በሕፃናት አስተዳደግና ሰብዕና ቀረጻ ላይ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ

እያንዳንዱ ሰው ወደዚች ምድር በሚመጣበት የእንግድነት ዘመኑ ከለቅሶ ያለፈ እራሱን የሚገልጽበት ድምጽ/ቋንቋ የለውም፤ በተለይም ከሁለት እስከ ሦስት ዓመት እድሜው እሳትና ውሃን እንኳን ለይቶ አያውቃቸውም። ሰው ሙሉሰው በሚባል ደረጃ ላይ የሚደርሰው ከሕፃንነቱ ጀምሮ በወላጆቹና በአካባቢው ማህበረሰብ ድጋፍና ክትትል እየተደረገለት እያንዳንዱን ዝግመተ ለውጥ አልፎ ክፉና ደጉን ለመለየት በሚያስችል ቁመና ላይ ሲደርስ ወይም እርሱም እንደ ወላጆቹ ለኃላፊነት ሲበቃ ነው።

በሕፃናት አስተዳደግና ሰብዕና ቀረጻ ሂደት ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ቤተሰብ ነው ቢባልም ትምህርት ቤቶችና የአካባቢው ማህበረሰብም የየራሳቸው ድርሻ አላቸው። እነዚህ ሦስት ባለድርሻዎች ሕፃናት ወደ ሙሉ ሰውነት በሚያደርጉት ጤናማም ሆነ ጤናማ ያልሆነ ሽግግር ውስጥ ዐሻራቸውን ማሳረፋቸው የማይቀር በመሆኑ በልጆች አስተዳደግ ወይም በሚይዙት ሰብዕና ተወዳሽም ተወቃሽም መሆናቸው የማይቀር ነው።

የሕፃናት አዕምሮ የጻፉበትን ሁሉ የሚቀበል ነጭ ወረቀት ነው የሚል ተለምዷዊ አባባል አለ። አባባሉ እውነት ነው። ሕፃናት እድሜያቸው ለአቅመ ትምህርት ከደረሰ በኋላ ያዩትን ወይም የሰሙትን መጥፎም ይሁን ጥሩ ነገር በአዕምሯቸው መዝግበው የመያዝ ተሰጥኦ አላቸው። ገና ክፉና ደጉን መለየት የሚያስችል እድሜ ላይ ባለመድረሳቸው ጉዳትና ጥቅሙን አያመዛዝኑም። የሚስፈልጋቸውን ብቻ ወስደው የማያስፈልጋቸውን የመተው ልምድ የላቸውም። ይልቁንም የሰሙትን እና ያዩትን ሁሉ አግበስብሰው ለመያዝ ይሞክራሉ እንጂ።

ታዲያ የወላጅ፣ የጎረቤት፣ የመምራን ወይም የታላላቆቻቸው ድጋፍና እገዛ የሚያስፈልጋቸው በዚህን ጊዜ ነው። ይሄ ጥሩ ነው ቀጥሉበት፤ ይሄ መጥፎ ነው፤ አይጠቅማችሁም ተውት፤ እያለ ቀናውን ሁሉ የሚያመላክታቸውና ክፉውን አቅጣጫ የሚያስተዋቸው መንገድ መሪ ያስፈልጋቸዋል። ከጥንት ጀምሮ ትውልድ ያለፈበት መንገድም ይሄው ነው። በየዘመኑ ‹‹ሀይ የዛሬ ልጆች!›› እየተባልንም ቢሆን ለዘመናት ያሳለፍነው የሕፃናት አስተዳደግ ባህላችን ይህንን መንገድ የተከተለ እንደነበር በተለይም በእድሜ ከፍ ያልን ሰዎች የምናውቀው ሐቅ ነው።

ሕፃናት ልክ እንደ ችግኝ ናቸው። ችግኝ እንክብካቤና ክትትል ይፈልጋል፤ ከለላና ጥበቃ ይደረግለታል፤ ውሃ ይጠጣል፤ ጎብጦ እንዳያድግም ይቃናል። ሕፃናትም እንዲሁ ናቸው፤ እንክብካቤን ይሻሉ፤ በተለይም ሰብዕናቸው የተበላሸ እንዳይሆን ገና በለጋ እድሜያቸው በምክር፣ በተግሳጽ አንዳንዴም በቁንጥጫ ፈር እንዲይዙ ይደረጋል። በእያንዳንዱ ዘመን ያለ ልጅ በአባቶቹ እግር ተተክቶ የሀገሩ ተረካቢ እንዲሆን በሥነ-ምግባር ተኮትኩቶ የማደጉ ጉዳይ ዘመናትን ተሻግሮ የመጣ ነው። ወደፊትም መቀጠል ያለበት ነው።

ዛሬ ሕፃናት በተለይም የእጅ ስልኮች ተጠቃሚ መሆን በመጀመራቸው ድሮ ከምናውቀው ከዚያ የአስተዳደግ ሥርዓት እና ከማህበራዊ አውዱ በመጠኑም ቢሆን አፈንግጠው የሚያድጉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። የእጅ ስልክ መያዙም ይሁን ሌላ ቴክኖሎጂን መጠቀሙ ዘመናቸው ለእነርሱ ያበረከተላቸው አንዱ እድል ሊሆን ይችላል፤ እርግጥ ነው ልጆችን ከተቀረው ዓለም ጋር አብረው እንዲራመዱና ለነገሮች አዲስ እንዳይሆኑ ከቴክኖሎጂዎች ጋር ማላመዱ ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም። ዋናው ጉዳይ ግን ያገኙትን የቴክኖሎጂ እድል በወጉ ወይም በኃላፊነት የሚጠቀሙ ስለመሆናቸው ምን ያህል እርግጠኞች ነን? የሚለው ነው።

ባለንበት ዘመን አብዛኛዎቹ ታዳጊዎች የእጅ ስልኮች ላይ አቀርቅረው ማሳለፍን ስለሚወዱ ከሰዎች ጋር ያላቸውን ተግባቦት ቀንሰዋል። በዚህም ስለሀገራቸውና ስለባህላቸው ከአያቶቻቸው፣ ከወላጆቻቸውና ከታላላቆቻቸው የሚያገኟቸውን ጠቃሚ ምክሮች አጥተዋል። በምትኩ በማህበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ እና እነርሱን የማይመጥኑ ጸያፍ አባባሎችን እያዳመጡና ምስሎችን እያዩ ከሀገራቸው እሴቶች ላፈነገጡ መጥፎ አስተሳሰቦችና ባህሪዎች ተጋላጭ ሆነዋል።

ያለንበት ዘመን ዓለም ወደ አንድ መንደር የተሰባሰበችበት ነው። ለዚህም ትልቁን ሚና የተጫወተው የኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ነው። ዛሬ በግለሰብ ደረጃ ከአንዱ የዓለም ጠርዝ ወደ ሌላው የዓለም ጠርዝ በማይክሮ ሰከንድ ውስጥ የድምጽና የምስል መረጃ ተደራሽ መሆን ይችላል። እንደፌስ ቡክ ፣ቴሌግራም፣ ቲዩተር፣ ዩቲዩብ፣ ቲክቶክ፣ የመሳሳሉትና ሌሎቹም የማህበራዊ ሚዲያ መተግበሪያዎች ይህን ሚና ለመወጣት ጥቅም ላይ ውለዋል።

በእነዚህ መተግበሪያዎች አማካኝነት በርካታ ቁም ነገሮች መተላለፋቸውን አንክድም። አስተማሪና አዝናኝ መረጃዎች ተደራሽ ሆነዋል፤ አዳዲስ ግኝቶች ተዋውቀዋል፣ ችግረኞች ተጎብኝተዋል፤ ግብይቶች ተፈጽመዋል፤ በአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ሳይንሳዊ ሁነቶች ተንሸራሽረዋል፤ በዚህ ሂደትም የሰዎች የመፍጠር አቅም አድጓል።

ማህበራዊ ሚዲያዎች እንደተባለውም ዓለምን ወደ አንድ መንደር ያሰባሰቡ ናቸው፤ የአንዱን ሀገር ባህልና አሠራር ለሌላው ሀገር የማስተዋወቅ ሚናቸውም የጎላ ነው። ይሁንና የአንዱ ሀገር ባህል ከሌላው ሀገር ባህል ጋር ሊጋጭ የሚችልበት አጋጣሚ ሰፊ ነው። አንዳንድ ቁጥጥር የማይደረግባቸውና ልቅ ሆነው ትውልድን ልቅ የሚያደርጉ ማህበራዊ ሚዲያዎች ከሚያበረክቱት አስተዋጽኦ በላይ በትውልድ ሥነ-ምግባር ቀረጻ ላይ የሚያሳድሩት ተጽእኖ የከፋ ሊሆን ይችላል።

በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያሉና የራሳቸው ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴት ያላቸውን ሀገራት ማህበራዊ መዋቅር ከመጉዳትና ከማፍረስ አንጻር አሉታዊ ግጽታ አላቸው። በተለይም ሕፃናት በሀገር በቀል ወግና ሥርዓት ተገርተው እንዳያድጉ፤ ከሀገራቸው እሴት ያፈነገጡ አስተምህሮዎችን እንዲከተሉ ተጽዕኖ ሊያሳድሩባቸው ይችላሉና ነው። ይህ ደግሞ በተግባርም ጭምር የታየ ነው። ልጆች ከመስማትና ከማየትም አልፈው አጫጭር የቪዲዮ ክሊፖችን እየሠሩ ሲለጥፉም ጭምር ታይቷል።

የሰብስክራይበርስን ቁጥር ለማብዛት ሲሉም ከኢትዮጵያዊ ወግና ባህል ያፈነገጡ ጸያፍ ንግግሮችንና ድርጊቶችን ሳይቀር በማህበራዊ ሚዲያ ሲያስተላልፉ ተመልክተናል። ወላጆች ልጆቻቸው የሚጠቀሙትን የማህበራዊ ሚዲያ አይነትም ሊመርጡላቸውና በተገቢው መንገድ እንዲጠቀሙ አቅጣጫ ሊያመላክቷቸው ግድ ይላል።

‹‹ወፍ እንደ ሀገሯ ትጮለች›› ይባላልና ከውጪ ዓለም የምናገኛቸውን አዳዲስ እውቀቶች ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ማጣጣም ግድ ይለናል። ሕፃናት ተንቀሳቃሽ ስልክ በእጃቸው አስገብተው በባእዳን አስተሳሰብና ባህል ከመጠለፋቸው በፊት የራሳቸውን እሴት አውቀው እንዲያድጉ ማድረግ ያስፈልጋል።

ወላጆች ልጆቻቸውን በኢትዮጵያውያን እሴትና በጥሩ ሥነ-ምግባር ኮትኩቶ የማሳደግ ኃላፊነት አለባቸው። ልጆቻቸው ማገናዘብ በማይችሉበት የእድሜ ክልል ላይ እያሉ የእጅ ስልክ ገዝቶ ከመስጠት ሊቆጠቡ ይገባል፤ ስልክ መስጠት ግድ ሆኖ ከተገኘም መጠቀም ያለባቸውን እና መጠቀም የሌለባቸውን ነገር ማሳወቅ እንዲሁም አጠቃቀማቸውን መከታተልና መቆጣጠር ከወላጆች ይጠበቃል።

በአሁኑ ሰዓት አሜሪካንን ጨምሮ አንዳንድ ሀገራት የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም በሕፃናት ላይ እያሳደረ ያለውን ተጽዕኖ እየገመገሙ ይገኛሉ፤ በተለይም ‹‹ቲክቶክ›› ላይ ማእቀብ እስከ ማድረግ የደረሱ ሀገራት እንዳሉ ሲዘገብ ሰምተናል። በሀገራችንም የሕፃናትና የማህበራዊ ሚዲያ ቁርኝት ልጓም ሊበጅለት ይገባል።

በተለይም የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በዚህ ጉዳይ እልባት ሊሰጥ ይገባል፤ ወላጆች ልጆቻቸው የማህበራዊ ሚዲያ ሱሰኛ ሆነው ከኢትዮጵያዊ ወግ ልማዳቸውና ባህላቸው እንዳያፈነግጡና መልካም ሥነ-ምግባር ተላብሰው እንዲያድጉ ኃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል እንላለን።

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You