የፕሮጀክቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሐዋሳ እየተካሄደ ነው

2ኛው የኢትዮጵያ ታዳጊ ፕሮጀክቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሐዋሳ ስታዲየም እየተካሄደ ነው፡፡ ሻምፒዮናው ትናንት በሲዳማ ክልል አስተናጋጅነት መካሄድ የጀመረ ሲሆን፣ በውድድሩ ዕድሜያቸው ከ16 እና 18 ዓመት በታች የሆኑ ከአስር ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ የታዳጊ ፕሮጀክት አትሌቶችን ያፎካክራል፡፡

ሻምፒዮናው በተለያዩ ውድድሮች ትናንት ሲጀመር የፍጻሜና የማጣሪያ ፉክክሮች ተካሂደዋል። ከሚያዝያ 16 እስከ 19/2016 ዓ.ም በሚካሄደው በዚህ ሻምፒዮና ትናንት ከ18 ዓመት በታች የ3 ሺ ሜትር ውድድርን ጨምሮ አራት የሜዳ ተግባራት ፉክክሮች ፍጻሜ አግኝተዋል፡፡ በርዝመት ዝላይ ሴቶች፣ በወንዶች አሎሎ ውርወራ፣ በሴቶች ጦር ውርወራ እና ዲስከስ ውርወራ ፍጻሜ ያገኙ የሜዳ ተግባራት ውድድሮች ናቸው።

በሴቶች ከ18 ዓመት በታች ዲስከስ ውርወራ የፍጻሜ ውድድር ሴና ሴሊ ከኦሮሚያ ክልል 23.49 በመወርወር የወርቅ ሜዳሊያ አጥልቃለች። በተመሳሳይ ሜቲ ረታ ከኦሮሚያ ክልል 19.70 በመወርወር የብር ሜዳሊያ እና ሜሮን ኃይሉ ከድሬዳዋ 15.94 ሜትር በመወርወር የነሐስ ሜዳሊያ ተሸልመዋል።

ከ18 ዓመት በታች ወንዶች አሎሎ ውርወራ ፈይሳ ሮቤ ከኦሮሚያ ክልል 12.86 ሜትር በመወርወር የወርቅ ሜዳሊያ ወስዷል። ዓባይነህ ሙዴ ከሲዳማ ክልል 12.08 ወርውሮ የብር ሜዳሊያ አሸናፊ ሲሆን ብሩክ ሉባሞ 11.32 ሜትር በመወርወር የነሐስ ሜዳሊያ አጥልቋል። ከ18 ዓመት በታች ሴቶች ርዝመት ዝላይ ደራርቱ ዳንጊሳ ከሲዳማ ክልል 4.78 በመዝለል 1ኛ ሆና ስታጠናቅቅ፣ መዓዛ ገረመው ከአዲስ አበባ 4.61 ሜትር በመዝለል የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ፣ ኮኬት እምሩ ከኦሮሚያ 4.41 በመዝለል 3ኛና የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ መሆን ችላለች።

ከ16 ዓመት በታች ሴቶች የጦር ውርወራ ሌላው ፍጻሜ ያገኘ ውድድር ሲሆን ብዙነሽ አድማሱ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ሽቶ ባናታ ከኦሮሚያ ክልልና ቢቱ በርሶ ከኦሮሚያ ክልል ከ1ኛ እስከ 3ኛ በመውጣት የወርቅ ብርና የነሐስ ሜዳሊያ ተሸልመዋል።

የ3 ሺ ሜትር ከ18 ዓመት በታች ወንዶችና ሴቶች ውድድር ከፍተኛ ፉክክር በማስተናገድ አሸናፊዎቹ ተለይተዋል። በሴቶች መካከል በተካሄደው ፉክክር አስቴር አርኬ ከሲዳማ 9:17.87 ሰዓትን አስመዝግባ በቀዳሚነት ጨርሳለች። ጥበበ እንየው ከአዲስ አበባ 9:54 ሰዓት 2ኛ እና ህልፈይ ካሣይ ከትግራይ ክልል 9:28.37 3ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀዋል፡፡ በወንዶች መካከል ከፍተኛ ፉክክር የተደረገ ሲሆን ኃይሉ አያሌው ከድሬዳዋ 1ኛ በመሆን የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆናል፡፡ አማኑኤል ሀብቱ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ 2ኛና የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ፣ ተስፋዬ ወዳይ ከኦሮሚያ 3ኛና የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ በመሆን አጠናቀዋል።

የ 800 ሜትር፣ 400 ሜትርና የ100 ሜትር ከ16 ዓመትና ከ18 ዓመት በታች የማጣሪያ ውድድሮች የተካሄዱ ሲሆን ወደ ቀጣይ ዙር ያለፉ አትሌቶች ተለይተዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተሳትፎና ውድድር ዳይሬክተር አቶ አስፋው ዳኜ የውድድሩ ዋና ዓላማ በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ለሚገኙ የፕሮጀክት አትሌቶች የውድድር ዕድል መፍጠር መሆኑን ተናግረዋል። የፕሮጀክቶችን የሥልጠና ሂደት በውድድር በመለካትና በመገምገም ድጋፍ ለማድረግ አመቺ ሁኔታን ለመፍጠር መሆኑንም አክለዋል። በተጨማሪም ከክልልና ከተማ አስተዳደር ለሚመጡ አትሌቶች፣ አሠልጣኞችና ባለሙያዎች የእርስ በርስ የሙያና የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ይጠቅማል። ተተኪና ሀገርን በአሕጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚወክሉ ውጤታማ አትሌቶችን ለማፍራት የሚያግዝ የታዳጊዎች ውድድር መሆኑንም ገልጸዋል።

አቶ አስፋው የታዳጊዎች ውድድር ጥንቃቄ የሚፈልግ በመሆኑ ጠንካራ የሆነ ዝግጅት መደረጉን ገልጸው፣ አትሌቶች በውድድር ተግባራት፣ ከተወዳዳሪዎች ብቃት የአሯሯጥ ቴክኒክ ልምድን የሚቀስሙ ስለሆነ በሙያቸው ብቁ የሆኑና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሥልጠና የወሰዱ ልምድ ያላቸው ዳኞች ተመርጠው ውድድር እየተካሄደ ነው። ከምዝገባ ጀምሮ የውድድሩን ሕግና ደንብ ለሚመለከታቸው አካላት ከማድረስ ጀምሮ ሰፊ ሥራዎች ተሠርተው ወደ ውድድር መገባቱንም አስረድተዋል።

ፌዴሬሽኑ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ከአበረታች መድኃኒትና ከዕድሜ ማጭበርበሮች ጋር ጥንቃቄ እንዲደረግ ቀድሞ ደብዳቤ መላኩን የገለፁት አቶ አስፋው፣ የሕክምና ቡድኑ ለየት ያሉ ቅጾችን በማዘጋጀት ክልሎችን የዕድሜ ግምገማ አሠርቶ እንዲመጡ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ ዕድሜ አጭበርብረው የሚገኙ አትሌቶች፣ አሠልጣኝን እና የቡድን መሪን ተጠያቂ እንደሚያደርግ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል። ይህ እንዳይሆን የማስተማርና የማስጠንቀቅ ሥራ እየተሠራ እንደሆነም ተጠቅሷል።

የዘንድሮ ውድድር በተወዳዳሪ ብዛት የተሻለና ብዙ አትሌቶች በትክክለኛ የእድሜ ደረጃ በመምጣታቸው ይሄንን አጠንክሮ ለማስቀጠል እንደሚሠራም አቶ ዳኜ ገልጸዋል። በሕክምና ቡድኑ ለታዳጊዎች በአበረታች ቅመሞች ዙሪያ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተሠራም ይገኛል። ታዳጊ አትሌቶች ንጹሕ የሆነ አዕምሮቸው ወደ ሌላ እሳቤ ሳይሸጋገር ቅድሚያ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ተብሏል።

በውድድሩ ከ10 ክልሎችና ከሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ ዕድሜያቸው ከ16 ዓመትና 18 በታች የሆኑ 203 ሴትና 247 ወንድ በአጠቃላይ 450 አትሌቶች ይሳተፋሉ። ውድድሩ ዛሬ፣ ነገና ከነገ በስቲያ ቀጥሎ የሚካሄድ ሲሆን የተለያዩ የማጣሪያና የፍጻሜ ውድድሮችም ይጠበቃሉ።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You