አዲስ አበባን የሚመጥነው ልማት

ዜና ሀተታ

በአዲስ አበባ ዋና ዋና ጎዳናዎች የግንባታ ባለሙያዎች እዚህም እዚያ በሥራ ላይ ተጠምደዋል፡፡ የኮሪደር ልማቱ እየተፋጠነ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ከተማዋን ገጽታ ከማስዋቡ ባለፈ ለነዋሪዎቹም ምቹ አካባቢ የሚፈጥር መሆኑን ለኢፕድ አስተያየታቸውን የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ይገልጻሉ፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ ራስ መኮንን አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ብሩክ ኃይሉ(ፕ/ር) ፤ አዲስ አበባ የተለያዩ የዓለም እና የአፍሪካ ተቋማት መቀመጫ ናት፡፡ በዲፕሎማሲውም ከኒዮርክ ቀጥሎ ሶስተኛ የዲፕሎማሲ ውክልና የተሰጣት ከተማ ስለሆነች፤ እንደስሟ አበባ ማድረግ የግድ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

ከ38 ዓመት በላይ በራስ መኮንን አካባቢ መኖራቸውን የገለጹት ፕሮፌሰር ብሩክ፤ ሁልጊዜ በተመሳሳይ ነገር መኖር አይቻልም፡፡ ከተሞች ሁሌም እየተሻሻሉ ይሄዳሉ፡፡ ታሪካዊ ቅርሶችን ከታሪካዊ እና ከክብደታቸው አንጻር በማስቀረት መሻሻል ያሉባቸውን ነገሮች ማሻሻል አስፈልጊ መሆኑን አያጠያየቅም ይላሉ።

በመዲናዋ እየተሰሩ የሚገኙት የኮሪደር ልማቶች፣ መንገዶች እና የወንዝ ዳር ፕሮጀክቶች የአፍሪካ ከተማ ብቻ ሳትሆን ዓለም አቀፍ ከተማ እንድትሆን ደረጃዋን ያሻሽላሉ ሲሉም አስረድተዋል፡፡

ከሌሎች የዓለም ሀገራት አንጻር እንኳን ስንመለከት መንገድ የሌለው ከተማ ቀጭጮ ነው የሚቀረው ያሉት ነዋሪው፤ የኮሪደር ልማቱ ለንግድ እና ለመዝናኛ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ለከተማዋ ነዋሪም ሳቢ አካባቢን ይፈጥራል፡፡ በዚሁ ልክም የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር አስተያየታቸውን ሰጥተውናል፡፡

አራት ኪሎ ሥላሴ ቤተክርስቲያን አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ጽጌ ኃይሌ በበኩላቸው፤ ሌላ ሀገር አይቶ ለመጣ ሰው እየተሠራ ያለው ሥራ በጣም ደስ የሚል እና ሀገሬ አማረባት ብሎ ደፍሮ ለመናገር የሚያስችል ነው ይላሉ ፡፡

ልማቱ የሚደገፍና በነጻነት የአካባቢውን ውበት እያደነቁ ለመንቀሳቀስ ያስችላል ያሉት ወይዘሮ ጽጌ፤ የልማት ተነሺ እንደመሆናችን የሚሰጠን ተለዋጭ ቦታ ከኖርንበት አካባቢ ብዙ ባይርቅ ጥሩ ነው ሲሉ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

አራት ኪሎ አካባቢ አርመን ህንጻ ነዋሪ የሆኑት ሰለሞን አሊ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የልማት ሥራው ከቱሪዝም እና ከኢኮኖሚ ጠቀሜታው ባሻገር ሕዝቡ በምቹና ማራኪ በሆነ አካባቢ እንዲኖር የሚያስችል ነው ። ዘመናዊ መሠረተ ልማቶች የተሟሉለት ከተማ ለማድረግ ያስችላል፡፡ ከዚህ አኳያ የኮሪደር ልማቱ የሚደገፍና ይበል የሚያሰኝ ነው ይላሉ፡፡

40 እና 50 ዓመት አብረው የኖሯቸው ጎረቤቶቻቸው ወደ ሌላ ቦታ ተዛውረው የተሻለ ቤት እንደተሰጣቸው የገለጹት ነዋሪው፤ ወደፊትም እንደዚህ አይነት ልማቶች ሕዝቡን በጥልቀት በማማከርና በማሳተፍ ሊቀጥሉ ይገባል ነው ያሉት፡፡

የአራት ኪሎ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አቶ ማስረሻ ታደሰ በበኩላቸው፤ አንድ ከተማ ሁልጊዜም በተመሳሳይ ሁኔታ መቀጠል የለበትም፡፡ አዲሱ ትውልድ በየጊዜው አዳዲስ ነገሮችን እያሻሻለ መሄድ አለበት፡፡ ከዚህ አኳያ እንደማህበረሰብ የልማት ሥራውን እደግፋለው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም አቶ ማስረሻ፤ ከተማውን በማልማት ሂደት ለሚነሱ ነዋሪዎች ተመጣጣኝ ነገር ቢሰጥ መልካም ነው፡፡ ሥራቸው የመኖሪያ ቦታቸው አካባቢ ለሆኑ ሰዎች እሩቅ ቦታ የሚሄዱ ከሆነ ጫና ስለሚፈጥር በዚህ ረገድ ቢታሰብበት ጥሩ ይሆናል ሲሉ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

አራት ኪሎ አራዳ ክፍለ ከተማ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አቶ ተክለሃይማኖት አቦሴ የኮሬደር ልማቱ ከተማዋን የማስዋብ፣ መንገዶችን የማስፋትና መሠረተ ልማቶችን የማሻሻል ዓላማ እንዳለው ተመልክተናል፡፡ ይህ መልካም ተሞክሮ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች ሊስፋፋ ይገባል ነው ያሉት፡፡

የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት አቶ ጌታሁን መንገሻ እንደተናገሩት፤ ከዚህ በፊት በአካባቢው የተለያዩ ቆሻሻዎች እንደሚጣሉ በመግለጽ፤ አሁን በመንግሥት የተጀመረው ሥራ ከተማዋን ጹዱና ውብ የሚያደርጋት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ዘላቂ ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር ያስችላል ባይ ናቸው፡፡

አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና ሆና ሁሌም በተመሳሳይ ሁኔታ ትቀጥል ማለት የማያስኬድ ነው። ዳሩ ለመቷል አሁን ደግሞ መሀሉ ሊለማ ይገባል ብለዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ አካባቢዎች የተሠሩ መሠረተ ልማቶችን ለማገናኘት የሚያስችሉ አምስት የኮሪደር ልማቶችን እየሠራ እንደሆነ ይታወቃል።

ይህም ከዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም እስከ አራት ኪሎ፤ ከመስቀል አደባባይ- ቦሌ ድልድይ፤ ከቦሌ ድልድይ-መገናኛ-ሲኤምሲ-አዲስ አፍሪካ ኤግዚቢሽን እና ኮንቬንሽን ማዕከል፤ ከሜክሲኮ-ሳር ቤት-ወሎ ሰፈር እንዲሁም ከአራት ኪሎ- መገናኛ የኮሪደር ልማቱ አካል መሆኑ ተገልጿል።

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You