አዲሷ መነጽር

ከዓመታት በፊት ከዓለም ገበያ ላይ ወጥተን የሸመትናት ይህቺን አዲሷን መነጽር ስትንቶቻችን እንደምናውቃት ባላውቅም፤ እሷ ግን ከሰሞኑ አንድ አዲስ ነገር አስመልክታናለች:: የማላውቀው በዛና፤ አሁንም ስንቶቻችሁ ይህን አዲስ ነገር እንደተመለከታችሁት፤ አላውቅም ልበል:: ይሁንና ላየንም ላላየንም አሁን ገጭ አድርገን እንይባት::

አዲሷ መነጽር “አስተውሎት” በሚል መፈንቅለ እውርነት ቴክኖሎጂውን አንግባ፤ ከጥበብ ግዛት ላይ ገብታለች:: ደግነቱ ከጥበብ ጋር ለመወዳጀት እንጂ ጦርነትን ለማወጅ አይደለም:: መግባባት ሲኖርብን ግራ እንዳንግባባ፤ “አስተውሎት” ማለት በኢትዮጵያ ሀገራችን፤ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰውና ሮህቦቶች በጋራ የተወኑበት ሳይንሳዊ ፊልም ነው:: የፊልሙ ዋነኛ ባለቤትነት፤ ከአራት ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ እምብርት ላይ የተመሠረተው የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ነው::

ሀገራችንን ዛሬ ላይ ከእያንዳንዱ የሠለጠኑ ሀገራት ዓይን ላይ ባለው የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የቴክኖሎጂ መነጽር ሽክ ቅብርር እንድትል በማሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቋቋመው ይሄው ተቋም፤ የመጀመሪያ የሆነውን የ “አስተውሎት” ፊልምን ይዞ ብቅ በማለት ጀባ ብሎናል:: ኪነ ጥበብ በራሱ ያልገባን እንዲገባን፤ ያልመሰለን እንዲመስለን ግዙፉን የዓይን ተራራ፤ ራስ ዳሽንን መስሎ የተቆለለውን የአዕምሮ ተራራን፤ በብልሃቱ የመናድ ክህሎቱ ጥልቅ የሆነ መነጽር ነውና ከቴክኖሎጂው መንደር ወዲሁ ከተፍ ማለታቸውም ይህንኑ በማጤን ነው::

ዓለም አንድ ሁለት እያለች 4ኛው የቴክኖሎጂ አብዮት ላይ ደርሳለች:: የሦስተኛው ዓለም ሀገራት ግን ከቅዠት መልስም የነቃን አይመስልም:: ህልም ከማየቱ ህልም ፈቺነቱ ተመችቶናል:: አሁን ግን “አሁንስ በቃኝ!” ሳትል አይቀርም:: ለዚህም ይመስላል ከዓመታት በፊት “የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት”ን አቋቁማል “በል ግባ…!” ማለቷ:: አዙሪት እንደያዛት በግ፤ ካገኙት ጋር ሁሉ በእውርነት ከመደንበር፤ እንዲህ አይነቱን የጅምር መሠረት ማኖሩ ፋይዳው ይህ ነው ተብሎ መቼስ ለህጻንም አይነገር:: ቅሉ ግን እንዲህ አይነቱ ቴክኖሎጂ ሳይጋጨን አልቀረምና የሚጎረብጠን ነገር አለው:: ታዲያ ኪነ ጥበቡም አጀንዳውን ሳይዝ፤ ሀዲስ እና ብሉይ ኪዳኑን ሳያገላብጥ፤ ቁርአኑንም ሳይቀራ ዳዊቱንም ሳይደግም ፤ ጠጠሩን የሚያልም ምርጥ ሰባኪ ነው:: እናስ…ቴክኖሎጂውም የኪነ ጥበብን ፍቱን መድኃኒትነት ፈልጎ፤ ከጥበብ ቤት ጎራ ቢል ምኑ ያስገርምና:: የቴክኖሎጂውንም ሆነ የተቋሙን ስም አግዝፎ ለማቆም፤ ሁነኛውን ኪነ ጥበብ በመሻት ተወዳጅተዋል::

ይህንን ተከትሎም በሀገራችን የፊልም ኢንዱስትሪ ውስጥ በይዘቱም ሆነ በአቀራረቡ የመጀመሪያ የሆነው “አስተውሎት” የተሰኘ ፊልም ተሠራ:: እንግዲህ ቴክኖሎጂና ጥበብ ተዳቅለው ይህን የፊልም ልጅ ሰጥተውናል:: ማንን ይመስላል ካላችሁ፤ ለጊዜው መልኩ ግራጫ ነው:: የሚለይለት ወደፊት ይሆናል:: ይህን ስላችሁ፤ ገና በጅምርና ዓላማዊ ግብሩን አሃዱ ብሎ የሚጀምር ስለሆነ፤ ግቡን መምታት በቻለው መጠን ወደፊት መልኩን እናየዋለን:: “አስተውሎት”፤ ከአባቱ ቴክኖሎጂ እና ከእናቱ ጥበብ፤ ከሃሳብ ጽንስነት አንስቶ ፊልም የመሆን ሂደቱን በማጠናቀቅ ተወልዶ ለመመረቅ በቃ:: ሚያዚያ 8 ቀንም በግዙፉ ዋርካ፤ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲሱ ህንጻ ውስጥ፤ ይህንኑ የፊልም ልጅ በርካቶች ስመውና እንትፍ ብለው እደግ ተመንደግ ሲሉ መርቀውታል::

“አስተውሎት” በሚካኤል በላይነህ ተደርሶና ዳይሬክት ተደርጎ፤ በሰውኛ ፊልም ፕሮዳክሽን ተዘጋጅቶ፤ በኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ደግሞ ቀርቧል:: “ኤ አይ”ን በመጠቀም፤ የሰው ልጅና በቴክኖሎጂ የተሠሩ ሮህቦቶች አብረው በመሥራት ለሀገራችን የበኩር ፊልም ነው:: ይህን ፊልም ሠርቶ ለማጠናቀቀም አንድ ዓመት ተኩል ያህል ጊዜ ፈጅቷል::

ዓለማችን በአስተውሎት ስታስብ ስትሠራ፤ ደግሞ ስታስብ ሌላ ስትሠራ፤ በአንድ እጇ የቴክኖሎጂ ቆሎ ዘግና እሱኑ ቆርጥማ ሳታላምጠው፤ ደግሞ እንደገና ለሌላ ቴክኖሎጂ እጇን ስትሰድ… በላይ በላዩ ስትል በስተመጨረሻም ከዚህኛው ዘመን ላይ ደርሳለች:: አሁን ግን መሥራት ብቻም ሳይሆን የሚያስፈልገኝ፤ በራሱ እያሰበ የሚሠራልኝን ነው በማለት፤ በሮህቦታዊ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ላይ ወድቃለች:: ድካም ለምኔ…ሰው ፈጣሪ የሆነበት ሌላ የቴክኖሎጂ ፍጥረት መጥቷል:: እየመጣልንም ነው:: በአንዲት ትዕዛዝ “ታዛዥ ነኝ ጌታዬ!…እሺ እሜትዬ!” እያለ ከማድ ቤቱ ገብቶ እንጀራውን ከምጣዱ፤ ወጡን ከድስቱ ላይ ሲወጠውጥ፤ ውሃውን በማሞቅ እግር አጥቦ ሲያደራርቅ፤ አንዳንዴም ሃሳብ ላይ መሆናችንን ተመልክቶ “ምን ላስብሎት?” ሲል…ይታያችሁና እንዳትጎመዡ:: ዓለም ይህንኑ መሳይ ድንኳን ውስጥ ብትገኝም፤ የኛው ጅምርና ዓላማው የቅንጦት ሙዳ ሳይሆን፤ የችግር አጥንት ነው:: የቅንጦት እየመሰለን አሁን ወግድ እንዳትደርስብኝ! ያልነው እንደሆን፤ ኋላ ዓለም ከኛ ርቃ በሂልኮፕተሯ ከተሳፈረች በኋላ ደንብረን በቅሎ ፍለጋ ወደጓሮ እንዳንሄድም ጭምር ነው:: በፊልሙ ውስጥ እንደምንመለከተውም፤ የቴክኖሎጂውን ጫፍ ለመያዝ ከቻልን፤ ለእያንዳንዱ የሕይወት ዘመን ችግሮቻችን መፍትሔው ከመዳፋችን ስር ነው:: በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የታጠረ ትውልድን ማፍራት፤ በሠለጠነ ወታደር ሀገርን እንደመጠበቅ ነው:: ጊዜው እንደቀድሞው ጋሻና ጃግሬ…ጠመንጃውን ይዘን የምንጠብቅበት አይደለም:: አንድ ቴክኖሎጂ ለመላው ዓለም ነውና ቴክኖሎጂን በቴክኖሎጂ እንጂ በሰደፍና ቆመጥ አይታገሉትም::

በአስተውሎት ውስጥ ነገ ትልቁ የዓይን ማረፊያ ነው:: ትናንት እንደሆንን ሆነን አልፈናል፤ ዛሬም እንዳለን ሆነን አለን፤ ታዲያ ነገስ ? እንዲሁ እንዳለን ሆነን ወደ ነገ ቤት እንግባ…ተዛለቅናታ!፤ ይሄን እንኳን የሚመጣው ጎርፍ የሚፈቅድ አይመስለኝም:: እኛ እሺ ብንል እንኳን ቀጣዩ የዓለም እጣ ፈንታ አይፈቅድልንም:: ቁጭ ብንልም እየገፋ መንዳቱ አይቀርም:: ቴክኖሎጂው በዋናነት፤ የሰው ልጅን የማሰብ የመገንዘብና የማመዛዘን ፤ የማቀድ ምክንያታዊ የመሆን፤ የመማር ቋንቋን የመረዳት አቅምን፤ የሰው ልጅ የራሱን ቀመር በመጠቀም በፍጥነት ለመከወን ያስችላል:: ፊልሙ የተሠራው አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን በመጠቀም ዓለማት ከደረሱበት የቴክኖሎጂ ዋርካ ላይ ቢያንስ ለመንጠልጠል እንኳን መፍጨርጨር አለብን በማለት፤ እስካሁን ለመያዝ የቻለውንም ቅርንጫፎች ለማሳየት ሲሆን፤ ፊልሙ በራሱ ቴክኖሎጂዎቹ በተግባር የተሳተፉበት ነው::

በፊልሙ ውስጥ ከዚያም ከዚህም እያለ የሚነካካቸው፤ በርከት ያሉ ጭብጦችን እናገኝበታለን:: የታሪክ ፍሰቱ፤ በዋናነት በሀገራዊ ጉዳዮች ትከሻ ላይ ተደግፎ የሚሄድ ቢሆንም፤ ቤተሰብ፤ በሳንካ የማይቆም ፍቅር፤ ሙያዊ ሃላፊነት፤ በእውቀትና በጥበብ የበራ የቴክኖሎጂ ላምባ፤ ከአስፋልቱም ከጢሻውም ውስጥ እየመራ ወደ አንድ አቅጣጫ ይወስደናል:: ችግርና ብሶት በወለደው የኀዘን ስሜት ዓይናችንን በእንባ እያረጠበ፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ ጥርሳችንን በፈገግታ ያንቦገቡገዋል:: ትልቁ ነገር ግን አዕምሯችንን በአስተውሎት ጨረርና በለውጥ ሳሙና ሙልጭ በማድረግ፤ በአዲስ ሃሳብና በተስፋ ቁጭት ዛሬን ተግቶ ነገን የብርሃን ሀገር ማድረግ ላይ ነው:: ያጣነው እውቀትና ጥበብ ያለውን ትውልድ አይደለም:: ያጣነው ይህን ጉልበት አንድ አድርጎ ወደ ኃይልነት ለመቀየር እኔ ብሎ የሚወጣውን ቆራጥ ነው::

ከፊልሙ እንጎቻ ላይ ጥቂት ለመቃረም ካልን፤ ፊልሙ ገና ሲጀምር የአብዮቱ ሞተር ለመሆን ይችላል ተብሎ ለታመነበት ሰው ከመንግሥት የተጻፈ የሹመት ደብዳቤ ይደርሰዋል:: ስለቀጣዩ ወሳኝ መንገድ በሁለት ዓይነት ስሜቶች ከፊቱ ላይ ያስመለክተናል:: ትንፋሹን ሳብ አድርጎ በረዥሙ ከተነፈሰ በኋላ በፍጥነት ወደ ተልዕኮው ስፍራ ያቀናል:: ሲደርስ ግን አካባቢው በቆሻሻ ክምር ተሞልቶ ለዓይንም ለአፍንጫም የሚሰነፍጥ ነበር:: ጥቂት በማዘን ኮቱን አውልቆ ሸሚዙን ከእጁ በመጠቅለል፤ ያረጀውንና የዛገውን የበር ቁልፍ ታግሎ ይሰብረዋል:: ወደ ውስጥ ዘልቆ በመግባትም ተዘግቶ የሰነበተውን ጭርንቁስ ቤት ሲያጸዳ ይታያል:: የፊልሙ ዳይሬክተር የማህበረሰቡን ችግር ለማመልከት የተጠቀመው ይህንኑ የሚሰነፍጠውን ቆሻሻና ቤት ነው:: ተፊሪ ዓለሙ ተመስሎ የሚተውነው የለውጡ ሞተር በገሃድ ያለን አንድ የመንግሥት ሹምን ማንነት በመወከል ነው::

ታዳጊው ወጣት ከወደ ክፍለ ሀገር፤ ከአባቱ ሰፊ የቡና ማሳ፤ ጠባቧ የቴክኖሎጂና የፈጠራ መንገድ ተመችታዋለች:: ከቡናው ይልቅም የወዳደቁ ሽቦና ገመዶችን መለቃቀሙ ማርኮታል:: እንደ እናትም እንደ አባትም ሆኖ ያሳደገው አባቱ ግን፤ አንድያ ልጁ ልክ እንደ እርሱ ሀብታም ገበሬ እንዲሆንለት ምኞቱ ነው:: ከወደ ትምህርት ቤት ደግሞ ከአንደኛው አስተማሪው ጋር አይጥና ድመት ሆነዋል:: አስተማሪው በኩርኩምና በማስባረር ታዳጊው ተማሪ ደግሞ፤ የአስተማሪውን ጉዶች በፈጠራት በድሮን ካሜራው በመሰለልና የክፍሉን ተማሪ ሁሉ ሰብስቦ በማሳየት፤ ሁለቱም እልካቸውን ለመወጣት ይዳክራሉ:: ሁሉን ጥሎም ታዳጊው ከክፍለ ሀገር ተነሥቶ ወደ አዲስ አበባ ይጠፋል:: በማያውቃት ከተማ ውስጥ በየጎዳናው የነብሱን ጥም ፍለጋ ይናውዛል:: በሌላ በኩል ወጣቱ ሊቅ፤ ከግል የሙከራ ክፍሉ ውስጥ ሆኖ፤ ተአምር ለመሥራት ሌት ተቀን አቀርቅሮ አንዴም ከቀጫጭኖቹ ውስብስብ ገመዶችና ከፈጠራት ሮህቦት ጋር፤ ሌላ ጊዜም ከአውሮፕላን አጋፋሪ ውሃ አጣጩ ፍቅር ጋር ሲባትል ይሰነብታል:: ብዙ ደክሞ ብዙ ቢሠራም ከሀገሩ አለውልህ ሲል የሚደግፈውም ሆነ የሚቀበለውን በማጣት፤ ተስፋ ቆርጦ አይኑን ወደ ውጭ ያዞራል:: የፈጠራ ሥራውን ይዞ ለመሰደድ ወደ አየር ማረፊያው በማቅናት ላይ ሳለ፤ አብዮተኛው ሹም ደርሶ ከመንገዱ ይመልሰዋል:: በአዲስ የተስፋ ብርሃን ሊሞላው እየታገለ፤ ዳግም በተሻለ ወኔና ሞራል ሲቀጥል ያሳየናል:: በዚሁ መሃል ብዙ የደከመበትና ህልሙ የነበረ ግዙፍ ፕሮጀክት መና ይቀርና በንዴት ገንፍሎ መስሪያ ቁሳቁስን ያወድማቸዋል:: አስቀያሚው አጋጣሚ ደግሞ ባለቤቱ በአውሮፕላን አደጋ አንድ እግሯን ታጣለች:: ይሄኔ ግን የወረወራቸውን ቁሳቁስ ፍለጋ… ተአምር ለመሥራት ይነጉዳል::

አስተውሎት በኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ ውስጥ ፋይዳ ይኖረው ይሆን? ታዲያ ምን ጥርጥር ይኖረውና፤ ለፊልሞቻችን አዲስ እይታ ይፈጥራል:: በፊልም መልክ በመሠራቱና ቁጥሩን በአንድ ከፍ ስላደረገ፤ እንዲሁም አዳዲስ ተዋንያንን ለኢንዱስትሪው ስላበረከተ ብቻም አይደለም:: እስካሁን ባልነበረና አዲስ በሆነ መንገድ ላይ ሄዶ በማሳየቱ፤ ኢንዱስትሪው ዳገት የሆነበትን ቢያንስ አንዱን አለት አንከባሎለታል:: የውጭውን ዓለም ዞር ብለን ከቃኘነው እጅግ በከፍተኛ ገቢና ዝና የሚትረፈረፍበት፤ በሰው ልጆች በሚተወኑ ፊልሞቻቸው ብቻ አይደለም:: ከዚህ ባልተናነሰ መልኩ የሰው ልጆችን ከሌሎች የቴክኖሎጂ ፈጠራ ከሆኑ ገጸ ባህሪያት ጋር በማጣመር፤ እንዲሁም ደግሞ ያለ ሰው ልጆች ፈጠራዎቹን ብቻ በመጠቀም እጅግ ተወዳጅ ፊልሞችን ለዓለም ያበረክታሉ:: ለአብነትም እንደ ካርቱንና አንሜሽን ያሉት ናቸው:: እነርሱ በእነዚህ ድስቶች ላይ አብስለውበታል፤ በትሪውም ደህና አድርገው በመብላት አልፈው ወደ ሮህቦቶች ገብተዋል:: እንደኛ ደግሞ ገና ውሃውንም አላሞቅነውም:: ቢሆንም መሞቁም ሆነ መብሰሉ አይቀርምና ምራቅ እየዋጡም ለማድረስ መትጋት ነው:: ለጥበብ አፍቃሪው አሊያም ለኢንዱስትሪው ብቻም ሳይሆን፤ ቢያድል ለኢትዮጵያ ብሎም ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ነው:: በዚህ ቴክኖሎጂ ለዓለም የሚመጥን ድንቅ ፊልም ቢሠራና ገንዘቡ ቢጎርፍ ኢንዱስትሪው በሩን ዘግቶ ለብቻው አይበላውም:: የሚመጣውና የሚሄደው ሁሉ ከሀገራችን ኢኮኖሚ ላይ ነውና::

ሚያዚያ 8 ቀን ይህንኑ ፊልም ለማስመረቅ ጥሪ ደርሶት ከየአቅጣጫው ያልጎረፈ አልነበረም። ሊቅ ከደቂቁ፤ ተማሪው ከነደንብ ልቡስ፤ ሚዲያው ከነትጥቁ፤ ሙሽራውም ከነአጃቢው ደርሶ አስተውሎትን ለማስተዋል ችሏል። ያ ግዙፍ ዋርካ ሆኖ ቻለው እንጂ እንደታዳሚው ብዛት ቢሆንማ፤ መቆሚያውም መቀመጫውም ከዓይን ይርቅ ነበር። ከብዙም አንድ ይመረጣል:: ፊልሙ ከመጀመሩ አራት ያህል ደቂቃዎች ቀደም ብሎ ነበር… በሰዓቱ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ውላጅ፤ መልክና አለባበሷ የኛው፤ የአማርኛው ቅላጼዋ ግን የፈረንጅ መሳይ አንዲት ሴት፤ ከግዙፉ እስክሪን ላይ ዝግጅቶቹን በማስተዋወቅ ላይ ነበረች። ድንገት ከአዳራሹ ውስጥ ያልተጠበቀ ጭብጨባና ፉጨት በረከተ። ሰው ሁሉ በነቂስ ከመቀመጫው ላይ ተነስቶ ቆሟል። ከጎኔ ቁጭ ብሎ የስልኩ ስክሪን ላይ ካፈጠጠው ሰውዬና ከወንበሮቹ በቀር። በአንድ እግሩ የቆመው አዳራሽ እረገብ ሲል፤ መቀመጫዬን እንዳልስታት በከፊል ጎንበስ ብዬ ብመለከት ሰውዬው፤ በግራ መጋባት ፈጦ እኔኑ ይመለከተኛል። ቁጭ እንዳልኩ “ምንድነው?” አለኝ፤ ዶ/ር ዐቢይ አልኩት… ወይኔ ምን ነክቶኝ ነው ከዚህ ሁሉ ሰው መሃል ብቻዬን ከወንበሩ ላይ መጎለቴ እኔ ማነኝና፤ ብሎ ያሰበ ይመስላል። በጥርጣሬ ግራ ቀኙን ገርመም እያደረገ፤ ለመካስ ይሁን ካለፈ ኋላ መቆም ማጨብጨብም ሳይዳዳው አልቀረም። አኳኋኑ እኔንም ግራ እያጋባኝ በቀስታ ብመለከተው፤ “ፖለቲካና ጉንፋን የት ያዘህ አይባልም…” ሲል በአፉ ሲልጎመጎም ውሃውን አንስቶ ፉት አላት። በትልቁ ለመሳቅ አስቤ በትንሹ ፈገግ አልኩኝ። ምኑን ከምኑ እንዳደረገው ግን ምንም ትዝ አይለኝም። ይሁንና፤ ፊልሙን ከታዳሚው ጋር አብረው ለመመልከት የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፊልሙም ሆነ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፤ የሃሳቡ ምንጭ ናቸው። ከአራት ዓመታት በፊት የሃሳቡን ድፍድፍ በመጠንሰስ ከቴክኖሎጂው መቅረዝ ላይ አበባውን አኑረውበታል። በወቅቱም፤“…በትልቁ እናስባለን፤ በትንሹም እንጀምራለን” ብለው ነበርና ሲገቡ ጀምሮ ሃሳብና ዓይኑን ከተቀመጡበት አካባቢ ሳይነቅል፤ ዛሬስ ምን ይሉ ይሆን እያለ ድምጻቸውን በአካለ ቅርበት ለመስማት የቋመጠ ሁሉ ሳይሆንለት ቀርቷል። እሳቸውም፤ እስቲ ዝም ብላችሁ ፊልማችሁን ተመልከቱ፤ እኔም ልረፍበት ያሉ ይመስላል:: ቁጭ ብለው ፊልማቸውን ኮምኩመው ሲያበቁ፤ አንዳችም ሳይተነፍሱ በገቡበት አግባብ ተመልሰው ወጥተዋል።

በዚህኛው ትውልድ ሆነን፤ አሻግረን ሌላ ትውልድ የምንመለከትባትን የ “አስተውሎት” ፊልምን ዳሰሳዊ ቡትረፋ ይህችን ታህል ከነጨብን ይበቃልና ቀሪዋን ከፊልሙ ጥገቧት::

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You