ተቋሙ የስኬት ተምሳሌት ወደሚሆንበት ፈጣን የለውጥ ትግበራ መግባት ይኖርበታል !

አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በለውጥ ወቅት ራሳቸውን እያዘመኑ ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ይጠበቅባቸዋል። በተለይም በለውጥ ማግስት ያሉ የለውጥ መነቃቃቶችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የአገልግሎት አሰጣጣቸው ላይ የሚታዩና የሚጨበጡ ለውጦችን ማምጣት ይኖርባቸዋል። ይህን በማድረግ ውጤታማ መሆንም ከአንድ የለውጥ አመራር በቀዳሚነት የሚጠበቅ ዋነኛ ተግባር ነው።

ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተያያዘ የሕዝብ ርካታ ማጣት ለለውጥ ገፊ ከሆኑ ምክንያት አንዱ ነው። ይህንን ገፊ ምክንያት በአግባቡ ተረድቶ ፈጣን ምላሽ መስጠት፤ በለውጡ ተስፈኛ ለሆነው ሕዝብ ትልቅ የእርካታ ምንጭ ከመሆን ባለፈ፤ በለውጡ ላይ ያለውን እምነት የሚያጠነክር ፣ለለውጡ ያለውን አጋርነት የሚያጎለብት ነው።

ይህን ታሳቢ በማድረግ የለውጥ ኃይሉ ወደ ስልጣን ከመጣ ማግስት ጀምሮ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለሕዝብ ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሏቸውን የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎች ተግባራዊ እንዲያደርጉ አቅጣጭ አስቀምጧል። ለስኬታቸውም ስትራቴጂ ነድፎ ተንቀሳቅሷል።

የሥራ አካባቢን ለሥራ አመቺ ከማድረግ ጀምሮ፣ በአሰራር ሥርዓት ፣ በሰው ኃይል እና በቴክኖሎጂ የተደገፈውን የሪፎርም ሥርዓት ለመተግበር መንግሥት አስፈላጊ የሆነውን ሀብት መድቧል፤ የአመራር ለውጦችንም አድርጓል። ይህንን ተከትሎ በሕዝቡ ውስጥ ርካታን የፈጠሩ ጥቂት ሊባሉ የማይችሉ ተቋማት ተስተውለዋል።

ከዚህ በተቃርኖም፤ ከመንግሥት ለውጥ የማምጣት መነቃቃት እና ከሕዝብ የለውጥ መሻት ጋር በሚጠበቀው መልኩ አብረው መጓዝ፤ በተጨባጭ በአገልግሎት አሰጣጣቸው ላይ ተጠባቂ ለውጥ ማምጣት ያልቻሉ ተቋማት ስለመኖራቸው ለመናገር የሚከብድ አይደለም። ዛሬም አገልግሎት ፈላጊዎችን ያልተገባ ዋጋ የሚያስከፍሉ እና በለውጡ ያላቸውን ተስፋ የሚያቀጭጩ ተቋማት መኖራቸው የአደባባይ ምስጢር ነው።

ከእነዚህ ተቋማት መካከል አንዱ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ነው። አገልግሎቱ ቀደም ባለው ጊዜ በተለያዩ ችግሮች ተጠላልፎ ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ቅሬታ የነበረበት ነው። በተቋሙ ውስጥ የነበረው የገነገነ የሙስና ችግር የተቋሙን ገጽታ በብዙ መልኩ ያጠለሸ እንደነበርም ከችግሩ ጋር በተያያዘ አደባባይ የወጡ መረጃዎች የሚያመላክቱት ነው። የአዲስ ዘመን የቅርብ ጊዜ ዘገባዎችም ችግሩን ፍንትው አድርገው አሳይተዋል፡፡

በርግጥ፤ በተቋሙ ከስድስት ወር በፊት በተጀመረ የሪፎርም ሥራ፤ በመሠረታዊነት የተቋሙን አሠራር በማዘመን የተሻለ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን መሠረት መጣል ቢችልም፤ ሪፎርሙ በሚጠበቀው ፍጥነት ተግባራዊ ባለመሆን፤አሁንም የተቋሙ የአገልግሎት አሰጣጥ የዜጎች የቅሬታ ምንጭ እንደሆነ ነው።

ዜጎች ዛሬም አዲስ አበባን ጨምሮ በየከተማው ባሉ የተቋሙ ቢሮዎች የፓስፖርት አገልግሎት ለማግኘት እንግልት ይደርስባቸዋል። ከሌሊቱ አስር ሰዓት ጀምሮ ብርድ ፣ ፀሐይ እና ዝናብ እየተፈራረቀባቸው ወረፋ መጠበቅ ይኖርባቸዋል። ከዚህም ባለፈ የፀጥታ አስከባሪዎች ወከባ እልፍ ሲልም ዱላ ይጠብቃቸዋል።

መንግሥት በሕጋዊ የውጪ ሀገር የሥራ ስምሪት ዜጎች ራሳቸውን ፣ ቤተሰባቸውን እና ሀገራቸውን የሚጠቅሙበት የተመቻቸ ሁኔታ እየፈጠረ ባለበት አሁናዊ ሁኔታ፤ የፓስፖርት አገልግሎት ለማግኘት በዜጎች ላይ የሚደርሰው አላስፈላጊ እንግልት፤በመንግሥት ጥረት ላይ ቀዝቃዛ ውሃ የመቸለስ ያህል ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡

የመንግሥት አገልግሎቶች ቀልጣፋና ፈጣን እንዲሆኑ ለማስቻል መንግሥት በስፋት በሚንቀሳቀስበት፤ ለዚህም የሚሆን ከፍተኛ ሀብት መድቦ እየሠራ ባለበት ሁኔታ፤ በዜጎች ላይ የሚደርሰው እንዲህ አይነቱ እንግልት ምንም ምክንያት ሊቀመጥለት የሚገባ አይደለም።

በተለይም ተቋሙን እየመራ ያለው የለውጥ ኃይል ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሩ በዜጎች ላይ እያስከተለ ካለው ከፍ ያለ ቅሬታ አንጻር፣ የተለያዩ የመፍትሔ አማራጮችን መከተል፤ በተለይም ችግሮች በቴክኖሎጂ ታግዘው ፈጣን መፍትሔ የሚያገኙበትን መንገድ መፍጠር ይጠበቅበታል።

እንደ ተቋም የጀመረውን ሪፎርም በተጠናከረ መንገድ በማስቀጠል በአገልግሎቱ ዙሪያ ያሉ የሕዝብ ቅሬታዎችን ፈጥኖ በመፍታት ለዜጎች አገልግሎት የርካታ ምንጭ መሆን፤ እንደ ሀገር የተጀመረው ለውጥ የስኬት ምሳሌ ወደሚሆንበት ፈጣን የለውጥ ትግበራ መግባት ይኖርበታል፡፡

በተቋሙ ውስጥ ያለው የለውጥ አመራር፤ በለውጥ ውስጥ ያሉ ፈተናዎችን ተሻግሮ ስኬታማ መሆን የሚችለው የትናንት ችግሮችን አግዝፎ በመመልከት እና በነርሱ በመቆዘም ሳይሆን፤ ከተለመደው አሠራር ውጪ የሪፎርም ሥራዎችን ከፍ ባለ ተነሳሽነት እና ቁርጠኝነት ቀን ከሌሊት በመሥራት እና በማሠራት ነው። ለዚህ ደግሞ ምሳሌ የሚሆኑ በቂ የለውጥ አመራሮች በየአደባባዮቻችን እና መንገዶቻችን ማየት ከጀመርን ውለን አድረናል!።

አዲስ ዘመን ሚያዚያ 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You