ሀገራት ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ብልፅግናን ለመቋደስ የአንድነትን ኃይል፣ የሕብረትንም የድል ምስጢር ጠንቅቀው በመረዳት በተለይ በንግድና ኢንቨስትመንት እርስ በእርስ መተሳሰርን አማራጭ ማድረግ ከጀመሩ ዓመታትን አስቆጥረዋል።
ዓለም አቀፉ ምስል
ከመገፋፋት ይልቅ መደጋገፍ ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ ራስ ወዳድ እና ስግብግብነትን በማስወገድ እርስ በእርስ ያላቸውን መስተጋብር ለማጠናከር እንዲሁም በኢኮኖሚ አቅም በእኩል ደረጃ መወዳደርም ሆነ መደራደር የሚያስችላትን አቅም ለማጎልበት በአሁን ወቅትም የተለያዩ ተግባራት በማከናወን ላይ ተጠምደዋል።
በኢኮኖሚ ልዕልና ስማቸው አንቱ የሚባልላቸውን ጨምሮ በርካታ ሀገራትም በዚሁ መንፈስ እየተመሩ መጪውን ለማሳመር በመትጋት ላይ ይገኛሉ። በተለይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ልዩ ትኩረት ሰጥተው፣ የተለያዩ ተግባራትን በመከወን ላይ ናቸው።
የምጣኔ ሀብት ምሁራን እንደሚያስረዱት፣ አንድን ሀገር ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ተፈላጊና ሳቢ የሚያደርጋት የዘረጋችው ሀገራዊ ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ነው። ይሁንና ምቹ የሕግ እና የፖሊሲ ማዕቀፍ መኖሩ ብቻ ፍሰቱን እንዲጨምር ላያደርግ ይችላል። ሀገራት በተለይ ውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመትን ለመሳብ በየጊዜው አሉኝ የሚላቸውን አማራጮች ብሎም ምቹ ሁኔታዎችን ማስተዋወቅ የግድ ይላቸዋል።
በአሁን ወቅትም በዓለም አቀፍ ደረጃ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና ለመሳብ የሚያደርግ ፉክክሩ ይበልጥ እያጦዘ መጥቷል። ይህ እንደመሆኑም ሀገራት የተቀናጀ ጠንካራ ሥራ መሥራትና ሁሉ አቀፍ ተወዳዳሪነትን ማጠናከር ግድ ብሏቸዋል።
ኢንቨስተሮችም በአንድ ሀገር መዋዕለ ነዋያቸውን ፈሰስ ከማድረጋቸው አስቀድሞ ውጤታማ መሆን የሚያስችላቸውን በርካታ መመዘኛዎች ያስቀምጣሉ። መዋዕለ ነዋያቸው ፈሰስ ለማድረግ ሲያስቡም የገበያ አዋጭነት፣ የደንበኞች ቁጥር፣ የግብዓት እንዲሁም የመሠረተ ልማት አቅርቦትን እና ተደራሽነት መጠንን ይቃኛሉ። የቢዝነስ አመቺነት ‹‹Ease of Doing Business››ን ጨምሮ በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ነክ ተቋማት የሚወጡ መረጃዎችንም ያማትራሉ።
የኢትዮጵያ መልክ
ኢትዮጵያ ከአንድ መቶ አስር ሚሊየን በላይ ሕዝብ ያላት ሀገር ናት። ይህ ቁጥር በገበያ መነፅር ሲታይ ከፍተኛ አቅምና ፍላጎት እንዳለ ማረጋገጫን የሚሰጥ ነው። ከሰው ኃይል ባሻገር ሀገሪቱ በዓይነት ብዙ የተፈጥሮ ሀብት የተንቆጠቆጠች መሆኗም ለኢንቨስትመንት ገበያ ምቹ እንድትሆን ከፍተኛ አቅም ከሚፈጥሩት መካከል የሚጠቀስ ነው።
ይሁንና ኢትዮጵያ ቢዝነስ አመቺነት ስትቃኝ መሻሻሎችን ብታሳይም መሆን ከሚገባት ደረጃ ላይ እንዳልሆነች የሚካድ አይደለም። የተለያዩ የምጣኔ ሀብት ምሁራንም፣ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና ከትርፉ ተጠቃሚ ለመሆን ከሁሉ በላይ የተቋማት አቅም መጎልበት በተለይ ሕግ እና ሥርዓትን በአግባቡ መተግበር የግድ ነው ይላሉ። በተለይ የውጭ ኢንቨስመንትን ወደ ሀገር ውስጥ ለመሳብ ኢንቨስተሮች ጉዳያቸው በቀላሉ ማስፈፀም እንዲችሉ የማድረግ ተግባር ጠንካራ የድጋፍና የክትትል አሠራርን እንዲሁም ቅንጅትን እንደሚጠይቅ አፅእኖት ይሰጡታል።
ይህ ተግባር እንደ ኢትዮጵያ ባሉ መዋቅራዊ አደረጃጀቶች ከወረዳ ጀምሮ እስከ ከተማና ክልል እንዲሁም ፌዴራል ደረጃ የሚዘልቅ ነው። ይሁንና በሀገሪቱ ይህን ሥራ በተሻለ በሆነ መልኩ እየተከናወነ ስለመሆኑ መናገር የሚቻለው በፌዴራል ደረጃ ብቻ ነው። ኢንቨስተሮቹ ወደ ክልልና ዞን ብሎም ቀበሌ ሲወርዱ የሚገጥማቸው በፌዴራል ደረጃ ከሚያገኙት የተቃረነ ነው። ችግሩም ለኢንቨስተሮቹ ምሬት እና ተስፋ መቆረጥ በአጠቃላይ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ሁነኛ ማነቆ ሆኖም ቆይቷል።
ለውጦች
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስተዳደር ወደ ስልጣን ከመጣ ጊዜ አንስቶም፣ ይህን መልክ ለመቀየርና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ ለማበረታታት፣ ለማስተዳደርና ለመጠበቅ የሚያስችል አመቺ ከባቢ ሁኔታን ለመፍጠር አዳዲስ ተከታታይ የሪፎርም ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።
ቀደም ባሉት ዓመታት የወጡና የዘርፉን እድገት የሚገዳደሩ አንዳንድ ሕጎችና ደንቦች እንዲወገዱም ተደርጓል። የኢንቨስትመንት ፖሊሲን ስር ነቀል በሆነ መልኩ በማጎልበት በየጊዜው ከታዩ ልምዶች ትምህርት በመውሰድ፣ ለውስጥም ሆነ ለውጭ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታዎች ለመፍጠር የተለያዩ ርምጃዎች በመውሰድ ላይ ናቸው።
በተለይም ተጨማሪ ሀብት፤ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ መፍጠርና ማጎልበትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ባለፉት ስድስት ዓመታት በመንግሥት ተይዘው የነበሩ ዘርፎችን ሙሉ በሙሉና በከፊል ወደ ግሉ ዘርፍ የማዞር ብሎም ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት ለማድረግ ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን የሚታወስ ነው። ከውጭ ባለሀብቶች ባሻገር የግል ዘርፉን በተለይ የሀገር ውስጥ ኢንቨስተሮች ለማበረታታትና ሁለንተናዊ አቅማቸውን በማሳደግ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚወረወሩትን ጠጠር ለማብዛትም ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል።
መንግሥት ከዚህ ጎን ለጎን የሀገር ውስጥ ኢንቨስተሮች ፍትሐዊ ያልሆነ ውድድር እንዳይገጥማቸው፣ በጥራትና በብዛት የመሥራት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ገበያ የእሴት ሰንሰለት የመዋሃድ አቅማቸውን በማሳደግ፣ በሂደትም እሴት የታከሉባቸው ኢንቨስትመንቶችን መፍጠር እንዲችሉ በሚል የተወሰኑ የንግድ ዘርፎችን ከውጭ ሀገሮች ኢንቨስተሮች ተሳትፎ ከልሎ መቆየቱም የሚዘነጋ አይደለም።
መንግሥት በተለይም የሀገር ውስጥ ነጋዴዎችን ለመጠበቅ በጅምላና ችርቻሮ ንግድ ላይ የውጭ ባለሀብቶች እንዳይገቡ ሲከላከል ቆይቷል። ይህም ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ከለላ ሲሰጥ ራሳቸውን ጠቅመው ሀገርንም ይደግፋሉ በሚልና የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪ እንዲያድግ ማድረግን ታሳቢ በማድረግ ነው።
ይሁንና ይህ ከለላ የሚፈለገው ለውጥ ማምጣት አልሆነለትም። ይህን ተከትሎም አማራጭ ማፈላለግ ግድ ሆኖበታል። ካለው የሀገሪቱ ፍላጎት አንፃር የግብይት ሥርዓቱ በተጨማሪ ተዋንያኖች ካልታገዘ የሚያስከትለው ጉዳት ቀላል እንዳልሆነ ግንዛቤ ተወስዷል። ከሰሞኑም እስካሁን ለሀገር ውስጥ ኢንቨስተሮች ተለይተውና ተጠብቀው በቆዩ የንግድ ዘርፎች ላይ ማሻሻያ መደረጉ ተገልጿል።
ባሳለፍነው ሚያዝያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም የኢንቨስትመንት ኮሚሽንና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የውጭ ኢንቨስተሮች ከዚህ ቀደም ተከልክለው በነበሩ ማለትም የወጪና የገቢ ንግድ፣ እንዲሁም የጅምላና የችርቻሮ ንግድ ውስጥ እንዲሳተፉ የሚፈቅድ መመሪያ በኢንቨስትመንት ቦርድ መፅደቁን ገልጸዋል። በመመሪያው ውስጥ የተቀመጡ መስፈርቶችን ያሟሉ የውጭ ባለሀብቶች ፈቃድ እንደሚሰጣቸው ተመላክቷል።
ፋይዳው
ለኢትዮጵያውያን ብቻ ይፈቀዱ የነበሩ የንግድ ሥራዎች ለውጭ ኩባንያዎች ቀስ በቀስ እየተከፈቱ ስለመሆናቸው አንድ ማሳያ ተደርጎ የተወሰደው ይህ ማሻሻያ፣በኢትዮጵያ የግብይት ሥርዓት ውስጥ ተጨባጭ ለውጥ እንደሚያመጣም ታምኖበታል።
ሕጉ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ተከልሎ የነበረውን የጅምላና ችርቻሮ የንግድ ሥራ ለውጭ ኩባንያዎች በመፍቀድ ብቻ የተገደበ ሳይሆን በወጪና ገቢ ንግድ ላይም የውጭ ባለሀብቶች ተሳታፊ የሚሆኑበትን በር የሚከፍት በመሆኑ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ አዲስ አሠራር እንደሚፈጥርም አያከራክርም።
በዘርፉ የውጭ ኩባንያዎች ከገቡ ቢዝነሱ በተወዳዳሪነት ላይ የተመሠረተ አገልግሎት የሚሰጥበት እንደሚሆን አያጠርጥርም። ይህ ደግሞ በቀጥታም ይሆን በተዘዋዋሪ የግሉ ዘርፍ ልምድም እንዲቀሰምበት እንዲያድግ ምክንያት ይሆናል። ከውድድር በተጨማሪ ቴክኖሎጂ፣ እውቀትና አዳዲስ አሠራሮችን ያስተዋውቃል።
ማሻሻያው በጥቂቶች የተያዘውን የጅምላና ችርቻሮ ንግድ ሥራ ተወዳዳሪ እንዲሆን በማድረግ ገበያን ማረጋጋት የሚቻልበት ዕድል ሰፊ ነው። በተለይም ንግዱ ዘርፍ የሚታዩ ሕገ ወጥ አሠራሮችን ለማሻሻልና ፍትሐዊ የንግድ ሥርዓት ለመዘርጋት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል። በተለይ ሕጋዊ የግብይት ሥርዓት እንዲሰፍን በማድረግ ለዋጋ መረጋጋት ከፍተኛ አቅም ለመፍጠር አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ከሸማቹ ወገን ፋይዳቸው ጉልህ ነው።
የኮንትሮባንድ ንግድን በማስቀረት በሕጋዊ መንገድ የሚደረግ የንግድ እንቅስቃሴን የማሳደግ አቅሙም ግዙፍ ነው። የግብይት ሥርዓቱን መስመር ከማስያዝ ባሻገር የመንግሥትም የግብር ገቢ በማሳደግ ረገድ ያለው ፋይዳም እጅጉን ከፍተኛ የሚባል ነው።
የሀገሪቱ የግብይት ሥርዓትን ለማስተካከል ከመርዳቱም በላይ ሀገሪቱ በወጪ ንግድ ዘርፍ ያላትን ተወዳዳሪነት ይጨምራል። ማሻሻያው በተለይ ሀገሪቱ ለዓመታት የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት የምታደርገውን ጉዞ ለማሳለጥ፣ የሚኖረው አስተዋፅኦም በቀላሉ ሊታይ አይገባም።
የማሻሻያው አጠቃላይ ድምር ውጤትም የኢትዮጵያን ኢንቨስትመንትና ኢንቨስተሮች ለማጎልበትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አቅም የሚፈጥሩ ናቸው። በተለይም አዳዲስ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ የሚደርገውን ጥረት በማገዝ ረገድ ሚናቸው የጎላ ነው።
ስጋቶች
ይሁንና ማሻሻያው መሰል ትሩፋቶች እንዳሉት የውጭ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ መግባታቸው በሀገር ውስጥ ተመሳሳይ ሥራ በሚሠሩ ነጋዴዎች ላይ ጫና ይፈጥራል። የውጭ ኢንቨስተሮች የውጭ ምንዛሪ የማቅረብ አቅማቸው ከፍተኛ ስለሆነ ብዙ የውጭ ምንዛሪ ይዘው ስለሚመጡ የሀገሬው ነጋዴ ሊወጣ ይችላል የሚል ስጋት ያላቸውና መከራከሪያ የሚያቀርቡ ወገኖች አሉ። የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች ተወዳዳሪ አቅም እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑም ለጭንቀታቸው ዋነኛ ምክንያት አድርገው ያቀርባሉ። የጥቁር ገበያ ችግርም ሌላኛው ራስ ምታት መሆኑን ያነሳሉ።
በርግጥም መሰል ስጋቶች ተገቢ ናቸው። ይሁንና ኢትዮጵያ በየትኛውም መስፈርት ከዓለም የግብይት ሥርዓት ውጪ ልትሆን አትችልም። ሁለንተናዊ አቅምን ለማጎልበት መዘጋጀት እንጂ ስጋትን ታሳቢ በማድረግ የሀገር ውስጥ ኢንቨስተሮች ራሳችንን አልቻሉምና ሊመጡ አይገባም ማለት ከዚህ በኋላ ብዙ ርቀት የሚያስኬድ አይደለም።
እስካሁን በመጠበቅ የተከፈለው ዋጋም ለዚህ ምስክር መሆን የሚችል ነው። ይህ እንደመሆኑም አሁን ላይ መፍትሔው ከፍ ላለ ውድድር ራሳቸውን ማዘጋጀት ብቻ ነው። ከዚህ ባለፈ እንዴት ባለ መልኩ በጥምረት /በጆይንት ቬንቸር /መሥራት እንደሚችሉ መዘየድን ሊዘነጉ አይገባም።
ትኩረት የሚፈልጉ ጉዳዮችና ቀጣይ ሥራዎች
መንግሥት በየደረጃው ለግል ኢንቨስትመንት መስፋፋት እየወሰዳቸው ያሉ ወሳኝ የሆኑ ሥራዎች ትርጉም ያለው ውጤት ሊያስገኙ የሚችሉት የተለያዩ አካላት የተቀናጀ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ እንደመሆኑ በዚህ ረገድ ሰፊ ሥራዎችን መሥራት የግድ ይላል።
ኢንቨስተሮቹ ከመጡ በኋላ እንዴት ውጤታማ በሆነ መልኩ መስተናገድ አለባቸው፣ በሥራ ሂደት የሚያግጥሙ የተለያዩ ችግሮችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እንዴት ፈጣን በሆነ መልኩ መፍታት ይቻላል የሚለውን ታሳቢ ያደረገ ሥራ መሥራትም ይገባል። ይህን የሚከታተሉ ባለሙያዎችን አቅም በየጊዜው ማጎልበት ተገቢ ነው።
በትግበራ ወቅት ከቁጥጥር ጋር በተያያዘ በሚስተዋሉ ድክመቶችና በሚፈፀሙ ሕገ ወጥ ተግባራት ሀገር የሚያስፈልጋትና ወደ ሀገር የሚገባው የተለያየ ሊሆን ይችላል። የዘርፉ ተዋናዮች እንጂ ሀገር የምትፈልገው ላይገባም የሚችልበት እድል ይኖራል። አሠራሩ ጥንቃቄ ካልተደረገበት ግለሰቦች በትይዩ ገበያ ገዝተው ያስቀመጡትን ወይም ያጠራቀሙትን የውጭ ምንዛሪ የሚያጠቡበት ወይም ሕጋዊ የሚያደርጉበት ሁኔታን ሊያመቻች ይችላል።
በተለይም ሕግና ደንቦችን ተከታትሎ የማስፈጸም አቅሙ ደካማ ከሆነ ማሻሻያው አደገኛ መሣሪያ የመሆን ዕድል እንደሚኖረው እሙን ነው። ይህ እንደመሆኑም በአስገዳጅነት የተቀመጡ ድንጋጌዎችንና አሠራሮችን በአግባቡ ስለማካሄዳቸው መቆጣጠር የግድ ይላል።
በአጠቃላይ ማሻሻያው ያላግባብ ጥቅም ላይ እንዳይውል መጠንቀቅ ያስፈልጋል። የማሻሻያውን ዓላማ ለማሳካት ሳይሆን የራሳቸውን ጥቅም ለማዳበር የሚፈልጉ ግለሰቦች ያላግባብ እንዳይጠቀሙበት ሂደቱ በጥብቅ ሥነ ምግባር ሊመራ ይገባል።
በማሻሻያ ውጤት ታይቷል? ገበያውስ ተረጋግቷል? የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ በየጊዜው መቃኘት መዘንጋት አይኖርበትም። አፈፃፀሙን በየጊዜው በመከታተል የተፈለገውን ውጤት አምጥቷል፣ አላመጣም፣ ችግሮችና መፍትሔዎቹስ የሚለውን መገምገም ያስፈልጋል። ከዚህም ከፍ ሲል ውጤቱ እየታየ ማሻሻያዎች ካስፈለገ ተግባራዊ ማድረግ የግድ ይላል።
ሌላው ልዩ ትኩረት እና መፍትሔ ሊሰጠው የሚገባ ሀገሪቱ ውስጥ ስር ሰዶ የሚገኘው ግዙፍ የሙስና ወንጀል መከላከል ማስቆም መሆኑም የሚያከራክር አይደለም። ሙስናን መቆጣጠር አለመቻል ገበያውም ጤናማ አየር እንዳይተነፍስ በማድረግ በኢንቨስመንት ፍሰት እና በኢንቨስተሮች ሥነ ልቦና ላይ ከባድ ጫናን ይፈጥራል። ይህ እንደመሆኑም ማሻሻያው የተፈለገውን ግብ እንዲመጣ ሕገ ወጥ ተግባሩን የእውነት መታገል ያስፈልጋል።
በተለይም ከሰላም እና ጸጥታ ጋር ተያይዞ የሚነሱት ችግሮች ፈጣን እልባት መስጠት፣ ሎጂስቲክስና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት፣ በቋሚነት የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግና ከውስጥ ፍላጎት አልፎም የውጭ ምንዛሬ ማስገባት የሚያስችሉ ዋና ዋና ምርቶችን በስፋት በሀገር ውስጥ ማምረት ብሎም ለውጭ ገበያ ማቅረብ ታሳቢ አድርጎ ዘወትር መሥራት ይገባል። በተለይ የፍላጎትና አቅርቦት ምጥን ልዩነቱን ለማስተካከል ሀገር ውስጥ በተሻለ ማምረት የሚችልበትን መንገድ መቀየስና ለዚህ ተግባራዊነትም ሌት ተቀን መትጋት የግድ ይላል።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 22 ቀን 2016 ዓ.ም