ከተሞችን በአዲስ እሳቤ የሚያስተዳድር መሪ ለመፍጠር እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፡በኢትዮጵያ የሚገኙ ከተሞችን ሁለንተናዊ እድገት እውን ለማድረግ በአዳዲስ እሳቤዎች መምራት ስለሚጠበቅ ብቁ አመራር ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ የከተማ አመራሮችን ለማብቃት ከአፍሪካ አመራር የልህቀት አካዳሚ ጋር ስምምነት ተፈራርሟል።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ስምምነቱን በተፈራረሙበት ወቅት እንዳብራሩት፤ እስካሁን ከተሞች በሚመሩበት አስተሳሰብና እውቀት መቀጠል የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል።

የኢኮኖሚ፤ ማህበራዊና ፖለቲካዊ አጀንዳዎችን ቀድሞ መፍጠር የሚችል ኃይል የሚኖረው በከተሞች ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ በዚህ ላይ የከተሞች እድገት እና የነዋሪዎች ፍላጎት በየወቅቱ እየጨመረ የሚመጣ በመሆኑ ሁሌም ለውጥ እንዲኖር ይጠበቃል ብለዋል።

ወይዘሮ ጫልቱ እንደገለጹት፤ የከተሞች መቀየር የሚወሰነው በሚያስተዳድሯቸው መሪዎች አቅም ነው። ለዚህም የከተማ አመራሮች ሁኔታዎችን ቀድመው በመረዳት ከተሞችን ለመምራት በሚያስችላቸው ደረጃ አቀማቸው መገንባት አለበት። ለዚህም አዳዲስ እሳቤዎች እና አስተምህሮዎች የሚነሱበት የአስተዳደር ሥርዓት ያስፈልጋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የከተማ ልማት ዘርፎችን የሚመሩ አካላትን አቅም ማጎልበት በአዋጅ የተሰጠው ኃላፊነት መሆኑን ሚኒስትሯ ጠቁመው፤ ይህንን እውን ለማድረግም እስካሁን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመነጋገር ከመጀመሪያ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ስልጠና ሲሰጥ ቆይቷል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ደግሞ የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ጋር በመሆን በሥራ ላይ የሚወሰዱ የአጫጭር ጊዜ ስልጠናዎችን ለመስጠት ከስምምነት መደረሱን ገልጸው፤ እነዚህ ስልጠናዎች በተግባር የሚገጥሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሚያስችል አቅም ለከተማ ልማት አመራሩ የሚያስጨብጡ እንደሚሆኑም አብራርተዋል።

ስልጠናው ከተሞችን ካሉበት ደረጃ በማውጣት፣ በማሳደግና በመለወጥ የራሳቸውን አሻራ ማስቀመጥ የሚችሉ አመራሮችን ለመፍጠር የሚያስችል ይሆናል ያሉት ወይዘሮ ጫልቱ፤ በተጨማሪም ሁሉም ከተሞች በተመሳሳይ የማስፈጸም አቅም ላይ የማይገኙ በመሆኑ ቀድመው የሄዱት ለሌሎች ተሞክሯቸውን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እንዲያካፍሉ የሚጠቅምም ይሆናል ብለዋል።

የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዛዲግ አብርሃ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ሁሉም ከተሞች ሊባል በሚያስችል ደረጃ እየተመሩ ያሉት በሳይንሳዊ መንገድ አይደለም ብለዋል።

በሌላ በኩል በከተሞች የሚኖረው ሕዝብ ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ የሚሄድ በመሆኑ ነገን ታሳቢ ያደረጉ እቅዶችና ትግበራዎች ያስፈልጋሉ ያሉት አቶ ዛዲግ፤ ሁሉን አቀፍና ውጤታማ የሆነ፤ የተለያዩ ነገሮችን ለማስተዳደር የሚችል የአመራር ብቃት ያለው መሪና የአመራር ልማት ሥርዓት ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል።

በሌሎች ሀገራት ከንቲባዎች በከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሾሙ ሲሆን፤ በሥራ ላይ እያሉም አዳዲስ ሃሳብ ሰንቀው እንዲወጡ ሁኔታዎች ይመቻቹላቸዋል ሲሉም አቶ ዛዲግ ጠቁመዋል።

ይህ አካሄድ በሀገራችን የተለመደ አልነበረም ያሉት አቶ ዛዲግ፤ በትምህርትና ስልጠና ደረጃም የከንቲባነት ልማት ፕሮግራም እንዳልነበረና አሁን አካዳሚው የሚሰጣቸው ስልጠናዎቸ እነዚህን ክፍተቶች የሚያሟሉ በመሆናቸው ለኢትዮጵያ ከተሞች አዲስ የምሥራች ነው ብለዋል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን  ሚያዝያ 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You