዳዳሪ ሆነው ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አማራጭ አቀጭጮባቸዋል።

ሀገሪቱ ለኢንዱስትሪዎች መስፋፋት የሚሆን ከፍተኛ የተፈጥሮ ሀብት እና የሰው ኃይል ቢኖራትን ይህን ሀብት አልምቶ መጠቀም ፣ የሚያስችል አቅም እና የተመቻቸ ፖሊሲ አለመኖሩ ለዘርፉ እድገት ትልቅ ተግዳሮት ሆነው ቆይተዋል። ችግሩን በዘርፉ የተሠማሩ ዜጎችን ሕይወት በብዙ ተፈታትኗል ።

ከ2010 ሀገራዊ ለውጥ ማግስት ይህንን ሀገራዊ ችግር ለመፍታት ሰፊ ጥረቶች ተደርገዋል። በወቅቱ በዘርፉ የተጀመሩ ውጭ እና የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንቶች የበለጠ ተጠናክረው የሚቀጥሉበትን የፖሊሲ አቅጣጫ ከመቅረጽ አንስቶ ፣ የኢንዱስትሪው ዘርፍ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የጎላ ስፍራ እንዲኖረው ለማስቻል በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል።

በዚህም የኢንዱስትሪው ዘርፍ ሀገሪቱ ተግባራዊ እያደረገችው ባለው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ውስጥ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች መካከል አንዱና ዋነኛው እንዲሆን ተደርጓል። በዚህም የውጭውም ሆነ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በራሳቸው አቅም ሆነ ተቀናጅተው የሚሠሩበትን የተመቻቸ ሁኔታ ለመፍጠር ተሞክሯል።

በሀገሪቱ የሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በየአካባቢው ከማስፋፋት ጀምሮ በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በስፋት የሚሳተፉበት የተመቻቸ ሁኔታ ተፈጥሯል። ግብርናን ከኢንዱስትሪው ጋር በማቀናጀት የዘርፉን ሀገራዊ አቅም ለማሳደግ ሰፋፊ ሥራዎች ተሠርተዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮቪድ ወረርሽኝ ፣ የሰሜኑ ጦርነት እና በየአካባቢው የነበሩ የሰላም እጦቶች ዘርፉን ለማሳደግ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተጀመሩ ጥረቶች ላይ ጉልህ ተጽእኖ አሳርፈዋል። በተጠበቀው መልኩ ውጤታማ እንዳይሆንም ተግዳሮት ሆነዋል።

ይህም ሆኖ ግን መንግሥት ለዘርፉ ከሰጠው ከፍ ያለ ትኩረት የተነሳ ፣ ዘርፉ ከፍ ባለ መነቃቃተት ውስጥ የሚገኝበት ሀገራዊ ሁኔታ ተፈጥሯል። ለዚህም “ኢትዮጵያ ታምርት” በሚል በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ የተደረገው ንቅናቄ በዋኛነት ተጠቃሽ ነው።

ንቅናቄው በሀገሪቱ የሚገኙ ፋብሪካዎች ያሉባቸውን ችግሮች በጥናት በመለየት መፍትሄ ማፈላለግን መሠረት ያደረገ ፤ ፋብሪካዎቹ ባላቸው አቅም ወደ ምርት የሚገቡበትን መልካም አጋጣሚ በመፍጠር ምርታማነታቸውን በእጥፍ እስከ ማሳደግ የደረሰ ተሞክሮ መፍጠር ያስቻለ ነው።

በዚህም በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶችን የመሥራት መነቃቃት ከፍ ማድረግ ተችሏል። በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች /ወዛደሮችም ጊዜያቸውን ፣ አቅም እና ክህሎታቸውን ተጠቅመው የተሻለ ተጠቃሚ የሆኑበት ተጨባጭ እውነታ ተፈጥሯል። ሀገሪቱም በቀጣይ ከዘርፉ ተጠቃሚ የምትሆንበትን ተሰፋ በተጭባጭ አመላክቷል።

የዛሬውን የዓለም የወዝአደሮች ቀንን ስናከብር ፤ ዘርፉ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም እንዲሆን በሁለንተናዊ መልክ የጀመርናቸው እንቅስቃሴዎች የበለጠ ስኬታማ እንዲሆኑ በተለይም ባለሀብቱ፣ ወዝአደሩ እና ሌሎች የዘርፉ ተዋንያን ከፍ ባለ የኃላፊነት መንፈስ ለመንቀሳቀስ ቃል እየገቡ ሊሆን ይገባል!

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You