ልጓም አጥብቆ መያዝን የግድ የሚለው የሀሰተኛ መረጃዎች ስርጭት ጉዳይ…

አዲሱ ሚዲያ ለማህበረሰብ ትስስር መጠናከር ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ ምንም አይነት ጥርጥሬ ውስጥ አያስገባም። በየትኛውም ርዕሰ ጉዳይ ሰፊ መረጃን በቀላሉ ለማግኘት፣ የማህበረሰቡንም የእርስ በእርስ ግንኙነት በማሳለጥ የሃሳብ ልውውጥ እንዲሰፋ አስችሏል፤ የተራራቁ ሰዎችን አቀራርቧል፣ የተጠፋፉትንም አገናኝቷል። ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው አንጻርም ሰፊ የገበያ አብዮት ፈጥሯል።

በሌላ በኩል ደግሞ ሚዲያው ጽንፈኛ ትርክቶች በከፍተኛ ሁኔታ ገንግነው እንዲወጡ ሰፊ እድል ሰጥቷል። ሚዲያው ተገቢ አጠቃቀም እንዲኖረው ካልተደረገ አደጋው ከእስከ አሁኑም በላይ ፈታኝ እንደሚሆን በተጨባጭ ከተስተዋሉ ሁኔታዎች መገመት ይቻላል። ሆን ብሎ የተሳሳተ መረጃን ሀገርንና ሕዝብን ለሚጎዳ ዓላማ ለመጠቀም ሥራ ላይ እንዲውል እየተደረገ ያለበት ሁኔታ ሚዲያው በእርግጥም ከፍተኛ አደጋ መደቀኑን ያመላክታል።

በሚዲያው የሚሰራጨው መረጃ ሀሰተኛ ስለሆነ ብቻም አይደለም ችግሩ፣ መረጃው ከእውነተኛ ጉዳይ ላይ የተነሳ ሆኖ ግነት እየበዛበትና ለጥፋትና መሰል ተግባሮች ጥቅም ላይ እንዲውል እየተደረገ ያለበት ሁኔታ ችግሩ ምን ያህል እየተስፋፋ እንዳለ ይጠቁማል። እነዚህ ሁሉ ችግሮች አዲሱን ሚዲያ ተከትለው የመጡ ፈተናዎች ናቸው።

በአዲሱ ሚዲያ ስልቶች ውስጥ በጉልህ ከሚስዋሉት ችግሮች መካከል በባህሪው የተነሳ ሰፊው ኅብረተሰብ መረጃዎችን በጥልቀት የመገምገም፣ የመተንተን ግዴታም ኃላፊነትም እምብዛም ብዙም ስለሌለበት ለተሳሳቱ መረጃዎች ተጋላጭነቱ ሰፊ ነው።

በዚህ ምክንያት የተሳሳቱ መረጃዎችን በመቀበል፤ ጥላቻ፣ ጽንፈኝነት፣ የአጥቂ እና ተጠቂነት ድባብ እንዲጎለብት ዕድል ፈጥሯል። ይህ ችግር በማህበረሰቡ ውስጥ አለ ማለት ኢኮኖሚ ላይም ቀጥተኛ የሆነ አሉታዊ ተጽእኖ እንዲያሳርፍ ያደርገዋል። በመሆኑም ችግሩን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲቻል ቀድሞ መንቃት ኅብረተሰብንም ማንቃት የሚበጅ ይመስለኛል።

የማህበራዊ ሚዲያ የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃን የተመለከተ ሀገራዊ ሪፖርት ሰሞኑን ይፋ መደረጉ ይታወሳል። በሪፖርቱ መሰረት ባለፉት ስድስት ወራት በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በፍረጃ፣ ሰብአዊነትን በማዋረድ፣ በጭካኔ አገላለጽ፣ ጽንፍ በያዘ አገላለጽና የጋራ እሳቤዎችን በሚንድ መልኩ የጥላቻ ንግግሮች ተላልፈው ተገኝተዋል።

በስድስት ወራቱ የጥላቻ ንግግር ይዘቶች የተላለፉበት ቅርጽ በዋናነት በጽሁፍ ሲሆን፤ ይዘቶቹም በኤክስ ገጽ 66 በመቶ፣ በፌስቡክ 63 በመቶ እና በቴሌግራም 59 በመቶ በስፋት ጥቅም ላይ ውለዋል። በቪዲዮ የተሰራጩ የጥላቻ ይዘቶች ደግሞ በቲክቶክ 74 በመቶ እና በዩቲዩብ 70 በመቶ ሆነው ታይተዋል።

የተሰራጩት የጥላቻ መልዕክቶች ለአመጽና ለጥቃት የማነሳሳት፣ የግለሰብን ሰብእና የመጉዳት ይዘት ያላቸውና የማህበረሰብን ባህልና ወግ በመናድ የህዝብን አብሮ የመኖር እሴት መሸርሸርን የሚያስከትሉ መሆናቸውንም ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል።

በጥናቱ ግኝት መሠረት ለጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ ስርጭት መስፋፋት የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ጉልህ ድርሻ አላቸው:: በጥቅሉ ሪፖርት ከተደረገላቸው ውስጥ ሁለት በመቶው ብቻ ከእይታ ማገዳቸውንም ውጤቱ አሳይቷል።

ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ጥንትም በዘመናዊው ዓለምም በተለያዩ ሀገሮችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ሰነዶች ላይ በግልጽ ሰፍሮ ይገኛል። በጥንታዊ አቴንስ ከክርስቶስ ልደት በፊት በስድስተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ትኩረት ያገኘ መሰረታዊ መብት መሆኑን የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እ.ኤ.አ.1945 ዓ.ም ከተመሰረተ ጀምሮ ትኩረት ያገኘው የሰብአዊ መብት ጥበቃ፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅን መብት በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት እንዲያገኝ አድርጎታል። እ.ኤ.አ. በ 1948 የወጣው አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ድንጋጌ በአንቀፅ 19 ላይ ማንኛውም ሰው ሃሳቡን ያለገደብ በነፃነት የመግለፅና የማሰራጨት መብት እንዳለው አረጋግጧል።

እኤአ በ1966 በወጣው ዓለም አቀፉ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ድንጋጌ አንቀፅ 19 ላይ የተቀመጠው ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት አሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት ላገኘው ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት እንቅስቃሴ መሰረት ጥሏል።

ኢትዮጵያም በ1987ዓ.ም ባወጣችው ሕገመንግስቷ በአንቀጽ 29 የአመለካከትና ሃሳብን በነጻነት የመያዝና የመግለጽ መብት ሕጋዊ ማእቀፍ እንዲያገኝ አድርጋለች። መብቱ በአዋጁ ቢሰፍርም ገደብ የተጣለባቸው እንደ ጦርነት ቅስቀሳዎች፣ የወጣቶችን ደህንነትና ሰብአዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎችን ይከለክላል።

ማህበራዊ ሚዲያው መደበኛ የመገናኛ ብዙኃንን በመተካት ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ ነፃነትን ላልተገባ ተግባር አውሎታል። ዓለምን ያስተሳሰረው የቴክኖሎጂ እድገት የራሱን ችግሮች ይዞ ብቅ ብሏል። የመገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም የሚፈፀሙ የሽብርና የጥላቻ ንግግሮች የፈጠሩት ተፅእኖ ቴክኖሎጂውን ለመቆጣጠር አቅም የሌላቸውን ብቻ ሳይሆን፣ በቴክኖሎጂ የበለፀጉትንም ሀገራት ጭምር ፈተና ውስጥ ከቷል።

ይህ ችግር በተለይ በታዳጊ ሀገሮች ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ ይገኛል። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ማህበራዊ ሚዲያው ከፍተኛ የመረጃ ምንጭ ተደርጎ ስለሚቆጠር የራሱ በጎ ተጽዕኖ ቢኖረውም፣ የጥላቻና ሀሰተኛ ወሬዎችን በማሰራጨት ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል።

የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭት አዋጁ የተከለከሉ ተግባራትን በሚመለከት፤ የሌላ ግለሰብን፣ የተወሰነ ቡድንን ወይም ማህበረሰብን ብሔርን፣ ሃይማኖትን፣ ቀለምን፣ ፆታን፣ አካል ጉዳተኝነትን ዜግነትን፣ ስደተኝነትን፣ ቋንቋን፣ ውጫዊ ገፅታን መሰረት በማድረግ ሆነ ብሎ እኩይ አድርጎ የሚስል የሚያንኳስስ፣ የሚያስፈራራ፣ መድልዎ ወይም ጥቃት እንዲፈፀም የሚያነሳሳ ጥላቻ አዘል መልዕክትን በመናገር፣ ፅሁፍ በመፃፍ፤ በኪነ ጥበብ እና እደ ጥበብ፣ በድምፅ ቅጂ ወይም ቪዲዮ ብሮድካስት ማድረግን ወይም በማህበራዊ ሚዲያ ማሰራጨትን ይከለክላል።

የሐሰት መረጃን በተመለከተም የፍሬ ነገር ወይም አንኳር ይዘቱ ውሸት መሆኑን እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው፤ ሁከት ወይም ግጭት የማስነሳት ወይም ጥቃት እንዲደርስ የማድረግ እድሉ ግልፅ በሆነ መልኩ ከፍ ያለ መረጃን ሆን ብሎ በማንኛውም መንገድ ማሰራጨትና ለህዝብ እንዲደርስ ማድረግ እንደሆነ አስቀምጧል።

በበይነ መረቦችና ማህበራዊ ገፆች ላይም የተለያዩ ማህበረሰቦችን ለጥቃት የሚያነሳሱ፣ ግድያንና መፈናቀልን ሊያስከትሉ የሚችሉ መልዕክቶች በተለያዩ ጊዜያት ተላልፈዋል። የሰው ልጅ በአደባባይ የተሰቀለበት ገጠመኝን ጨምሮ ለጆሮ የሚሰቀጥጡ ዜናዎች መጥፎ ጠባሳ አሳርፈዋል። የእነዚያ መረጃዎች ራቁታቸውን መሰራጨት ሊያስከትል የሚችለውን ክፉና በጎ ሳይለዩ ለሕዝብ እንዲደርሱ ከተደረጉባቸው መንገዶች አንዱና ዋናው ማህበራዊ ሚዲያ መሆኑ ይታወቃል።

በኢትዮጵያ የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትና የጥላቻ ንግግር እያስከተለ ያለው ችግር አሳሳቢ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ድርጊቱን ለመቆጣጠርና ለመከላከል፣ የድርጊቱን ፈጻሚዎች ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል ሕግ ቢደነገግም፣ የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃዎች ስርጭቱ ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት ጠንቅ እየሆነ ነው። ድርጊቱን ተከትሎ ህይወት ጠፍቷል፣ በርካታ ዜጎች ተፈናቅለዋል፣ ለግምት የሚዳግት ንብረትም ወድሟል።

ለውጡ ያመጣውን መልካም እድል አለአግባብ መጠቀም በመስተዋሉ፣ ማህበራዊ ሚዲያውን በመጠቀም በተሰራጩ መጥፎ መረጃዎች የተነሳ በማህበረሰቡ መካከል መጠራጠር እና ፍራቻ የነገሰበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ስልጡንነት በጎደለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ በሚነዛ ከንቱ ፕሮፓጋንዳ፣ ይህንና የመሳሰሉትን በማራገብ እንጀራቸውን የጋገሩ የሚመሰላቸው አካላት የሚነዙት ሀሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ይገኛል። መረጃና ንግግርን ሳያስተውሉ የሚጠቀሙና ለሌሎች የሚያስተላልፉም እንዲሁ ችግሩ ተባብሶ እንዲቀጥል እያደረጉ ናቸው።

ይህ ሁሉ ትክክል አይደለም። ለሕዝብ የሚተላለፍ ንግግር ኢትዮጵያዊ እሴትን በተላበሰ መንገድ ሕዝብን የሚያቀራርብ እና የሚያግባባ በሆነ መልኩ መገለጽ አለበት። በንግግር ወቅትም ሆነ መረጃ በመለዋወጥ ወቅት መከባበርና መቻቻል ሊኖር ይገባል።

ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች እና የመብት አራማጆች በማህበራዊ ሚዲያ በሚያደርጓቸው የሃሳብ ልውውጦች ነፃነቱ የሚጠይቀውን ኃላፊነትና ጨዋነት ባግባቡ ካልተወጡ አሁንም ወደፊትም ቢሆን ድርጊቱ ከፍ ያለ ዋጋ ማስከፈሉ አይቀሬ ይሆናል። ለመናገር የተሰጠው ነጻነት፣ ገደብ እንዳለውም መገንዘብ ያስፈልጋል።

በመሆኑም መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ ሕግ እንዳወጣ ሁሉ በሕጉ ላይ ኅብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ እንዲይዝ ማድረግ፣ ሕጉ በሚገባ በሚተገበርበት እንዲሁም ሕጉን ተላለፈው በሚገኙትም ላይ አስተማሪ ቅጣት የሚጣልበት ሁኔታ ላይ በትኩረት መስራት ይኖርበታል። በተለይም በጉዳዩ ላይ የሕዝብ ለሕዝብ ተግባቦት እንዲኖር በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አማካይነት የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው።

ለተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎችና መልሶች በሙሉ ጥላቻንና ጥቃትን ምላሽ ያደረጉና ሃይ ባይ ያጡ መልዕክቶች ለፖለቲካዊ ቀውስ ምክንያት ሊሆኑ ስለሚችሉ እነዚህን መልእክቶች ማስተላለፍ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል። በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚተላለፉ በግድያ፣ በጦርነት፣ በዘር ማጥፋትና በመሳሰሉት የሚተላለፉ መልእክቶችን የተለመዱ ነገሮች አድርጎ መቀስቀሱ፣ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት የሚደርስባቸው መፈናቀል፣ ለሞት መዳረግ እንዲቆሙ መስራት ይገባል። በመረጃ ነፃነት አዋጅ ሰበብ መረን የወጣውን የማህበራዊ ሚዲያ አፍራሽ ተግባር በተፈጠረለት ልጓም አማካይነት አደብ እንዲገዛ ማድረግም ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆን የለበትም።

ሜሎዲ ከኳስ ሜዳ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዚያ 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You