የሕዝብን ሠላምና ደኅንነት የማስጠበቅ ሥራው የበለጠ ውጤታማ እንዲሆ

ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሦስት ልዩ ቦታው ሚሊኒየም አዳራሽ አካባቢ በኅቡዕ ተደራጅተው የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የፅንፈኛ ቡድን አባላት ላይ እርምጃ ስለመወሰዱ በተለይ የፀጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረኃይል ባወጣው መግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ የጋራ ግብረ ኃይሉ ርምጃውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጿል፡፡

የቡድኑ አባላት ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ባደረጉት የተኩስ ልውውጥ ሕጋዊ እርምጃ እንደተወሰደባቸውና ሁለቱ ሞተው አንደኛው በቁጥጥር ስር እንደዋለም ይታወቃል፡፡ የፅንፈኛው ቡድን አባላት የተለያዩ የሽብር ጥቃቶችን ለማድረስ በአዲስ አበባ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ኅቡዕ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ከፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል እይታ ውጪ እንዳልነበሩም በወቅቱ ተጠቁሟል፡፡

እነዚህ የፅንፈኛው ቡድን አባላት በቀጥታ ጥቃት ያደረሱት መሣሪያ ይዘው በፀጥታ ኃይሎች ላይ ነው፡፡ በዚህም ሁለት የፀጥታ ኃይሎች ከባድ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡ አባላቱን በመኪናቸው እንዲጭኑ የተገደዱ ነገር ግን አልተባበርም ያሉ የአንድ ዜጋ ሕይወትም በጥቃቱ ተቀጥፏል፡፡

ጥቃቱ ከፀጥታ ኃይሎች በተጨማሪ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ንጹሓን ዜጎችንም ነክቷል፡፡ በርግጥ እኚህ ንፁህ ዜጋ ለፅንፈኛ ቡድኑ አባላት አልተባበርም በማለታቸው ሕይወታቸው ቢቀጠፍም በተመሳሳይ ሌሎች ንጹሓን ዜጎችም ለእንዲህ አይነቱ ፅንፈኛ ድርጊት ቦታ እንደማይሰጡ ያመላክታል ፡፡ ከፀጥታ ኃይሎች ጎን እንደሚቆሙም ያሳያል፡፡

ጥቃቱን ለማስቆም የፀጥታ ኃይሎች ያደረጉት ርብርብም ለሕዝቡ ሠላምና ደኅንነት መጠበቅ እስከመጨረሻው ድረስ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ያሳያል። ለዚህም ሁለት የፀጥታ ኃይሎች ባደረጉት ፍልሚያ የደረሰባቸው ከባድ የአካል ጉዳት ምስክር ነው። የፀጥታ ኃይሎች ጥቃቱን ለማክሸፍ ያደረጉት ተጋድሎ ልክ እንደ ዜጋው ሁሉ እነርሱም ለሠላምና ደኅንነት መጠበቅ ቅድሚያ የሚሰጡ መሆናቸውንም ያመላክታል፡፡

በርግጥ እንዲህ አይነት የሽብር ድርጊቶች በአዲስ አበባ ከተማም ሆነ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ሲፈፀሙ ይህ የመጀመሪያ አይደለም፡፡ ከዚህ በፊትም ተመሳሳይ የሽብር ድርጊቶች ተከስተዋል፡፡ አሁንም ከዚህ ቀደምም የነበረው የፀጥታና ደኅንነት ተቋም ጠንካራ ሥራዎችን በጥንቃቄ የሚሠራ በመሆኑ አብዛኛዎቹን የሽብር ድርጊቶች ከመፈፀማቸው በፊት አስቀድሞ ማክሸፍ በማቻሉ ነው፡፡ እዚህ ጋር ታዲያ የኅብረተሰቡ ቀና ትብብርና ሠላምና ፀጥታ ጉዳይ ያለው ቁርጠኛ አቋምም ኢትዮጵያ በዚህ ጉዳይ ስሟ በብዙ እንዳይነሳ ማድረግ ችሏል፡፡

የሽብር ድርጊት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን አሜሪካንን ጨምሮ በሌሎች ጠንካራ የደኅንነት መዋቅር አለን በሚሉ ሀገራት ጭምር የሚፈፀም ነው፡፡ ኢትዮጵያም ከዚህ ውጪ አይደለችም። ግን ደግሞ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሠላም ወዳድ በመሆኑና አሸባሪዎችን አጋልጦ ለፀጥታ ኃይሎች የሚሰጥ በመሆኑ የሽብር ድርጊቶቹ የጎሉና አነጋጋሪ አይደሉም፡፡ ከሰሞኑ በፅንፈኛው ቡድን ላይ የተወሰደው እርምጃም ምንም እንኳን በኅብረተሰቡ ላይ ጉልህ ጉዳት ሳያመጣ ቢከሽፍም የሚናቅ ጥቃት ባለመሆኑ የደኅንነትና ፀጥታ ማስከበር ሥራው እንደዚህ ቀደሙ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡

ዛሬ በመዲናዋ አዲስ አበባ ቦሌ ሚሊኒየም አዳራሽ አካባቢ የተፈፀመው ጥቃት ነገ ከነገ ወዲያ በሌሎችም የከተማዋ አካባቢዎች ሊከሰቱ ይችላሉና የሕዝቡን ሠላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ የጋራ ግብረ ኃይሉ ከወዲሁ ጠንካራ የፀጥታና የደኅንነት ሥራዎችን በተደራጀ እና በተጠናከረ መንገድ አጠናክሮ መቀጠል ይጠበቅበታል፡፡

ይህ በፅንፈኛው ቡድን ከሰሞኑ የደረሰው ጥቃት በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎችም ጭምር ሊደርስ ስለሚችል ይህን ታሳቢ ያደረጉ ጠንካራ ሥራዎች በፀጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረኃይሉ ከወዲሁ ይሠራሉ ተብሎ ይጠበቃል፤ ይህም በሀገሪቱ አስተማማኝ ሠላምና ፀጥታ በማስፈን ረገድ ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሠላምና ፀጥታ ወዳድ መሆኑን እንደሰሞኑ አይነት እኩይ ተግባሮች አድማሳቸውን እንዳያሰፋ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመቆምና አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ አጋርነቱን አሳይቷል፡፡ ነገም ቢሆን ተመሳሳይ ጥቃቶች በሌሎች አካባቢዎች ሊደርሱ ይችላሉና ለፀጥታ ኃይሎች ያሳየውን ይህ አጋርነት አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡

የፀጥታ ኃይሎች ከሕዝቡ ቁጥር ጋር ሲነፃፀሩ ኢምንት ናቸው፡፡ በአሸባሪዎች ሊፈፀሙ የታሰቡ እኩይ ድርጊቶችን ሁሉንም ሊደርሱባቸው አይችሉም፡፡ ከእነርሱ ይልቅ ሕዝቡ እነዚህን ሴራዎች በቅርበት ሊመለከት ይችላልና እንግዳና ያልተለመዱ እንቅስቃሴዎችን ሲያይ በአፋጣኝ ለፀጥታ ኃይሎች መረጃዎችን መስጠትና ጥቆማዎችን በማቅረብ ሠላም ወዳድነቱን ይበልጥ ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ይጠበቅበታልም፡፡ ይህ ደግሞ የሁሉም ዜጋ ግዴታም ጭምር ነው፡፡

በሌላ በኩል ብዙ ግዜ አሸባሪዎች እኩይ ዓላማቸውን ለማሳካት በኅቡዕ ሲንቀሳቀሱ እንደሽፋን የሚጠቀሙት ሕዝቡን ነው፡፡ በሕዝቡ ውስጥ ተሸሽገው ነው ሴራቸውን የሚጠነስሱት። በዚህ ረገድ ሕዝቡ እነዚህ አሸባሪዎችና ፅንፈኛ ቡድኖች ማጋለጥና ለፀጥታ ኃይሎች አሳልፎ መስጠት ይኖርበታል፡፡ ለደኅንነቱ የሚሰጋ ከሆነ ደግሞ በስልክ አልያም በአካል ፖሊስ ጣቢያዎች በመሄድ መረጃ መስጠት ይኖርበታል፡፡ ከፀጥታ ኃይሎች ጋርም በትብብር ሊሠራ ይገባል፡፡

ከዚህ ባለፈ ሆቴሎች፣ እንግዳ ማረፊያዎች የኪራይ ቤቶች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ኪራይ መኪናዎችም ብዙ ግዜ በአሸባሪዎችና በፅንፈኛ ቡድኖች እይታ ውስጥ የሚገቡና ጥቅም የሚሰጡ ናቸው፡፡ ስለዚህ ሆቴሎች፣ የእንግዳ ማረፊያዎች፣ የቤትና የመኪና አከራዮች እንዲሁም የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። አገልግሎቱን ሲያቀርቡ ተጠቃሚውን መታወቂያና ማንነቱን መጠየቅና ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ግለሰቡ አጠራጣሪና እንግዳ ሆኖ ከታያቸው ለሚመለከተው የፀጥታ አካል ማመልከት ይኖርባቸዋል፡፡

የሕዝቡና የፀጥታ ኃይሉ የጋራ ትብብርና ሥራ ነው በሀገሪቱ ሠላምና ፀጥታ የሚያመጣው። ሠላምና ፀጥታ በመዲናችን አዲስ አበባም ሆነ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች እንዲኖር ደግሞ የማይፈልግ ማንም የኅብረተሰብ ክፍል የለም፡፡ ይህ ፍላጎት ካለ ደግሞ ሕዝቡም፣ መንግሥትም፣ የፀጥታ ኃይሉም ሌሎችም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት በጋራ ሊሠሩ ይገባል፡፡ ያኔ የሚፈለገው ሠላምና ፀጥታ ይረጋገጣል፤ ልማትና ብልፅግናውም ይፋጠናል!!

ሙዘይን አሕመድ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You