‹‹በብዝሃነት የደመቀ ኢትዮጵያዊ አንድነት›› በሚል መሪ ሃሳብ ለ13ኛ ጊዜ ዛሬ በአዲስ አበባ የሚከበረው የኢትዮጵያ ብሔር፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ላለፉት ዓመታትም በተለያዩ ክልሎች መከበሩ ይታወሳል፡፡
በአገሪቱ ሲከበር የቆየው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ለበርካታ ዓመታት ትኩረት ተነፍጎት ለቆየው የሕዝቦች ባህል፣ እምነት፣ ቋንቋ እና ሌሎች እሴቶች እውቅና ለመስጠት ታስቦ የተጀመረ መሆኑን የደቡብ ክልል ፕሬስ ሰክሪቴሪያት አቶ ፍቅሬ አማን ይናገራሉ።
በዓሉ በየክልሎቹ እየተዘዋወረ ሲከበር መቆየቱ ህዝቦችን ለማስተሳሰር እና አንድነትን ለማጠናከር በመታሰቡ ነው፡፡ ያልተለመዱ እና ቀደም ሲል ያልነበሩ መስተጋብሮችን የፈጠረና በመፍጠር ላይ ያለ ነው፡፡ በአገሪቱ ያሉ ብሔር ብሔረሰቦችም በእጅጉ እያቀራረበ ይገኛል፡፡
በኢኮኖሚው ረገድም በዓሉ ትልቅ መነቃቃት የፈጠረ መሆኑን አቶ ፍቅሬ ይጠቅሳሉ፡፡ በግለሰብ ደረጃ ሲታይ በርካታ እንግዶች በዓሉን ስለሚታደሙ በመስተንግዶና ሌሎች መሰል ተግባራት የተለያዩ ድርጅቶች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡
ሰፋ ባለ መልኩ ደግሞ የእንግዶች መቀበያ፣ ስታዲየሞች ሲገነቡና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ሲሟሉ ቆይተዋል፡፡ በዚህም የአንድ ቀን በዓልን ታሳቢ በማድረግ የሚገነቡ መሠረተ ልማቶች የክልሎችን ልማት እንዲነቃቃ አብርክቷቸው የጎላ ነው፡፡ ከዚህም በዘለለ በዓሉ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ አንድምታው የጎላ ስለመሆኑ ይመስክራሉ፡፡
እንደ አቶ ፍቅሬ ገለፃ፤ በበዓሉ ወቅት ህዝቦች ባህል ተለዋውጠዋል፣ ልምድ ተቀያይረዋል፣ መግባባት ታይቷል፡፡ በዚህ ዓመት የሚከበረውም የበለጠ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ እንደሚሆን ይናገራሉ፡፡ በተለይም በአገሪቱ የተጀመረው የለውጥ ሂደት የሚጠናከርበት ፣ ኢትዮጵያዊነት በተገቢ ሁኔታ የሚገነባበት በዓል እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ይገልጻሉ፡፡
‹‹ቀደም ባሉት ዓመታት የመጣንበት ርቀት ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ብሔርተኝነት የጎላበትና ኢትዮጵያዊ አንድነት የተዘነጋበት በመሆኑ የዘንድሮው በዓል ኢትዮጵያዊ አንድነት ይበልጥ የሚታደስበት ይሆናል›› ይላሉ፡፡ ከዚህም በዘለለ እንደ አገር የተጀመረው ለውጥ በሚፈለገው መጠን ወደፊት እንዲሄድም አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡
የአማራ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሰማኸኝ አስረስ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት በበርካታ አገራዊ እውነታዎች ውስጥ ሆኖ በዓሉን ማክበር ታሪካዊ እንደሚያደርገው ይናገራሉ፡፡ በተለይ በብሄራዊ ማንነትና ኢትዮጵያዊ አንድነትን ለማጠንከር መታሰቡም ትርጉም ከፍ ያለ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
እንደ አቶ አሰማኸኝ ገለጻ፤ የበዓሉ በየዓመቱ መከበር በርካታ ፋይዳዎች የነበሩት ቢሆንም በተለይም ላለፉት 27 ዓመታት ልዩነት ላይ ብቻ ትኩረት ተደርጎ መሠበኩ ኪሳራ አስከትሏል፡፡ የልዩነት መንገዶች ተበራክተው የአንድነት መስመሮች ተዛብተዋል፡፡ በመሆኑም በዓሉን ማክበሩ እንዳለ ሆኖ አገራዊ አንድነትን እና ብሔራዊ ማንነት ሚዛኑን ጠብቆ መጓዝ እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡
በበበየጋምቤላ ክልል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጋትሏክ ዌል በበኩላቸው፤የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በየክልሉ ሲከበር በርካታ መሰረተ ልማት መከናወኑንና በየአካባቢው ልማታዊ እንቅስቃሴ ለመፍጠር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደነበረው ያስታውሳሉ፡፡ ለአብነትም አዳራሾችና የእንግዳ ማረፊያዎች ተገንብተዋል፡፡ ስታዲየምና ሌሎች በርካታ መሠረተ ልማቶች እውን ሆነዋል።
በበዓሉ ወቅት ክልሎችን የማያውቁም ክልሉን ጎብኝተዋል፡፡ ይህ ሁሉ በዓሉ ያመጣው ገፀ በረከት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ህዝቦችን በማስተሳሰር እና በማቀራረብ ረገድም ሚናው የጎላ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ በዓሉ ሲከበርም በኢትዮጵያዊ አንድነትና የጋራ እሴቶች ላይ በሚገባ መሠራት እንዳለበትም ያሳስባሉ፡፡
ክፍለዮሐንስ አንበርብር