ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀብትን በማስተባበር የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች ነው

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀብትን በማስተባበር ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ አስረኛው የአፍሪካ ዘላቂ ልማት ቀጣናዊ ፎረም (ARFSD-10) በትናንትናው ዕለት በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተካሂዷል፡፡

በፎረሙ ላይ ንግግር ያደረጉት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ አጀንዳ 2063 የዘላቂ ልማት ግቦችን በመተግበር የመጡ ለውጦችንና ችግሮችን ለመገምገም ጊዜውን የጠበቀና አስፈላጊ ፎረም ነው።

የኢትዮጵያ የልማት ተሞክሮ የሚደነቅና አበረታች ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ኢትዮጵያ የሀገርና የውጭ ሀብትን በማስተባበር ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች መሆኑን ገልጸዋል።

በአጀንዳ 2063 አተገባበር ዙሪያ አስገራሚ ውጤት ካሳዩ ጥቂት የአፍሪካ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን ጠቁመው፤ ይህ ተሞክሮ ቀሪ የአጀንዳ 2063ን ሥራዎችን ለመፈጸም እንደ አብነት ያገለግላል ነው ያሉት።

የሀገር ውስጥ ሀብትን ለኢንቨስትመንት ማዋል ያለውን ጠቀሜታ አይተናል ያሉት ዶክተር ፍጹም፤ የሀገር ውስጥ ገቢን ለውሃ፣ አፈርና ደን ጥበቃ፣ ለአየር ንብረት ለውጥና ለትምህርት መሻሻል በማዋል ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ በተሠራው ሥራም ውጤት ስለመገኘቱ ገልጸዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አፍሪካ ብዙ ችግሮች አጋጥመዋታል ያሉት ሚኒስትሯ፤ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የጂኦ ፖለቲካል ውጥረት፣ የኑሮ ውድነትና የኢኮኖሚ አለመረጋጋቶች ከችግሮች መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

ችግሮቹ ዓለም አቀፍ ቢሆኑም በተለየ ሁኔታ አፍሪካን እየጎዱ መሆኑን አመልክተው፤ የዘላቂ ልማት ትግበራን ለማሳካት እንቅፋት መሆናቸውን ጠቅሰዋል። በአሕጉሪቷ ችግሮችን ለመቅረፍና ድህነትን ለማስወገድ ብሎም ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የሁሉንም ወገን ቁርጠኝነትና ፈጠራ የታከለበት ሥራ ያስፈልጋል ብለዋል።

እንደ ዶክተር ፍጹም ገለጻ፤ በአፍሪካ ድህነት ቅነሳ፣ የሠላም ግንባታ፣ ጥራት ያለው ትምህርት መስጠት፣ መሠረተ ልማት ማሟላት፣ የጤና ጥበቃን ማስፋፋት ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ዓይነተኛ መንገዶች ናቸው ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሐፊና የዋና ጸሐፊው ተወካይ አሚና መሐመድ እንደገለጹት፤ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ችግሮች የተነሳ የአፍሪካ አሕጉር ተጎጂ እየሆነ ነው።

በቅርቡ የተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ የአየር ንብረት መዛባት፣ የአየር ብክለት ለአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ እድገት መቀነስ የራሱ የሆነ አሉታዊ አስተዋፅዖ ማድረጉን ገልጸዋል።

ግጭትና አለመረጋጋት የአፍሪካን አጀንዳ 2063 እያስተጓጎሉት መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ዋና ጸሐፊዋ፤ የዘላቂ ልማት ግቦች በተያዘላቸው ጊዜ እንዳይሳኩ እያደረገ ነው ብለዋል። አጀንዳ 2063 ዘላቂ ልማትን ለማሳካት በተደረገው ጥረት በመጀመሪያው አስር ዓመት ውስጥ የተሳኩ ብዙ ሕልሞች ቢኖሩም፤ አሁንም የሚቀሩ ስለመኖራቸው አመልክተዋል።

የአፍሪካ ኅብረት ሕልሞችን ለማሳካት ኢንቨስትመንትን ማፋጠን፣ ፖሊሲን ማሻሻል፣ ቴክኖሎጂን ማሳደግ፣ ትምህርትን ማስፋፋትና መሰል ሥራዎችን በጋራ መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

አጀንዳ 2063 ከፊቱ ብዙ ፈተናዎች ስለመደቀናቸው ያነሱት ምክትል ዋና ጸሐፊዋ፤ አሁን የተመዘገቡ ውጤቶች በቂ ባለመሆናቸው እንደ አሕጉርና እንደ ሀገራት ሁኔታ የኢኮኖሚ እድገትን በማሳደግ፣ ግጭትን በመቀነስና በጋራ በመሥራት ዘላቂ ልማትን ማሳካት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ም/ዋና ጸሐፊዋ እንደገለጹት፤ ድህነት ዘላቂ የአፍሪካ አሕጉር ችግር ነው፤ ይህን ለመቅረፍ ዘላቂ የምግብ አቅርቦትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ለዚህም የግብርና መርሐግብርን በማዘመንና በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ይገባል።

ሞገስ ፀጋዬ

 አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You