የአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት የሚወሰነው ለለውጥ የተነቃቃ እና ለውጥን በጠንካራ ዲሲፕሊን መሸከም የሚችል ትውልድ መፍጠር ሲቻል ነው። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ስለ ለውጥ ሆነ ከለውጥ ሊገኝ ስለሚችሉ ትሩፋቶች ማሰብ ከምኞት ያለፈ ትርጉም ሊኖረው አይችልም ።
በተለይም እንደኛ ዓይነት በትውልዶች መካከል ከፍ ያለ ተለውጦ የመታየት መሻት ባለባቸው ሀገራት፤ ለውጥን በተጨባጭ እውን ለማድረግ፤ ከሁሉም በፊት እንደ ማኅበረሰብ ራስን በአግባቡ ለማወቅ የሚያስችል ድፍረት፤ ለዚህ የሚሆን በቂ ዝግጁነት መፍጠር ያስፈልጋል ።
የአንድ ማኅበረሰብ ማንነት የሚመሠረተው በዛ ማኅበረሰብ ውስጥ ባሉ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ እሳቤዎች ነው። በነዚህ ውስጥ በዋንኛነት መንፈሳዊ እና ባሕላዊ እሴቶች ትልቁን ስፍራ የሚይዙ ናቸው። እነዚህን እሴቶች በለውጥ እሳቤ የመቃኘቱ እውነታ በለውጥ ወቅት በቂ ትኩረት የሚሻ ነው ።
እነዚህ እሴቶች ታሳቢ ያደረጉ ትርክቶች ምን ያህል ለለውጡ አቅም ስለመሆናቸው ጊዜ ወስዶ ማየት አስፈላጊ ነው። ትርክቶቹን በአግባቡ በመግራት፣ ከማኅበረሰቡ የመለወጥ መሻት ጋር ተናበው የሚሄዱበትን/ዘመኑን የሚዋጁበትን የአስተሳሰብ መሠረት መገንባትም ያስፈልጋል ።
በየትኛውም የዓለም ክፍል የተደረጉ ስኬታማ የለውጥ ፍላጎቶች፣ ለስኬታቸው እንደ ዋነኛ አቅም ተደርጎ የሚወሰደው፣የማኅበረሰቡን የቀደሙ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ እሳቤዎች በመግራት አዲሱን የለውጥ እሳቤ መሸከም የሚችሉበትን ዕድል መፍጠር በመቻላቸው ነው ።
ይህን ማድረግ ባልተቻለበት ሁኔታ፣ የትኛውም አይነት የለውጥ መነቃቃት ተጨባጭ የለውጥ አቅም ሆኖ በማኅበረሰብ ውስጥ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት አይቻልም። ቢሞከር እንኳን “በአሮጌ አቁማዳ አዲስ ወይን ጠጅ” እንደሚባለው ውጤቱ ኪሳራ እንጂ ስኬት ሊሆን አይችልም። ለውጥ በባሕሪው ሰፊ ማኅበራዊ መሻቶችን የያዘ ነው፤ ብዙ ተጠባቂ ትሩፋቶችንም የተሸከመ ነው፤ ጉዞው በተለወጠ ማንነት፤ በጥንቃቄ፣ በትዕግስት እና በሆደ ሰፊነት ሊመራ ይገባል። ይህን ማድረግ ካልተቻለ ሊያስከትል የሚችለው ጥፋት ይዞት ከተነሳው ተስፋ የከፋ እንደሚሆን የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ያመለክታሉ ።
በእኛም ሀገር በተለያዩ ወቅቶች የተደረጉ የለውጥ ንቅናቄዎች፤ በብዙ ተስፋ ታጅበው፤ ከፍ ባለ ሕዝባዊ ተሳትፎ ቢጀመሩም፤በተለወጠ ማንነት ባለመመራታቸው እና ለውጡን ሊሸከም የሚችል ማኅበራዊ የአስተሳሰብ መሠረት መገንባት ባለመቻሉ ፍጻሜያቸው በብዙ ጥፋት የታጀበ ስለመሆኑ ታሪካችን በተጨባጭ የሚዘክረው ነው ።
በቅርቡ በብዙ ተስፋ እና ሕዝባዊ መሠረት የጀመርነው ለውጥም ቢሆን በተገቢው መልኩ ለውጡን የሚሸከም ሕዝባዊ የአስተሳሰብ መሠረት መፍጠር ባለመቻላችን፤ በለውጥ ወቅት በሚያጋጥሙ መንገጫገጮች ለመፈተን የተገደደበት ሁኔታ ተፈጥሯል፤ በዚህም ለውጡን በእልልታ የተቀበሉ ግለሰቦች እና ቡድኖች ሳይቀሩ በለውጡ ላይ ጠላት የሆኑበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
እነዚህ ኃይሎች ባልተለወጠ ማንነት የለውጡ አካል እና አቅም ሆነው ለመጓዝ ያደረጉት ጥረት፤ “በአሮጌ አቁማዳ አዲስ ወይን ጠጅ” እንደሚባለው፤ ለለውጡ የችግር ምንጭ ከመሆን ያለፈ ፋይዳ እንዲኖራቸው አላስቻላቸውም። ለራሳቸው ግራ ተጋብተው የለውጥ ወቅት ግራ መጋባት ምንጭ ሆነዋል። በዚህም ሀገር እና ሕዝብን ያልተገባ ብዙ ዋጋ አስከፍለዋል ።
ይህ በየዘመኑ ሀገርን የሚፈታተን ባልተለወጠ ማንነት የለውጥ ኃይል ለመሆን የሚደረግ ግርግር፤ “ግርግር ለሌባ ይመቻል“ እንደሚባለው ብዙ የማኅበረሰባችንን በጎ እሴቶች ለአደጋ ተጋላጭ አድርጓል። ይህ እንደ ጥላ የሚከተለን ሀገራዊ ችግር አንድ ቦታ ላይ መቆም ካልቻለ፤ የሕዝባችን የለውጥ መሻት መቼም ቢሆን ተጨባጭ እውነት ሊሆን አይችልም ።
ለዚህ ደግሞ ከሁሉም በላይ የለውጥ ባለቤት የሆነው ሕዝባችን እውነታውን በአግባቡ ሊያጤነው ይገባል። በተስፋው ላይ የሚቆምሩ ግለሰቦች እና ቡድኖችን በቃችሁ በማለት፤ መሻቱን እውን የሚያደርግበትን ሀገራዊ ዓውድ መፍጠር ይኖርበታል። ይህን በማድረግ ለራሱም ሆነ ለመጪው ትውልድ የተሻለች ሀገር መፍጠር የሚያስችል መሠረት መጣል ይኖርበታል፤ ለዚህ ደግሞ ከዛሬ የተሻለ ጊዜ የለም፤ አይኖርምም!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17 ቀን 2016 ዓ.ም