አሜሪካ ለዓለም ፍጻሜ መሸሸጊያ የሚውል አውሮፕላን እንዲሠራ አዘዘች

አሜሪካ ለዓለም ፍጻሜ መሸሸጊያ የሚውል አውሮፕላን እንዲሠራ አዘዘች።

የዓለማችን ልዕለ ኃያል ሀገር አሜሪካ እንደ ኑክሌር አይነት ጦርነት ቢነሳ ከአደጋ መጠበቅ የሚቻልበት አውሮፕላን እንዲሰራ ማዘዟ ተገልጿል።

እንደ ሮይተርስ ዘገባ አሜሪካ በ1970ዎቹ የተሠራ የክፉ ቀን መጠለያ አውሮፕላን የሠራች ሲሆን፤ ይህ አውሮፕላን አርጅቷል በሚል አዲስ ልዩ አውሮፕላን እንዲሠራ ስምምነት ላይ ተደርሷል።

ለክፉ ቀን ማምለጫ ይሆናል የተባለው ይህ አውሮፕላንም 13 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ይፈጃል የተባለ ሲሆን፤ ሴራ ኔቫዳ ኮርፖሬሽን የተሰኘው ኩባንያ አዲሱን አውሮፕላን እንደሚሠራው በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።

ኢ-4ቢ የተሰኘ ስያሜ ያለው ይህ አዲስ አውሮፕላን በፈረንጆቹ 2036 ላይ እንደሚጠናቀቅም ተገልጿል።

የአሜሪካ አየር ኃይል ንብረት የሆነው ይህ ልዩ የክፉ ቀን መሸሸጊያ አውሮፕላን የሀገሪቱ ፕሬዚዳንትን ጨምሮ ሌሎች ቁልፍ አመራሮች፣ ባለሙያዎች እና ሌሎች እጅግ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች እና ቴክኖሎጂዎችን ይይዛል ተብሏል።

እንዲሁም አውሮፕላኑ እንደ ኑክሌር ጦርነት፣ አውዳሚ አደጋዎች እና ሌሎች አስጊ ክስተቶች ቢከሰቱ መሪዎች በዚህ አውሮፕላን ላይ በመሆን ትዕዛዝ እና ውሳኔዎችን እንዲያካሂዱ ያገለግላልም ተብሏል።

የመሰብሰቢያ ቢሮዎች፣ የነዳጅ መሙያዎች እና የተግባቦት መሳሪያዎችም ያሉት ሲሆን፤ አሁን በሥራ ላይ ያለው የክፉ ቀን መሸሸጊያ አውሮፕላን ከ2030 በኋላ ከአገልግሎት ውጪ እንደሚሆን ተገልጿል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You