ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርሕ የባሕር በር ተጠቃሚ የምትሆንበትን መንገድ ማጠናከር ይገባል

ባሌ ሮቤ፡- ኢትዮጵያ በሠጥቶ መቀበል መርሕ የባሕር በር ተጠቃሚ የምትሆንበትን መንገድ ማጠናከር እንደሚገባ መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ አመላከተ::

በመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ “የባሕር መውጫና ኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ የፓናል ውይይት መድረክ ትናንት ተካሂዷል::

ዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ፣ ምርምር፣ ማኅበረሰብ አገልግሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት በዛብህ ወንድሙ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ባደረገ አካሄድ የባሕር መውጫ ባለቤት የምትሆንበትን አማራጮች ማስፋት ይኖርባታል::

ከባሕር በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ በሠላማዊ መንገድና በውይይት ከምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሀገራት ጋር በመሥራት ዓላማዋን ለማሳካት አስቦ መንቀሳቀስ ይገባል ብለዋል::

የባሕር በር ጉዳይ አሁንም ወሳኝ አጀንዳ መሆን እንዳለበት ያነሱት በዛብህ (ዶ/ር)፤ መገናኛ ብዙኃን፣ ምሑራንና የተለያዩ የኅብረተሰብ አካላት ጉዳዩ ተገቢውን ውጤት እስኪያስገኝ ድረስ ይበልጥ መሥራት እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል:: ዩኒቨርሲቲው በባሕር በር ሀሳብ ላይ ጥናትና የውይይት መድረክ በማዘጋጀት ማኅበረሰቡ ጉዳዩን አጀንዳ አድርጎ እንዲቀጥል የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል::

በዩኒቨርሲቲው ተመራማሪና የቴክኖሎጂ ሽግግርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር ሙሐመድ ጀማል (ዶ/ር)፤ በባሕር በር ጉዳይ ለውይይት መነሻ የሚሆን ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል::

በጽሑፋቸው የባሕር በር ከሌላቸው 44 የዓለም ሀገራት መካከል ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላት ሀገር ኢትዮጵያ መሆንዋን ጠቁመው፤ በአፍሪካ ከሚገኙ 17 የባሕር በር አልባ ሀገራት መካከል ደግሞ ሲሶው ሕዝብ የሚኖረው በኢትዮጵያ መሆኑን አስረድተዋል::

ከቀጣናው ሀገራት ጋር የጋራ ተጠቃሚነትን ማዕከል ያደረጉ የውይይት መድረኮችን በመፍጠር ሠፊ ሕዝብ ያላትና ከባሕር በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኘውን ሀገር የወደብ ባለቤት የምትሆንባቸው አማራጮችን ማጠናከር ይገባል ሲሉ ተናግረዋል::

በፍትሕና በርትዕነት ላይ የተመሠረቱ የዲፕሎማሲ መንገዶችን መጠቀም እንደሚገባ ያመላከቱት ሙሐመድ (ዶ/ር)፤ የተደራጀና የወደፊቱን የሚያይ የነቃ ማኅበረሰብ ካለን የባሕር በር ባለቤትነትን በሠላማዊ መንገድ ማሳካት ይቻላል ብለዋል::

በኢኮኖሚያዊ አቅም የተደገፈ ፍላጎትን ለማሳካት ቤልጂየምና ኔዘርላንድ እንዲሁም የሰሜን አሜሪካና ሌሎች ሀገራት እንዳደረጉት መሬት እስከመለዋወጥ የሚደርስ ስምምነት በመመሥረት የባሕር በር ማግኘት የሚቻልበት አማራጭ መኖሩን አመላክተዋል::

የውይይቱ ተሳታፊዎች ታሪክን መነሻ በማድረግ በሠላማዊ መንገድ የባሕር በር ባለቤትነትን ማሳካት እንደሚገባ ሀሳብ ሰጥተዋል:: በመድረኩ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የአስተዳደና የፀጥታ አካላት እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ተገኝተዋል::

ጌትነት ተስፋማርያም

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16/2016 ዓ.ም

Recommended For You