የብርቱዎቹ ሀገር – ቻይና

ቆይታዬን የምተርክላችሁ ድህነትን በወሬ ሳይሆን በተግባር የቀበረች፤ እልፍና አልፍ መሆን ጸጋ እንጂ ርግማን አለመሆኑን በብልጽግናዋ ያስመሰከረች፤ ቢሊዮን ሕዝቦችን አቅፋ አንድነቷን ያጸናች፤ በጥቂት አስርት ዓመታት አስደማሚ ልፋትና ትጋት በኢኮኖሚው፤ በፖለቲካውና ማኅበራዊ ዘርፍ ከዓለም ቀደምት ሀገራት አንዷ ስለሆነችው የብርቱዎች ሀገርና የትጋት ተምሳሌት ቻይና ነች።

በዚህች የትጉኃን ሀገር “የሕዝብ ቁጥር መብዛት የዕድገት ሰንኮፍ ነው፤ የብልጽግና ጸር ነው” የሚል አባባል ከተረትነት ያለፈ ትርጉም የለውም። ለምን ቢባል አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ሕዝቦችን አቅፋና አንድነቷን አጽንታ የዓለም ፖሊስ ነን የሚሉ ሀገራትን ጭምር ባስገረመ መልኩ የልዕልና ጫፍ ላይ ደርሳ ታይታለችና። በዚህም እጅ፣ እግርና ጭንቅላት ያለው ሰው በአግባቡ ከተመራና ከሠራ ሸክም ሳይሆን ጸጋ መሆኑን በአደባባይ አረጋግጣለች። ቻይና ከድህነት ለመውጣት ባደረገችው ጥረት “የዋን ቻይልድ“ የአንድ ልጅ ፖሊሲን በጥንቃቄ መተግበሯ ዛሬ ላይ የሕዝብ ቁጥር ዕድገት የማያሳስባት ሀገር እንዳትሆን አስችሏታል።

እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ከአፕሪል 01 እስከ 06/2024 በቻይናዋ ወደብ ከተማ ውቧ ዢያሜን የነበረኝ ቆይታ በብዙ መደመም፣ መገረምና ቁጭት የተሞላ ነበር። የከተማዋ አረንጓዴነት፣ ጽዳት፣ የሕዝቡ ስልጣኔና ሕግ አክባሪነት የመደመሜና የመገረሜ ምክንያት ሲሆን፤ ሁሉ ሞልቷት አሁንም በድህነት ውስጥ ያለችው የሀገሬ ሁኔታ ደግሞ የቁጭቴ መንስዔ ነበር።

ዢያሜን የቻይና የወደብ ከተማ ስትሆን እጅግ የሚያማምሩ ሰማይ ጠቀስ ህንጻዎች፣ ያለምንም መጨናነቅ ሽው ዕልም የሚባልባቸው ዘመናዊና ውብ መንገዶች፣ የአረንጓዴ ስፍራዎችና ወደብን ጨምሮ የእልፍ መዝናኛዎች መገኛ ናት። ከቻይና መዲና ቤጂንግ ዢያሜን ለመድረስ ሦስት ሰዓት የሚፈጅ የአየር በረራ ማድረግን የሚጠይቅ ነው። እኔ ዢያሜን የደረስኩት በሀገሩ ሰዓት አቆጣጠር ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ሲሆን ነበር።

ከኤርፖርት እስከተያዘልኝ ሆቴል በነበረኝ ጉዞ በዚያ ሌሊት በዢያሜን የተመለከትኩት የመኪና ብዛትና የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ቻይናውያን ሌት ተቀን ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ለኑሮና ዕድገት እንደሚተጉ የመሰከረልኝ እውነት ነው። በመዲናችን አዲስ አበባ ረፋድና እኩለቀን ላይ በየሆቴሉና በየመዝናኛ ስፍራው ተደርድረው የምመለከታቸው መኪኖች ብዛትና የቻይናውያኑ የእኩለ ሌሊት የመኪና ጥድፊያ የሀገሬንና የቻይናን የዕድገት ልዩነት ምክንያት በተወሰነ መልኩ እንድረዳ አስችሎኛል።

ከአሥርት ዓመታት በፊት በዕድገት እዚህ ግባ በማይባል ደረጃ ላይ ትገኝ የነበረችው ሕዝባዊት ሪፑብሊክ ቻይና ፣ በምሥራቅ እስያ የምትገኘ አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ሕዝቦችን አቅፋ የያዘች ሀገር ናት። ቻይና አምስት ጂኦግራፊያዊ የሰዓት ዞኖች መገኛ ስትሆን፤ ከ14 ሀገራት ጋር መዋሰኗ ግዙፍነቷን ይመሰክራል። 9.6 ሚሊዮን ስኩየር ሜትር የሚደርሰው የቆዳ ስፋቷም በዓለም ሦስተኛዋ ትልቅ ሀገር አድርጓታል።

ለመግቢያ ያህል ስለዚህች የብርቱዎች ሀገር ይህቺን ካልኩኝ፣ በቆይታዬ ከታዘብኳቸውና እኛም ሀገር ቢተገበሩ ይጠቅሙናል፤ ይለውጡናልም ብዬ ቅናት ቢጤ ካስያዙኝ ጉዳዮች መካከል ዋናዋናዎቹን አጠር አጠር አድርጌ ላስቃኛችሁ ወደድኩና ብዕሬን አነሳሁ።

የትጉሃን ሀገር

እግር ጥሎት ቤጂንግም ሆነ ዥያሜን የተገኘ በተለይም እንደ እኔ ላለ አፍሪካዊ እንግዳ የመጀመሪያ ጥያቄ የሚሆነው ጎዳናዎችን ተመልክቶ ያ ሁሉ ሕዝብ የት ነው ያለው? የትስ ገብቶ ነው የሚል ነው። ከአንዴም ሁለቴ በቻይና በነበረኝ ቆይታ የተረዳሁት በቻይና ጎዳናዎች ላይ ሕዝብ ሲርመሰመስ ለማየት መመኘት የማይጨበጥ ህልም መሆኑን ነው።

በርካታ ዘመናዊና ቅንጡ መኪናዎች የሚጠቀሙት ቻይናውያንን ጎዳና ላይ ታች ሲሉ በፍጹም አይታዩም። ይኼንኑ ጥያቄዬን ያቀረብኩላት የወርክሾፕ አስተባባሪ በቻይና ሰከንድ ውድ መሆኗንና ሁሉም ቻይናዊ በሚባል ደረጃ ሰዓቱን በሥራ ስለሚያሳልፍ ጎዳና ወይም ካፌ ላይ በብዛት አይታይም። እንኳንስ ጊዜን አልባሌ በሆኑ ጉዳዮች አሳልፎ እየተሠራም ቢሆን የሕይወት ፍላጎትን አሟልቶ መዝለቅ ከባድ ነው ስትል መልሳልኛለች።

የተዝናኖትና የቱሪዝም ማዕከሏ ቻይና

ከላይ ከጠቀስኩት ኦና የቻይና ጎዳናዎች በተቃራኒው ግን ጊዜ ተመርጦለትና ተወስኖ እንደ ቻይናውያን የሚዝናና ሕዝብ ያለ ደግሞ አይመስልም። በተለይም በታሪካዊ ቦታዎች፣ በመናፈሻዎችና በገበያ ቦታዎች ከሕፃን እስከ አዋቂ ቻይናውያን መዝናናቱን በሚገባ ተክነውታል። በገበያ ስፍራዎችና ካፍቴሪያዎች ቻይናውያን ጥንዶች ቀለል ባለ አለባበስ አይስክሬም እየላሱና በርገር ብስኩት እየገመጡ ዘና ፈታ ይላሉ።

በየገበያው ሞልም በመጫወቻ መኪናዎች (ቶይ ካርስ) ሕፃናት ቻይናውያን ዓለማቸውን በሚገባ ይቀጫሉ። አዛውንትና ጎልማሳ ቻይናውያን ደግሞ በቱሪዝም መስህብ ስፍራዎች እልፍ ሆነው ይታያሉ። ቻይናውያኑ የሀገር ውስጥ የቱሪዝም ሀብታቸውን ለመጎብኘት የሚያደርጉት ጥረትና እንቅስቃሴ አስደማሚና በተለይም ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው ብዬ አምናለሁ። “እስኪያልብህ ሥራ፤ ቋቅ እስኪልህ ተዝናና” የቻይናውያኑ ብሂል ይመስለኛል።

በዜና ገንብተህ በዘፈን የማታፈርስባት ቻይና

በእኔ እምነት ቻይና የተለወጠችው በተለወጠ ማኅበረሰብ ነው። ዛሬ የገነባኸውን ነገ የሚያፈርስ፣ የተሠራን የማያበላሽ፣ ቆሻሻ በየቦታው የሚጥልና ባገኘበት የሚጸዳዳ አንድም ዜጋ በቻይና የለም ብል ማጋነን አይመስለኝም። ውቦቹ መንገዶችና የከተማቸው ንጽህና ቻይና የጨዋ፣ የተለወጡና የሕግ አክባሪ ዜጎች ሀገር መሆኗን አፍ አውጥተው ይመሰክራሉ።

ይህ የሆነበት ዋነኛ ምክንያት ደግሞ ለቀደሙትና ለታላላቆቻቸው እሴቶች ቻይናውያኑ ተገዥ መሆናቸውና “ሜይን ስትሪም ሚዲያውና ሶሻል ሚዲያው” ተናበውና ተቀናጅተው የመሥራታቸው ውጤት እንደሆነ ይሰማኛል። ቻይና በርካታ የግዛት (Province) ሚዲያዎች ቢኖራትም በሚያስተላልፉት መልዕክት አንደኛው ከሌላው በፍጹም አይጋጩም።

የዜናና ፕሮግራሙ የዘፈኑና ግጥሙ ማዕከላዊ ጭብጥ ሀገራዊ አንድነት፣ ሰላም፣ ትጋት፣ ፈጠራና ቴክኖሎጂ ነው። ይህ ጉዳይ በእኛ ሀገር መገናኛ ብዙኃን ከሚታየው የክልሎች አራምባና ቆቦ ዘገባ እና በዜና ገንብቶ በዘፈን የማፍረስ ተግባር በእጅጉ የተለየ ነው።

በቻይና ሁሌም ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ በሁሉም ግዛት የሚገኙ መገናኛ ብዙኃን በጋራ የሚያስተላልፉት የሀገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን የሆነውን የCCTV ዜና ነው። በዚህም መላ ቻይናውን ከጫፍ እስከጫፍ የሀገራቸውንና የዓለምን ውሎና እንቅስቃሴ በተመሳሳይ ድምጽ እንዲረዱና አንድነታቸው እንዲጠናከርም ረድቷቸዋል። ይህ ጉዳይ በእኛም ሀገር በዘመነ ኢህአዴግ ለተወሰነ ጊዜ ተተግብሮ ደብዛው የጠፋ እንደሆነ አውቃለሁ።

ሶሻል ሚዲያ ለቀልድና ለቧልት ፍጹም የማይፈቀድባት ቻይና

ብልኋ ቻይና የሶሻል ሚዲያ አሉታዊ ጎን ቀድሞ ነው የገባት። ስለሆነም በመረጃና በግለሰብ ነፃነት ስም ሶሻል ሚዲያው የወንጀለኛ፣ የሥራ ፈቶችና የስም አጥፊዎች መፈንጫ እንዲሆን በፍጹም አልፈቀደችም። ይልቁንም ቴክኖሎጂውን ችላ ሳትል “ዊ ቻት እና ቢሊቢሊን” የመሳሰሉ ሀገር በቀል ዲጂታል ፕላት ፎርሞችን ገንብታ ለበጎ ተግባር አውላዋለች።

በቻይና ቲክቶክን በተካው ቢሊቢሊ ዳኒ ሮስት፣ ሞጣ፣ ሻኩር ወዘተ እያሉ ሲቀልዱ፣ ሲያፌዙና ሲጃጃሉ ማየት አይታሰብም። ከዚህ ይልቅ የቻይናው ቢሊቢሊ ዋነኛ ትኩረትና ይዘት ሞራል፣ ማኅበረሰባዊ እሴት፣ ፈጠራና ፍቅር ብቻ ነው። የትጉዎቹ ቻይናዎች ዊ ቻትን ለመክፈት ከግለሰብ ትክክለኛ የማንነት መረጃ ጋር ስለሚያያዝ በዚህ ፕላት ፎርም ተጠቅሞ ማፌዝ፣ ማናቆር፣ ማጋደልና ስም ማጠልሸት ፈጽሞ አይሞከርም። ይልቁኑ ዊ ቻት አዎንታዊ የመረጃ ምንጭ ሆኖ ከማገልገሉም በላይ ለግብይት መጠቀሚያም ሆኖ የቻይናን የዲጂታል ዘመን ብሩህና ፋይዳ ብዙ አድርጎታል።

ኪው አር የቻይናውያን ልብ

በእኛ ሀገር በየሆቴልና በየገበያ ቦታው ቫት ከፍለንና ገንዘቡ ከእኛ ላይ ተቀንሶ እኛም ጋር መንግሥትም ጋር የማይደርስበት ሁኔታ እንዳለ ለማናችንም ብርቅ የሆነ ጉዳይ አይደለም። የመንግሥት ተቋማትና የፀጥታ ኃይሎች በስፋት ባሉበት አራት ኪሎ ኢፕድ ሕንፃ አጠገብ እንኳን የውጭ ሀገር ሱፎችንና ጫማዎችን ሲገበዩና በካፌም ሆነ በምግብ ቤቶች ሲገለገሉ ዋጋው ተደምሮብን መክፈላችንን እያወቅን አንድም ቀን የሽያጭ ደረሰኝ ተቆርጦልን አያውቅም። በዚህ ጉዳይ ተጨቃጭቄና ተገልምጬ ደረሰኝ ካልመጣ አልከፍልም በማለት በነፃ የተመገብኩበት ጊዜም የቅርብ ጊዜ ትውስታዬ ነው።

በሀገረ ቻይና ተግቶና ሠርቶ መክበር ይፈቀዳል እንጂ ተጭበርብረህም ሆነ አጭበርብረህ ታክስ መሰወር በፍጹም አይታሰብም። ከካፌ እስከ ትልልቅ ሆቴሎች ከነሸምሱ መሰል ሱቆች እስከ ኤች ኤም ያሉ ግዙፍ ሞሎች ምንም ገዛህ ምን ዕቃው ላይ በተቀመጠ ልዩ ኮድ ታክስን ጨምሮ የተቀመጠውን ዋጋ መክፈል ግድ ነው። በሀገረ ቻይና ዕቃ ትመርጣለህ፤ ኪው አር ኮዱ ወደ ኮምፒውተሩ ገብቶ ዋጋ ይነገርሃል፤ በዲጂታል ዘዴ ትከፍላለህ አለቀ፤ ደቀቀ። ከዚህ ውጪ ያ አማራጭ አይታሰብም፤ አይሠራምም።

ዶላር ሞገሱ የተገፈፈባት ቻይና

እግረ መንገዳችንን ወይም ጉዳይ ገጥሞን በኢትዮጵያ ሆቴል፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲሱ ሕንፃ ወይም ጋንዲ አካባቢ ስንገኝ ቼንጅ ፈልገው ነው? ያ ነገር አለ ወዘተ የሚሉ በርካታ ጥሪዎች ከዚህም ከዚያም ይጎርፍልናል የእነዚህ ጥያቄዎች ጀርባ ያሉ ጉዳዮች ዶላር እና የውጭ ምንዛሬ ናቸው።

በወርቃማው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሕንፃ የውጭ ምንዛሪ ለመጠየቅና ለማግኘት ያለውን ግፊያና ትርምስ ተመልክቼ ቻይና ስሄድ የገጠመኝ ነገር እጅግ ተቃራኒ ነበር። በብርቱዎች ቻይናውያን ዘንድ ዶላር ለመዘርዘር ጥቁር ገበያን ደፍሮ የሚሞክር የለም። ዶላር መመንዘር የፈለገ በኢቲ ኤም አንዱን የአሜሪካን ዶላር በ5.25 የቻይና ዩዋን ይመነዝራል። ከዚህ ውጪ ሌላ ምንም ዓይነት አማራጭ የለም።

ከዚህም ባለፈም አነስተኛ ሱቅ ተሄዶ እንኳ ዕቃ ለመግዛት በዶላር ልክፈል ቢባል ፈላጊ የለውም። ቻይናውያኑ ዶላሩን ተመልክተው የሚያሳዩት የንቀት ገጽ ሰርተውና ለፍተው የዶላርን ገናናነት ገደል እንደከተቱት ማሳያ ይመስለኛል።

ሕግ አክባሪዎች ቻይናዎች

በቤጂንግ ኤርፖርትም ሆነ በዥያሜን በነበረኝ ቆይታ አንድም የቻይና ፖሊስ በመንገድም ሆነ በኤርፖርት አልተመለከትኩም። ከዚህ ይልቅ ቻይናውያኑ ጎዳናና ዋና ዋና አደባባዮችን ብቻ ሳይሆን መንደሩን ሳይቀር በሲሲቲቪ ካሜራዎች ቁጥጥር ስር አውለውታል። ስለሆነም ህሊና ያለው ፈጣሪውን፤ ህሊናው ምንም የማይመስለው ደግሞ ስውር ካሜራዎችን ፈርቶ ሕግ ያከብራል፤ ያስከብራል።

ውብ ሠፊና በአረንጓዴ ዛፎች የተሞሉትና የተንጣለለ የእግረኛና የብስክሌት መንገድ ባላቸው የዥያሜን ጎዳናዎች በየመንገዱ እልፍ ብስክሌቶች ተቀምጠው ይታያሉ። ቻይናውያኑን መጠቀም የፈለገ ማንኛውም ዜጋ በነፃነት ይጠቀምባቸዋል። ለዚህ አገልግሎት የሚፈለገው ብቸኛ ቅድመ ሁኔታ ኪው አር ኮድን አስገብቶ መመዝገብና አስፈላጊውና ክፍያ መፈጸም ብቻ ነው።

ይህን ካደረጉ በኋላ በከፈሉት መጠን ልክ ተጠቅሞ ብስኪሌቶቹን በሚገባው ቦታ መመለስ ውለታ ሳይሆን ግዴታ ነው። በማን አለብኝነት ብስኪሌቶችን በፈለጉት ቦታ መተው ወይም ደግሞ ይዞ መሰወር አይታሰብም፤ አይቻልምም።

ሽርፍራፊ ሰኮንዶች ውድ የሆኑባት ቻይና

ጊዜ ክቡር ነው የሚለው አነጋገር እውነተኛ ትርጉሙን ያገኘው ቻይናውያኑ ዘንድ ነው ብል ምንም ዓይነት ማጋነን የለበትም። ቻይናውያኑ ዘንድ ሽርፍራፊ ሰኮንዶች እጅግ ውድ ዋጋ አላቸው። የሆነ ስፍራ ለመጓዝ አስበው ራይድ ሲያዝዙ በስልክዎ ስንት ሰዓት እንደሚደርስ ጥቆማ ይሰጥዎታል። በተባለው ሰዓት ያለምንም መዛነፍም ታክሲው የሚጠብቁት ቦታ ደርሶ ያገኙታል።

በቆይታዬ በነበረ የአፍሪካ ቻይና የኢንተርኔትና የሚዲያ ትብብር ጉባዔ መክፈቻና መዝጊያ ሰዓቱ በፕሮግራሙ ላይ በተቀመጠው መሠረት ያለአንዳች መዛነፍ ሲከፈትና ሲዘጋ አስተውያለሁ። ለሻይ የተሰጠው 15 ደቂቃ በሚገባ ተከብሮ ተሰብሳቢው ሁሉ በተጠበቀው ሰዓት በአዳራሹ ተገኝቶም ተመልክቼያለሁ።

ይሄንን ጉዳይ 3 ሰዓት የተባለ ስብሰባ 4:00 ሰዓት ከሚጀምርበት እና ለሻይ የተሰጠ 30 ደቂቃ ወደ አንድ ሰዓት ተገፍቶ ሰው በልመና ወደ አዳራሽ ከሚገባበት ከእኛ ሀገር ሁኔታ ጋር አነጻጽሬው ራሴንና ሕዝቦቼን ታዝቤያለሁ። ለድህነታችን ትልቁ ምክንያት ለጊዜ የምንሰጠው ክብር የወረደ ከመሆኑ ጋር በእጅጉ መቆራኘቱንም ይበልጥ ተረድቻለሁ።

በአጠቃላይ በትጉኃኑ ሀገር ቻይና የነበረኝ ቆይታ በግልም ሆነ እንደ ሀገር ብዙ የተማርኩበት እና ጠንክረንና ተግተን ከሠራን ብልጽግናችን አይቀሬ መሆኑን ያረጋገጠልኝ ነበር!።

ፍቃዱ ከተማ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You