የትራንስፖርት አገልግሎት ሥርዓቱ ሊፈተሽ ይገባል!

በአሁኑ ጊዜ የትራንስፖርት ታሪፉን የሚወሰነው የመንግሥት አካላት ናቸው? ወይስ ተራ አስከባሪዎች? የሚለው ጥያቄ ሁሌ በጭንቅላቴ ይመላለሳል። ይህን የምልበት ምክንያት ጨለምተኛ ሆኜ ወይም ሰዎችን የመኮነን አባዜ ኖሮኝ ሳይሆን በየታክሲ ተራውና በየመኪና መናኸሪያው ለተጓዦች ታሪፉን አስቀድመው የሚናገሯቸው ተራ አስከባሪዎች በመሆናቸው ነው፤ የትራንስፖርት ታሪፍ የሚወሰነው በመንግሥት አካላት ነው? ወይስ በተራ አስከባሪዎች ነው? የሚለው ጥያቄ በአዕምሮዬ እንዲመላለስ ያደረገው።

ድንገት ደፍረው ለምን? የሚሉ ተሳፋሪዎች ካሉ “ካልተስማማህ መውረድ ትችላለህ” (“ካልተስማማሽ መውረድ ትችያለሽ”) የሚለው መልሳቸውም ሁልጊዜ ተሳፋሪዎችን የሚያሸማቅቅ ነው። የሚገርመው ለምን? ያለው ተሳፋሪ የግልምጫና የስድብ ውርጅብኝ የሚጎርፍበት በሹፌሮች፣ በረዳቶችና በተራ አስከባሪዎች ብቻ እንዳይመስላችሁ፤ ከሌሎች ተሳፋሪዎችም ጭምር ነው።

ድሮ የአጭር ርቀት ታሪፍ 35 ሣንቲም፣ የረጅም ርቀት ታሪፍ 70 ሣንቲምና ከዚያ በላይ በነበረበት ጊዜ ለታክሲ ረዳቶቹ 40 ሣንቲም ወይም 50 ሳንቲም ወይም አንድ ብር ከተሰጣቸው 05፣ 15 እና 30 ሳንቲሞችን አስበው ነበር የሚመልሱት። ካልመለሱም ከተሳፋሪው የመልሱልኝ ጥያቄ ይቀርብላቸዋል።

አሁን አሁን ደግሞ በተቃራኒው በመንግሥት የተወሰነው ታሪፍ 5 ብር፣ 7ብር ከ50 ሣንቲም፣ 10 ብር እና 15 ብር ቢሆንም እንኳን በተራ አስከባሪዎቹ እና በታክሲ ረዳቶቹ ውሳኔ ከ5 ብር እስከ 7 ብር ከ50 ሣንቲም ላለው ታሪፍ የትም ቢሆን የሚከፈለው 10 ብር ነው ወይም 15 ብር ነው ስለሚባሉ መልስ ይሰጠኝ ብሎ የሚጠየቅ ተሳፋሪ የለም። ከጠየቀም የስድብ ናዳ ይወርድበታል፤ ወይም አሽሟጣጭ ይበዛበታል። የ5 ብር ታሪፍ የትም 10 ብር ነው፤ የ10 ብሩ ታሪፍ የትም 20 ብር ነው፤ የ15 ብሩ ታሪፍ የትም 30 ብር ነው በሚል እጥፍ አስከፍሎ መጫን እየተለመደ መምጣቱን ታዝባችሁ ታውቃላችሁ?

ተሳፋሪዎች አቤት ቢሉም አብዛኛውን ጊዜ ሰሚ ስለማያገኙ የተጠየቁትን ከፍለው ከመጓዝ ውጭ ምርጫ የላቸውም። በመንግሥት የተወሰነው ታሪፍ 5 ብር፣ 7ብር ከ50 ሣንቲም፣ ወይም 12 ብር ቢሆንም 2 ብር ከ50 ሣንቲም፣ 3 ብር እና 5 ብር መመለስ ክልክል እስኪመስል ድረስ መልስ የሚሰጡ ረዳቶች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው ቢባል ማጋነን አይመስለኝም።

የትራንስፖርት ታሪፍን የመንግሥት አካል የማይቆጣጠረው እስከማይመስል ድረስ ከብዙሃን ትራንስፖርት (አንበሳና ሸገር አውቶብሶች) በስተቀር አብዛኞቹ ታክሲዎችና በተለምዶ ሚኒባስ የሚባሉት ወደ መካከለኛ ርቀት የሚሄዱ መኪኖችም መንግሥት ባወጣው ታሪፍ ሳይሆን እነሱ ባወጡት ታሪፍ ነው የሚጭኑት።

የሚገርመው ደግሞ ከታሪፍ በላይ አስከፍለውም ጠጋ ጠጋ በሉ ማለትም የማይቀር ነው። አሁን አሁን አንዳንድ የብዙሃን ትራንስፖርትም (አንበሳና ሸገር አውቶብሶች) ረዳቶች ማለቴ ነው፤ አንዳንዴ መልስ የለኝም ስለሚሉ ተሳፋሪው መውረጃው ሲደርስ ጥሎላቸው ስለሚወርድ ይችን ዘዴ መጠቀም ጀምረዋል።

ጠጋ በሉ ወይም ይህን ያህል ክፈሉ ሲባሉ ለምን ብለው የሚጠይቁ ተሳፋሪዎች ካሉም ገብጋባ፤ ድሃ ከሚለው አሸማቃቂ ስድብ በላይ “ካልተስማማህ ውረድ” (“ካልተስማማሽ ውረጅ”) የሚል ማስጠንቀቂያ ስለሚከተላቸው ደፍሮ የሚከራከር ተሳፋሪም አይኖርም።

የሚገርመው ጠጋ በል ሲባል አልጠጋም የሚል ተሳፋሪ ካለም እንደመብት ስለሚቆጠር ግልምጫና የስድብ ውርጅብኝ የሚደርስበት ከተራ አስከባሪዎች፣ ከረዳቶችና ከሹፌሮች ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ተሳፋሪዎችም ጭምርም መሆኑ ነው። ከተሳፋሪዎቹ መካከልም እባካችሁ በሠላም እንሂድበት የሚለው ተስፋ አስቆራጭ ንግግርም ለረዳቶቹና አሽከርካሪዎቹ የልብ ልብ የሰጣቸው ይመስላል።

ይህን የምለው ሕግ ጠብቀው የሚያስከፍሉ መልካም ሥነ ምግባር ያላቸው ረዳቶችና በአግባቡ የሚያሽከረክሩ አሽከርካሪዎች መኖራቸውንም ሳልዘነጋ ነው። ፀሐይ እያቃጠላቸው፤ ዶፍ እየወረደባቸው፣ ውርጭና ብርዱ እያንገበገባቸው በየመንገዱ ቆመው በአግባቡ የሚቆጣጠሩ የትራፊክ ፖሊሶችና የመንገድ ትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎችም የሚዘነጉ አይደሉም።

ተሳፋሪዎች የታሪፉን ዋጋ ካወቁ ለምን ብለው መጠየቅ እንደሚችሉ ማወቅ አለባቸው። አለበለዚያ መንግሥት ለእያንዳንዱ ተሽከርካሪና አሽከርካሪ የትራፊክ ፖሊስ ወይም የትራንስፖርት ተቆጣጣሪ ማቆም እንደማይችልም መገንዘብ ይጠበቅባቸዋል።

ለዛሬ የራሴን ገጠመኖች ላውጋችሁ። አንዴ ከአውቶቡስ ተራ ወደ ቦሌ ማተሚያ ተሳፍሮ ሲሄድ የነበረ አንድ ተሳፋሪ ታሪፉ 5 ብር መሆኑን ስለሚያውቅ 10 ብር ሰጥቶ የትም 10 ብር ነው በሚል ሰበብ መልስ አልሰጠው ከሚለው ረዳት ጋር እየተጨቃጨቁ ሲጓዙ ተሳፋሪው የትራፊክ ፖሊስ አይቶ ለመንገር አንገቱን በመስኮት ብቅ ሲያደርግ 5 ብሩን ተጣድፎ የመለሰለትን አጋጣሚ አልረሳውም።

ሌላ ጊዜ ደግሞ ከቦሌ ማተሚያ እስከ ተክለሃይማኖት መንግሥት ያወጣው ታሪፍ 7ብር ከ50 ሣንቲም ቢሆንም ተሳፋሪዎች ጭቅጭቁ ስለሰለቻቸው 10 ብር እየከፈሉ ለመጓዝ እየተገደዱ ያሉበት ሁኔታ አሁንም አልተለወጠም። ያን ቀን አንድ ተሳፋሪ ከሁለት ልጆቹ ጋር ሲጓዝ 50 ብር ሰጥቶ 20 ብር ይመልስልኛል ብሎ ሲጠብቅ 5 ብር ብቻ ስለተመለሰለት ለምን ብሎ ሲጠይቅ ለአንድ ሰው 15 ብር ነው አለው ረዳቱ።

አላግባብ ከታሪፍ ውጭ ስላስከፈልከኝ የትራፊክ ፖሊስ ካየሁ ግን ስንት እንደከፈልኩ እናገራለሁ አለና ጉዟችን ቀጥለን እያለ ረዳቱ ቀድሞ የትራፊክ ፖሊስ ስላዬ የተሰጠውን 5 ብር ተቀብሎ 20 ብር ሲመልስለት በድርጊቱ ተፀፅቶ መስሎን ነበር። ነገር ግን 20 ብሩን የመለሰለት የትራፊክ ፖሊስ ስላዬ መሆኑን ሳይ በጣም አዘንኩ። እስከ መቼ ነው የሌባና ፖሊስ ጨዋታ የሚጫወቱት የሚለውም አሳሰበኝ።

እንዲሁ በተመሳሳይ ከአምቦ ወደ አዲስ አበባ ስንመጣም አንድ ተሳፋሪ በታሪፉ መሠረት ሂሳብ ሲሰጠው ረዳቱ ያስጨምራል አለው። ተሳፋሪውም ታሪፉን ስለሚያውቅ የታሪፉን ዝርዝር አሳየኝና

እጨምራለሁ እንጂ ከተወሰነው ታሪፍ በላይ አልከፍልም ስላለው አዲስ አበባ ሲደርስ ሂሳብ የተቀበለበትን አጋጣሚ አስታውሳለሁ።

እያንዳንዱ ተሳፋሪ መብቱን ማስጠበቅ ያለበት ራሱ ነው። መንግሥት በእያንዳንዱ መኪና የትራፊክ ፖሊስና የትራንስፖርት ተቆጣጣሪ ማቆም ስለማይችል መንግሥትን ብቻ ማማረርም ተገቢ አይመስለኝም። ይልቅስ እያንዳንዱ ተሳፋሪ ተባብሮ ሕገ ወጦችን መከላከል ይጠበቅበታል።

አንዱ ለትራፊክ አደጋ መንስኤ የሚሆነውም መኪናዎቹ ከአቅማቸው በላይ ስለሚጭኑ ይመስለኛል። የሚመለከተው አካልም ሁኔታው መኪናዎቹ በአቅማቸው ልክ እንዲጭኑ ለማድረግ ቁጥጥሩን ጠበቅ ማድረግ አለበት ።

በርግጥ ተሳፋሪዎች ለምን ጠጋ በሉ እንባላለን፤ ለምንስ ከታሪፍ በላይ እንጠየቃለን ብለው የማይከራከሩትም አብዛኛውን ጊዜ ሰሚ ስለሚያጡ መፍትሔ ለሌለው ነገር መጨቃጨቅ ሰልችቷቸው እንደሆነ ለመገመት ብዙም የሚቸግር አይደለም ፤ ችግሩን ለዘለቄታው ለመፍታት የሚመለከተው አካል መፍትሔ የመስጠት ግዴታ ያለበት ይመስለኛል።

በተለይ በሥራ ጉዳይ በአንድ መስመር በተከታታይ የሚመላለሱ ተሳፋሪዎች ሁሉም አሽከርካሪዎችና ረዳቶች አድመው ስለማይጭኗቸው እና ከሥራቸው ቢቀሩ ወይም ቢያረፍዱ የሚገጥማቸውን ችግር ስለሚያውቁ ከሥራ ከመቅረትና አርፍዶ ከመግባት ተጠጋግቶ ከመቀመጥና የጠየቁትን ከፍሎ ከመሄድ ውጭ ምርጫ የላቸውም።

አንዳንድ የታክሲ ተራ አስከባሪዎች እና ረዳቶችም መብታቸው እስኪመስል ድረስ ተሳፋሪዎችን ያመናጭቃሉ፤ ሲያሻቸውም ይሳደባሉ። ለዚህ ጋጣወጥ ባሕሪያቸው ሀይ የሚላቸው አካል ሊኖር ይገባል። ችግሩ የሚፈጠረው ሀይ የሚል የመንግሥት አካል በመታጣቱ ስለሆነ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እየተከታተሉ የማስተካከል ግዴታ አለባቸው።

ተሳፋሪዎችም ጠጋ በሉ ሲባሉ እና ከታሪፍ በላይ ሲጠየቁ በኅብረት ለምን ብለው መጠየቅ ይኖርባቸዋል። አለበለዚያ መንግሥት ለእያንዳንዱ መኪና የትራፊክ ፖሊስ ወይም የትራንስፖርት ተቆጣጣሪ ማቆም ስለማይችል ለሁሉም ነገር መንግሥትን ተጠያቂ ማድረግ ተገቢ አይመስለኝም። የመኪናዎች ባለቤቶችም ቢሆኑ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ፈቃድ ሲያወጡ ሕዝብን በአግባቡ ለማገልገል መሆኑን መዘንጋት የለባቸውም።

ከከተማ ውጭ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ በተለምዶ ሚኒባስ የሚባሉት መኪና አሽከርካሪዎችና ረዳቶች መኪናቸውን አቁመው የሚጠፉት ደግሞ ከተወሰነ ሰዓት በኋላ ታሪፍ ጨምረው ለመጫን ነው፤ ተሳፋሪውም ስለሚጨንቀው የጠየቁትን ከፍሎ ይሄዳል።

አሁን አሁን ተሳፋሪዎች የግድ እየሆነባቸው እንጂ መንገድ ባይሄዱ ይመርጣሉ። ምክንያቱም በአንድ በኩል ተሳፋሪው በእጁ ከያዘው ገንዘብ በላይ ስለሚጠየቅ የያዝኩት ገንዘብ ባይበቃኝስ ምን እሆናለሁ? በሚል ስጋት፤ በሌላ በኩል መኪናዎቹ ከአቅማቸው በላይ ሰውና ዕቃ ስለሚጭኑ በትራፊክ አደጋ ሕይወቴን ወይም አካሌን ባጣስ? በሚል ስጋት።

ረዳቶቹ የእግር መቆሚያ እስከማይኖር ድረስ ካልጫኑ የጫኑ ስለማይመስላቸው ሕጉን ተከትለው በትክክል የሚሠሩ የትራፊክ ፖሊሶች ካሉ እነሱን እስኪያልፉ ወይም ከመናኸሪያ እስኪወጡ ድረስ በመቀመጫ ልክ ይጭናሉ። ከመናኸሪያ ከወጡና በትክክል የሚሠሩ ፖሊሶች አለመኖራቸውን ካረጋገጡ ተሳፋሪው የእግር መረገጫ እስኪያጣ ድረስ ይጭናሉ።

መኪናው ከአቅሙ በላይ ከጫነ ለትራፊክ አደጋ ሊያጋልጥ ይችላል ብለው የሰጉ አንዳንድ ተሳፋሪዎች ሲጠይቁም ከረዳቶቹና ከአሽከርካሪዎቹ የሚሰጣቸው መልስ “ምን አገባህ” (“ምን አገባሽ”) ስለሚባሉ ደፍሮ የሚጠይቅ አይኖርም። ተሳፋሪዎቹ ደፍረው ከጠየቁም “ካልተመቸህ ውረድ” (“ካልተመቸሽ ውረጅ”) ስለሚባሉ ፈጣሪን በመማፀን ከመጓዝ በስተቀር ሌላ ምርጫ አይኖራቸውም። ለዚያውም ደግ ረዳትና ሹፌር ከገጠማቸው እንጂ ከምን አገባህ በላይ ስድብና ግልምጫም ሊከተል ይችላል።

ለመሆኑ የትራንስፖርትና የታክሲ የአገልግሎት ታሪፍ እና የተሽከርካሪውን የመጫን አቅም የሚቆጣጠረው ማን ነው? የሚለው ጥያቄ የሚያጭርብኝ ለዚህ ነው። እናንተስ ራሳችሁን ጠይቃችሁ ታውቁ ይሆን? 12 እና 14 ሰዎችን እንዲጭን የተፈቀደለት ተሸከርካሪ 18 ሰው ጭኖ 20 ካልሞላ ስለማይንቀሳቀስ በሽተኞች፣ ሕጻናት እና ነፍሰ ጡር እናቶች ሲጨነቁ ማየት የተለመደ ተግባር በመሆኑ ሌላውን ተሳፋሪም ያስጨንቃል። ወንበሩ ማስቀመጥ የሚችለው ሁለት ሰዎችን በመሆኑ ሦስተኛ ተሳፋሪ አላስቀምጥም የሚል ተሳፋሪ ካለም የሚደርስበት ግልምጫና ዘለፋ አይጣል ነው።

በታክሲው ውስጥ የተጫኑት ተሳፋሪዎች ደኅንነት ግድ ሳይሰጠው መንገድ ላይ የቆሙ ሰዎች ስላዬ ብቻ መኪናው ቆሞ እንዲጭን ምልክት የሚሠጠውን ረዳት እና መኪናውን አቁሞ የሚጭነውን አሽከርካሪ በዓይነ ሕሊናችሁ ስታስታውሱ ጨንቋችሁ አያውቅም? አንዳንድ አሽከርካሪዎችና ረዳቶች ሰዎችን አጭቀው በመጫን ስለሚሰበስቡት ገንዘብ እንጂ ለተሳፋሪዎች ደኅንነት ግድ ስለማይሰጣቸው ተሳፋሪ ባዩ ቁጥር አስቁመው ይጭናሉ።

ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ሥራውን ለማከናወን የሚተጋ የትራፊክ ፖሊስ አሽከርካሪውን ለምን ትርፍ ጫንክ ብሎ መጠየቅ ሲጀምር አማላጁ ብዙ ነው። አለበለዚያም “ሰሞኑን ዓመት በዓል ደረሰ እንዴ! ምነው አንቀዠቀዠው?” ይሄ የትራፊክ ፖሊስ ምነው ችክ አለ? ብለው የሚሳለቁ እና የሚያሽሟጥጡ ተሳፋሪዎችም ጥቂት አይደሉም።

ከታሪፍ በላይ ከፍለው የተሳፈሩ ተሳፋሪዎችን የትራፊክ ፖሊሱ ወይም የትራንስፖርት ተቆጣጣሪው ሲጠይቃቸው የሚናገሩት በትክክለኛው ታሪፍ እንደከፈሉ ነው እንጂ ከታሪፍ በላይ እንደከፈሉ አይናገሩም። አንዴ ምን ሆነ መሰላችሁ፤ ሁላችንም ተሳፋሪዎች ከታሪፍ በላይ ከፍለን እየተጓዝን ሳለ ተቆጣጣሪዎች ድንገት አስቁመው የከፈልነውን ታሪፍ ሲጠይቁን ፤ ከፊት ከተቀመጡት ሰዎች አብዛኛዎቹ በታሪፉ መሠረት እንደከፈሉ ሲናገሩ አንዲት ተሳፋሪ የከፈለችውን በትክክል ተናገረች። ከአሽከርካሪው፤ ከረዳቱና ከሌሎች ተሳፋሪዎች የወረደባት ትችትና ግልምጫ ትዝ ይለኛል።

አንዳንድ ቸልተኛ የትራፊክ ፖሊሶች ባሉባቸው አካባቢዎችም ቁጥጥሩ አነስተኛ በመሆኑ የተሽከርካሪውን የመጫን እቅምና ታሪፉን የሚጠይቁ የትራፊክ ፖሊሶች ጥቂት በመሆናቸው ሰው በሰው ላይ ተደራርቦ በመቀመጥ የሚሄድበት አጋጣሚ ብዙ ነው። እንዲህ ሲባል ግን በየመንገዱ ቆመው የትራፊክ ፍሰቱ እንዳይስተጓጎል ሥራቸውን በአግባቡ የሚያከናውኑ ትራፊክ ፖሊሶች የሉም ማለት እንዳልሆነ ግንዛቤ ይያዝልኝ።

ችግሩ የአሽርካሪዎችና ረዳቶች ብቻ ነው ብሎ መደምደምም ስህተት ይመስለኛል። ምክንያቱም አንዳንድ ተሳፋሪዎች ተሽከርካሪው አለመሙላቱን እያዩም ወደኋላ ሄደው ላለመቀመጥ ሁለት ሰው ከሚያስቀመጠው ወንበር ቀድመው ሦስተኛ ሆነው ሲቀመጡ ረዳቱ ወደ ኋላ ሄደው እንዲቀመጡ ሲጠየቃቸው ከረዳቱ ጋር ጭቅጭቅ የሚገጥሙ፤ ተሽከርካሪው ከአፍ እስከ ገደፉ መሙላቱን እያዩ ሌላ ተሳፋሪ ሦስተኛ ሆኖ እንዲቀመጥ የሚጋብዙ ካልተሳፈርን ብለው የሚታገሉ ተሳፋሪዎችም አሉ። የትራንስፖርት እጥረቱ አስገድዷቸው የሚሳፈሩትን ሳይጨምር ማለቴ ነው።

ሌሎች ተሳፋሪዎች ደግሞ ሁለት ተሳፋሪ በሚያስቀምጠው ወንበር ረዳቱ ሦስተኛ ተቀመጡ ስላላቸው ብቻ መብት ነው ብለው ስለሚያስቡ ቀድመው የተቀመጡ ሰዎችን “ጠጋ በል” ወይም “ጠጋ በይ” ብለው ካልተጠጉላቸው በግልምጫ የሚደባልቁ፤ የተሳፋሪው መብት ከማስጠበቅ ይልቅ፤ የሕገወጥ አሳፋሪዎችን ድርጊት የሚተባበሩ ተሳፋሪዎች አሉ።

በተለይ በሥራ መግቢያና መውጫ ተደራርቦ የመቀመጥ መጠኑ ይጨምራል። መንግሥት ለመንግሥት ሠራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ባያዘጋጅ ኖሮ በሥራ መግቢያና መውጫ ምን ሊፈጠር ይችል እንደነበርም አስቡት። ይህም ሆኖ ግን በሥራ መግቢያና መውጫ፤ እንዲሁም በተማሪዎች መግቢያና መውጫ ሰዓት ረጅም ሰልፍ ማየት የተለመደ ነው።

በመግቢያና በመውጫ ሰዓት መንግሥት ለመንግሥት ሠራተኞች የትራንስፖርት አገልግሎት ማዘጋጀቱ ለመንግሥት ሠራተኛው ብቻ ሳይሆን በተዘዋዋሪ የሌላውንም የትራንስፖርት ችግር ፈትቷል ማለት ስለሚቻል በዚህ ዘመን ከተሠሩት መልካም ሥራዎች ውስጥ ይህ ተግባር መንግሥትን ከሚያስመሰግኑት ውስጥ ይመደባል።

ከመሸ በኋላ ለመንቀሳቀስ የፈለገ ተሳፋሪ በኪሱ ተጨማሪ ገንዘብ ስለመያዙ እርግጠኛ መሆን አለበት፤ በቂ ገንዘብ ካልያዘ ግን ትራንስፖርት አጥቶ ለችግር ሊጋለጥ ይችላል። ለ8 ብር መንገድ 2 ብር ስለማይመለስለት 10 ብር መክፈል የተለመደ ቢሆንም በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓትና መሸት ሲል የትም 20 ብር ነው በሚለው ብሂላቸው አንድ ፌርማታ ቢሄድም እንኳን 20 ብር ካልከፈልክ ተብሎ ተሳፋሪው ራሱ ባወጣው ተመን 10 ብር ልክፈል ቢል የሚሰማው የለም።

ከአዲስ አበባ ውጭ ትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጡ ውለው ማታ ማታ ወደ አዲስ አበባ መጥተው አገልግሎት የሚሠጡ ተሽከርካሪዎች ከወንበሩ ሁለትና ሦስት እጥፍ የሚበልጡ ሰዎች ቆመው እንዲሄዱ ሲፈርዱባቸው ማየትም የተለመደ ነው። እነዚህ ተሽከርካሪዎች ብዙ ተሳፋሪዎችን ስለሚጭኑ መቆሚያ እንጂ መያዣ ስለማይገኝ ተሳፋሪዎች እርስ በእርሳቸው ከወዲያ ወዲህ እየተጋፉ እና ከወንበር ጋር እየተጋጩ መሄድም የተለመደ ነው።

ቅርብ ለመውረድ በትናንሽ ኩሪሲዎች የተቀመጡ ተሳፋሪዎች አዲስ ተሳፋሪ በመጣ ቁጥር ደጋግመው ለመውረድና ለመውጣት ስለሚገደዱ መንታፊዎች በኪሳቸው የያዙትን ሞባይል እና ገንዘብ ሳይወስዱባቸው ወደ ቤታቸው ከገቡም ተመስገን ያሰኛል። በዚህ ሁኔታ የተጓዙ ተሳፋሪዎችን ከታሪፍ በላይ ማስከፈል ግን ሕሊና ቢስነት ነው።

ነፍሰ ጡር እናቶችንና ትንሽ ወፈር ያሉ ሰዎችን ሲያዩም ለእርስዎ አይመችዎትም በማለት የሚያሳፍሩ ረዳቶችም አሉ። ለምን ከተባለ እነዚህ ሰዎች ከተሳፈሩ ሁለት ሰዎችን በሚያስቀምጠው ወንበር ሦስተኛ ተሳፋሪ ማስቀመጥ አንችልም ብለው ስለሚያስቡ ነው።

መሸት ካለም “ቅርብ የትም 20 ብር ወይም 30 ብር ነው” የሚለው ማስታወቂያም የተለመደ ነው። ተሳፋሪዎች ለምን ብለው ከጠየቁ “ካልተመቸህ ውረድ” (“ካልተመሽ ውረጅ”) ይባላሉ፤ አልወርድም ብሎ መብቱን ከጠየቀም የስድብ ውርጅብኝ ይወርድታል።

ተሳፋሪዎችም በሚነሳው ጭቅጭቅ ጊዜያቸውን ላለማባከን፤ ረዳቱ ያሰባትን ሳንቲም ላለማጣት፣ ሾፌሩ ለምን ተነካሁ በሚል የሚነሳውን ጭቅጭቅ ስለሚፈሩ ዝምታን ይመርጣሉ። ጭቅጭቅ ከተነሳም ጭቅጭቁ ተውትና በሠላም እንሂድበት የሚለው ተማፅኖም ለረዳቶችና አሽከርካሪዎች የልብ ልብ የሰጣቸው ይመስለኛል።

ልጆች ይዛ የምትጓዝ እናት ልጇን ከአጠገቧ ብታስቀምጥ እንኳን ረዳቱ ገና ሲያያት ለልጅሽም ትከፍያለሽ የሚል ማስጠንቀቂያ ስለሚሰጣት መውረድ ወይም መክፈል ነው ምርጫዋ። ተሳፋሪዎች መካከል አንዱ ወንበሩ እኮ ለሁለት ሰዎች እንጂ ለሦስት ሰዎች አልተሠራም ብሎ ከጠየቀም ቅድም ስትገባ ነግሬያታለሁ ያኔ መውረድ ትችል ነበር የሚሉ ረዳቶችም አሉ።

ከዚያ በኋላ እያንዳንዱ እጁን ከአፉ ላይ ጭኖ ከመጓዝ በስተቀር የሚጠይቅ ተሳፋሪ አይኖርም። በተለይ የዘወትር ተጓዥ ከሆኑ ሁሌም እንደሚያመናጭቋቸውና እንደሚያንጓጧቸው ስለሚያውቁ ከዚህ በላይ መከራከር አይፈልጉም።

በመላ ሀገሪቱ ያለውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ በእያንዳንዱ ከተማ ያለ የትራንስፖርት ኃላፊ የአንበሳውን ድርሻ መውሰድ ቢኖርበትም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ግን የብዙ ባለድርሻ አካላትን ርብርብ የሚጠይቅ ይመስለኛል።

አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት ያለውን የትራንስፖርት ችግር ለመፍታት የከተማ አስተዳደሩ የአንበሳና የሸገር አውቶቡሶችን አሰማርቶ፣ ምልልሳቸውን ማፍጠንና እንቅስቃሴያቸውን መከታተል መፍትሔ ይመስለኛል። የዛሬን አበቃሁ ፤ቸር እንሰንብት!

ጋሹ ይግዛው (ከወሎ ሠፈር)

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You