አዲስ አበባ፡- ስምምነቱ 40 ሚሊዮን ዜጎችን የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባን ለመተግበር የዲጂታል መታወቂያ ቁሣቁስ አቅራቢ ከሆነው ላሚኖ ኢንጂነሪንግ ጋር ቁሣቁሦችን ለመግዛት በትናንትናው እለት የግዥ ውል ተፈራርሟል ፡፡
የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር የቦርድ ሊቀመንበር አቶ አቤ ሳኖ እንደገለጹት ስምምነቱ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ግቦችን ለማሳካት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ 6ሺህ የምዝገባ ቁሣቁሦች ለመግዛት የተደረገ ነው፡፡
ይህ የግዢ ውል ስምምነት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በ11ሺህ የባንክ ቅርንጫፎች 40 ሚሊዮን ዜጎችን የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡
አቶ አቤ ይህንን ውል ስምምነት ለመፈጸም ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጥቶ አምስት ተቋማት ቢወዳደሩም ላሚኖ ኢንጂነሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ማሸነፉን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ጨረታውን አሸንፎ ውል የተፈራረመው ተቋም በውል ስምምነቱ መሠረት ቁሣቁሦችን በወቅቱ በማቅረብ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ሊቀመንበሩ አሳስበዋል፡፡
የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ዮዳሔ አርዓያሥላሴ በበኩላቸው በስምምነቱ መሠረት በቀጣይ ወደ ሥራ የሚገባው ግዥ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ በፋይናንስ ዘርፉ ተደራሽ እና አካታች እንዲሆን ከማስቻል ባለፈ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ቀልጣፋ የፋይናንስ ሥርዓትን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡
በባንኮች የሚኖረው ስድስት ሺ የመመዝገቢያ ማሽኖችም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ምዝገባውን ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል፡፡
አቶ ዮዳሔ ስምምነቱ በኢትዮጵያ ማንነትን የሚያረጋግጥ ሰነድ በማጣት ምክንያት በፋይናንስ ዘርፍ ላይ ያልተካተተው 30 በመቶ በላይ የሚሆነው የሀገሪቱ ነዋሪ በፋይናንስ ሥርዓት እንዲካተት አቅም እንደሚፈጥር ገልጸው፤ የፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ለተካተቱ 40 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ደንበኞች ቀልጣፋ፣ ተዓማኒ እና የተሻሻለ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን ለማድረስም ጥቅሙ የጎላ መሆኑ ጠቅሰዋል፡፡
ይህም የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን በፋይናንስ ዘርፍ መተግበር በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ ግልጽነትን እና አካታችነትን ለማጎልበት ትልቅ ሚና የሚጫወት መሆኑን አመልክተው፤ በቁሳቁሦቹ ላይ የሚያስፈልገውን የሶፍትዌር መጫን እና ማዘጋጀት ሒደት የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የሚያከናውን ይሆናል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር 32 ባንኮችን በአባልነት አካቶ መያዙም ተገልጿል፡፡
መስከረም ሰይፉ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17 ቀን 2016 ዓ.ም