በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ ያለው ችግር የሕዝባችንን የለውጥ ተስፋ እንዳያቀጭጭ ማድረግ ይገባል!

በሀገራችን የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት/ የመንግሥት አገልግሎት ከመቶ አስራ አምስት ዓመት በላይ እድሜ ያስቆጠረ ነው። በነዚህ ረጅም ዓመታት የተለያዩ የለውጥ ምዕራፎችን ለማለፍ የተገደደባቸው ሁኔታዎች ቢኖሩም አሁንም አገልግሎቱ በሚጠበቀው መልኩ ውጤታማ መሆን አልቻለም።

በአንድ በኩል በሀገሪቱ ወጥ የሆነ የፖለቲካ ሥርዓት፤ ከዚያም ባለፈ ሲቪል ሰርቪሱ ከፖለቲካ ነፃ ሆኖ ሥራዎችን የሚያከናውንባቸው የተመቻቸ ሁኔታ አለመኖር፤ ተጠያቂነት የሰፈነበት፣ ቀልጣፋ እና ዘመናዊ የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት በሀገር አቀፍ ደረጃ እውን እንዳይሆን ዋነኛ ተግዳሮት ሆኗል።

በተለያዩ ወቅቶች ሲቪል ሰርቪሱን ለማሻሻል/ዘመኑን እንዲዋጅ የተደረጉ ጥረቶችም ቢሆኑ በወቅታዊ ሀገራዊ ፖለቲካ ተጠልፈው፤ በመሠረታዊነት የተነሱበትን ዓላማ ሳያሳኩ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ“ እንደሚባለውም ለአገልግሎቱ ተጨማሪ ፈተና ሆነው አልፈዋል። ሀገርንም ለብዙ ብክነት ዳርገዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሳይቀር ብዙ ጫና ተደርጎባቸው፤ ከፍተኛ ሀብት የፈሰሰባቸው የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራሞች ሳይቀሩ ከፍ ባለ ሞቅታ እና መጯጯህ ቢጀመሩም፤ በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ ተጨማሪ ግርግር እና አለመረጋጋት ከመፍጠር ባለፈ ይህ ነው የሚባል ትርጉም ያለው ውጤት ማስመዝገብ አልቻሉም።

ብዙ እንደ ተባለላቸው፤ እንደ ተዘመረላቸው ሳይሆን የአንድ ወቅት ጩኸት ሆነው፤ በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ የሚፈለገውን ለውጥ ሳያስገኙ አሳዛኝ ትዝታዎችን ጥለው አልፈዋል። በአገልግሎቱ ውስጥ የነበሩ ችግሮች ለዘለቄታው ከመፍታት ይልቅ የበለጠ የሚገነግኑበትን ሁኔታ ፈጥረው አልፈዋል።

ከዚህ የተነሳም ከመቶ አስራ አምስት ዓመት በላይ እድሜ ያለው የሀገራችን የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት ራሱን በሁለንተናዊ መንገድ አዘምኖ ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ሳይችል ቀርቷል። በዚህም ዛሬም አገልግሎቱ የሕዝባችን ዋንኛ የቅሬታ ምንጭ እንደሆነ ነው።

በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ ያለውን ይህን የገነገነ ችግር ለመፍታት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል። አገልግሎቱ በተሻለ ሥርዓት፣ እውቀት፣ ክህሎት እና የሕግ አግባብ የሚመራበትን፣ በቴክኖሎጂ እየታገዘ ዘመኑን እንዲዋጅ ለማድረግ ረጅም ርቀት ተኬዷል። በዚህም ተስፋ ሰጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

ይህም ሆኖ ግን እንደ ሀገር ገብተንበት ከነበረው አስቸጋሪ ፈተና ጋር በተያያዘ አገልግሎቱን ቀልጣፋ እና ዘመናዊ ለማድረግ የተደረጉ ጥረቶች የተጠበቀውን ያህል ውጤታማ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል። እንዲያውም ተጨማሪ የችግር ምንጭ በመሆን ለውጡን ክፉኛ ሲፈታተኑ ታይተዋል።

በዚህ የለውጥ ወቅት፣ በሀገሪቱ የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት ውስጥ ኃላፊው ቢሮ የለም፣ መመሪያው አይፈቅድም፣ ሲስተም የለም፤ ወዘተ የሚሉ የተለመዱ ከትናንት ያልተሻገርናቸው ችግሮች አሉ፤ የአገልግሎት ፈላጊዎች ከበሬታ መንፈግ፣ ረጅም ሰልፍ፤ ያልተገባ እንግልት ብዙ ቦታ የሚስተዋሉ ናቸው።

በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም መመሪያ ባለመኖሩም፤ በመንግሥት የሥራ ሰዓት ባለጉዳይ ጉዳዩን የሚፈጽምለት እጥቶ ረጂሙን የመንግሥት የሥራ ሰዓት በሶሻል ሚዲል ሚዲያ ውስጥ የሚያሳልፉ የመንግሥት ሠራተኞች ቁጥር ቀላል አይደለም። እነዚህን ሠራተኞች ለአገልግሎቱ ተጨማሪ ፈተና ሆነዋል።

ሕጋዊ የቢሮ አገልግሎቶችን በእጅ መንሻ፤ ከዛም ባለፈ አስገዳጅ በሆነ ድርድር ለመፈጸም ወደ ቢሮ የሚገቡ፣ ሌብነትን ዋነኛ የቢሮ ሥራቸው አድርገው የሚንቀሳቀሱ የመንግሥት ሠራተኞችን በስፋት እንደሚታዩም ተገልጋዩ እያነሳ ነው።

ችግሮቹ አሁን ላይ መላው ሕዝባችን በብዙ ተስፋ እና መስዋዕትነት የጀመረውን ለውጥ በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈታተነ ነው። ፈጣን እና የማያዳግም ርምጃ ካልተወሰደበት፣ ለውጡን የበለጠ ስጋት ውስጥ በመጨመር ከቀደሙት ጊዜያት በከፋ መልኩ ተጨማሪ የአደጋ ምንጭ መሆኑ የማይቀር ነው።

መንግሥት ይህንን ከትናንት የተሻገረ ዛሬ ላይ ሀገር እና ሕዝብን ብዙ ዋጋ እያስከፈለ ያለ ሀገራዊ ችግር ለመፍታት የጀመራቸውን የለውጥ እንቅስቃሴዎች በላቀ ዲሲፕሊን ሊመራ ይገባል። ለእያንዳንዱ ችግር የማያዳግም ርምጃ በመውሰድ ችግሩ የሕዝባችንን የለውጥ ተስፋ እንዳያቀጭጭ ማድረግ ይጠበቅበታል!

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You