ሕገ ወጥ የእንስሳት እርድን ለመከላከል ሕብረተሰቡ እንዲተባበር ጥሪ ቀረበ

– ድርጅቱ ለመጪው የፋሲካ በዓል ከ7 ሺህ 500 እስከ 8 ሺህ እርድ ለማካሄድ አቅዷል

አዲስ አበባ፡- ሕገ ወጥ የእንስሳት እርድ ሲፈጸምና ፍቃድ ባልተሰጠው ተሽከርካሪ ዝውውር ሲከናወን ከተመለከተ ጥቆማ በማቅረብ ሕገ ወጥ ድርጊቱን ለመከላከል እና ለማስቆም ሕብረተሰቡ ተባባሪ እንዲሆን የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት አሳስቧል፡፡ ለመጪ ፋሲካ በዓል ከ7 ሺህ 500 እስከ 8 ሺህ እርድ ለማካሄድ ማቀዱን አስታውቋል

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ሰይድ እንድሪስ የትንሳኤ በዓልን በማስመልከት ትናንት በሰጡት መግለጫ፤ ህብረተሰቡ ስጋ አቅራቢዎች ሕጋዊ የእንስሳት እርድ ፍቃድ የተሰጣቸው እና የተመረመረ ስጋ አቅራቢ መሆናቸውን አጣርቶ ገዝቶ ሊጠቀም እንደሚገባ መክረዋል፡፡

ለንግድ የሚቀርብ ሕገ ወጥ የእንስሳት እርድ እና ዝውውር ከሕብረተሰቡ የተደበቀ ባለመሆኑ ሕብረተሰቡ ድርጊቱን ለመከላከል በሚደረግ ሂደት ለሕግ አካላት ጥቆማ በማቅረብ ተባባሪ መሆን እንዳለበትም ነው የተናገሩት፡፡

ከወትሮው በተለየ መልኩ እንስሳቶች እርድ ለማከናወን በቂ ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል፡፡ ድርጅቱ የከብት ስጋ የፍየል እና የበግ ስጋ በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚሸጥም ተናግረዋል፡፡

ከፍተኛ መጠን ያለውን እርድ ለማከናወን ዝግጅት መደረጉን በመጠቆምም፤ ድርጅቱ ከ7 ሺህ 500 እስከ 8 ሺህ እርድ ለማካሄድ በማቀድ ተጨማሪ የሰው ሃይል በመጨመር ቅድመ ዝግጅቱን ማጠናቀቁንም ተናግረዋል::

መደበኛ የዕርድ አገልግሎት ዋጋ ለዳልጋ ከብት አንድ ሺህ 400 ሲሆን በልዩ ሁኔታ ደግሞ አንድ ሺህ 700 ብር መሆኑን እንዲሁም ለፍየል እና ለበግ የአገልግሎት ዋጋ 167 ብር፣ በልዩ ሁኔታ ደግሞ 230 ብር እንደሚያስከፍል አመልክተዋል፡፡

በሕገ ወጥ የእንስሳት ንግድ ጋር ተያይዞ ከግብር እና መሰል የታክስ ስወራ ከተማ አስተዳደሩ አንድ ነጥብ 35 ቢሊዮን ብር እንደሚያጣ ነው ያመለከቱት፡፡

ከጾም በፊት በሉካንዳ ቤቶች በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ሕገ ወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው የተገኙ 85 ቤቶች እንዲታሸጉ መደረጉን ጠቁመው፣ በቀጣይ ሕገወጥ እርድን ለመከላከል የተጠናከረ ርምጃ እንዲሚወሰድም ነው የገለፁት፡፡

ሕገ ወጥ እንስሳት እርድ ተፈጽሞ ሲገኝ ስጋውን መውረስ እና ማስወገድ ሲተገበር እንደነበር በማስታወስም፤ በቀጣይ በሁሉም ማህበራዊ የግንኙነት አውታሮች ሕገ ወጥ እርድ የሚፈጽሙና የሚሸጡ አካላትን ለህብረተሰቡ የማሳወቅ ሥራ ይከናወናል ብለዋል፡፡

በሕጋዊ መልኩ ፍቃድ አውጥተው በሕገ ወጥ ንግድ የሚንቀሳቀሱትን አካላት የንግድ ፍቃዳቸውን እንዲሰረዝ የሚደረግበት አሠራር መዘርጋቱንም ጠቁመዋል፡፡

ሕገ ወጥ እንስሳት እርድ የተስፋፋው ከግንዛቤ ችግር፣ ቄራዎች ተደራሽ ካለመሆናቸው እና ለግብር ስወራ ታስቦ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ድርጊቱን የሚፈጽሙና የሚያስፈጽሙትን ከፍትህ ቢሮ ጋር በመነጋገር በሕግ እንዲጠየቁ የሚደረግበት ሥራ ይሠራል ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ሕገ ወጥ ስጋ የሚያዘዋውሩ ተሽከርካሪዎች እንዲወረሱ ለሚመለከተው አካል ጥቆማ በማቅረብ ድርጊቱን የመከላከል ሥራ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ አየለ ሳህሌ በበኩላቸው፤ ህብረተሰቡ ሕጋዊ የእርድ ፍቃድ አገልግሎት ከተሰጣቸው አካላት በመጠቀም ጥራቱና ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት ማግኘት እንዳለበት መክረዋል፡፡ ማህበሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ሕገ ወጥ እርድ የሚፈጽሙ አካላትን ለመከላል እንደሚሠራም ነው የገለፁት፡፡

ዘላለም ግዛው

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You