በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የገቢ ምርቶችን ከመተካት እንዲሁም የወጪ ምርቶችን ለማምረት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ወሳኝ ሚና ከሚጫወቱት መካከል የማምረቻ መሣሪያዎች ወይም ማሽኖች ይጠቀሳሉ። ይህን በሚገባ የተረዳው መንግሥት ዘርፉ እነዚህን ማሽኖች በማሽነሪ ሊዝ አማካይነት እንዲያገኝ ለማድረግ በርካታ ተግባሮችን አከናውኗል።
የአምራቾቹን የማምረቻ መሣሪያዎች ፍላጎት ታሳቢ ባደረገ መልኩ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ እንዲሁም ከውጭ የሚገቡ ማሽነሪዎችን ለማቅረብ እየተሠራ ሲሆን፣ በተለይ የማምረቻ መሣሪያዎቹን በሀገር ውስጥ አምርቶ ለአምራቹ ማቅረብ መቻል ፋይዳው ብዙ እንደመሆኑ በዚህ ላይ በትኩረት እየተሠ ራ ነው።
የማሽነሪ አምራቾችን ለማገዝ የሚያስችል ሀገራዊ አቅም መፍጠርን ያለመ መድረክ በቅርቡ በተካሄደበት ወቅት እንደተጠቆመው፤ የገቢ ምርትን ለመተካት በሚከናወን ሥራ 30 በመቶ የነበረውን የገበያ ድርሻ ወደ 60 በመቶ ለማሳደግ ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል። የአምራች ኢንዱሰትሪው ዘርፍ በአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት /ጂዲፒ/ ያለውን ድርሻ አሁን ካለበት ሰባት በመቶ ወደ 17 በመቶ ለማሳደግም ታቅዷል።
የማምረቻ ማሽኖችን በሀገር ውስጥ እያመረቱ ለአምራቾች ማቅረብና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ በመንግሥት በኩል ታምኖበትም እየተሠራ ነው። መንግሥት የዘርፉን እቅዶች ለማሳካት ባለው ቁርጠኝነት ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ ከ32 ሺ በላይ ማሸነሪዎች ለአምራች ኢንተርፕራይዞች በሊዝ ፋይናንስ እንዲተላለፉ አድርጓል።
ይህን ሁሉ ተከትሎም እንደ ሀገር ማሽን የማምረት አቅም እያደገና ከሀገሪቱ አልፎም እንዳንድ ምርቶችን ለውጭ ገበያ መላክ መጀመሩንም የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። እውን እዚህ ሀገር ውስጥ የተመረቱ ናቸው ወይ የሚያሰኙ ማሽነሪዎች በሀገር ውስጥ እየተመረቱ መሆናቸውም ታውቋል። ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች መተካት የሚያስችል አቅም መኖሩን ያመላካቱ ለውጦች እንዳሉም አስታውቋል።
ይሁንና የሀገር ውስጥ የማምረቻ ማሽኖችን ከመጠቀም አኳያ ግን ሰፊ ክፍተት ታይቷል። ለአምራቾች በማሽነሪ ሊዝ ከተላለፉት 32 ሺ የማምረቻ ማሽኖች ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው በሀገር ውስጥ የተመረቱት። የሚገርመው ደግሞ በሀገር ውስጥ ማሽኖችን የማምረት አቅሙ በጥሩ ደረጃ ላይ ባለበት ሁኔታ ነው ይሄ እየሆነ ያለ ው።
ገቢ ምርትን በሀገር ውስጥ ለመተካት በትኩረት እየተሠራ ነው በሚባልበት ሁኔታ የሀገር ውስጥ የማምረቻ ማሽኖች ለአምራቾች ከማቅረብ ይልቅ ከውጭ የመጡት እንዲቀርቡ እየተደረገ ነው፤ ከፍተቱ ደግሞ እጅግ ሰፊ ነው። በሀገሬ ምርት እኮራለሁ በሚባልበት ሁኔታ ከውጭ ለሚመጡ ምርቶች ቅድሚያ መስጠት ሀገርን በተለያዩ መልኩ በእጅጉ ይጎዳል፤ በሌላ የውጭ ምንዛሬ ከውጭ የማምረቻ መሣሪያ ማስመጣት ለሌላ የተሻለ ልማት ሊውል የሚችል ሀብት ያባክናል።
ሥራ አጥነት በተንሰራፋበት እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ የሚጠይቁ በርካታ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ሸቀጦችና አገልግሎቶች ባሉበት እንደ ኢትዮጵያ ባለ ሀገር ሁሉንም የማምረቻ ማሽን ከውጭ ማስገባት አይቻልም። እንኳንስ የማምረቻ ማሽኖችን የማምረት በቂ አቅም እያለ አቅሙን ፈጥሮ ማሽኖችን ማም ረት የግድ ነው።
የማምረት አቅም መኖሩ ታይቷል። ይህ በሆነበት ሁኔታ ከውጭ የሚመጡ ማሽኖችን መጠበቅ እንዲሁም ለውጭ ማሽኖች ግዥ ትኩረት መስጠት የሀገሪቱን የዘርፉን እቅድም ሆነ ራእይ ለማሳካት በሚደረገው ጥረት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳርፋል።
በሀገር ውስጥ የማምረቻ ማሽኖች የማምረት አቅም ስለመኖሩ በመንግሥት በኩል ተለይቷል። መሠረታዊው ችግር ያለው በማሽነሪ አምራች ኢንዱስትሪዎችና በሊዝ ፋይናንስ ተቋማትና ማሽን ፈላጊ ኢንዱስትሪዎች መካከል ያለው ሰፊ የመረጃና ተቀናጅቶ የመሥራት ክፍተት መሆኑም እንዲሁ ታውቋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት በቅርቡ ያካሄዱት መድረክ ዋና ዓላማም በእነዚህ ተቋማት መካከል ትስስር መፍጠርና ክፍተቱን መሙላት ነው። ይህ አይነቱ መድረክ ለገቢ ምርቶች መተካቱም ሆነ ለአጠቃላይ ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ውጤታማነት ወሳኝ እንደመሆኑ ሊበረታታ የሚገባውና በቀጣይም በስፋት ሊሠራበት የሚገባ ነው።
ይህን ማድረግ ማሽነሪዎችን በሀገር ውስጥ የማምረት አቅም ይበልጥ እንዲጎለብት፣ ኢንዱስትሪዎችም ለሀገር ውስጥ ምርት ትኩረት እንዲሰጡ ያስችላል። የኢንዱስትሪዎቹ የማምረት አቅሙ ሊጨምር የሚችለው ገበያ ሲኖር እንደመሆኑ ምርቶቹን ለፈላጊዎች ለማድረስ የተያዘው ርብርብ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል።
ማሽነሪ አምራቾች፣ ማሽነሪ አቅራቢዎች እንዲሁም ገዥ አካላትን ማስተሳሰር የሚያስችሉ መድረኮችን መፍጠር አንድ ነገር ሆኖ፣ እነዚህ አካላት ምን ያህል ተሳስረው እየሠሩ ነው፤ ትስስራቸው ምን ለውጥ አምጥቷል፤ ምንስ ተግዳሮት ገጥሟቸዋል፣ ተግዳሮቶቹስ እንዴት ይፈታሉ የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ለትስስሩ መጠናከርና ውጤታማነት ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ጭምር በትኩረት መስራት ያስፈልጋል!
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም