ከተማ አስተዳደሩ በሕገ ወጥ መንገድ ተይዞ የነበረን መሬት የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ማዕከል አደረገ

አዳማ፡- በሕገ ወጥ መንገድ እና በተወሰኑ አካላት የተያዘ ከአንድ መቶ በላይ ሔክታር መሬትን ወደ ሕጋዊነት በማምጣት የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ማዕከል አድርገናል ሲሉ የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ኃይሉ ጀልዴ አስታወቁ፡፡

አቶ ኃይሉ ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች እንዳስታወቁት፤ ከተማ አስተዳደሩ ከመቶ ሔክታር በላይ ምንም ካሳ ያልተከፈለበት እንዲሁም ያለሥራ ተቀምጦ የነበረን መሬት ለሥራ ዕድል መፍጠሪያ ማዋል ችሏል፡፡

ለሥራ እድል መፍጠሪያ ማዕከል የዋለው መሬት ከአንድ መቶ ሔክታር በላይ መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባው፤ የተወሰኑት ቦታዎች በሕገ ወጥ መንገድ የተያዙ እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት መሬቱን ወደሕጋዊነት ሥርዓት የማምጣት ሥራ በመሥራቱ ለወጣቶችና ለሥራ አጦች የሥራ እድል ማግኛ ለመሆን መብቃቱን አስረድተዋል፡፡

ከንቲባ ኃይሉ እንደተናገሩት፤ ሥራዎች ገና በተጀመሩበት አካባቢ የሚፈጸምባቸው አቅጣጫዎች ላይ ጭምር ግልጽነት አልነበራቸውም፡፡ እያደር ግን ኢንሼቲቩን በመገንዘብ ለሼዶች ብቻ ከመቶ ሔክታር በላይ ምንም ካሳ ያልተከፈለበት እንዲሁም ያለሥራ ተቀምጦ የነበረን መሬት ለዚህ ሥራ ማዋል ችለዋል፡፡

አጠቃላይ ድምር ውጤቱም ሲታይ ብዙ ሀብት ለዚህ ሥራ ውሏል ያሉት ከንቲባው፤ ይህም ወጣቶችና ብዙ ሥራ አጦች የሥራ ዕድል አስገኝቷል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ለዚህ ሥራ ውሏል ያሉት ከንቲባው፣ ይህ ማለት ለአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ለንብ ቀፎ የተደረገውን ዝግጁነት ሳይጨምር ማለት እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ይህ ወጪ ከመንግሥት የወጣው ከሃያ በመቶ የማይበልጥ ሲሆን፣ የሕዝብን አቅም በመጠቀም የተሠራ ሥራ ነው፡፡

መንግሥት በዚህ ሥራ ውስጥ ሼድ መገንባት ብቻ ሳይሆን የሥራ እድል የተፈጠረበት ሁሉም ማዕከላት ላይ መሠረተ ልማት ማሟላቱን በመጥቀስ፤ ውሃና መብራትን ጨምሮ ሌሎች መሠረተ ልማቶች እንዲሟሉ መንግሥት በትጋት መሥራቱን አብራርተዋል፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፣ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል የሥራ እድል ፈጠራ ቢሮ በጋራ በመሆን በሥራ እድል ፈጠራ ላይ ያተኮረ የመስክ ምልከታን ለጋዜጠኞች ማስጎብኘታቸው ይታወሳል፡፡

አስቴር ኤልያስ

 

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 19 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You