በኤክስፖው ከ30 ሺህ በላይ ዜጎች ነፃ የሕክምና ምርመራና የምክር አገልግሎት ያገኛሉ

  • ዓለም አቀፍ የጤና ኤክስፖ ከግንቦት 9 እስከ 11 በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፡- በአፍሮ ኤዥያ ኤክስፖ ከ30 ሺህ በላይ ዜጎች ነፃ የሕክምና ምርመራና የምክር አገልግሎት እንደሚያገኙ የኤክስፖው አዘጋጅ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡ ኤክስፖው “ድልድዮችን እንገንባ ሕይወትን እናድን” በሚል መሪ ቃል ከግንቦት 9 እስከ 11 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ይካሄዳል፡፡

የኤፍ ዚ ማርኬቲንግ እና ኮሙኒኬሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ዝክረ ሔኖክ በጉዳዩ ላይ ትናንት በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ እውቀት ለመለዋወጥ፣ ትብብርን ለማጎልበት እና የላቀ የጤና አጠቃቀም መፍትሔዎችን ለማሳየት በርካታ ነፃ ምርመራዎችን ለማኅበረሰቡ ለመስጠት ያለመ ነው፡፡ በዚህም ከ30 ሺ በላይ ለሚሆኑ ጎብኚዎች ነፃ የጤና ምርመራ እና የምክር አገልግሎቶችን ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል፡፡

ለኤክስፖው አፍሮ-ኤዥያ የሚለው ስም መመረጡ ኢትዮጵያ ከአፍሪካም ሆነ ከኤዥያ ጋር ያላትን ጂኦግራፊያዊ፣ ታሪካዊ እና ባሕላዊ ትስስር የሚያመላክት ነው ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ ስያሜው አፍሪካን እስያ ላይ አፅንዖት ቢሰጥም ኤክስፖው ዓለማቀፋዊ ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም ከሀገራችን እና ከተለያዩ የዓለማችን ሀገሮች የተውጣጡ ከ400 በላይ የጤና ተቋማት፣ የኢንዱስትሪ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ይሳተፉበታል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የሀገራችን ባለሙያዎችን ጨምሮ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተውጣጡ ከሁለት ሺህ በላይ የጤና ባለሙያዎች እንደሚሳተፉ ጠቅሰው፤ ኤክስፖው የእውቀት ልውውጥ፣ ፈጠራና የትብብር መድረክ በመፍጠር ለማኅበረሰቡ ነፃ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል ጠቁመዋል፡፡

ኤክስፖውን ኤፍ ዚ ማርኬቲንግ እና ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከሠላም ሔልዝ ኮንሰልታንሲ ጋር በትብብር እንዳዘጋጁት የተገለጸ ሲሆን፣ ጤና ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን፣ ላልማር ኮንሰልታንሲና የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት በአጋርነት እንደሚሳተፉ ተጠቅሷል።

ፋንታነሽ ክንዴ

 አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You