ችግሮቻችንን በውይይት እና በድርድር፤ በሠላማዊ እና በሕጋዊ አግባብ የመፍታት የፖለቲካ ባሕል ከማዳበር ይልቅ በኃይል እና በሴራ ለመፍታት የሄድንባቸው መንገዶች ለትናንት ውድቀታችን ሆነ ለአሁናዊ ፈተናዎቻችን ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው። ችግሩ ይህንን ትውልድ ጨምሮ በየዘመኑ የነበሩ ትውልዶችን ብዙ የተፈታተነ እና ከፍ ያለ ዋጋ ያስከፈለ ነው።
አብዛኛውን የታሪካችንን ክፍል ለያዘው የጦርነት/የርስበርስ ግጭት ምክንያት የሆነው ይህ ሰንካላ የፖለቲካ ባሕላችን፤ በአንድ ወቅት የሥልጣኔ ቁንጮ ከሆንበት ስፍራ አውርዶ፤ ተመልሰን ወደቀደመው ስፍራችን እንዳንመለስ፣ ሁለንተናዊ ድንዛዜ ውስጥ ከትቶናል። ከዚህም ባለፈ ጦርነት “የባሕል ጫወታችን ነው” የሚሉ ግለሰቦች እና ቡድኖች እንዲፈጠሩ አድርጓል።
እያንዳንዱ ማኅበረሰብ በክፉም፣ በደግም፤ በጥሩም፣ መጥፎም የሚጠቀሱ ባሕሎች አሉት። እነዚህ ባሕሎች በትውልዶች መካከል በሚኖራቸው አዎንታዊ መስተጋብር አቅም ገዝተው ለዛ ማኅበረሰብ አሁናዊ ማንነት ትልቅ ጉልበት እንደሚሆኑ ፤ ለቀጣይ ትውልዶችም የማንነት መሠረት ሆነው እንደሚያገለግሉ ይታመናል። ባሕል የአንድን ማኅበረሰብ አሁናዊ ፖለቲካዊ ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እሴቶችን በማስተሳሰር የዛን ማኅበረሰብ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ነገዎች የተሻሉና ብሩህ ተስፋ የተላበሱ እንዲሆኑ ያደርጋል። ከዚህ የተነሳም በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ትልቅ ስፍራ፤ ትኩረት እና ጥበቃ ይደረግለታል።
የማኅበረሰብ ፍላጎቶች በጊዜ ሂደት ውስጥ ተለዋዋጭ ከመሆናቸውም አንጻር፤ ባሕልም እንዲሁ ዘመኑን በሚዋጅ ሁኔታ እየተለወጠ የሚሄድ ነው። ትናንት ላይ ካስገኘው ማኅበራዊ ትርፍ እና ኪሳራው እየተሰላም ቀጣይነት ባለው የአትራፊነት ስሌት ውስጥ እንዲያልፍ ይደረጋል። ለዚህ ደግሞ የማኅበረሰብ ንቃተ ሕሊና ወሳኝ እንደሆነ ይታመናል።
የሰው ልጅ ፍጥረታዊ ማንነቱ ከትናንት ስህተቶቹ ተምሮ፤ ዛሬ እና ነገዎቹ በትናንት ስህተቶቹ ጥላ እንዳይጋረዱ የሚያስችል መንፈሳዊ፤ አዕምሯዊ እና ስነልቦናዊ እውቀት ባለቤት ነው። የዚህ እውቀት ባለቤት መሆኑም ለሕልውናውም ሆነ አሁን ለደረሰበት ሁለንተናዊ እድገት ተጠቃሽ ነው ።
እኛም እንደ ሀገር/ትልቅ ማኅበረሰብ በክፉም፣ በደግም፤ በጥሩም፣ መጥፎም የሚታሰብ የረጅም ታሪክ ባለቤት ነን ። በዚህ ረጅም የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ የትላልቅ ሥልጣኔዎች ባለቤት ሆነን እንደመጠቀሳችን ሁሉ፤ የድህነት እና የኋላ ቀርነት ማሳያ ተደርገን እየተወሰድን ያለበት አሁነኛ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ እንገኛለን። ለቀደመው ሥልጣኔያችን ሆነ ለአሁናዊ ውድቀታችን ሊጠቀሱ የሚችሉ ምክንያቶች አሉን። ዛሬያችን ሆኑ ትናንቶቻችን የጋራ እሳቤዎቻችን ውጤቶች ከመሆናቸው አንጻር እነዚህ ምክንያቶች በአንድም ይሁን በሌላ እንደ ማኅበረሰብ ካካበትናቸው የጋራ እሳቤዎቻችን የሚመነጩ ስለመሆናቸው መገመት የሚከብድ አይደለም ።
የቀደሙትን የሥልጣኔ ትርክቶቻችን ስናስብ፤ ለዛ ያበቁን ከፍ ያሉ ማኅበራዊ እሴቶች/እሳቤዎች እንደነበሩን፤ ዛሬ ላይ ላለንበት ውድቀት ደግሞ ዘመናቸውን መዋጀት የተሳናቸው የወረዱ ማኅበራዊ እሴቶች/እሳቤዎች እንዳሉ፤ በተለይም በውድቀቱ ምክንያት ብዙ ዋጋ ለመክፈል ለተገደደው ለዚህ ትውልድ የተሰወረ አይደለም።
ከእነዚህ ዘመኑን መዋጀት ከተሳናቸው እሳቤዎቻችን መካከል በዋነኛነት የሚጠቀሰው ችግሮቻችንን/ልዩነቶቻችን በውይይትና በድርድር በሠላማዊ መንገድ የመፍታት የፖለቲካ ባሕል ባለቤት አለመሆናችን ነው። ይህ ችግራችን ከከፍታችን ከማውረድ ባለፈ ዛሬዎቻችንን በአግባቡ እንዳንኖር ዋንኛ ተግዳሮት ሆኖብናል። የፖለቲካ ባሕላችን በየዘመኑ እና ወቅቱ፤ ዘመንና ወቅት በሚዋጅ መንገድ እየተገራ አለመምጣቱ፤ እንደ ሀገር በተለያዩ የእርስ በርስ ግጭቶች እና ጦርነቶች ውስጥ እንድናልፍ አስገድዶናል። በእነዚህ ጦርነቶች እና ግጭቶችም እንደ ሀገር ከባድ ኪሣራ ደርሶብናል።
ከብዙ ኪሳራ በኋላ ጦርነቱ በሠላም ስምምነት/በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት/መቋጨቱ፤ ችግሮችን በአዲስ መንገድ በውይይት እና በድርድር ለመፍታት የሚያስችል ተሞክሮ ከመፍጠር ባለፈ፤ እንደ ቀደሙት የጦርነት እና የግጭት ታሪኮቻችን ተጨማሪ ሀገራዊ የታሪክ ስብራት ከመፍጠር ያለፈ ትርፍ አላስገኘልንም። ቀድሞ በመንግሥት እንደተነገረውም ከጦርነት ምንም ትርፍ እንደማይገኝ ተረጋግጧል፡፡
በርግጥ ጦርነቱን በሠላም ስምምነት ማስቆም፤ ለትውልድ የአሸናፊ ተሸናፊ ትርክትን ከቂም ጋር ላለማውረስ የተደረገ በሳልና ቆራጥ ውሳኔን የጠየቀ፤ በመንግሥት በኩል ስለ ሠላም ያለውን እና ቀድሞም የነበረውን ቁርጠኝነት በተጨባጭ ያሳየ ነው። መንግሥት የሠላም ስምምነቱ ከተፈረመ ማግስት ጀምሮ ከገባው ግዴታ ባለፈ መተማመን ለመፍጠር እና ሠላምን ለማጽናት አስፈላጊ ናቸው ያላቸውን ርምጃዎች በተከታታይ ወስዷል። በስምምነቱ እስካሁን የተገኘው ውጤት እና እፎይታ እንደተጠበቀ ሆኖ ቀሪ ሥራዎችም እንዳሉም ይታመናል።
በተለይ በፕሪቶሪያ ስምምነት እንደተገለጸው፣ በሕገ መንግሥታችንም እንደተደነገገው፣ እንደ ሀገር የሚኖረን አንድ የመከላከያ ሠራዊት ብቻ ነው። ክልሎች በክልል ደረጃ ሕግ ለማስከበር ከሚያስፈልጋቸው ፖሊስ እና ሚሊሺያ ያለፈ የታጠቀ እና የተደራጀ ሠራዊት ሊኖራቸው አይችልም።
በስምምነቱ ላይ በግልጽ የተቀመጠው የሕወሓት ታጣቂዎች ትጥቅ የመፍታት ጉዳይ፤ ከሕገመንግሥታዊ ድንጋጌም ሆነ በአካባቢው ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ ዘለቂ ሠላም እና መረጋጋት ለመፍጠር ካለው ሁለንተናዊ ጠቀሜታ አንጻር ትኩረት ተሰጥቶት ፈጥኖ ተግባራዊ ሊሆን ይገባል። የማንነት እና የአስተዳደር ወሰን ጥያቄ ያለባቸውን አካባቢዎች ጉዳይ ጨምሮ ፤ በጦርነቱ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስና ለማቋቋም የተጀመረው ሥራ፤ ከፍ ባለ የኃላፊነት መንፈስ በተጠናከረ እና በተቀናጀ መንገድ ሊቀጥል ይገባል። በጉዳዩ ዙሪያ ለሚፈጠሩ ችግሮች ፈጣን ምላሽ አስቀምጦ መንቀሳቀስም ያስፈልጋል።
እነዚህን የፕሪቶሪያ የሠላም ስምምነት ዋነኛ አካል የሆኑ ጉዳዮችን፤ በስምምነቱ መሠረት ተግባራዊ ላለማድረግ ምንም አይነት ምክንያት ተቀባይነት የለውም። በጉዳዮቹ ዙሪያ የተቀመጡ ግዴታዎችን አክብሮ መንቀሳቀስ፤ ካለፈው ስህተት በአግባቡ ተምሮ መቆምን አመላካች ነው።
ለስምምነቶቹ ተግባራዊነት ፍላጎት ማጣት፤ ከትናንት አስከፊ ስህተት ካለመማር የተነሳ፤ ለተጨማሪ ስህተት እና ጥፋት ራስን ከማዘጋጀት ተለይቶ የሚታይ አይደለም። ለዚህ አይነት ጥፋት ራሳቸውን ያስገዙ ግለሰቦች እና ቡድኖች አደብ ግዙ ሊባሉ ይገባል!
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 18 ቀን 2016 ዓ.ም