ጤናማ ዜጋና ጽዱ ከተማን የመፍጠር ጥሪ

ከኢትዮጵያ ሕግጋት አብዝተው ከሚጠቀሱ ጉዳዮች መካከል “ክልክል ነው” የሚለው ማስጠንቀቂያ አንዱ ነው፡፡ በዚህ ጥቅስ መነሻነት ብዙ ማስታዎቂያዎች እንዲያው ለደንቡ በሚመስል ሁኔታም ቢሆን የተከለከሉ ነገሮች ተለጥፈው ማየታችን የየዕለት ምልከታችን ነው፡ ፡ ከዚህ ውስጥ ደግሞ በየጥጋጥጉ ተለጥፎ የሚታየው “መሽናት ክልክል ነው” የሚለው ማስጠንቀቂያ ይጠቀሳል፡፡

በአዲስ አበባ የተለያዩ አውራ ጎዳናዎችን ጨምሮ “መሽናት በሕግ ያቀስጣል” የሚሉ ማስጠንቀቂያዎች ተለጥፈው ቢታዩም ክልከላው በተለጠፈባቸው ሥፍራዎች ጭምር ብዙዎች ሲጸዳዱ ማየት የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ መንገድ ላይ መጸዳዳትን እንደ ነውር አለመቁጠርና የመጸዳጃ ቤቶች እጥረት አንዳንዶችን በውጪ እንዲጸዳዱ ገፊ ምክንያት እንደሆናቸው ይነገራል፡፡ ይህ ደግሞ የሀገርን ገጽታ ከማበላሸት በዘለለ በርካታ ዜጎችን ለበሽታ የዳረገ ጉዳይ ሆኗል፡፡

ስለ ጽዳት ያለው ሸውራራ ግንዛቤ እንዲቃናና በቂ የሆነ መጸዳጃ ቤት ተሰርቶ ዜጎች ጤናቸው እንዲጠበቅ እንዲሁም ጽዱና አረንጓዴ ከባቢን ለመፍጠር “ጽዱ ኢትዮጵያ” የተሰኘው ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ተጀምሯል፡፡ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ በርካቶች በንቅናቄው ተሳታፊ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

ንቅናቄውን ያስጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ትኩረት ከተሰጠባቸው ነገሮች አንዱ ጽዱና አረንጓዴ ከካባቢ መፍጠር ነው፡፡ ክብር ያለው የንጽህና ባህል መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ክብር ያለው የንጽህና ባህል ማለት በተገቢው ቦታ ክብርን ጠብቆ መጸዳዳት ሲሆን፤ ለዚያ ሥርዓት ማበጀትና የመጸዳጃ ቦታ መገንባት አስፈላጊ ሥራ ነው፡፡

“ሥርዓቱን በተመለከተ በማስተማርና ህግ በማስከበር ልናመጣውና ልናሳድገው እንችላለን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የመጸዳጃ ቦታውን መገንባት ደግሞ ተጠባቂ ሥራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የግንባታውም ተግባር ቶሎ መጀመር አለበት በማለት፤ ንቅናቄው የመጸዳጃ ቤቶችን ተደራሽ ማድረግና ክብርን ጠብቆ የመጸዳዳት ባህልን ለማዳበር እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በመልካም ተግባር ላይ የሚሳተፉ ኢትዮጵያዊያን ወገኖች ከተማዋን ጽዱ፣ አረንጓዴና ውብ ለማድረግ እንዲተባበሩ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

“ይህ ንቅናቄ የሥራ እድል ይፈጥራል፡፡ ጤናችንን እንድንጠብቅ በእጅጉ ያግዛል፡፡ የኑሮ ዘዬችንን ያዘምናል፡፡ በከተማችን በርከት ያሉ የመጸዳጃ ቤቶች መገንባት ባለን መሻት የዚህ ዓላማና ሃሳብ ተጋሪ የሆናችሁ ኢትዮጵያዊያን ግለሰቦች በገንዘብ አሊያም መጸዳጃ ቤቶቹን በመገንባት ከጎናችን እንድትቆሙ እየጠየቅኩ በተባበረ ክንድ ከተማችንን እናስውብ፣ እናጽዳ የኑሮ ዘዬአችንን እንቀይር ሥልጣኔን ለልጆቻችን እናውርስ” ሲሉ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንቅናቄውን ያበሰሩት፡፡

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ እንደሚሉት፤ ባለፉት ዓመታት በጤና ሴክተር ውስጥ ሲሰራባቸው ከነበሩ ጉዳዮች ውስጥ የግልና የአካባቢ ንጽህና አንዱ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ማህበረሰቡንና የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞችን በማሳተፍ አካባቢን ጽዱ ማድረግ ከዛም አልፎ ውጪ ላይ ከመጸዳዳት ነጻ የሆኑ ወረዳዎችና ቀበሌዎች በማለት የተለያዩ ንቅናቄዎች ተደርገዋል፡፡ በተወሰነ መልኩ ለውጦች ታይተዋል፡፡ ነግር ግን በሚፈለገው ደረጃ የሚፈለገው የአካባቢ ጽዳት እንዲሁም የባህሪ ለውጥ ማምጣት አልተቻለም፡፡ ክብሩን ጠብቆ የሚጸዳዳ ዜጋ መፍጠር ላይ ሰፊ ክፍተት ተስተውሏል፡፡

የአካባቢ ንጽህና ከ50 በመቶ በላይ ለሚሆኑ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መንስዔ ነው ያሉት ዶክተር ደረጄ፤ የአካባቢ ጽዳትንና የግል ንጽህናን በመጠበቅ በርካታ በሽታዎችን፣ ሞትንና አካል ጉዳተኝነትን መቀነስ እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡ በኢትዮጵያ በርካታ በሽታዎች ከንጽህና ጋር ተያይዞ የሚመጡ ስለሆነ፤ ይህ ተግባር አሁንም በቀዳሚነት መታየት ያለበት ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን “ጽዱ ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሃሳብ የጀመሩት ንቅናቄ በተለይ ንጽህናቸው የተጠበቁ መንገዶችን እንዲኖሩ ለማድረግ፤ ዜጎች ውጭ ላይ ከሚጸዳዱ መጸዳጃ ቤቶችን በመገንባት ሰፋፊ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የተለያዩ መጸዳጃ ቤቶችን በመገንባት ማህበረሰቡን ጤናውን እንዲጠበቅ ለማድረግ ጉልህ ሚና ያለው እንደሆነም አንስተዋል፡፡

ንቅናቄው ለጤና ሴክተሩ በርካታ ጠቀሜታዎች ያሉት ነው በማለት፤ “በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንደሚባለው ንቅናቄው ጽዱ ከባቢን ከመፍጠር ባሻገር፤ ግንባታውን ለማከናወን አጋር ድርጅቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ባለሀብቶች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ሰፊው ማህበረሰብ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሀብት የሚያሰባስቡበት ብዙ ሥራዎችን መስራት እንደሚቻል ማሳያ የሚቀርብበት መልካም አጋጣሚ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ዜጎች በመንገድ ላይ ሲጸዳዳ ይስተዋላል ያሉት ዶክተር ደረጄ፤ ንቅናቄው ኩሩና ክብሩን ጠብቆ የሚጸዳዳ ዜጋ ለመፍጠር እንደሚያስችልም ጠቅሰዋል፡፡ በተለይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ በርካታ ዜጎቿ ውጭ ላይ ይጸዳዳሉ ከሚባሉት ሀገራት ተርታ ውስጥ የምትሰለፍ እንመሆኗ ንቅናቄው ይህንን በእጅጉ የሚቀንስ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡

ዶክተር ደረጄ፤ በንቅናቄው የሚሰራው ሥራ የባህሪ ለውጥ ለማምጣትና የበሽታ ምንጭን ከመቀነስ አንጻር ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ውጭ ላይ መጸዳዳት አካባቢን የሚበክልና ክብርምም የማይገልጽ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ይልቁንም መርዛማ ኬሚካሎችን በማመንጨት በሽታን በማስተላለፍ በተለይ ሕፃናትን ለችግር የሚዳርግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ንቅናቄው ለብቻው የሚቆም እንዳልሆነ፤ እንደ ሀገርም ከታሰቡ ትልልቅ ጉዳዮች ጋር ተሳስሮ የሚተገበር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ውጭ ከመጸዳዳት ይልቅ አካባቢዎችን ነጻ ማድረግ እንዲሁም አካባቢን ማጽዳት ተብሎ የተቀመጠውን እቅድ የሚደግፍ፤ በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ጋር ተመጋጋቢ የሆነ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የጽዳት ጉዳይ መንገዶች ሲሰፉ ከተሞችን ምቹና አረንጓዴ እንዲሁም ለኑሮ ተስማማሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ከሚሰሩ ኢንስትመንቶች ጋር ተሰናስሎ የሚተገበር መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በግል ደረጃ መጸዳጃ ቤት መኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ ህዝብ በሚበዛባቸው፣ ገበያ ቦታዎች፤ የትራንስፖርት ሥፍራዎችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አካባቢዎች በርካታ መጸዳጃዎችን በመገንባት ማህበረሰቡ እንዲገለገል ያደርጋል ነው ያሉት፡፡ ለዚህም የተጀመረው ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና ህዝቡ ለዚህ አቅሙ በፈቀደው መጠን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You