የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በቅርቡ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታ ወቀው፤ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይና በአዲስ አበባ ከተማ በተከተሰተ የኮሌራ ወረርሽኝ አስከአሁን የተያዙ ሰዎች ቁጥር 525 የደረሰ ሲሆን፣ 8 ሰዎች በዚሁ በሽታ ምክንያት ህይወታቸው ማለፉን አስታውቋል። ለኮሌራ ወረርሽኝና ለተፈናቀሉ ወገኖች የጤና ምላሽ ለመስጠት 206 ያህል የጤና ባለሞያዎች ተመድበው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 72 የጤና ባለሞያዎች ለኮሌራ ወረርሽኝ ምላሽ አገልግሎት እየሰጡ ናቸው።
ከመጋቢት ወር ጀምሮ አስከአሁን ድረስ በአጠቃላይ 847 ባለሞያዎች ተመድበው እንዲሠሩ መደረጉንም ኢንስቲትዩቱ ያመለከተ ሲሆን፤ በዘጠኝ ሳምንታት ውስጥ ለኮሌራ ምላሽና ለተፈናቀሉ ወገኖች የጤና ምላሽ ለመስጠት 134 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን ገልጿል፡፡
መጪውን የክረምት ወቅት ተከትሎ በተለይም በጎርፍ ምክንያት የውሃ መበከል ሊያጋጥም ስለሚችል በሽታው በቀላሉ ከሰው ወደሰው ሊተላለፍና ሊስፋፋ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው የጤና ባለሞያዎች ይናገራሉ። ህብረተሰቡ በኮሌራ በሽታ እንዳይጠቃ ምን ዓይነት ቅድመ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትና በሽታው ከተከሰተ በኋላም ምን ዓይነት የመፍትሔ መንገዶችን መከተል እንደሚገባ በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች የተግባቦት ባለሞያ ከሆኑት አቶ መላኩ አበበ ጋር አዲስ ዘመን ጋዜጣ ያደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርቦታል፡፡
አዲስ ዘመን፡– የኮሌራ በሽታ እንዴት ይከሰታል?
አቶ መላኩ አበበ፡– በሽታው በአብዛኛው የሚከሰተው በግልና በአካባቢ ንፅሕና ጉድለት ነው፡፡ በተለይም እጅ ብዙ ነገሮችን ስለሚነካካ ወደ አፍ በሚደርስበት ጊዜ የበሽታውን የመከሰት ዕድል ከፍ ያደርገዋል፡፡ ቫይብሪዮ ኮሌራ /Vibrio cholera/ የተሰኘው የኮሌራ አምጪ ተህዋሲያን ከምግብ ጋር አብሮ ወደ አንጀት ይገባል፡፡ ይህም የአንጀት መመረዝን ያስከትላል።በዚህ ምክንያት የሚፈጠሩ መርዛማ ነገሮችን ለማስወጣት በሚል አጣዳፊና ብዛት ያለው ፈሳሽ በተቅማጥ ወይም በትውከት መልክ ከሰውነት ይወጣል፡፡ በመሆኑም በአብዛኛው በሽታው የሚከሰተው የእጅ፣ የምግብና የውሃ ንፅሕናን ባለመጠበቅ እንዲሁም ከመፀዳጃ ቤት አጠቃቀምና ከቆሻሻ አወጋገድ ችግሮች ጋር በተያያዘ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡– በኢትዮጵያ በየትኛው ምክንያት ነው የኮሌራ በሽታ የተከሰተው?
አቶ መላኩ አበበ፡– በኢትዮጵያ ለኮሌራ በሽታ አጋላጭ ሁኔታዎችና ባህሪዎች አሉ። በዋናነት የበሽታው አጋላጭ ባህሪዎች ከእጅ አስተጠጣብ፣ ከመፀዳጃ ቤት አጠቃቃም ጋር በተያያዘ የሚመነጩ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የውሃና መፀዳጃ ቤት አቅርቦት የበሽታው አጋላጭ ሁኔታዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም እነዚህ ምክንያቶች በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለኮሌራ በሽታ መከሰት አጋላጭ ሁኔታዎችና ባህሪዎች በመሆን ይጠቀሳሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡– የኮሌራ በሽታ በኢትዮጵያ እየተከሰተ ያለበት ሁኔታ እንዴት ይገለጻል?
አቶ መላኩ አበበ፡– የአጣዳፊ ተቅማጥና ተውከት ወረርሽኞች በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ተከስተዋል፡፡ አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት ከሚያመጡ ተህዋሲያን መካከል አንዱ ደግሞ ኮሌራ ነው፡፡ ይሁንና አጣዳፊ ተቅማጥና ትውክት የሚያስከትሉ /rotavirus/ ሮታ ቫይረስ፣ የአንጀት ባክቴሪያና ሌሎች በቫይረስ የሚመጡ በሸታዎችም አሉ፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ከተከሰተው አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታ ውስጥ በኮሌራ ባክቴሪያ የመጣ ተቅማጥና ትውከት መኖሩ በላብራቶሪ ተረጋግጧል፡፡
በአፍሪካ ጎረቤት ሀገራትን ጨምሮ በበርካታ ሀገራት የኮሌራ ወረርሽኝ በተዳጋጋ ይከሰታል፡፡ ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ በሽታው መከሰቱ አዲስ አይደለም፡፡ ይሁንና በሽታው ጥንቃቄ ካልተደረገበት አደገኛና ገዳይ በመሆኑ በሽታውን ለመከላከል አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡– የበሽታው አደገኛነት እንዴት ይገለፃል?
አቶ መላኩ አበበ፡– በሽታው በእጅጉ ተላላፊ ነው፡፡ ከታማሚው የሚወጣው ትውከትና ተቅማጥ በአግባቡ ካልተወገደና ተገቢው እንክብካቤ ከተደረገ በኋላ የእጅ ንፅሕናን መጠበቅ ካልተቻለ ወይም ታማሚው የተጠቀመባቸው ቁሳቁስ በንፅሕና ካልተያዙ በሽታው በቀላሉ ከሰው ወደሰው ይተላለፋል፡፡ በሸታው በእጅጉ ተላላፊ ነው ሲባል ግን በበሽታው የተያዘ ሰው ህልውና አደጋ ላይ ወድቋል ማለት አይደለም፡፡
በሽታው በሰውነት ውስጥ የተፈጠረውን መርዛማ ነገር ለማስወገድ ሲል ሰውነት በአንድ ጊዜ ብዙ ፈሳሾችን ያስወጣል፡፡ ከሰውነት ውስጥ የወጣውን ፈሳሽ መተካት ካልታቸለ ግን ብዙ የጎንዮሽ ጉዳቶችን የሚያስከትልበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ከሰውነት ውስጥ በርካታ ንጥረ ነገሮች በተለይም የልብን፣ ኩላሊትንና ሳምባን እንቅስቃሴ የሚያግዙ ንጥረ ነገሮች አብረው ስለሚወጡ ንጥረ ነገሮቹን ለመተካት ፈሳሽ በብዛት መውሰድ የግድ ይላል፡፡ በመሆኑም የበሽታው አደገኝነት የሚወሰነው በሰዎች ቶሎ የመወሰንና ያለመወሰን ጉዳይ ላይ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡– በበሽታው በተያዘ ሰው ላይ የሚታዩ ዋና ዋና ምልክቶች ምንድን ናቸው?
አቶ መላኩ አበበ፡– የበሽታው ዋና ዋና ምልክቶች ብዙ ናቸው፡፡ ቶሎ ቶሎ የሚወጣ አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት አንዱ ነው፡፡ ይህ አጣዳፊ ተቅማጥ ሲመጣ እንደ ሌሎቹ የተቅማጥ ዓይነቶች ቁርጠት፣ትኩሳትና ራስ ምታት ያለው አይደለም፡፡ በድንገትና ጊዜ ሳይሰጥ ይመጣል። ከሰውነት የሚወጣው ፈሳሽም ውሃማና ብዛት ያለው ነው፡፡
ታማሚው ከሰውነቱ የወጡ ፈሳሾችን መተካት ካልቻለ ይህን ተከትለው የሚመጡ የጎንዮሽ ጉዳቶች አሉ፡፡ እነዚህም ታማሚው ከሰውነቱ ውስጥ ፈሳሽ በመቀነሱ ምክንያት የሚመጡና የቆዳ መሸብሸብ፣ የዓይን መስርጎድ፣ የእንባ መድረቅ፣ የከንፈርና የምላስ መድረቅ ከዚህ አልፎ የሽንት ማጣት፣ ቅልጥም አካባቢ የቁርጥማት ስሜት መሰማት እንዲሁም የድካም ምልክቶች ይታያሉ፡፡ እነዚህም ታማሚው ወደከፋ ደረጃ ምን አልባትም ወደሞት እያመራ ስለመሆኑ ጠቋሚ ምልክቶች ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡– በሽታውን ለመከላከል መፍትሔው ምንድን ነው?
አቶ ማላኩ አበበ፡– በሽታውን በቀላሉ መከላከል ይቻላል፡፡ በመሆኑም በቅድሚያ ሰዎች ምግቦቻቸውን በአግባቡና በንፅህና መያዝ፣ ማብሰልና በትኩሱ መመገብ ይኖርባቸዋል፡፡ የውሃ አቃቀምን በሚመለክት ደግሞ የመጠጥ ውሃው የቧንቧ ከሆነ ውሃው የሚቀመጥበት ዕቃ በውሃ ማከሚያ የታጠበ፣ ለዝንብና ለአቧራ የተጋለጠ መሆን የለበትም፡፡ ውሃው አጠራጣሪ ከሆነም በውሃ ማከሚያ ኬሚካል በማከም ወይም በማፍላት መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ የአካባቢ ንፅህናን መጠበቅም ያስፈልጋል፡፡
እጅ በርካታ ነገሮችን የሚነካካ ከመሆኑ አኳያ ምግብ ከማዘጋጀት በፊትና ከመመገብ በፊት በሚገባ በሳሙና ሳሙና ከሌለም በአመድ ማፅዳት ይገባል፡፡ ልጆችን ከመመገብ በፊት እንዲሁም ከመፀዳጃ ቤት መልስ በተመሳሳይ እጅን በሳሙና ማፅዳት ያስፈልጋል፡፡ በበሽታው ለተያዙ ህሙማን ዕርዳታ ከሰጡ በኋላም እጅን መታጠብ ይገባል። በበሽታው የሞተ ሰው ካጋጠመም በአካባቢው የሚገኙ የጤና ባለሞያዎችን ማማከር ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን፡– በሽታውን ከመካላከል አኳያ በኢንስቲትዩቱ በኩል ምን ዓይነት እየተሠራ ነው?
አቶ መላኩ አበበ፡– ህብረተሰቡ ስለበሽታው በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው በዋናነት እየተሥራ ይገኛል፡፡ ከውሃና አካባቢ ንፅሕና ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮች እንዲቃለሉም የክልል ጤና ቢሮዎች የሚያስተባብሯቸው የህብረተሰብ ጤና ስጋቶች መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ተዘጋጅተዋል፡፡ የውሃ ማከሚያዎችና ሌሎችም በበሽታው ለተያዙ ሰዎች የሚያገለግሉ የህክምና ግብአቶችን የማሟላት ሥራዎችም እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡
በተጨማሪም በጤናው ሴክተር ላይ የሚሠሩ ሁሉም የልማት ድርጅቶችን በማስተባበር በጋራ ምላሽ የሚሰጡበት መንገድ ተመቻችቶ እየተሠራ ነው፡፡ በኢንስቲትዩቱ በኩል የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ማስተባበሪያ ተቋቁሞ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማስተባበር በሽታውን የመከላከል ሥራ እየተሠራ ይገኛል። በተጨማሪም ህብረተሰቡ መረጃ እንዲኖረው በየሳምንቱ ጋዜጣዊ መገለጫ ይሰጣል፡፡
አዲስ ዘመን፡– በሽታው ስጋት እንዳይሆን ምን ሊደረግ ይገባል?
አቶ መላኩ አበበ፡– በቀጣይ ህብረተሰቡ ለምግብነት የሚገለገልባቸው ግብአቶች በዝናብ ምክንያት በሚከሰት ጎርፍ ሊበከሉ ይችላሉ።በተመሳሳይም የምግብ ማዘጋጃ አካባቢዎችም ጥንቃቄ የጎደላቸው ከሆኑ ሊበከሉ ይችላሉ። በመሆኑም በተቻለ አቅም ለበሽታው አጋላጭ ሁኔታዎችን መከላከል ያስፈልጋል። ለጎርፍ ተጋላጭ የሚሆኑ አካባቢዎች ላይ የሚመጡ የምግብ ግብአቶችን በምግብ ማፅጃ ኬሚካሎች በሚገባ አፅድቶና አብስሎ መመገብ ይገባል፡፡
በወንዞች አካባቢ ከሚከናወኑ ህገወጥ የእንስሳት እርዶች መራቅ፣ ትምህርት ቤቶች አካባቢ ሕፃናት ምግባቸውን ከመመገ ባቸው በፊት እጃቸውን እንዲታጠቡ፣ ምግባቸው ለዝንቦችና ለአቧራ እንዳይጋለጥ ማድረግ፣ ሌሎች በሽታውን አምጭ የሆኑ መንገዶች ትኩረት እንዲያገኙ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነት ውሰድው መሥራት ይጠበቅ ባቸዋል። የባህሪ ለውጥ በማምጣት የበሽታውን አጋላጭ ሁኔታዎች መቆጣጠር ካልተቻለ በሽታው አሁንም ስጋት ሊሆን ስለሚችል በጤናው ሴክተር ላይ የሚሠሩ ባለሞያዎችም ሆኑ ሌሎች ባለድርሻ አካላት የጋራ ርብርብ ማድርግ ይኖርባቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡– ለሰጡን ሙያዊ ማብራሪያ ከልብ እናመሰግናለን!!
አቶ መላኩ አበበ፡– እኔም አመሰግናለሁ!!
አዲስ ዘመን ሰኔ 11/2011
አስናቀ ፀጋዬ