የሠላም ጥሪን መቀበል፤ ሀገር ያፀናል

ዕውቁ ግሪካዊ ፀሐፊ እና የታሪክ ሰው ሔሮዶቱስ የጦርነትን አስከፊነት በመጥቀስ ሠላም ለሰው ልጆች ከውሃና አየር የማይተናነስ ዋጋ እንዳለው ፍንትው አድርጎ የሚገልጽ አባባል አለው። “In peace, sons bury their fathers. In war, fathers bury their sons.” አባባሉ ወደ አማርኛ ሲመለስ ‹‹በሠላም ጊዜ ልጆች አባቶቻቸውን ይቀብራሉ፤ በጦርነት ጊዜ አባቶች ልጆቻቸውን ይቀብራሉ” የሚል ትርጓሜ ይኖረዋል። ጦርነት መተኪያ የሌለውን የሕይወት ዋጋ ያስከፍላል። ሀገርን የኋሊት ያስጉዛል። ጦርነት ሕፃናትን ያለ ወላጅ፣ አዛውንትን ያለ ጧሪና ቀባሪ፣ ሀገርን ያለ ተረካቢ ያስቀራል።

የዚህ ግሪካዊው ታሪክ አዋቂ አባባል እንደእኛ የጦርነት ጠባሳው ባልሻረ ሕዝብ ውስጥ ምን ማለት እንደሆነ የተሰወረ አይደለም። እንዲህም ሆኖ ግን፤ ከጦረኝነት ስሜት ለመውጣት ዛሬም አልበገረንም። ከጦርነት ያተረፍን እስኪመስል ኃይልን መሠረት ባደረገ የፖለቲካ እሳቤ ብዙ ያልተገባ ዋጋ እየከፈልን ነው።

አሁንም በተለይ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል እና በኦሮሚያ ክልል በሕዝብ ጥያቄ ሽፋን በአፈሙዝ ወደ ሥልጣን ለመምጣት ውጤት አልባ የጥፋት መንገድ ከተጀመረ ሰነባብቷል። ይህ ዓይነቱ ጦረኛ እሳቤ ሀገር እና ሕዝብን ተስፋውን ከማሳጣት ያለፈ ምንም ፋይዳ የለውም ።

ከዘመን በተጣላ ጽንፈኛ አስተሳሰብ ፖለቲካዊ ፍላጎትን ለማሳካት ሕዝብን ሠላም መንሳት፣ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው እንዲፈናቀሉ፣ በሀገራቸው ከቦታ ወደ ቦታ በሠላም መንቀሳቀስ እንዳይችሉ እያደረጉም ይገኛል። በብዙ ልፋት እና ጥረት የተገኘን የሀገር ሀብት በማውደም በቀደመው ድህነታችን ላይ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ“ እየሆነ ነው።

ችግሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንቱታ ካተረፍንባቸው ማኅበረሰባዊ የሞራል እሴቶቻችን ያፈነገጡ ድርጊቶች እንዲፈጸሙ በር ከፍቷል። በሠላም ተከባብሮ መኖር የለመደው ሕዝብን ያልተገባ ዋጋ ማስከፈል ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። እንደ ሀገር በተለየ መነቃቃት የተጀመሩ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ማሻሻያዎች በሚጠበቀው ፍጥነት እንዳይጓዝ ጋሬጣ ሆኗል።

ይህ ዓይነቱ ሀገር አፍራሽ ድርጊት በአንዳንድ አካባቢዎች በስፋት እየተስተዋለ ይገኛል። የዜጎች ሥጋት የመሆኑ ልክ ከፍ ወዳለ ደረጃ ላይ ደርሷል። ይህን ሀገራዊ ችግር ለመሻገር/ለመቀልበስ የሀገርን ሠላም ማፅናት የሚችል ሁነኛ መፍትሔ መፈለግ ያስፈልጋል።

ከምንም በላይ ደግሞ በሀገር ሠላም እንዲሰፍንና የዜጎች ደህንነት የመጠበቅ ግዴታ ያለበት መንግሥት ነው። በመሆኑም በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የታጠቁ ቡድኖች እንቅስቃሴ ከወዲሁ ‹‹እናቴ በእንቁላሉ ጊዜ….›› ሕግን በማስከበር፤ አልያም በሌሎች የሠላም አማራጮች መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል።

መንግሥት ለሠላም ያለውን ቁርጠኝነት ትላንት ፕሪቶሪያም ሆነ ዳሬሰላም ላይ በመገኘት አሳይቷል። በተጨማሪም ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን ከሃሳብ ይልቅ በጠብመንጃ ማስፈጸም ከሚፈልጉ ጽንፈኛ ቡድኖች ጋር ተወያይቶ ወደ ሠላማዊ ሕይወት እንዲመለሱ አድርጓል። በጋምቤላ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በኦሮሚያ፣ በሱማሌ፣ በአማራ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ በርካታ የታጠቁ ኃይሎች በተዘጉት የሠላም እጆች በይቅርታ ወደ ማኅበረሰቡ ተቀላቅለው መደበኛ ሕይወታቸውን እየኖሩ ይገኛሉ።

ዛሬም መንግሥት ሠላምን አብዝቶ በመፈለግ ሕግን ከማስከበሩ ጎን ለጎን፤ በተሳሳተ አስተሳሰብ ተመርዘው በጠብመንጃ አፈሙዝ ወደ ሥልጣን ለመምጣት ለሚቋምጡት አንዳንድ አካላት የዘረጋውን የሠላም እጁ አላጠፈም። መንግሥት እነዚህ ቡድኖች ከነበሩበት የጥፋት መንገድ በመውጣት ወደ ሠላማዊ ሕይወት እንዲመለሱ ያቀረበውን ጥሪ እየተቀበሉም ይገኛል። መንግሥት ሀገርን ወደ ዘላቂ ሠላም ለማምጣት የጀመራቸው የሠላም እንቅስቃሴዎች ውጤት እያመጡ እንደሚገኙ ታዝበናል።

ከሰሞኑም በኦሮሚያ ክልል የጽንፈኛው ኦነግ ሸኔ እና በአማራ ክልል በፋኖ ሥም የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች የሠላም ጥሪውን ተቀብለው እጃቸውን እየሰጡ ነው። ከነበሩበት የጥፋት መንገድ በመውጣት ወደ ሠላማዊ ሕይወት ለመመለስ በስፋት እጃቸውን ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እየሰጡ ናቸው።

ይህ ውሳኔያቸው ሀገራዊ ሠላም እና መረጋጋት ለመፍጠር፤ በተለይም ጽንፈኞችና ጽንፈኛ አስተሳሰቦች በሀገሪቱ እና በትውልዱ ላይ ተጨማሪ የጥፋት አቅም እንዳይኖራቸው ትልቅ ጉልበት እንደሚሆንም ይታመናል።

አያት ቅድመ አያቶቻችን ዛሬ በኩራት ኢትዮጵያ ብለን የምንጠራትን ሀገር፤ በስሟ የምንምልባት ሀገር አጽንተው ሊያቆዩልን የቻሉት፤ የሐሳብ ልዩነታቸውን በይደር፤ የሀገር ፍቅራቸውን በልባቸው አኑረው ነው።

በአፈሙዝ ፖለቲካዊ ፍላጎትን ለማስፈጸም የሚደረግ ጽንፈኛ አካሄድ ሀገር አፍራሽ ነው። ለብዝኃ ጎጇችን ኢትዮጵያ የሚበጅ አይደለምና፤ በመንግሥትን የተሰማውን የይቅርታ ድምፅ በመስማት አሸናፊ መሆን ይገባል።

መንግሥትም መሰል ሠላማዊ አካሄዶችን እንደሚከተል በተደጋጋሚ ሲገልፅ ይሰማል። ከየትኛውም አካላት ጋር በጋራ ለመሥራት ዝግጁ እንደሆነ ይገልፃል፤ በተግባር አሳይቷል። በአጠቃላይ የሠላም ጥሪን መቀበል ሀገርን የሚያፀና እንጂ፤ አንገት የሚያስደፋ አለመሆኑን መረዳት ብልህነት ነው።

የጦር መሣሪያ አስቀምጦ እስክሪፕቶ እና ሀሳብ ይዞ በመወያየት ለሠላምና ለዕድገት ምቹ የሆነች ሀገር እንድትሆን መትጋት ያስፈልጋል። ስለዚህ በጦርነት እንዳልተጠቀምን እናውቀዋለንና አሁንም ለሠላምና ለመነጋገር ቦታ መስጠት ይገባል። በጦርነት ድል ማድረግ ቢቻል እንኳ ድሉ ጊዜያዊና በሌላ ጦርነት የሚወሰድ መሆኑን ታሪክ አሳይቶናል። ከዚህ በመማር ለሠላም የተዘረጉ እጆች ሠላማዊ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል።

ዳንኤል ዘነበ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 16 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You