በዓለማችን በርካታ አህጉርና ዓለም አቀፍ ተቋማት አሉ። የተወሰኑት ታሪካዊ ሲሆኑ አብዛኞቹ የዘመናዊው ዓለም አስተሳሰብና አኗኗር ውጤቶች ናቸው። ከእነዚህ ዘመናዊ አስተሳሰብ፣ ርእዮትና አዝማሚያው ፀንሶ ከወለዳቸው ተቋማት መካከልም በእአአ 2009 በአራት ሀገራት (ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ እና ቻይና) በጋራ ስምምነት “ብሪክ”፤ በ2010 ደግሞ ደቡብ አፍሪካን በመጨመሩ ምክንያት “S“ን ጨምሮ ብሪክስ (BRICS) በሚል የተመሠረተው (“ብሶት የወለደው“) ድርጅት አንዱ ነው።
ኢትዮጵያም ጥቅሞቿን ሊያስጠብቁ ከሚችሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር መሥራቷን እንደምትቀጥልና ብሪክስን ለመቀላቀል በይፋ ጥያቄ ማቅረቧን አሳውቃ ነበር። ባሳለፍነው የጥምረቱ 15ኛ ጉባዔ በደቡብ አፍሪካዋ የንግድ መዲና ጆሃንስበርግ ሲካሄድ የኢትዮጵያ ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱም አይዘነጋም፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ሌሎች ሀገራትም (ግብፅ፣ ኢራን እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስና ሳውዲ አረቢያ) ተመሳሳይ ጥያቄን በማቅረባቸው ምክንያት ብሪክስን ቢቀላቀሉ ከዓላማና ተልእኮው ጋር አብረው ይሄዳሉ ተብለው በብሪክስ አመራር የታመነባቸው ሀገራት ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቶ ሙሉ የብሪክስ አባል ሆነዋል። በቅርቡም ከ40 በላይ ሀገራት ጥምረቱን ለመቀላቀል ይፋዊ ጥያቄ ማቅረባቸው ታውቋል፡፡
የሰሜን አሜሪካ እና የምዕራብ አውሮፓ የበለጸጉ ሀገራትን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ኃይል ለመቋቋም እና ለመገዳደር በዓለም ላይ በጣም ወሳኝ የሚባሉ፤ በመልማት ላይ ያሉ ሀገራትን አንድ ላይ ለማሰባሰብ በማለም፣ በሀገራት ፈቃደኝነት የተመሠረተውና ጠቅላይ መምሪያውን ሻንጋይ (ቻይና) ያደረገው ብሪክስ፣ (በአይነቱ Intergovernmental organization ነው)፡፡ ያደረገው ተቋም ለመመሥረቱ ዐቢይ ምክንያቶች ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሲሆኑ፤ ቀዳሚ ዓላማውም በአባል ሀገራት፤ በሂደትም በየትም ቦታ ኢንቨስትመንትን በማካሄድ የኢኮኖሚ አቅምን መገንባት፤ እንደ ጦር መሣሪያ እያገለገለ ካለው የዩኤስ ዶላር መገላገል ነው።
የአሜሪካ ቅጥ ያጣ የበላይነት የወለደው ነው የሚሉ ሃይላት እንዳሉ ሆነው፤ እንደ አይኤምኤፍ እና ዓለም ባንክ ያሉ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትን አሠራር የማሻሻያ መንገዶችን በአማራጭነት ለመፈለግ፤ እንዲሁም ለታዳጊ ሀገራት ምጣኔ ሀብት ድምጽ እና ውክልና ለመፍጠር ታስቦ የተቋቋመ መሆኑ የሚነገርለት ብሪክስ፣ ለዚሁ ዓላማ ይመስላል በ2014 (እአአ) በማደግ ላይ ባሉ የብሪክስ ሀገራት ውስጥ ለመሠረተ ልማት እና ለዘላቂ ልማት ፕሮጀክቶች ሀብት የማሰባሰብ ዓላማ ያለውን ‘ኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ’ (ኤንዲቢ) በ250 ቢሊዮን ዶላር አቋቁሟል። የባንኩ ትኩረት በኃይል፣ በትራንስፖርት መሠረተ ልማት፣ በውሃ አቅርቦትና እና ንጽህና አጠባበቅ፣ ዲጂታል መሠረተ ልማት፣ የአካባቢ ጥበቃ እና ማኅበራዊ መሠረተ ልማት ላይ ይሆን ዘንድ ስምምነት ላይ ተደርሷል።
ባንኩ በአሁኑ ሰአት በአባል ሀአገራቱ ውስጥ ያለውን ከፍተኛ የመሠረተ ልማት የገንዘብ አቅርቦት ክፍተት ለመፍታት በመሥራት ላይ ሲሆን፣ እስከ 2016 ብቻ ባለው ጊዜም 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ማበደር ከመቻሉም በላይ፤ እስከ 2017 (እአአ) ድረስ በአጠቃላይ በ11 ግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ መዋዕለ ነዋይ አፍስሷል።
በጎልድማን ሳክስ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ፣ ብሪታኒያዊው ጂም ኦ’ኔል ሃሳብ አመነጪነት የተፀነሰው፤ ስያሜውንም በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት የሚያስመዘግቡ ሀገራት መሆናቸውን ከወዲሁ በማመን “ብሪክስ“ ሲል የሰየመው ድርጅት ባቋቋመው ባንክ (NDB) ለአባል ሀገራት መሠረተ-ልማት ፕሮጀክቶች ገንዘብ ማበደር ላይ አጥብቆ የሚሠራ እንደ መሆኑ መጠን፤ “ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ ያቋቋሙት ባንክ “አዲስ የብድር ምንጭ“ ሊሆናት“ እንደሚችል ይታመናል፡፡
ዋና መሥሪያ ቤቱ በምሥራቅ ሻንጋይ የሚገኘውና የቀድሞዋ የብራዚል ፕሬዚደንት የሚመሩት ይህ ባንክ ከላይ የጠቀስናቸው ሀገራት “እነሆ″ ባሉት 50 ቢሊዮን ዶላር መነሻ ካፒታል እነዓለም ባንክን ለመገዳደር የተቋቋመ መሆኑ የሚነገርለት ሲሆን፤ በባንኩ ዓላማና ተልእኮ የአባል ሀገራቱ ልብ ከወዲሁ በተስፋ እንዲሞላ እያደረገ እንደሚገኝ በተከታታይ እየወጡ ያሉ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች፤ የብሪክስ መግለጫዎች ያስረዳሉ።
እንደሚታወቀው፣ ቡድን 20 (ጂ20) በ1999 (እአአ) በበለፀጉ እና በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ስብስብ ተቋቁሟል። ዓላማውም በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ነው። ብሪክስም ይህንን ዓላማ ለማክሸፍ የተቋቋመ ድርጅት ነው የሚሉ ብዙዎች ናቸው። ይህ የዚህ ጽሑፍ ጉዳይ ባለመሆኑ ልናልፈው እንችላለን።
በ2023ቱ የቡድኑ ስብሰባ ላይ ባይነገርም፤ በብራዚል እና በሩሲያ ያሉ ታዋቂ ፖለቲከኞች የዶላርን የበላይነት ለመቀነስ የብሪክስ ገንዘብ እንዲጀመር ሃሳብ አቅርበዋል። “ይቻላቸዋልን?“ የሚለው ያነጋገረ ቢሆንም፤ ፕሮፌሰር ካርሞዲ እና ሌሎች “የብሪክስ ሀገራት ኢኮኖሚ በጣም የተለያየ ስለሆነ የጋራ መገበያያ ገንዘብ መፍጠር ተግባራዊ ሊሆን አይችልም” የሚል አስተያየትን እየሰነዘሩ ነው። “ለዓለም አቀፍ ንግድ ክፍያዎች የሚውል አዲስ ምንዛሪ ለመፍጠር ወይም ለዓለም አቀፍ ንግድ የሚውል ክሪፕቶከረንሲ መፍጠር ላይ እያሰቡበት ብቻ ሳይሆን ወደ ማጠናቀቁ መድረሳቸውን የሚናገሩ ደግሞ በሌላው ወገን ይሰማሉ። እንደውም፣ እንደ አንዳንድ ውስጥ አዋቂዎች ከሆነ ጉዳዩ አልቋል፤ ተጠናቅቋል።
በአሁኑ የብሪክስ መሪ፣ በፑቲን አማካኝነት እንደ ተገለፀው፣ ዋነኛ ከሚባሉት የዓለማችን የሀገራት ስብስብ መካከል አንዷ የሆነችው፣ የብሪክስ መሥራችና አባሏ ሩሲያ ፍላጎት በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ የብሪክስን ሚና ማሳደግ፤ በባንኮች መካከል ትብብርን ማዳበር እና የብሪክስን የገንዘብ አጠቃቀም ማስፋፋት፤ እንዲሁም፣ የግብር እና የጉምሩክ ትብብርን ማበረታት ነው። ይህ ሰፋ ተደርጎ ሲተነተን ምን ማለት እንደ ሆነ ለአንባቢያን እንተወውና ወደ ሌላኛው ነጥብ እናዝግም።
መሥራች ሀገራቱ የመሠረቱትና አሁን ተጨማሪ አራት ሀገራት የተቀላቀሉት ይህ ስብስብ (ብሪክስ) በዓለም አቀፉ ፖለቲካ እና ምጣኔ ሀብት ላይ የበለጠ ተጽኖ እንደሚፈጥር ከወዲሁ የብዙዎች ፍራት፣ ስጋት እና ተስፋ እየሆነ መጥቷል። በተለይ ዶላርን ከግብይት ውጪ ለማድረግ (De-dollarization ይሉታል) De-dollarization Strategyን በመጠቀም ጥርሱን ነክሶ ያለ እረፍት እንደሚሠራም እንደዛው።
ሰሞኑን አይኤምኤፍ በ2024 3 ነጥብ 2 በመቶ በማደግ የዓለምን ኢኮኖሚ ትመራለች በማለት የተነበየላት ሀገር መሪው ፑቲን ገና በ2022 የብሪክስ አባል ሀገራት ጉባዔ በበይነ መረብ ሲካሄድ ባስተላለፉት መልዕክት፥ “የመካከለኛው ምስራቅ ቀውስ የከሸፈ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ማሳያ ነው፤ ለጋዛ ጦርነት ፖለቲካዊ መፍትሄን ለማፈላለግ የብሪክስ አባል ሀገራት ቁልፍ ድርሻ አላቸው”፤ እንዲሁም “የጋዛ ውጥረት እንዲረግብና የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ የተቀናጀ ጥረት ማድረግ አለበት፤ ለእስራኤልና ፍልስጤም ግጭት ፖለቲካዊ መፍትሄ መፈለግ ይኖርበታል፤ ለዚህም የብሪክስ አባል ሀገራት ቁልፍ ሚና አላቸው” ማለታቸው ከብሪክስ ርእዮተ-ዓለማዊ አቅጣጫ አንፃር ድርጅቱ የትኛውን እንደሚያራምድ ብዙዎች “ግልጽ ነው” በማለት ሲገልፁትም ይሰማል።
የብሪክስን አስፈላጊነትና ወቅታዊነትን አስመልክተው ከመሥራች ሀገራቱ አንዱ፣ የሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሱብራህማንያም ጃይሻንካር “ዓለም ባለብዙ መልክ ስለሆነች ባረጀው መንገድ አዲሱን አጀንዳ መፍታት አይቻልም”፤ “ከምንጋፈጣቸው ችግሮች አንዱ የምጣኔ ሀብት ጉዳይ ሲሆን ብዙ ሀገራት በጥቂቶች በጎ ፈቃድ እንዲኖሩም ሆነዋል” ብለው የነበረ መሆኑ ሆነ፤ “ሩሲያ [ብሪክስን] ከምዕራቡ ዓለም ጋር የምታደርገው ትግል አካል አድርጋ ትመለከታለች። ከዩክሬን ወረራ በኋላ የተጣለውን ማዕቀብ ለማሸነፍም ይረዳታል” የሚለው የጉዳዩ ተመራማሪዎች አስተያየትም በዚሁ ልክ ግልጽ ነውና በዚህ ጉዳይ ከዚህ በላይ መሄዱ አያስፈልግም።
ዓለማችን “ያደጉ” እና “ያላደጉ”፤ “ግራ”፣ “ቀኝ” ወዘተ ከሚባለው ጎራ ወጥታ (በከፊልም ቢሆን) “ጨፍልቀው ያደጉ” እና “በማደግ ላይ ያሉ” ሀገራት በሚሉ ምድቦች ተከፍላ እየተጠራች ትገኛለች። እነ ብሪክስም “በማደግ ላይ ያሉ” እና “ባለ ተስፋዎች” እየተባሉ ከሚገለፁት ቀዳሚዎቹ እየሆኑ ነው። (እዚህ ላይ “ያላደጉ” (አፍሪካን ለማለት ነው) የሚለው “በማደግ ላይ ያሉ” (ዴቨሎፒንግ) በሚል ከተተካ ሰንበት ያለ መሆኑን፤ ለውጡም የከባድ ፖለቲካዊና ርእዮተ-ዓለማዊ ትግል ውጤት መሆኑን ልብ ይሏል።) “ብሪክስን ተጠቅሞ ቀስ በቀስ አፍሪካ ከምዕራባውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ የባህል የሥርዓት ተፅእኖ ሙሉ በሙሉ ነፃ ለመውጣት ቀስ በቀስ አፍሪካን ሊገነባ ይችላል“ እና የመሳሰሉ አስተያየቶችም እየተሰነዘሩ ይገኛሉ። የሰሞኑ የሀገራችን ብሪክስን የተመለከቱ ውሳኔና እንቅስቃሴዎችም የዚሁ አካል ተደርገው ሊወሰዱ የሚችሉ ናቸው።
ወደ ኢኮኖሚው ዘርፍ እንምጣ፤
ሰሞኑን፣ “ከዓለም የቆዳ ስፋት 27 በመቶ በሚሸፍኑት፣ ከዓለም ሕዝብ የ42 በመቶው ባለቤት በሆኑት፣ ለጠቅላላው የዓለም ምርት 27 በመቶ ያህሉን በሚያበረክቱት፤ እንዲሁም፣ በፈጣን የምጣኔ ሀብት እድገት ላይ ከሚገኙ የዓለም ሀገራት መካከል ግንባር ቀደም በሆኑት ሀገራት ጥምረት የተመሠረተው ብሪክስ የአባል ሀገራቱ የገቢ ንግድ ከፍተኛ መሆኑ “ለወደፊት ተስፋና ተፅእኖ ፈጣሪነቱ እንደ መሠረት ድንጋይ እየተቆጠሩለት ይገኛሉ። በተለይ በምእራቡ ዓለም በኩል እነዚህን ለመድፈቅ በማሰብ ብሪክስን የማጣጣሉ ዘመቻ በስፋት እየተሄደበት መሆኑ ሌላው ለብሪክስ ተፅእኖ ፈጣሪነት በማያሻማ መልኩ ማሳያ መሆኑም እየተስተጋባ ነው።
ፈረንሳይ፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ጀርመን፣ ጃፓን፣ ጣሊያን እና ካናዳን ካካተተው ጥምረት ጂ7 (ቡድን 7) በተፎካካሪነት የቆመው፤ ሁሉም አባል ሀገራት በዙር ለአንድ ዓመት በፕሬዚዳንትነት የሚመሩት ብሪክስ “አባል ሀገራቱ በዓለም ላይ ያሉ ሸቀጦችን ወደ ሀገራቸው በማስገባት ረገድ 14 በመቶ ጥቅል ድርሻ አላቸው፤ የቻይናን የገቢ ንግድ ብቻ ብንመለከት እስከ ሁለት ትሪሊዮን ዶላር ሲደርስ፣ በጥቅሉ አምስቱ ሀገሮች ብቻ 3 ነጥብ 6 ትሪሊዮን ዶላር የገቢ ንግድ ልውውጥ “ያላቸው መሆኑ፤ በአባልነት የሚያካትታቸው የብሪክስ ሀገራት (ኢራን፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ሳዑዲ አረቢያ) 44 በመቶ የሚሆነውን ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ማምረታቸው፤ ብሪክስ ከዓለም ጂዲፒ 4 በመቶውን መያዙ የድርጅቱን አካሄድ ከወዲሁ ከባድና ተፅእኖ ፈጣሪ (potential impact) እንደሚያደርገው የብዙዎች ከግምት ያለፈ እምነት እየሆነ በመምጣት ላይ ይገኛል።
በደብሊን ትሪኒቲ ኮሌጅ የዴቨሎፕመንት ጂኦግራፈር የሆኑት ፕሮፌሰር ፓድሬግ ካርሞዲይ እንዳሉትና በጥናቶች ተጠቅሶ እንደሚታየው የብሪክስ አባል ሀገራት በሚገኙባቸው ቀጣናዎች ወሳኝ ሀገራት ናቸው፤ ይህ እንዳለ ሆኖ፣ በብሪክስ አማካኝነት አሁን ላይ ያለውን የዓለም ኢኮኖሚ ሥርዓት (dollar’s dominance) እንዲወገድ አሊያም እንዲሻሻል በመጠየቅ በደቡባዊው የዓለም ክፍል የራሷ ድምጽ ከፍ ብሎ እንዲሰማ እየሠራች ያለችው ቻይና ደግሞ የበለጠ ተፅእኖ ፈጣሪ ናት።
ከዚህ አንጻር በመልማት ላይ ያሉ ሀገራት “የበለጠ ድምጽ እና ውክልና” እንዲኖራቸው በማስፈለጉ መነሻነት ለህልውና የበቃው ብሪክስ፣ ሰሞኑን ይፋ እንዳደረገው ሁሉን ነገር ጨርሶ የራሱን ገንዘብ (BRICS currency) ይፋ ያደረገና በቅርቡ ለአባል ሀገራቱ በቀላሉ ሊያቀርብ፤ የ55 ዶላር አቻ ዋጋ 1 ብሪክስ እንደሚሆን ይፋ አድርጎ የዓለምን ነባር የኢኮኖሚክስና የገበያ ፍልስፍናና አስተሳሰብ ከስሩ በመነቅነቅ እያንጫጫው ይገኛል።
ባንኩም እአአ በ2022 መገባደጃ ላይ ለመንገዶች፣ ድልድዮች፣ የባቡር መስመሮች እና የውሃ አቅርቦት ፕሮጀክቶች 32 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ለአባል ሀገራት አቅርቧል። የመሠረተ ልማት ጉዳይ የብሪክስ ዋና ጉዳይ እንዲሆን የምትፈልገውና የደቡቡ ዓለም መሪ ድምጽ መሆን የምትሻው ቻይናም ለዚህ የባንኩ ተግባር የተከፈተ ልብ እንዳላት በተደጋጋሚ ገልፃለች።
በብሪክስ እጅ ምን አለ?
እንደ “ዶላር እማያስፈልገኝ ደረጃ ላይ ደርሻለሁ” የምትለው ቻይና እና በዓለም አቀፍ ንግድ ሂደቱ ዶላር ሀገሯ እንዳይገባ ያገደችው ሩሲያ ያሉ ታላላቅ የዓለም ኃያላን ሀገራትን ያቀፈው ብሪክስ፤ በአህጉራቸው ላይ ተጽዕኖ ያላቸውን እንደ ደቡብ አፍሪካ እና ብራዚልንም አካትቷል፤ ከአፍሪካ ቀንድም ኢትዮጵያን። ድርጅቱ ከ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ሕዝብን የሚወክል፤ ከዓለማችን የቆዳ ስፋት 30 ከመቶውን የሚሸፍን ሲሆን፤ ይህም 45 በመቶ የሚሆነውን የዓለም ሕዝብ ይይዛል። የአባላቱ ድምር ምጣኔ ሀብት ከ28 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ዶላር በላይ መሆኑ እየተነገረለት ያለው ብሪክስ፣ ከዓለም ኢኮኖሚ 28 በመቶውን፤ ከዓለም ጂዲፒ 36 በመቶ ያህሉን (G7 ሀገራት 30 በመቶ ነው ያላቸው) መሸፈኑም እንደ ትንግርት እየተነገረለት ነው።
ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርትን (በትሪሊዮን)ን በተመለከተም የተዘረዘረ አሃዝ ያለ ሲሆን፤ ቻይና 17∙96፣ ህንድ 3∙39፣ ሩሲያ 2∙24፣ ብራዚል 1∙92፣ ሳኡዲ አረቢያ 1∙92፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬተስ 0∙51፣ ግብፅ 0∙48፣ ደቡብ አፍሪካ 0∙41፣ ኢትዮጵያ 0∙31 ትሪሊዮን ዶላር እንዳላቸው የዓለም ባንክን ጠቅሰው ለንባብ ካበቁ ሚዲያዎች ለመረዳት ተችሏል።
እንደ ብሪክስ አተያይ፣ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ከ34 ትሪሊዮን በላይ እዳ ይጨፍርባቸዋል። ምእራባውያን ተብዬ አበዳሪዎች ደግሞ ከዚህ ሁሉ ትሪሊዮን ብድር ከሚገኝ ገቢ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮች መጠባበቂያን (reserves) ያከማቹ ዘንድ እድልን ፈጥሯል። ይህ መቆም አለበት። ባለ እዳ ሀገራቱም ፊታቸውን እየቀነሰና እየወረደ ከመጣው ዶላር ወደ ብሪክስ የመገበያያ ገንዘብ ያዞሩ ዘንድ ጊዜው አሁን ነው። ከሻገተው የጦርነት፣ የጣልቃ ገብነት፣ እኔ አውቅልሃለሁ ባይነት፣ ዘር ማጥፋት፣ አጉል የበላይነት ከተጣበቀው የቅኝ አገዛዝ ሥርዓትም እንደዛው። ይህንንም የቬኑዙዌላው ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማንዱሮ “old colonial world with wars, interventions, genocide and a superiority complex” is being replaced by “a new world with BRICS.” በማለት ከገለፁት ጋር መሳ ለመሳ መሆኑን በመግለፅ ሃሳባቸውን የሚያጠናክሩ ቁጥራቸው እየበዛ፣ የአባልነት ጥያቄዎቻቸውም እየጎረፈ ይገኛል።
የመጀመሪያው የድርጅቱ የመሪዎች ጉባዔ በሰኔ ወር 2009 በሩሲያ (ሴንት ፒተርስበርግ) አስተናጋጅነት የተካሄደው ብሪክስ የምዕራባውያን ሀገሮችን፣ ማለትም እንደ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እና የዓለም ባንክ ያሉ፣ እንዲሁም ለመንግሥታት ብድር የሚሰጡ “አንቱ” የተባሉ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትን መቆጣጠሩ አይቀሬ መሆኑን ከድርጅቱ አመራሮች ባለፈ የምጣኔ ሀብት ምሁራን በእርግጠኝነት አዝወትረው እየተናገሩለት ይገኛሉ።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በብሪክስ አባል ሀገራት እጅ (“ምን የሌለ ነገር አለ?“ እስኪባል ድረስ) ብዙ ነገር ያለ ሲሆን፤ የሚከተሉት ጥቂቶቹ ናቸው። “The BRICS Wealth report: Challenging the Global economic order” በሚል ርእስ ፌብሯሪ 2024 ለንባብ የበቃ ጽሑፍ እንደሚያስረዳው የድርጅቱ አባላት በከፍተኛ ደረጃ እያደጉና ሀብት እያፈሩ ሲሆን፤ እንደ አጠቃላይ ኢንቨስት ሊደረግ የሚችል (investable wealth) 45 ትሪሊዮን ዶላር ያላቸው ሲሆን፤ ሚሊየነር ባለሀብቶቹም በሚቀጥሉት 10 ዓመታት በ85 በመቶ ያድጋሉ ተብሎም ተተንብዮአል፡፡
በአሁኑ ሰአት በተለያዩ የሀብት ደረጃዎች ላይ ያሉ፤ በድርጅቱ ስር የሚገኙ ባለሀብቶች (BRICS millionaires፣ BRICS centi-millionaires እና BRICS billionaires) በርካቶች ሲሆኑ፣ ከ1 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት ማድረግ የሚችሉ 1 ነጥብ 6 ሚሊየነሮች፤ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት ማደረግ የሚችሉ 4ሺህ 716 ማካከለኛ ቢሊየነሮች፣ እንዲሁም፣ 549 ቢሊየነሮች ይገኛሉ።
እንደዚሁ ጥናታዊ ሪፖርት ባለፈው አስር ዓመት አባል ሀገራቱ በግሉ ዘርፍ በርካታ ለውጦችን እና እድገቶችን ያስመዘገቡ ሲሆን፤ ከፍተኛዋ ቻይና 92 በመቶ በማደግ 862 ሺህ 400 ሚሊየነሮችን፤ 2ሺህ 352 መካከለኛ ቢሊየነሮችን፤ እንዲሁም 305 ቢሊየነሮችን ማፍራት ችላለች። ከአባል ሀገራቱ በመጨረሻ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያም ከፍተኛ እድገትን በማስመዝገብ የነበሯትን ሚሊየነሮች በ30 በመቶ በማሳደግ ለብሪክስ ብሎክ የበኩሏን በማበርከት ላይ እንደምትገኝ ነው እየተነገረ ያለው።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም