መሠረታዊ የመድኃኒቶች መዘርዝር መዘጋጀቱ የእንስሳት ጤናን ለማሻሻል ይረዳል

አዲስ አበባ፡– መሠረታዊ የእንስሳት መድኃኒቶች መዘርዝር መዘጋጀቱ አጠቃላይ የእንስሳት ጤና ዘርፍን ለማሻሻል እንደሚረዳ የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ ገለጹ፡፡

ባለስልጣኑ ብሩክ ኢትዮጵያ ከተባለ መንግሥታዊ ካልሆነ ድርጅትና ከኢትዮጵያ እንስሳት ሐኪሞች ማኅበር ጋር በመተባበር አስፈላጊ የሆኑ የእንስሳት መድኃኒት መዘርዝርን በትናንትናው ዕለት ይፋ አድርጓል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ በወቅቱ እንደገለጹት፤ መሠረታዊ የእንስሳት መድኃኒቶች መዘርዝር መዘጋጀቱ መንግሥት አጠቃላይ ለእንስሳት ጤና ዘርፍ መሻሻል ካስቀመጠው ፖሊሲ አኳያ ውጤታማ ሥራ ለመሥራት የጎላ ሚና ይኖረዋል፡፡

የመድኃኒት መዘርዝሩ ለስድስት የእንስሳት ዝርያዎች የሚውል አስፈላጊ የመድኃኒት መዘርዝር መሆኑን ጠቅሰው፤ በእንስሳት ላይ የሚያጋጥሙ በሽታዎችን በነባሩ መድኃኒት መከላከል ባይቻል ተጨማሪ ጥናት ሳያስፈልግ በተዘጋጀው መዘርዝር መሠረት መድኃኒት ከውጭ ማስገባት ወይም በሀገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በሀገር አቀፍ ደረጃ አስፈላጊ የሆኑ የእንስሳት መድኃኒት መዘርዝር ባለመኖሩ ዘርፉ በከፍተኛ ደረጃ መፈተኑን ገልጸው፤ በቀጣይ በተዘጋጀው የመድኃኒት መዘርዝር መሠረት የእንስሳት በሽታን በቀላሉ መከላከል እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

ባለሥልጣኑ የእንስሳትና የግብርና ምርት ጥራትን ለማስጠበቅ በትኩረት እየሠራ መሆኑን የጠቆሙት አምባሳደር ድሪባ፤ የመድኃኒት መዘርዝሩ ለቀንድ ከብቶች፣ ለበግና ፍየል፣ ለአህያ፣ ለፈረስ፣ ለዶሮ፣ ለግመል፣ ለድመትና ውሻ የሚያገለግል ነው ብለዋል፡፡

የነበረው የእንስሳት መድኃኒት አቅርቦትና የጥራት ደረጃ አነስተኛ በመሆኑ የተዘጋጀው የመድኃኒት መዘርዝር አቅርቦቱን በማሻሻል የተለያየ የእንስሳት መድኃኒት አማራጮች እንዲኖሩ በማድረግ በኩል ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ አመልክተዋል፡፡

በመድኃኒት መዘርዝር ዝግጅቱ የእንግሊዝ መንግሥት፣ የተለያዩ አጋር አካላትና ከስድስት ዩኒቨርስቲዎች በተውጣጡ መምህራን ተጠንቶና ተገምግሞ ተግባራዊ እንዲሆን በግብርና ሚኒስቴር እንዲፀድቅ መደረጉን አምባሳደር ድሪባ አስረድተዋል፡፡

መንግሥት ከውጭ የሚገቡ የእንስሳት መድኃኒቶችን በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ አቅጣጫ ማስቀመጡን አውስተው፤ ለተግባራዊነቱ ባለሥልጣኑ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

የብሩክ ኢትዮጵያ ተጠሪ አቶ ዮሐንስ ቃሲም በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ መሠረታዊ የሆነ የእንስሳት መድኃኒቶችና ክትባቶች በበቂ ሁኔታ አለመኖር የእንስሳትን ደኅንነት ለማሻሻል የሚያስችል የእንስሳት ጤና አገልግሎት ግንባታ ላይ ተግዳሮት ሆኖ ቆይቷል ብለዋል።

ኅብረተሰቡ የእንስሳት መድኃኒትን በአግባቡ እንዲጠቀም የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡ የእንስሳት መድኃኒት አስመጭዎች ትርፍን ብቻ መሠረት አድርገውና ለኅብረተሰቡ ከሚሰጠው ጠቀሜታ አንፃር መዝነው ባለመሥራታቸው ዘርፉ በሚፈለገው ልክ ውጤታማ ሳይሆን ቀርቷል ብለዋል።

በቀጣይ የክልል ግብርና ቢሮዎች የእንስሳት መድኃኒት ግዥ ሥርዓታቸውን እንዲያሻሽሉና አስፈላጊ የሆኑ መድኃኒት ግዥ እንዲፈፅሙ የመድኃኒት መዘርዝሩ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።

አስፈላጊ የእንስሳት መድኃኒቶች በገበያ ላይ የሚገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸትና የተሻለ የእንስሳት በሽታን የመመርመር አቅም እንዲሻሻል ድርጅቱ የተለያዩ ሥራዎችን በአጋርነት እንደሚሠራም ጠቁመዋል፡፡

አማን ረሺድ

 አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You