ጊዜ ያለፈበት የነጻ አውጪ ድራማ በመሥራት ማትረፍ አይቻልም !

ጦርነት ከግጭት የፖለቲካ ትርፍ ለማጋበስ ለሚሞክሩ ለግጭት ነጋዴዎች አዋጭ፤ አትራፊ ሥራ ነው። ስውር የፖለቲካ አጀንዳ ላላቸው ኃይሎች እንደ መልካም አጋጣሚ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ለጽንፈኞች እና ለፀረ ሕዝብ ኃይሎች ደግሞ የድግስ ያህል የሚቆጠር ነው።

ለአንድ ሀገር እና ሕዝብ ግን የዕልቂትና መከራ ምንጭ ነው። እጅግ አስከፊ የሰው ሕይወት የሚበላ፤ የሀገር እና የሕዝብ ሀብት የሚያወድም ፤ ሀገር ካለችበት ከፍታ አውርዶ ዓመታትን የኋሊት የሚመልስ አውዳሚ ክስተት ነው።

እኛ ኢትዮጵውያን እንደ ሀገር በብዙ ጦርነቶች ውስጥ አልፈን ፤ እጅግ ብዙ ዋጋ እየከፈልን ዛሬ ላይ የደረስን ሕዝቦች ነን። በነጻ አውጪ ስም እራሳቸውን የሚሰይሙ “ፖለቲከኞቻችን” ልዩነቶቻቸውን በንግግር ከመፍታት ይልቅ በጠመንጃ ለመፍታት የሚተጉ ናቸው። ይህ ሁኔታ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ዛሬም የተጣበቀን የፖለቲካ ታሪካችን መጥፎ ገጽታ ነው።

በቀደመው ጊዜ በዓለም አደባባዮች ገነን የወጣንባቸውን የአክሱም እና የዛጉዌ ሥልጣኔን ያዳከመውና ያጠፋው ጦርነት ነው፤ በእነዚህ ጊዜያት የነበሩ ሥልጣኔዎች በጦርነት እንዳልነበር ባይሆኑ ዛሬ የት ልንደርስ እንደምንችልም መገመቱ ለማንም ቀላል ነው። ይህም ሆኖ ግን ዛሬም ከትናንት ስህተታችን የማንማር፤ ለእያንዳንዱ ችግራችን ጦርነትን መፍትሔ አድርገን የምንወስድ ሕዝቦች ነን።

በ21ኛው ክፍለ ዘመን ችግሮቻችን በሠለጠነ መንገድ በንግግር እና በውይይት ከመፍታት ይልቅ ጠበንጃ /ሃይልን/ እንደአማራጭ እየወሰድን ነው። ዛሬም ከትናንት ውድቀታችንና ስህተታችን አልተማርንም። እንደ ሀገር የሥልጣኔ ቁንጮ የነበርን ሕዝቦች በግጭትና ጦርነት ዳፋ ወደታች ወርደን የዓለም መሳቂያና መሳለቂያ ሆነናል። ዛሬም ከድህነት ለመውጣት ለምናደርገው ጥረት ግጭትና ጦርነት ሳንካ እየሆነበት ነው።

መቼ ይሆን ከዚህ አዙሪት የምንወጣው? መቼ ይሆን ከነጻ አውጪነት አባዜ ተላቀን በነጻ ምርጫችን የምንኖረው? መቼ ይሆን ‹‹የማን ቤት ጠፍቶ የማን ሊበጅ፣ የአውሬ መፈንጫ ይሆናል እንጂ” ከሚለው የጦርነት ሽለላ ቀረርቷችን የምንወጣው ? ፤ ሁላችንም እንደሀገር ተያይዘን እናልቃለን እንጂ ማንም አይተርፍም ከሚል ከዚህ አይነት ከንቱ ውዳሴ የምንገላገለው ?።

ሀገር የማናት ? የማን ቤት ጠፍቶ የማን ሊበጅ፤ እያልን የምንዘባበተውስ ማን ላይ ነው? ሀገርን አውድሞ፤ ሕዝብን አጥፍቶ የት ላይ ሊኖር? እንደዚህ አይነቶቹ የሚገራቸው ያጡ የጥፋት ሽለላና ቀረርቶዎቻችን መቋጫ ሊበጅላቸው ይገባል።

ጦርነት ትውልድ ያጠፋል። በጦርነት ምክንያት ሀገራቸውን ሠርተው መለወጥ የሚችሉ ወጣቶች የጦርነት ማገዶ ይሆናሉ። ለዚህ ሶሪያን፣ ኢራቅን፣ ወዘተ እንደ ማሳያ ማንሳት አያስፈልገንም ፤ ለዚህ የሚሆን የራሳችን በቂ የጦርነት ታሪክ አለን።

በቅርብ ዓመታት እንኳን ችግራችንን በንግግር መፍታት አቅቶን ባነሳነው ጠመንጃ የስንቱ ወጣት ሕይወት እንደ ቅጠል ረግፏል? ስንቷ እናት አድጎ ይጦረኛል፤ ራሱን ችሎ ይረዳኛል የምትለውን ልጇን ለጠመንጃ አረር ገብራ ብቻዋን ቁጭ ብላ በር በሩን ታያለች።

የሚያሳዝነው ከዚህ ስህተታችን ዛሬም አልተማርንም፤ ዛሬም ትርጉም አልባ ለሆኑ ጥያቄዎች በጠመንጃ ምላሽ ለማፈላለግ የሚባዝኑ፤ ባሩድ እያሸተቱ የሚያቅራሩ ፤ የጦርነት ፊሽካ ለመንፋትም እራሳቸውን የሚያዘጋጁም ጥቂት አይደሉም። በዚህም ሀገር እና ሕዝብን ብዙ ዋጋ እያስከፈሉ ነው።

እኛ ኢትዮጵውያን እንደ ሀገር ብዙ ሺ ዓመታትን አብረን የኖርን ነን ፤ ክፉ ደጉንም አብሮ አልፈናል፤ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ግለሰቦች እና ቡድኖች በፈጠሩት ግራ መጋባት ፤ በጥቂቶች የፉከራ እና ቀረርቶ ፖለቲካ የቱንም ያህል ያልተገባ ዋጋ ለመክፈል ብንገደድም ዛሬ አብረን ነን።

አሳዛኙ እውነታ እንደ ሀገር ወደ ጦርነት የምንገባባቸው ምክንያቶች አብዛኞቹ ተመሳሳይ ናቸው። የጦርነቶቻችን ምክንያቶች ከራስ ወዳድነትና ስግብግብነት ተጀምረው በዚያው የሚቋጩ ናቸው። እኔ ያልመራሁት፤ እኔ ያላዘዝኩበት ሀገር እና ሕዝብ መኖር የለበትም ከሚል እሳቤ የመነጩ ናቸው።

እንደ ሀገር እንለማለን፤ እንበለጽጋለን ከማለት ይልቅ አብረን እንለቅ የሚል የአስተሳሰብ መዛነፍ የተጠናወታቸው ናቸው። ይህ በአብዛኛው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሲመላለሱ የቆዩ አካላት የሚጋሩት፤ ዛሬም ነፍጥ አንስተው በየጫካው መሽገው የሚገኙ ቡድኖች የሚያራምዱት ነው።

እነዚህ ቡድኖች ቢመከሩ የማይሰሙ፤ ቢገሰጹ የማይገባቸው ልበ ደንዳኖች ናቸው። የሕዝብና ሀገር ጥቅም የሚባል ጉዳይ የማይገባቸው፤ ሀገርን ጥለው ብሄርና ኃይማኖትን አንጠልጥለው የራሳቸውን ጥቅም ሰርክ የሚያሳድዱ ናቸው። ነጻ አውጣኝ የሚል ሕዝብ ሳይኖር ነጻ አወጣሃለሁ ብለው እራሳቸውን የሚሾሙ፤ እታገልለታለሁ ብለው የተነሱትን ሕዝብ ሳይቀር የሚገድሉና ክብሩን የሚያዋርዱ ናቸው።

አስተሳሰባቸው ከፊውዳል ዘመን ያልተሻገረ፤ በአሸናፊነትና በተሸናፊነት ስሌት ውስጥ የሚዳክር፤ በጋራ ማሸነፍ የሚባለውን ዘመናዊ አስተሳሰብ የማያውቅ ፤ “እኔ የምኖረው እገሌ ሲጠፋ ነው” የሚል ቢሂል የተጫናቸው፤ ለዘመኑ አስተሳሰብ ባዕድ የሆኑ ናቸው።

እነዚህ የጦርነት ነጋዴዎች አደብ ማስገዛት የዚህ ትውልድ ሃላፊነት እንደሚሆን ይሰማኛል። ዘመኑ የሥልጣኔ፣ የእውቀት እና የፈጠራ ከመሆኑ አኳያ ሕዝባችን እነዚህን ከዘመኑ ጋር ተጣልተው ሀገር እና ሕዝብን ያልተገባ ዋጋ ከሚያስከፍሉ ግለሰቦች እና ቡድኖች አንቅሮ ሊተፋቸው ይገባል። ዛሬም በነጻ አውጪ ስም እንዲያሰቃዩት እና እንዲገድሉት ፤ ተስፋውን እንዲነጥቁት ሊፈቅድላቸው አይገባም።

በሕዝብ ስም መነገድና የብሄር ካባ ደርቦ ማታለል ዘመኑ ያለፈበት ፋሽን ነው። ዛሬ ሕዝብ ከሁሉም በላይ አዋቂ ነው። የሚጎዳውንና የሚጠቅመውን ያውቃል። ከዚህ ይልቅ ነጻ አውጪ ነን የሚሉ ኃይሎች መጀመርያ ከራሳቸው ደካማ አስተሳሰብ ነጻ ሊወጡ ይገባል። እራሱ ነጻ ያልወጣ ማንንም ነጻ ሊያወጣ አይችም።

በየጫካቸው ተሰግስገው ለሕዝብ ነጻነት እንታገላለን የሚሉ ኃይሎች መጀመርያ በነጻ አእምሮ ሀገር እና ሕዝብን ማስቀደም ይጠበቅባቸዋል። ኢትዮጵያ ከብሄር፤ ከሃይማኖት እና ከግል አስተሳሰብ በላይ መሆኗን ሊረዱ ይገባል።

ዓለም ሠልጥኖ በቴክኖሎጂ በሚራቀቅበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ዓለም ከመቶ ዓመት በፊት አስተናግዳ ባሰናበተችው የነጻ አውጪ፤ ድራማ የተዋጣለት ተዋንያን መሆን አይቻልም። ዛሬ ማንም ከማንም ነጻ አይወጣም። ዛሬ ሁሉም ነጻ መውጣት የሚፈልገው ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ነው። ከቻላችሁ ተባብረን ከድህነት ነጻ እንውጣ፤ ካልሆነም ተወት አድርጉን። አበቃሁ!

በእምነት

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You