“ሴቶች ወደ አመራርነት ከመጡ ብዙ ነገር መቀየር ይችላሉ” -ወይዘሮ ፋጡማ ሙሐመድ የኦዳ ወረዳ አስተዳዳሪ

ወጣቷ፣ በአዳማ ከተማ በአባ ገዳ ክፍለ ከተማ የኦዳ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ናት፤ ውልደቷ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በአርሲ ዞን፣ በሌ ገስጋር ወረዳ ሲሆን፣ የቀበሌዋ መጠሪያ ስም ደግሞ በሌ ይባላል። አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እዛው በሌ የተማረች ሲሆን፣ የአስረኛ ክፍል ትምህርቷን እንዳጠናቀቀችም ቀጥታ ያቀናችው ወደ ምዕራቡ የአገሪቱ ክፍል ወለጋ ወደሚገኘው የመምህራን ማሠልጠኛ ኮሌጅ ነው – የዛሬው የዘመን እንግዳችን ወይዘሮ ፋጡማ መሐመድ።

ይህች ወጣት የኮሌጅ ትምህርቷን እንዳጠናቀቀችም የመምህርነት ሥራዋን ተወልዳ ባደገችበት ዞን፣ አሚኛ ወረዳ፣ አደሌ ከተማ አንድ ብላ ጀመረች። ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ባለው ትምህርት ቤት ውስጥ ስታስተምር የቆየችው ግን ለሁለት ዓመት ብቻ ነው። አሚኛ ገስጋር ላይ የሴቶች ሊግ ኃላፊ በመሆን ጥቂት እንደሠራችም፤ የኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በመሆን ለማገልገል የሊግ ኃላፊነቷን ተወት አደረገችው። በዚህ ሙያም ሳትገፋ የአሚኛ ወረዳ የከተማው የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ለመሆን በቅታለች።

ይህች! የዛሬዋ እንግዳችን፣ በአርሲ ዞን ጥቂት ዓመታት እንዳገለገለችም ካላት የሥራ ትጋት የተነሳ የበዳቱ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ ሆና ወደአመራርነቱ እንድትመጣ ተደረገ። ወጣቷ ፋጤ፣ እዚያም ምክትል አስተዳዳሪ ሆና ብዙ አልቆየችም፤ ፈጣን የሆነ የሥራ እንቅስቃሴ በማሳየቷ በቀጥታ የኦዳ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ለመሆን በቃች። የኦዳ ወረዳን በዋና አስተዳዳሪነት ማስተዳደር ከጀመረች እነሆ ሁለት ዓመት አስቆጥራለች። የዛሬዋ የዘመን እንግዳችን የአስር ዓመት የሥራ ልምድ ያላት ሲሆን፣ በአስር ዓመት ቆይታዋ ብዙ ለውጦችን ለማምጣት ሞክራለች።

ወይዘሮ ፋጤ ትዳር የመሠረተችው ተማሪ እያለች ነው፤ በአሁኑ ሰዓት የአራት ልጆች እናት ናት። ብዙ ጊዜዋን የምታውለው ለሥራዋ ነው። ይሁንና ቤተሰቧን በኃላፊነት ስሜት መምራት እንዳለባትም አትዘነጋም። በሥራዋ፣ ትውልድ የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኝና በመልካምነት እንዲታነጽ የምትተጋ አመራር ስትሆን፣ ወደቤቷ መለስ ስትል ደግሞ የልጆቿን ደብተር መገምገምና ማስጠናትን ለአፍታም የማትዘነጋ እናት ናት። ፋጤ በአዳማ ከተማ ስር ካሉ 19 ወረዳዎች ውስጥ የኦዳ ወረዳን በአስተዳዳሪነት የምትመራ ሲሆን፣ በወረዳዋ የአመራር እርከን ላይ ያሉም ሁሉ በሚያስብል ደረጃ ሴቶች ናቸውና ይህ በሴቶች ብቻ እየተመራ ያለው ወረዳ ምን የተለየ ውጤት አመጣ የሚለውን ለሌሎች ለማጋራት የዛሬው እንግዳችን አድርገን አቅርበናታል።መልካም ንባብ።

አዲስ ዘመን፡- በአጭር ጊዜ የሥራ ልምድ ወደ ወረዳ አስተዳዳሪነት መምጣት ችለሻል፤ ወደ አመራርነት ለመምጣት በምታደርጊው የሥራ ትጋት ያጋጠመሽ ነገር ይኖር ይሆን?

ወይዘሮ ፋጡማ፡- ወደ አዳማ ከተማ ከመምጣቴ በፊት ኦሮሚያ ክልል ላይ ወደከተማ መስተዳድሩ እንድሔድ እና የሥራ ዕድል እንዳገኝ ተፈቅዶልኝ ነበር። በአዳማ ከተማ ካሉ ወደአንደኛው ክፍለ ከተማ አቀናሁ። ጉዳዩንም አስረድቼ ሥራ እንዲመድቡኝም ጠይቅኩ፤ ይሁንና በከፍተኛ አመራርነት ላይ ያሉ አካላት “በወረዳው ውስጥ ለአንቺ የሚሆን ቦታ የለንም፤ ያለን ክፍት ቦታ ቢኖር የፀጥታ አመራርነት ቦታ ብቻ ነው፤ እሱ ደግሞ ለአንቺ አይሆንም፤ ይከብድሻል” አሉኝ።

እኔም ሳላቅማማ ‘ይሁን ቦታውን ከሰጣችሁኝ መሥራት እችላለሁ’ አልኳቸው። ይህን ስላቸው ግን ሁሉም ሳቁብኝ።ሳቃቸውን ገታ አድርገውም ለጠየቅኳቸው ጥያቄ ምላሽ ሊሰጡኝ ሞከሩ፤ “እስከዛሬ ድረስ ባለው ሁኔታ ሴቶች የፀጥታ ኃላፊ ሆነው አያውቁም።” አሉኝ። ቀጥለውም “ለጊዜው ክፍት ቦታ ስለሌለ እንዴት እናድርግ?” ሲሉ መልሰው እኔኑ ጠየቁኝ። በእርግጥ በወቅቱ የሳቃቸው ምስጢር ምን መልዕክት እንዳለው ገብቶኛል። ሴት በፀጥታ ቢሮ ኃላፊነት መሥራት አትችልም የሚል ነው። በአቋማቸው ጸንተው ቦታውን ሳይሰጡኝ ቀሩ። በእነርሱ እይታ “ይመጥናታል” ያሉትን ቦታ ሰጥተውኝ ስሠራ ቆየሁ።

አዲስ ዘመን፡- ታዲያ እሱ ታሪክ እንዴት ተቀይሮ ወደ ወረዳ አስተዳዳሪነት መምጣት ቻልሽ?

ወይዘሮ ፋጡማ፡- የሚያስገርመው እሱን ታሪክ መቀየር የቻሉት የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ኃይሉ ጀልዴ ናቸው፤ እርሳቸው ሴቶች ወደ አመራርነት ቢመጡ የተሻለ መሥራት ይችላሉ የሚለውን ያምኑበታል። ማመን ብቻ ሳይሆን በሁለት ወረዳዎች ላይ ያለውን የአስተዳደር እርከን ሁሉ በሴቶች እንዲመራ እና ሴቶች መሥራት እንዲችሉ ለማሳየት ለመወሰን አልተቸገሩም። ምክንያቱም ይህን ያደረጉት አስበውበት ነው። ይህ ማለት ግን “ካለው የአመራርነት ቦታ ገሚሱ ለሴት ቢሰጥስ!?” በሚል መንፈስ አልነበረም።

ከዋና አስተዳዳሪነት ጀምሮ ምክትል አስተዳዳሪነቱን፣ ሥራ አስፈጻሚነቱን፣ የፀጥታ ዘርፉንና ሌሎቹንም አመራርነት ሁሉ በሴቶች እንዲያዝ አደረጉ።“ሴቶች ብቻ ሁለት ወረዳ ሙሉ እንዲመሩ አድርጌ ሥራው ቢበላሽስ!!?” የሚል ስጋት ሳያድርባቸው በእርሳቸው ቁርጠኝነት እንደምንሠራ ቀድመው በማመናቸው ሁሉን አሳልፈው ሰጡን።በሁለቱ ወረዳዎች ላይ ያለውን የአመራርነት ቦታ ሴቶች እንዲመሩና ሥራቸውን እንዲያሳዩ ዕድል አመቻቹ።

ያኔ ‘የፀጥታ ቦታውን ስጡኝ እና እኔ ልምራው’ ስላቸው የሳቁብኝ ሰዎች፤ ዛሬ ግን ሥራዬን በተግባር እያዩት ነው። በእርግጥም ሴቶች ዕድሉን ካገኘን “የወንዶች ናቸው” የተባሉ ሥራዎችን ከእነርሱ ባልተናነሰ ሁኔታ የምንሠራ መሆኑ መታወቅ አለበት። የሚከብድ ነገር አለመኖሩንም ሌሎች ትልልቅ ኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ሴቶች ሠርተው ማሳየት እንደቻሉ ሁሉ እኔም በተሰጠኝ የኃላፊነት ቦታ ያለምንም ስጋት በትጋት እየሠራሁ እገኛለሁ። ከንቲባችን “ሴቶች ዕድሉን ካገኙ መሥራት እንደሚችሉ አልጠራጠርም” በሚል በእኛ ላይ እምነት በመጣላቸው እኛም እምነታቸውን ላለማጉደል ብቻ ሳይሆን መሥራት እንደምንችል በተግባር በማሳየት ላይ ነን።

አዲስ ዘመን፡- የሠላም መጠበቅ ለሁሉም የግድ እንደሆነ የሚታወቅ ቢሆንም፤ በተለይ ለሕጻናትና ለሴቶች ደግሞ ፋይዳው ከፍ ያለ ነው፤ ከዚህ አኳያ ሴቶች በዘርፉ የአመራርነትን ቦታ መያዛቸው ምን የሚያመጣው ለውጥ አለ ትያለሽ?

ወይዘሮ ፋጡማ፡- በእኔ እምነት በጣም ብዙ ለውጥ መምጣት ይችላል። ለምሳሌ የእኛን ወረዳ ብትወስጂ እንዳልኩሽ በኃላፊነት ቦታ ላይ ያለነው ሁላችንም ሴቶች ነን። የወረዳችን ሠላም እንዳይደፈርስ በቀጣና ደረጃ ሁሌም ውይይት እናደርጋለን። የሻይ ቡና ሰዓት በማመቻቸትም ከሕዝቡ ጋር ምክክር እናደርጋለን።

በውይይታችን እና በምክክራችን ሰዓት ዋና ነጥባችን የሚሆነው የሠላም መጓደል የአንድ ሰው ብቻ አለመሆኑ ሲሆን፣ እዛ ላይ አፅንዖት እንሰጣለን። የሠላም መጥፋት ጉዳቱ በልጆችና በሴቶች ላይ ብቻ ነው ጉዳት የሚያመጣው ብለን የምናምን ከሆነ እሱ ስህተት ነው። እዛ ላይ ብቻ ተወስኖ አለመቅረቱን መረዳት መቻል እንዳለብን እንነጋገራለን። ምክንያቱም የሠላም መታጣት ሲያመጣ የነበረውን ጉዳት በተለያየ ጊዜ በተደጋጋሚ ሁኔታ አይተናል። ስለዚህ ሁሉም ሰው በተለይ ደግሞ ሴቶች ቤተሰባቸውን ከሰላም ጋር በተያያዘ ሁሌም ቦታ ሰጥተው መወያየት እንዳለባቸው በውይይታችን ወቅት እናስገነዝባለን።

ሴት እህትም እናትም እንዲሁም ሚስትም ናት፤ የቤቷ ሠላም መሆን ወደጎረቤትና ሰፈር እንዲሁም ሀገር ድረስ እንዲሆን የማድረግ ሚናዋ ከፍ ያለ ነው። በቤቷ ልጇን መጥፎው ከጥሩ መለየት እንዲችል አድርጋ ማነጽ ትችልበታለች። ቤተሰቧን በየትኛውም አካል ላይ ጥላቻ እንዳያሳድሩ ማድረግም አያቅታትም። የትዳር አጋሯም ሆነ ልጆቿ በሠላም ጉዳይ ልክ ለራሳቸው የሚፈልጉት ሠላም ሌላውም አካል አጥብቆ የሚሻት መሆኑን እንዳይዘነጉ የማድረግ ብቃት አላት ባይ ነኝ።

ሌላው ቀርቶ ሴት በአመራርነት ቦታ ላይ ስትቀመጥ የከረረ የሚመስል ፖለቲካን ፈር የማስያዝ አቅም አላት፤ ሥራዎችን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድም ማስኬድ ትችላለች። ሥራ፤ ዝቅም ከፍም ባለ ሁኔታም ሊሠራ ይችላል። ስኬት ማምጣት የሚቻለው ደግሞ ታች በወረዳ አካባቢ ያለው ሒደት ውጤት ማላበስ ሲችል በመሆኑ እኛ በቀጣና ደረጃ ያለውን ሥራችንን በወጉ በመወጣት ላይ እንገኛለን። ለምሳሌ ፖሊስ፣ ሚሊሻ የሥርዓቱ ጋሻ የተባለው (ጋጃና ሲርና) እና ሕዝቡ አለ። ይህን አካል ሁሉ በቀጣናው ላይ አቀናጅተን በቀጣናው ላይ በየብሎኩ በመሆን የሚከታተል ሲሆን፣ እዛ ብሎክ ላይ ችግር ከተፈጠረ ተጠያቂ የሚሆነው ብሎኩን የያዘው ሰው ነው።

ሥራውም በየቦታው ያሉትን ሰዎች ግንዛቤ የማስጨበጥ ሊሆን ይችላል። ችግር ከመምጣቱና ፀጥታ ከመጓደሉ አስቀድሞ መወያየት ሊሆን ይችላል፤ ከዚህ ጎን ለጎን ሰዎችን ቤት ለቤት የማወቅ ጉዳይ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ በወረዳችን ያሉ አመራር በቀጣናው ውስጥ ማን እንዳለ፤ ማን እንደሌለ ነዋሪውን ጠንቅቀው ያውቃሉ።ማን ጥፋተኛ እንደሆነም ስለሚያውቁ ቀርበው ይመክራሉ፡። በዚህ ሥራ እውነት ለመናገር በቀጣናው በማደራጀቱ ላይ በደንብ ሠርተናል።ለምሳሌ የሻይ ቡና መርሐግብር ያለን ሲሆን፣ ሰው በየብሎኩ ተራውን ጠብቆ የሚጠበቅበትን ያከናውናል።

አዲስ ዘመን፡- በዋና አስተዳዳሪነት በምትመሪው የአመራር እርከን ውስጥ ሁሉም ሴቶች ናቸው ማለት ነው?

ወይዘሮ ፋጡማ፡- ከሁለቱ ቦታ በስተቀር ሁሉም ሴቶች ናቸው። ለምሳሌ የወረዳው አምስቱም ሥራ አስፈጻሚ ሴቶች ነን። በወረዳው ውስጥ 16 የአመራር ቦታ አለ፤ ከእነዚህ ውስጥ ወንዶች ሁለቱ ብቻ ናቸው እንጂ ሁሉንም ቦታ በአመራርነት የያዙት ሴቶች ናቸው። ለምሳሌ ዋና አስተዳዳሪዋ እኔን ጨምሮ ምክትል አስተዳዳሪ፣ የፓርቲው ኃላፊ፣ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ፣ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ፣ የገቢዎች ጽሕፈት ቤት፣ የንግድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ የወረዳው አፈ ጉባኤና ሌሎች ቦታዎች እየተመሩ ያሉት በሴቶች ሲሆን፣ የወጣቶች ሊግ ኃላፊና የፀጥታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ብቻ ወንዶች ናቸው።

ይህን ያደረጉት ከንቲባ ኃይሉ ጀልዴ ሲሆኑ፣ በሴቶች መመራት እና ውጤት ማምጣት አለብን ብለው የመጀመሪያ ወረዳ ያደረጉት የእኛን ወረዳ ነው።ቀጥሎ ሁለተኛውን ወረዳ በተመሳሳይ በሴት አመራር እንዲመራ አደረጉ።

እርሳቸውም በሥራችን አመኔታ እንደጣሉ ሁሉ ሠርተን እያሳየን በመሆኑ አላፈሩብንም።እንደ አዳማ ከተማ ሞዴል ከመሆናችን በተጨማሪ ለሌሎች አካባቢዎችም አርዓያ መሆን ችለናል። የአማራ ክልልን ጨምሮ ከተለያዩ ክልሎች ወደእኛ በመምጣት ተሞክሮ መውሰድ ችለዋል።

በተለይ ባለፈው “ከእዳ ወደ ምንዳ” በሚል መሪ ሐሳብ በተዘጋጀው የሥልጠና መርሐግብር ላይ ወደብዙ ክልሎች እንድንሔድና ከልምዳችን እንድናካፍል ተደርጓል። እንደሀገር ልምዳችንን ያቀርብንባቸው ቦታዎች ሁሉ የሠራናቸውን ስንነግራቸውም ተደንቀዋል። ከሥልጠናው በኋላ ልምድ ለመቅሰምና ይበልጥ በተጨባጭነቱን ለማረጋገጥ ወደወረዳችን መጥተው ጎብኝተውናል። ከእነዚህ መካከል የደቡብ ኢትዮጵያ፣ የሐረሪ፣ የጋምቤላ፣ የሲዳማ እና ሌሎችም ጭምር መጥተው ልምድ ቀስመዋል። መጥተው ልምድ ከወሰዱ ክልሎች መካከል የሐረሪ ክልል እና ሌሎቹም ክልሎች የቀሰሙትን ተሞክሮ ወደትግበራ እየቀየሩት መሆኑን ከዚያ በኋላ ማወቅ ችያለሁ።

አዲስ ዘመን፡- ወረዳችሁ በሴት በመመራቱ ከሌሎቹ 18 ወረዳዎች ምን የተለየ ነገር ማምጣት

አስቻላችሁ? በተጨባጭ ምንስ ያመጣችሁት ለውጥ አለ?

ወይዘሮ ፋጡማ፡- በተጨባጭ ያመጣነው ለውጥ አንደኛ ከወረዳ በታች ያሉ አደረጃጀቶች አሉ፤ በእነዚያ አደረጃጀቶች ቤት ለቤት በመሄድ ሕዝቡ እርስ በእርስ በመተዋወቅ መተሳሰብ እንዲችል ማድረግ መቻሉ ነው። በተለይ በልማቱና በሠላሙ ዙሪያ ተቀናጅተው እንዲሠሩ ከፍ ያለ ጥረት አድርገናል።

ሰው ሳይቀናጅና ሳይደራጅ ምንም አይነት ሥራ ቢሠራ እንዲያው የታይታ ይሆናል እንጂ ከልቡ መሥራት አይችልም። እኛ ግን አደረጃጀት መፍጠር በመቻላችንና ክትትል በማድረጋችን ብዙ ሥራ መሥራት ችለናል። ለምሳሌ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የሚባለውን በመተግበር ደረጃ ወረዳችን ግንባር ቀደም ነው።

በወረዳችን ሰዎች ተቸግረውና ግራ ገብቷቸው ወደ ጽሕፈት ቤታችን ሊመጡ ይችላሉ፤ በመጀመሪያ የምናደርገው ችግራቸው ምን እንደሆነ ጆሯችንን ሰጥተን ማዳመጥ ነው። ማዳመጥ ብቻ አይደለም የችግሩን ጥልቀት ለመረዳት መኖሪያ ቤታቸው ድረስ በመሄድ እንመለከታለን። ችግሩን አይተን የምንችለው ከሆነ እንፈታለን። ከአቅማችን በላይ የሆነውን ለበላይ አካል እናሳውቃለን። ለአብነት ያህል ለመጥቀስ በጎረቤታሞች መካከል ከድንበር ጋር ተያይዞ ለሃያ ዓመት ያስቆጠረ ችግር መፍታትም ችለናል።ችግሩን መፍታት ብቻ ሳይሆን ቅራኔው በመካከላቸው የተፈጠረባቸውን አካላት በማስታረቅ በስምምነትና በፍቅር እንዲኖሩ ማድረግ ችለናል።

እኛ አንዱ የምንደሰትበት ነገር ቢኖር ሕዝቡን ማዳመጥ መቻላችን ነው። በትኛውም አይነት ሁኔታ ቢሆን ሰው እንዲከፋብን አንሻም። በእኛ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ሰው ቅር ተሰኝቶ እንዲሄድ አንፈልግም። ችግራቸውን ለመፍታት በብዙ እንጥራለን፤ አብዛኛውንም ችግር በትክክል እንፈታለን።

ሌላው እንደ አዳማ ከተማ የተማሪዎች ምገባ መርሐግብር አለ። በሦስት ትምህርት ቤት ውስጥ ወደ ሁለት ሺ የሚሆኑ ተማሪዎችን ዓመቱን ሙሉ በመመገብ ወረዳችን ከሌሎቹ ግንባር ቀደም መሆን ችሏል። ይህ ልዩ የሚያደርገንና እስከ ክልላችን ድረስ የሚታወቅም ጭምር ነው።

ሌላው የአረጋውያን መመገቢያ የሚሆን ቤት ሠርተናል፤ እሱም በቅርቡ የሚመረቅ ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ ስማርት ሲቲ አዳማ ፕሮጀክትን እውን በማድረግ ከተማዋ ምቹና ተመራጭ እንድትሆን በልዩ ትኩረት እየተሠራ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ እኛም ሁሉን ነገር ስናደራጅ ዲጂታል በሆነ መንገድ በማድረግ ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው ሲደራጅ ኦንላይን ላይ ይገባል፤ ሥራዎቻችንን ዲጂታላይዝ እያደረግን ስለሆነ የማጭበርበሪያ ስልቶችን እየዘጋን መምጣት ችለናል።

ከሌሎቹ ወረዳዎች የምንለይበት ብዙ ሥራ በመሥራታችን ነው፤ ለምሳሌ በንግድ ጽሕፈት ቤት አማካይነት የገበያን ሁኔታ በማረጋጋት ረገድ ትልቅ ሥራ መሥራት ችለናል። ሦስት የሰንበት ገበያዎችን ሠርተናል። ይህን ወደሌሎች ወረዳ ላይ ብትሔጂ አታገኚውም። በተመሳሳይ የተማሪዎች ምገባም ቢሆን እንዲሁ ነው። እንዲያውም ብዙዎቹ ‘ሴቶች ሁሉን መረዳት የሚችሉና ለልጆችም ቅርበት ያላቸው በመሆናቸው ነው የተማሪ ምገባ መርሐግብር ላይ ስኬታማ መሆን የቻሉት’ ይሉናል።

ሌላው እንደ አዳማ ከተማ ወረዳችን ገቢ በማስገኘትም ረገድ አንደኛ ነው።የምንሠራውን ሥራ የምንተገብረው ከልባችን ነው፤ ሥራችን ለታይታ ሳይሆን ትውልድ የሚማርበትም ጭምር ነው። ሥራውን ስንሠራ ደግሞ ማኅበረሰቡ ዘንድ ወርደን እኛ ራሳችን ሠርተን በማሳየት ጭምር ነው።

አዲስ ዘመን፡- አንዳንዶች ሴቶች ተስማምተው ለመሥራት ይቸገራሉ ሲሉ ይናገራሉ፤ እናንተ እንዲህ አይነቱ ፈተና አጋጥሟችኋል? እየሠራችሁ ያላችሁት እንዴት ነው?

ወይዘሮ ፋጡማ፡- በመጀመሪያ ደረጃ እኛ ሴቶች ጤነኛ ሆነን ማሰብ እስከቻልን ድረስ ምንም ነገር ለመሥራት አለመቸገራችን ግንዛቤ ውስጥ መግባት አለበት። በተለምዶ ግን እንዳልሽው “ሴቶች እርስ በእርስ አይግባቡም” የሚል አተያይ አለ። ይህ ግን በደመነፍስ የሚሰጥ ግምት ነው ባይ ነኝ። ምክንያቱም የእኛን ወረዳ ለአብነት መውሰድ ይቻላል። እንዳልኩሽ በአመራር ላይ ያለነው ሁላችንም ሴቶች ነን። ለብዙ ሰዎች የእኛ ተግባብቶ መሥራት ጥያቄ ሆኖ ቀጥሏል።

እንዲያውም አንዳንድ ሰው በግልጽ “እውን ሳትጣሉ ቀርታችሁ ነው ሥራችሁን እየሠራችሁ ያላችሁት!?” እያለ ጥያቄ ይጠይቀናል። አንዳንዶቹ ደግሞ “እየደበቃችሁት ነው እንጂ እርስ በእርስ ትጣላችሁ” ብለው ሲደመድሙ እንሰማለን። አንዳንዶቹ ደግሞ በየቀኑ እየተደባደብን የምንውል ይመስላቸዋል። የሚያስገርመው ነገር ቢኖር ግን እነርሱ እንደሚሉት ሳይሆን፣ ሁሉም የየራሳቸውን ሴክተር ስኬታማ ለማድረግ በተሻለ መትጋታቸው ነው።

ካልሠሩ ደግሞ እንደማንኛውም አመራር ሥራቸው ይገመገማል። በሥራችን መካከል አንዱ ከሌላው ጋር ሊጨቃጨቅ ይችላል፤ ይህ ደግሞ ተፈጥሯዊ ነው።ሥራን አስመልክተን በምንነጋገርበት ጊዜ አንዱ በሌላው ላይ ቅያሜ አይኖረውም፤ ‘የተናገረችኝ ለሥራው ነው’ የሚል ልምድ በመካከላችን ስለዳበረ ከዚህ የዘለለ ጭቅጭቅና ሙግት የለብንም።

ቢሮ የምንደርሰው አረፈድን ከተባለ አንድ ሰዓት፤ ከማለድን ደግሞ አስራ ሁለት ሰዓት ተኩል ላይ ነው። ከቢሮ ስንወጣ አምሽተን ነው። ምሳችንን የምንበላው አንድ ላይ ነው። የምንለያየው ለእንቅልፍ ሰዓት ነው ቢባል የተጋነነ አይሆንም። ከቢሮ ባሻገር ያለው ማኅበራዊ ሕይወታችንም የተያያዘ ነው። አንዷ በአጋጣሚ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት የምትቀር ከሆነ የእርሷን ቦታ ሸፍነን እንሠራለን።

እውነት ለመናገር ሴቶች ወደ አመራርነት ከመጡ ብዙ ነገር መቀየር ይችላሉ። በእኛ ወረዳ እየተሠራ ያለው የሚያሳየውም ይህንኑ ነው። ለአብነትም የባለጉዳይ ቀንን አክብረን ሕዝብን እናዳምጣለን፤ ሕዝብን ማዳመጥ በመቻላችን ብቻ ሕዝቡ ጥያቄው የተመለሰለት ያህል ስለሚቆጥረው ደስተኛ ነው። ሴት በባሕሪዋ ሰውን የመረዳት ክህሎት አላት። እኛ በአሁኑ ወቅት የምንሠራው ደስ እያለን ነው፤ ሕዝቡ ወዶንና ከሕዝቡ ጋር ተግባብተን ስለምንሠራ ስኬታማ እየሆንን ነው።

አዲስ ዘመን፡- ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ በእናንተ ወረዳ የተሠራ ሥራ ይኖር ይሆን?

ወይዘሮ ፋጡማ፡- ወጣቶችንና ሴቶችን በማደራጀት የሥራ ዕድል ተጠቃሚዎች ለማድረግም ሠርተናል። በተለይ በዶሮ እና በከብት እርባታ ብዙዎቹን በስፋት አደራጅተን ወደሥራ ማስገባት ችለናል። ወደሥራ ማስገባት ብቻ ሳይሆን የገበያ ትስስርም እንዲፈጠርላቸው የተለያዩ ሥራዎችን ተግብረናል። ለምሳሌ የገበያ ማዕከል በመሥራታችን ተጠቃሚ በመሆን ላይ ናቸው። በዘንድሮ በጀት ዓመት በወረዳችን ደረጃ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ወደ 125 የሚሆኑ ኢንተርፕራይዞች ሲሆኑ፣ እነርሱም በመደራጀታቸው ሥራ ጀምረዋል።

ይህ ወረዳ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች “ሴቶች አይችሉም፤ አቅም የላቸውም፤ ከዚህ የተነሳ መምራት አይችሉም” እያሉ ሴቶችን ሁሉ በአንድ ኮሮጆ የሚጨመሩ አካላትን እስከነአመለካከታቸው ውድቅ ያደረገ ነው። ምክንያቱም በየትኛውም ዘርፍ አቅቶን እገዛ የጠየቅንበት የለምና።

ይህ አይነቱ የማኅበረሰብ ክፍል በተለምዶ “ለሴት አመራርነቱ እንኳ ይከብዳታል” እያለ የሚናገረው ንግግር በወቅቱ ለጊዜውም ቢሆን ፈራ ተባ እንድንል አድርጎን ነበር። ይሁንና ሥራውን ስንጀምር ሴት መምራት፣ በራሷም መተማመንና በሥራችንም ሥራ ውጤታማ መሆን እንደምትችል እኛ በምንሠራው ሥራ ማሳየት ችለናል። ስለዚህ ሴት ዕድሉን ካገኘች መሥራት ያቀደችውን ማሳካትም ትችላለች።

በዚህ መልኩ የእኛ ወረዳ የተሞክሮ ማዕከል ሆኗል ማለት ነው።ይህ የተሞክሮ ማዕከልነት በክልሉ ብቻ ተወስኖ የቀረ ሳይሆን ከሌሎች ክልሎችም ወደእኛ እየመጡ ውጤታማ የሆንበትን አካሔድ ልምድ እየወሰዱ ነው።ለአብነት ያህል ከአማራ ክልል ወደ ወረዳችን መጥተው ተሞክሮ ሲወስዱ ነበር።

ለምሳሌ እንደ እኛ ወረዳ በሥራ ዕድል ፈጠራ ካስተዋልን የጎጆ ኢንዱስትሪን መጥቀስ ይቻላል።በርከት ያሉ ሥራ አጦችንም በማደራጀት የሥራ ፈጠራ ዕድሉን እንዲያገኙ በማድረግ በኩል በስፋት ተሠርቶበታል። በተለይም ሴቶች የሥራ እድል እንዲያገኙና ሥራ እንዲሠሩ ማድረግ ችለናል።

አስቀድሜ የጠቀስኩት የአረጋውያን መርጃ ማዕከልን በአሁኑ ሰዓት ግንባታውን አጠናቀን አቅም የሌላቸው አረጋውያን መጠቀም እንዲችሉ በቀን አንድ መቶ ሰው ለመመገብ ዝግጁ ሆነናል። ይህ ብቻ ሳይሆን በሌሎቹም የሥራ ዘርፎች በአግባቡ በመሥራት ላይ የምንገኝ ሲሆን፣ በዚያም ሥስራችን ውጤታማ ነን ማለት እችላለሁ።

ባሉት የልማት ሥራዎች ሁሉ ያለ አንዳች ማቅማማት የትኛውም ፈተና ሳይበግረን እየሠራን እንገኛለን።ለምሳሌ በፀጥታ ሥራ ብቻ የወሰድን እንደሆነ ዘርፉ ለወንዶች የተተወ አለመሆኑን እንደ ወረዳችን በአግባቡ ሠርተን በማሳየት ላይ እንገኛለን። ከዚህ የተነሳ አንዳች ችግር ሳያጋጥመን ወረዳችን ሠላማዊነቷን አስጠብቃ ዛሬ ላይ መድረስ ትላለች።

እንደ አጋጣሚ ሆኖ ወረዳችን ውስጥ የሚኖሩ የተለያዩ ኢትዮጵያውያን ከመሆናቸው የተነሳ ወረዳችን የብሔር፣ ብሔረሰብ ማዕከል ነች። በመሆኑም ትንሿ ኢትዮጵያ ናት ማለት ይቻላል። ሁሉም ተዋድደው፣ ተከባብረውና ተሳስበው አብረው እንዲሠሩና እንዲበለጽጉ በርካታ ሥራ እየሠራን ነው።

አዲስ ዘመን፡- የምትመሪው ወረዳ የት እንዲደርስ ትሽያለሽ?

ወይዘሮ ፋጡማ፡- እውነት ለመናገር በእኛ ወረዳ ቀጣይ የሚያሳስበን ነገር የሚበዙት የቀበሌ ቤቶች መሆናቸው ነው። እንደ እቅዳችን ኢንሼቲቭ ወስደን ከተማ ዳር ላይ የምንሠራቸው የዶሮና የከብት እርባታ በእኛ ወረዳ ቤት ለቤት ለመሥራት ከቦታው ጥበት የተነሳ በጣም ያስቸግረናል። ስለዚህ እንዲህ አይነቱ ችግር ላይ ሠርተን መፍትሔ በማምጣት የሕዝቡን የኑሮ ጫና ለማቃለል እንጥራለን። ይሁንና ችግሩ ገድቦናል።

ስለዚህ ሌላ አዲስ ሐሳብ በማፍለቅ የግድ ይለናል። በተለይ ሴቶች ለብዙ ነገር የተጋለጡ እንደመሆናቸው እነርሱን አደራጅተን ራሳቸውን እንዲችሉና እንዲበቁ ለማድረግ በቀጣዩ ዓመት አቅደናል። ከሴቶች ጎን ለጎን ደግሞ በነገው ሀገር ተረካቢ በሆኑ ወጣቶች ላይም እንዲሁ መሥራት እንፈልጋለን። ይህ ብቻ ሳይሆን ወጣቶች ስፖርት የሚሠሩበት፣ የሚዝናኑበትና እውቀት የሚገበዩበት ቤተ መጽሕፍትን ጨምሮ የመሥራት እቅድ አለን።

ወጣቶች በሱስ እንዳይያዙ እነዚህን ነገሮች ተግባራዊ ማድረግ የግድ ነው። በዘንድሮ ዓመት የቦታ ሁኔታ ምቹ ባለመሆኑ ባይሳካልንም በቀጣዩ ዓመት ተግባራዊ ለማድረግ ያቀድናቸው በርካታ ሥራዎች እንዳሉን ተግባራዊ ሲሆኑ ማጤኑ መልካም ይሆናል እላለሁ።

አዲስ ዘመን፡- ለቃለ ምልልሱ ፈቃደኛ ስለሆንሽ በጣም አመሰግናለሁ።

ወይዘሮ ፋጡማ፡- እኔም ዕድሉን ስለሰጣችሁኝ አመሰግናለሁ።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ሚያዚያ 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You