የ«ፅዱ ጎዳና – ኑሮ በጤና» ቴሌቶንን በመቀላቀል፣ ፅዱ ኢትዮጵያን እውን እናድርግ

ዜጎች በንጹህ እና ደህንነቱ የተጠበቀ አካባቢ የመኖር ሕገ መንግሥታዊ መብት አላቸው፡፡ ይሄ መሆኑ ደግሞ የሰው ልጆች በአካባቢ መቆሸሽና ብክለት ምክንያት ከሚፈጠርባቸው ዘርፈ ብዙ ችግር እንዲጠበቁ ያደርጋቸዋል፡፡ በተለይ ንጹህ አካባቢ ላይ የሚኖሩ ሰዎች ከቆሻሻ ጋር ተያይዞ የሚከሰት በሽታና ወረርሽኝ የተጠበቁ ናቸው፡፡

በዚህ ረገድ በከተሞች የሚታየው የጽዳት ሁኔታ እንደ ሀገር ካለን የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ጋር ተዳምሮ፣ ዜጎች ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ንጹህ ከባቢ የመኖር ሕገ መንግሥታዊ መብትን የማጣት ብቻ ሳይሆን፤ ከፍ ላለ የጤና ችግር ሲዳረጉ ማየት የተለመደ ሆኗል።

በተለይ በከተሞች አካባቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሕዝብ ቁጥር መጨመር እና የከተሞች መስፋፋት፤ ቆሻሻ አስተዳደር ሥርዓቱ ላይ የራሱን ችግር ይዞ መምጣቱ አልቀረም፡፡ ምክንያቱም ከተሞች በሰፉ እና ነዋሪዎቻቸውም በጨመረ ቁጥር፤ ከፍ ያለ ቆሻሻን የማምረት አቅም ይኖራቸዋል፡፡

ይሄ የሚመረት ቆሻሻ ደግሞ በአግባቡ ካልተወገደ እና ነዋሪዎችም በተገቢው መልኩ ቆሻሻን ካላስወገዱ፤ ከተሞች ከፍ ያለ የቆሻሻ ክምችትን ማስተናገዳቸው አይቀሬ ነው፡፡ ለዚህም ነው ዛሬ ላይ መዲናይቱን አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች የመንገድ ዳርቻዎች ላይ የቆሻሻ ክምችት የሚታየው፡፡

ይሄ ደግሞ በአንድ በኩል የዜጎችን ጤና የሚያውክ ጉዳይ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለዓይን የማይማርክ፤ ለአፍንጫም መልካም ያልሆነን ሽታ የሚጋብዝ አካባቢን የሚፈጥር ነው፡፡ እናም ችግሩ ከከተሞች ነዋሪዎች ባሻገር አልፎ ሂያጅ መንገደኛን፤ ውሎ አዳሪ እንግዳን ምቾት መንሳቱ እሙን ነው፡፡

ይሄን እግር ተገንዝቦ መፍትሄ ከመስጠት አኳያ ላለፉት ዓመታት በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡ ፡ በተለይ ከ2010ሩ ሀገራዊ ለውጥ ማግስት ከቤት እስከ አደባባይ፤ ከከተማ እስከ ሀገር የሚዘልቅ ውብና ንጹህ፣ ማራኪና ጽዱ የሆኑ አካባቢዎችን ለመፍጠር እየተሰራ ይገኛል፡፡

በዚህ ረገድ አዲስ አበባን ብቻ ብንወስድ፣ ለዓመታት የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ሆነው ታጥረው የቆዩ ቦታዎችን (ለምሳሌ፣ የሸራተን ማስፋፊያ እና ፒያሳ ማዘጋጃ ቤት አጠገብ የሚገኘው ቦታ) መቀየር ተችሏል፡ ፡ በዚህም የበርካታ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ፣ የአደገኛ ተግባራት መፈጸሚያ የነበረውን የሸራተን ማስፋፊያ፣ በገበታ ለሸገር ፕሮጀክት “ወዳጅነት አደባባይ” በሚል ታቅፎ አሁን ላይ ውብና ሁሉም ሄዶ ሊዝናናበት ወደሚናፍቀው ይዘት ተቀይሯል፡፡

በተመሳሳይ የፒያሳን ገጽ በብዙ መልኩ ሲያጠይም የኖረው እና የብዙ ቆሻሻና ክፉ ተግባር መድረክ ሆኖ የኖረው ቦታ፤ ዛሬ ላይ የዓድዋ ታሪክና ጀግኖች በክብር የሚታሰቡበት ሕያው ሙዚየም ተሰርቶበት፣ እንደ ሀገርም፣ እንደ አህጉርም የብዙዎች የኩራት ምንጭ፤ የቱሪዝም ሀብት መሆን ችሏል፡፡

እነዚህ እና መሰል ከተማንም ሀገርንም ውብ እና ጽዱ የማድረግ ተግባራት፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉ እና የተለያዩ ከተማም ሆነ ሀገር አቀፍ የሆኑ ችግሮችን እልባት በሚሰጡበት አግባብ እየተቀረጹና እየተተገበሩ ይገኛል፡፡ በዚህ በኩል፣ ከቆሻሻ አወጋገድ እና የመጸዳጃ ቤት ችግር ጋር የተያያዙ ሥራዎች ይገኙበታል፡፡

በዚህም በተለይ በከተሞች ያለውን የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ከማዘመን ጀምሮ፣ ነዋሪዎች በእንቅስቃሴ ላይ እያሉ ለሚገጥማቸው የመጸዳጃ ቤት ችግር መፍትሄ እስከ መስጠት የዘለቁ መልካም ጅምሮች ታይተዋል፡ ፡ ውጤት እየተገኘባቸውና ውብና ጽዱ አካባቢዎች ሲፈጠሩም ማየት ተችሏል፡፡

ይሁን እንጂ እንደ ሀገር ካለን ከፍ ያለ ስምና ዝና፤ እንደ አዲስ አበባም ከፍ ያለ የዲፕሎማቲክ መዲናነት፤ ይሄን መልካም ጅምር ማላቅና ኢትዮጵያንም ንጹህ ማድረግ፤ አዲስ አበባንም እንደ ዲፕሎማቲክ መዲናነቷ ማስዋብና ለነዋሪዎቿም፣ ለእንግዶቿም ማራኪ ማድረግ የተገባ ነው፡፡

በዚህ ረገድ እንደ ቀደሙት ድንቅ አፈጻጸም እንደታየባቸው ውጥኖች ሁሉ፤ አዲስ አበባን ውብና ማራኪ፣ ኢትዮጵያንም ጽዱና ለዜጎቿ የምትመች ለማድረግ የ“ጽዱ ኢትዮጵያ” ፕሮጀክት ንቅናቄ ተጀምሯል፡፡ ይሄ ፕሮጀክት ደግሞ ከተሞችን ንጹህና ውብ በማድረግ ለነዋሪዎቻቸው የተመቹ በማድረግ ሂደት ውስጥ፤ ኢትዮጵያን በልኳ የሚገልጽ የንጽህና መልክ ማላበስን ግቡ ያደረገ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ይሄ ታላቅ ውጥን በመንግሥት አቅም ብቻ ከዳር የሚደርስ አይደለም፡፡ ይልቁንም የሁሉንም ዜጎች ትብብርና ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው፡፡ ይሄንኑ እውነት የተገነዘቡ ቅን ኢትዮጵያውያንም ንቅናቄውን እየተቀላቀሉ ናቸው፡፡ ይሄ ደግሞ ከዜጎች የሚጠበቅ መልካም ተግባር ነው፡፡ በመሆኑም በቀጣይ ቀናት ይሄንኑ ”ፅዱ ጎዳና – ኑሮ በጤና” ቴሌቶንን በመቀላቀል፣ ፅዱ ኢትዮጵያን እውን የማድረግ ኃላፊነታችንን እንወጣ!!

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You